እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የሰው እግዚአብሔርን የመቀበል ችሎታ

የሰው እግዚአብሔርን የመቀበል ችሎታ

ከአዲሱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ የተወሰደ    ምዕ. 1 ቁ.27-35

1.የሰው እግዚአብሔርን መሻት

ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔርን መሻቱ በልቡ ተጽፎአል፤ ስለዚህ እግዚአብሔርም ሰውን ወደ ራሱ ከማቅረብ ከቶ አይቆጠብም። ሰው ያለ ማቋረጥ የሚፈልገውን እውነትና ደስታ ሊያገኝ የሚችለው በእግዚአብሔር ብቻ ነው።

የሰው ክብር ዋና መሠረቱ ከሁሉ በላይ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት እንዲኖረው መጠራቱ ነው። ይህ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲነጋገር ለሰው የቀረበለት ጥሪ የደረሰው ሕልውናውን እንዳገኘ ወዲያውኑ ነው። ሰው ሕያው ሆኖ የሚኖረው እግዚአብሔር በፍቅር አማካይነት ስለፈጠረውና በፍቅረ አማካይነት በሕይወት ስለሚጠብቀው ነው።

በታሪክ ሂደት እስከ ዛሬ ድረስ ሰዎች እግዚአብሔርን መሻታቸውን በበርካታ ሃይማኖታዊ እምነቶቻቸውና ድርጊታቸው በጸሎታቸው፣ በመሥዋዕታቸው፣ በአምልኮአቸው፣ በአስተያየታቸው፣ ወዘተ. ሲገልጹ ኖረዋል፣ በዚህ ዓይነት ሃይማኖታዊ መግለጫዎች አንዳንዴ አሻሚነት ቢኖራቸውም በመላው ዓለም የሚስተዋሉ በመሆናቸው ሰው ሃይምኖታዊ ፍጡር ነው ብሎ በልበ ሙሉነት መናገር ይችላል።

(እግዚአብሔር) እርሱ የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ቅመአያት ፈጠረ፤ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም አደረገ፤የሚኖሩባቸውን ዘመናትና ቦታዎች ሰጣቸው፣። ይህንንም ያደረገው ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲፈልጉና ምናልባትም ዳሰው እርሱ ማግኘት እንዲችሉ ነው፤ ሆኖም እርሱ ከእኛ ከእያንዳዳንቸን የራቀ አይደለም። “ሕይወት የምናገኘውና የምንቀሳቀሰው የምንኖረውም በእፉሱ ነውና።”

ነገር ግን ይህ “ቅርብና እጅግ አስፈላጊ የሆነ የሰውና የእግዚአብሔር ትስስር” ሊረሳ፣ ቸል ሊባል፣ ወይም ጭራሹኑ በግልጽ በሰው ዘንድ ተቀባይነት ሊያጣ ይችላል፤ የዚህ ዓይነት አመለካከቶች የተለያዩ መንስኤዎች ሊኖሯቸው ይችላል፤ እነርሱም በዓለም ላይ ባለው ክፋት ላይ ማመጽ ሃይማኖታዊ ማይምነት ወይም ግዴለሽነት፣ የዚህ ዓለም ሃብትና ምቾት፣ ከምእመናን በኩል በመጥፎ ምስላሌነት የሚመጣ እንቅፋት፣ ሃይምኖትን የሚጻረሩ አስተሳሰቦች፣ በመጨረሻም እራሱን ከፍርሃት የተነሣ ከእግዚአብሔር እንዲደብቅ እና ጥሪውን እንዲሸሽ ከሚያደርግ የኃጢአተኛ ሰው አመለካከት የመነጩ ሊሆኑ ይችላሉ።

“ጌታን የሚፈልጉ ልቦች ሐሴትን ያድርጉ።” ምንም እንኳን ሰው እግዚአብሔርን ሊረሳ ወይም ላይቀበለውም ቢመችልም እርሱ ግን፣ እያንዳንዱን ሰው እርሱን በመሻት ደስታን ሕይወትን ያገኝ ዘንድ መጣራቱን አያቋርጥም። ሆኖም ይህ እግዚአብሔርን ለማግኘት የሚደረግ ፍለጋ የሰውን ልጅ ከፍተኛ ጥረት ጽኑ ፍላጎት “ንፁህ ልብ” እና እግዚአብሕIርን ስለመፈለት የሚያስተምሩ የሌሎችን ምስክርነት ይጠይቃል።

ጌታ ሆይ አንተ ታላቅ ነህ ከፍ ከፍም ልትል ይገባሃል፣ ኃይልህን ታላቅ ጥበብህም ወሰን የለውም። የፍጥረትህ ትንሹ አካል ሰው ሊያስመሰግንህ ይሻል። በርግጥም ይህ ሰው ፈራሽ ነው። የኃጢያትን ምልክትና አንተ ትዕቢተኛውን የምታቃወም መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃም የተሸከመ ነው። ይህም ሁሉ ሆኖ ሰው ምንም እንኳ የፍጥረትህ ትንሹ አካል ቢሆንም ሊያመሰግንህ ይሻል። አንተው ራስህ በምስጋና ሐሴት እንዲያገኝ ታበረታታዋለህ። እኛን ለራስህ ሠርተኸናልና ልባች ባንተ እስኪያርፍ ድረስ ዕረፍት የለውም።

2. እግዚአብሔርን የምናውቅባቸው መንገዶች

በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሮ እርሱን ለማወና ለመውደድ የተጠራ፣ እግዚአብሔርን የሚሻ ሰው እርሱን የሚያውቅባቸው አንዳንድ መንገዶችን ያገኛል። እኒህ መንገዶች የእግዚአብሔር ህላዌ ማረጋገጫዎች ተብለው ይጠራሉ፤ ይህም በተፈጥሮ ሳይንሶች እንደሚታወቀው አይነት ሳይሆን “በሚጣጣሙና በአሳማኝ ክርክሮች” ላይ ተመስርቶ ስለ እውነታው እርግጠኛ እንድንሆን የሚያስችለን ነው።

እነኝህ እግዚአብሒርን ከፍጥረት አንጻር የመመርመር “ዘዴዎች” ሁለት አቅጣጫዎች ኣሏቸው። ቁሳዊው ዓለምና ሰብአዊው ፍጡር።

ዓለም ከእንቅስቃሴ፣ ከመሆን ፣ ከአጋጣሚና ከዓለም ሥርዓትና ውበት በመነሣት ማንም ሰው እግዚአብሔር የዓለም መነሻና መድረሻ የመሆኑን ዕውቀት መጨበጥ ይችላል።

ቅዱስ ጳውሎስ ስለ አሕዛብ እንዳለው፤ ስለ እግዚአብሒር ማወቅ የሚቻለው ሁሉ ለእነርሱ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ኣሳይቷቸውዋልና። ዓለም ከተፈጠረ ጀመሮ የርሱ ስውር ባሕርይ፣ ማለትም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ በፍጥረታቱ ሁሉ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ይታያል።

ስለዚህ ቅዱስ አውግስጢኖስም ይህን መጠይቅ ያቀርባል፤ እስቲ የመሬትን ውበት ተጠራጠሩ፣ እስቲ የባሕርን ውበት ተጠራጠሩ፣ እስቲ ራሱን በራሱ የሚያሠራጨውንና የሚሰበስበውን የአየር ውበት ተጠራጠሩ፣ እስቲ የሰማዩንም ውበት ተጠራጠሩ፣ እስቲ እነዚን ሁሉ እውነቶች ተጠራጠሩ፣ ሁሉም “እኛ ውብ ነን” ይላሉ። ውብታቸውን ምስክርንተ ነው። እነዚህ ውበቶች ለለውጥ ተገዥዎች ናቸው። ለለውጥ ተገዢ ካልሆነው ከአንዱ ውብ አምላክ በቀር ማን ሊሠራቸው ይችላል?

ሰብአዊ ፍጡር። ለእውነትና ለውበት ካለው ግልጽነት፣ ለበጐ ምግባር ካለው ስሜት፣ ከነጻነቱና ከሕሊናው ድምፅ በሚመነጭ ለዘለላለማዊነትና ደስታን ለመላበስ ካለው ጉጉት የተነሣ ሰው ራሱን ስለ እግዚአብሔር ህልውና ይጠይቃል። በእነዚህ ሁሉ የራሱን ረቂቅ ነፍስ ምልክቶች ይረዳል። “ቁሳዊ ወደ ሆነው ብቻ የማይሸነሸነውና በውስጣችን ያለው የዘላለማዊት ዘር” ነፋስ ምንጩ ሊሆን የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ዓለምና ሰው በውስጣቸው የመጀመሪያው ጥንስስም ሆነ መጨረሻ እንደሌላቸው፤ ነገር ግን መጀመርያና መጨረሻ በሌለው ራሱ በህላዌ እንደሚሳተፉ ይመሰክራሉ። ስለዚህ የፍጥረታት ሁሉ መጀመርያና መጨረሻ የሆነ ሰው ሁሉ “ ‘እግዚአብሔር’ ብሎ የሚጠራው” አንድ እውነት እንዳለ ሰብአዊ ፍጡር በብዙ መንገዶች መገንዘብ ይችላል።

የሰው ልጅ አእምሮ አካላዊ አምላክን ሊያሳውቀው የሚያስችል ብቃት አለው። ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመፍጠር እንዲችል እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ለመግለጥና ሰውም በእምነት እንዲቀበለው የሚያስችል ጸጋውን ለመስጠት ፈቀደ። የእግዚአብሔር ሕልውና ማረጋገጫዎች አንድን ሰው ከእምነት እንዲደርስና እምነት ከአመክንዮ ጋር እንደማይፃረር እንዲያይ ያግዙታል።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት