እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

16. የእግዚአብሔር ቃል እንደ እሳት ብርቱ ነው

16. የእግዚአብሔር ቃል እንደ እሳት ብርቱ ነው

  ለነቢዩ ኤርምያስ የእግዚአብሔር ቃል እንደ እሳት የበረታና የሚያቃጥል ነበር፤ እግዚአብሔር ይህን አረጋግጦለት ነበር፡፡ ሐሰተኞች ነቢያትን በሚመለከት፥ እግዚአብሔር ለኤርምያስ በሰጠው የትንቢት ቃል ውስጥ ስለ እውነተኛ ቃሉ ኃይልም ገልጾለት ነበር፡፡ ስለ ቃሉ ብርታት ሲናገር "ቃሌ እንደ እሳት፥ አለቱንም ሰባብሮ እንደሚያደቅቅ መዶሻ ነው" ሲል፥ ቃሉ ከእሳት ጋር ያለውን የጠበቀ ዝምድና ያረጋግጣል፡፡ ቀጥሎም "ቃሌ አለቱን ሰባብሮ እንደሚያደቅቅ መዶሻ ነው" የሚል ሐሳብ ማስከተሉ "እሳትና መዶሻ" በተለይ በድንጋይ ፈላጮች ዘንድ ያላቸውን ታላቅ ጠቃሚነት መለስ ብለን እንድናይ ያደርገናል፡፡ በተለይ ትላልቅና ጠንካራ የሆኑ ጥቋቁር ድንጋዮች እንዴት እንደሚፈለጡ ካየን፥ በቀጥታ በመዶሻ አይሰበሩም፡፡ መጀመሪያ በእሳት ይቃጠላሉ፡፡ የድንጋዩ ጥጣሬ በእሳት ከለዘበ በኋላ በመዶሻ (መራጃ) ይመታል፡፡ ያን ጊዜም በቀላሉ ይሰባበራል፡፡ በደረቁ ዝም ብሎ በመዶሻ ቢቀጠቀጥ ግን ጉልበት ከማባከን በስተቀር ውጤት አይገኝበትም፡፡

የኔና የናንተ ልቦች እንደዚያ ደረቅ ጥቁር ድንጋይ ሕይወት አልባ አለቶች ሆነው የአምላክን ፍቅር መቀበል ሲቸግራቸው፣ ጌታ በጭካኔ ልቦቻችንን በሚቀጠቅጡ ቃላትና ደረቅ ሕግጋት ሊያሸንፋቸው አልሞከረም፡፡ መጀመሪያ እንደ እሳት በሚያቃጥሉ፣ በሚያሞቁ፣ ድንዛዜን ሁሉ በሚያስወግዱት የፍቅር ቃላቱ ልቦቻችንን አለሰለሰ፡፡ የደረቁትን ደንዳና ልቦች በመንፈስ ቅዱስ ዘይቱ አለሰለሰ፡፡ ኋላም መሰበር ያለበትን ለመስበር፣ መድቀቅ ያለበትን ለማድቀቅ ኃይለኛውን መዶሻውን ወደ ልባችን ላከ፡፡

 

ቃሉ መጀመሪያ እንደ እሳት ኋላም እንደ መዶሻ እንጂ በተገላቢጦሽ ወደኛ ቢመጣ የደረቀውን ልብ ከመርታት ይልቅ የባሰ ባደነዘው ነበር፡፡ ጌታ ግን የልብ ንጉሥ ነውና በእሳት አሸነፈን፡፡ ለብዙ ዘመናት የሕይወት ለውጥ ሳይኖረን ቃሉን በየጊዜው ስንሰማ ኖረን ይሆናል፡፡ ግን የመንፈስ ቅዱስ እሳት ልባችንን ሲነካ ለዘመናት የሰማነውና ነጥሮ ሲመለስ የኖረው የጌታ ቃል ልክ ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሰማነው ቃል በሙሉ ኃይሉ ይረታናል፡፡ ቃሉ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ድንቅ ውጤት የሚኖረው አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ የሰዎችን ልብ ሲረታ ብቻ ነው፡፡ ቃሉ ራሱ ግን እንደ እሳት የበረታ ነው፡፡

 

የእግዚአብሔር ቃል እንደ እሳት የሚያቃጥል ኃይል እንዳለው ኤርምያስ ከሕይወት ልምዱ ተምሮታል፡፡ ስለ ቃሉ የተቀበለውን ግፍ በማስታወስ ብሶቱን ለጌታ በሚገልጽበት ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፡-

 

"... አምላክ ሆይ! አንተ ያዘዝኸኝን የትንቢት ቃል በመናገሬ የተናቅሁ መሳለቂያ ሆኜአለሁ፡፡ ነገር ግን ‹ከእንግዲህ እግዚአብሔርን እረሳለሁ በስሙም አልናገርም› በምልበት ጊዜ፥ ከአንተ የተሰጠኝ የትንቢት ቃል በውስጤ እንደ እሳት ይነዳል፤ በውስጤ ሰውሬ ልይዘው ብሞክርም አፍኜ ላስቀረው አይቻለኝም፡፡" (ኤር. 20፡8-9)

 

ቃሉ የመለኮታዊ እሳት ኃይል ስላለው ይፋጃል፤ የቀዘቀዙትን ልቦች ያሞቃል፤ አምቀው ሊያፍኑት ቢሞክሩ ወላፈኑ ፈነቃቅሎ ይወጣል፡፡

ኤርምያስም በቃሉ ምክንያት ከመቸገር ዝም ለማለት ወስኖ ነበር፤ ግን አልቻለም፡፡ ቃሉ እሳት ነውና በውስጡ ነደደ፡፡ ስለዚህ የፈለገው ችግር ሲያጋጥም መናገርና መተንፈስን መረጠ፡፡ በእርግጥ የጌታ ቃል እሳት ነው!

 

ጌታ ኢየሱስ ሞቶ ከተቀበረ በኋላ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል ነሥቶ ተነሣ፡፡ የትንሣኤውን ብስራት አንዳንድ ሴቶች በመጀመሪያ ሰሙ አዩም፡፡ ይህን የምሥራች ያልሰሙ ሁለት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኤማሁስ ወደምትባል መንደር እሑድ ዕለት በእግራቸው መጓዝ ጀመሩ፡፡ በመንገድ ያወሩት የነበረው ስለ ኢየሱስ ሞት ነበር፡፡ ድንገት አንድ የማያውቁት ሰው በመካከላቸው ገብቶ አብሮአቸው መጓዝ ጀመር፡፡ የመንፈስ ዓይኖቻቸው ተጋርደው ነበርና፣ አብሮአቸው የሚጓዘው ኢየሱስ እንደነበር ሊለዩት አልቻሉም፡፡ እርሱ ግን የደኅንነትን ታሪክ ከሙሴ መጻሕፍትና ከነቢያት መጻሕፍት አንስቶ ስለእርሱ የተጻፈውን ሁሉ አስረዳቸው፡፡ ሲመሽ አብረው ለማዕድ ቀረቡ እርሱም እንጀራውን በቆረሰ ጊዜ ጌታ ኢየሱስ መሆኑን አወቁ፡፡ ጌታ ግን ተሰወረባቸው፡፡ እርሱ ከነሱ እንደሄደ፥ በፊት ሲናገራቸው ልባቸው ውስጥ ይስማቸው የነበረውን እንግዳ ነገር ተነጋገሩበት፡፡ እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፡- "በመንገድ ሳለን ሲነግረንና ቅዱሳት መጻሕፍትንም እየጠቀሰ ሲያስረዳን ልባችን እንደ እሳት ይቃጠል አልነበረምን?" ተባባሉ፡፡ (ሉቃ. 24፡32)

 

ቃሉ በልባቸው እንደ እሳት ሲነድ መቆየቱን ጌታን የመለያ ምልክት አድርገው እንደተቀበሉት ጥቅሱ ያስረዳል፡፡ በእርግጥም መለኮታዊው እሳት ሁልጊዜ ስለ ኢየሱስ ምስክር ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተቀባ ስብከት ምን ያህል የሰሚዎችን ልብና ነፍስ በእሳት እንደሚያያይዝ የታወቀ ነው፡፡ የሐዋርያት ሥራም ይህን ሐቅ ያረጋግጥልናል፡፡ የጠወለገን እምነት የሚያለመልም፣ የጨለመን ተስፋ ብሩህ የሚያደርግ፣ የሽንፈትን ወሬ በድል ቃላት የሚተካ፣ የተሰበረን ልብ ጠግኖ ቀጥ የሚያደርግ፣ የመንፈስ ቅዱስ እሳት ያለበት የጌታ ቃል ብቻ ነው፡፡ ፍርሃት ለዋጠው ልብ ተስፋንና ድፍረትን የሚሰጥ በእሳት ተፈትኖ ያለፈው የጌታ ቃል ብቻ ነው (መዝ. 12፡6 እይ)፡፡ የሐዋ.ሥራ 18፡24-28 ስለ አጵሎስ ይነግረናል፡፡ አጵሎስ ከዮሐንስ ጥምቀት ባሻገር ስለ መንፈስ ቅዱስም ይሁን ስለ ክርስቲያናዊ ጥምቀት የሚያውቀው ነገር አልነበረውም፡፡ ግና "በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ" (ቁ.24) የጌታን ቃል ጠንቅቆ የተማረ ነበር፡፡ በውስጡ የነበረው የጌታ ቃልም በመንፈስ እንዲቃጠል ያደርገው ነበር፡፡ ምክንያቱም ቃሉ እሳት ነውና! "እርሱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠንቅቆ የተማረና ጥሩ የአነጋገር ችሎታም ያለው ሰው ነበረ፡፡ ስለ ጌታ መንገድ የተማረና በመንፈስም የተቃጠለ ሆኖ ስለ ኢየሱስ በትክክል ይሰብክና ያስተምር ነበር፡፡" (ቁ.24-25)

 

ክርስቲያናዊ ጥምቀትን ካለማወቁ የተነሣ (የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ ያውቅ ነበር) ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚያውቀው ነገር አልነበረውም፡፡ ቢሆንም በመንፈስ የተቃጠለ ነበር፡፡ የማያውቀው መንፈስ ቅዱስ እንዴት በውስጡ ይነድ ነበር? የጌታን ቃል በሚገባ ያውቅ ስለነበር በውስጡ ይነድ የነበረው የቃሉ ትኩሳት ነበር፡፡ ከአጵሎስ ሕይወት እንደምናየው የጌታ ቃልን (ጌታ ኢየሱስ የአብ ቃል ነው) እና መንፈስ ቅዱስን ነጣጥለን ልናያቸው እንደማንችል ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ባለበት መንፈስ ቅዱስ አለ፤ መንፈስ ቅዱስ ባለበት ስፍራም ጌታ ኢየሱስ አለ፡፡ አጵሎስ የጌታ ቃል እሳት መሆኑን በሕይወቱ ያየ ሰው ነበር፡፡ ቀርቶት የነበረውን ክርስቲያናዊ እውቀት ጵርሶቅላና አቂላ የተባሉ ባልና ሚስት አማኞች በሚገባ ስላስተማሩት፥ ሙሉ እውቀት ያለው ታላቅ የጌታ አገልጋይ ለመሆን ቻለ፡፡

 

ቃሉን ስናነብ ምንም ለውጥ የማይሰማን ከሆነ፣ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እንለምን፡፡ ያለ እርሱ ኃይል ቃሉ በእኛ ውስጥ ለመሥራት ያዳግተዋል፡፡ አስቀድሞ የመንፈስ ቅዱስ እሳት በልባችን ካለፈ ግን ልባችንን ለጌታ ቃል ታዛዥ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ እንዲሁም ተስፋ ስንቆርጥ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ግለትን በቃሉ አማካኝነት ወደ ልባችን ይልካል፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት