Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የእግዚአብሔር ሕዝብ በደም ትስስር በመሬትና በአገር ድንበር የቆመ አይደለም

መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔርና በሰው ልጅ መካከል የሚደረግ ቀጣይ ውይይት ነው

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የእለተ ረቡዕ ኣጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ

Papa1ውድ ወንድሞችና እህቶች፧ ባለፉት ወራት ጸሎትን በሚገባ ለመማር፤ በብሉይ ኪዳን በሚገኙ ታላላቅ የጸሎት ምሳሌዎች በመመልከት እንዲሁም መዝሙረ ዳዊት፤ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶችና የዮሐንስ ራእይ በመቃኘት፤ ከሁሉ በላይ ግን ኢየሱስ ከሰማያዊ አባቱ ጋር የነበረው ግንኙነት መሠረታዊና አንድያ የጸሎት ምሳሌ ላይ በማተኰር በእግዚአብሔር ቃል ብርሃን ተጉዘናል፣ እንደ እውነቱ ከሆነ በልጅነት መንፈስ ከሚያፈቅረው አባቱ ከእግዚአብሔር ጋር ጥልቅና የጋለ አንድነት ሊፈጥር የቻለው ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ የሆነው ክርስቶስ ብቻ ነው፣ ፍቅር በተሞላ ስሜት "አባ! አባታችን" ብለን ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የምንችለው በእርሱ ብቻ ነው፣ እንደ ሐዋርያት እኛም ኢየሱስን "ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን" (ሉቃ 11፤1) በማለት ደጋግመን እንደጠየቅነው አሁንም እንጠይቀው፣

ከዚህ ሌላም ከእግዚአብሔር ግላዊ ግንኙነት ለመረዳትና ይህንን በጋለ መንገድ ለመኖር፤ ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ክርስቶስ አንደኛ ስጦታ የሆነውን መንፈስ ቅዱስ መለመን እንዳለብን ተምረናል፤ ምክንያቱም "መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል"(ሮሜ 8፡26)፣

እዚህ ላይ በቅዱስ መጽሐፍ ተመርኩዘን ስለጸሎት ብዙ የትምህርተ ክርስቶስ ክፍለ ግዜዎች ካየን በኋላ "በመንፈስ ቅዱስ ለመታነጽ

ከእግዚአብሔር ጋር እና በእግዚአብሔር አስተሳሰብ ገብቼ ለመጸለይ እንዴት እችላለሁ? እንዴት መጸለይ እንዳለብኝ የሚያስተምረኝና ድካሜን በማገዝ ወደ እግዚአብሔር በሚገባ ለመጸለይ እንዴት ይረዳኛል? ብለን መጠየቅ እንችላለን።

ባለፉት ሳምንታት እንደተመለከትነው መጀመርያው የጸሎት ትምህርት ቃለ እግዚአብሔር ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔርና በሰው ልጅ መካከል የሚደረግ ቀጣይ ውይይት ነው፣ በዚሁ ውይይት እግዚአብሔር ቅርብ ሆኖ ይታያል፣ በዚህም ሁሌ ገጽታውን ድምጹንና ማንነቱን ለማወቅ እንችላለን፣ የሰው ልጅም እግዚአብሔርን ማወቅንና ከእርሱ ጋር መነጋገርን ይቀበላል፣ ስለዚህ ባለፉት ሳምንታት መጽሐፍ ቅድስን በማንበብ በዚሁ ቀጣይ ውይይት እንዴት አድርገን ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት እንደምንችል አስተንትነን ነበር፡፡

ከዚህ የተሻለ ሌላ ክቡር ነገር አለ፤ የጸሎት ሕይወትን የሚያሳድግ ከእግዚአብሔር ጋር ጠበቅ ያለ ግንኙነት ያለው የሕይወት ውኃ ምንጭ የሆነ እጅግ የከበረ ምንጭ አለ፣ ይህም የቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ ወይንም ሊጡርጊያ ነው፡፡

የሥርዓተ አምልኮ ምሥጢር እግዚአብሔር በሁሉም ጊዜና በሁሉም ቦታ በቅጽበት ወዲያውኑ ለእያንዳንዳችን የሚናገርበት እና ከእኛ መልስ የሚጠብቅበት ታላቅ ክንውን ነው።

ሥርዓተ አምልኮ ምንድር ነው? ሁሌ ታላቅ ሀብትና ምንጭ የሆነው አዲሱን የካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ ማንበብ እንችላለን "በመሠረቱ ቀደም ሲል ሥርዓተ አምልኮ የሚለው ቃል ትርጉሙ ሕዝባዊ ተግባር ወይም በሕዝብ የሚደረግ አገልግሎት ማለት ነው" (ቁ. 1069) ትምህርተ ንባበ መለኮት ይህንን ቃል ከግሪክ ቢወስደውም በመስቀል ላይ እጁን ዘርግቶ በአንዱ እግዚአብሔር ሰላም ለሰበሰበውና ክርስቶስ በወለደው አዲስ የእግዚአብሔር ሕዝብን ግምት ውስጥ በማስገባት ይህንን ትርጉም ሰጠው፣ "በሕዝብ ስም የሚደረግ አገልግሎት" ሲል በገዛ ራሱ የሚቆም ሳይሆን ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ ፋሲካ ምስጋና ይግባውና በዚህ ፋሲካ የቆመ ሕዝብ ነው፣ እንደ እውነቱም ከሆነ የእግዚአብሔር ሕዝብ በደም ትሥሥር በመሬትና ባገር ድንበር የቆመ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተግባርና በእርሱ በሚከናወነው የእግዚአብሔር አብ ኅብረት ይወለዳል።

በአዲሱ የቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ በክርስቲያን ትውፊት ሥርአተ አምልኮ የሚለው ቃል "ሕዝበ እግዚአብሔር "በእግዚብሔር ሥራ" አንደሚሳተፍ የሚገልፅ መሆኑን ያመለክታል። ምክንያቱም ሕዝበ እግዚኣብሔር እንዳለ የሚኖረው በእግዚኣብሔር ሥራ ስለሆነ ነው። ይህንን ጉዳይ የዛሬ 50 ዓመት የተካሄደው የቫቲካን ጉባኤም መክፈቻውን በሥርዓተ አምልኮ ጥናት ማድረጉና ታህሳስ 4 1963 ዓ.ም. ጉባኤው ለመጀመሪያ ያጸደቀው ሰነድ የሥርዓተ አምልኮ ሰነድ ነበር። ይህ የሆነበት ማለትም የጉባኤው የመጀመርያ ሰነድ የሥርዓተ አምልኮ መሆኑ ለብዙዎች የዕድል ጉዳይ መስሎ ይታይ ነበር። በጉባኤው ከጸደቁ ሰነዶች የሥርዓተ አምልኮው ሰነድ ብዙ የማያከራክር ቢመስልም የጉባኤውን የአሠራር ጥበብ እንዲያሳድግ አድርጎታል። ሆኖም ግን ያጋጣሚ ነገር ቢመስልም ያለ ምንም ጥርጥር ትክክለኛው ምርጫ መሆኑን ያረጋግጣል፣ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያንን ከሚመለከቱ ጉዳዮች በቅደም ተከተልና በይዘት የመጀመሪያ ደረጃውን የያዘ የሥርዓተ አምልኮ ርዕስ ነው፣ ጉባኤው ስለ ሥርዓተ አምልኮ ለማጥናት ሲጀምር ጥርት ባለ መልኩ የመጀመሪያውን ቦታ የሰጠው ለፈጣሪው ነው። ከሁሉምና ከምንም በላይ እግዚአብሔር ነውና፡፡ የጉባኤው ምርጫ እራሱ ሥርዓተ አምልኮን መሆኑን ይገለፅልናል። በእግዚአብሔርን ላይ ማተኮር ቅድሚያ ካልተሰጠው ሁሉም ነገር አቅጣጫውን ይስታል።

የሥርዓተ አምልኮ ዋና መመዘኛው ነጥብ በእግዚአብሔር ላይ ማተኮር ነው፤ እንዲህ በማድረጉም በእግዚኣብሔር ሥራ ይሳተፋል፣ ሆኖም ግን እኛ ልንሳተፍበት የተጠራነው በየትኛው የእግዚብሔር ሥራ ውስጥ ነው ብለን እራሳችንን መጠየቅ እንችላለን? ለዚህ መልሱ የጉባኤው የሥርዓተ አምልኮ ሰነድ ሁለት መልሶችን ይሰጠናል። በቁጥር 5 ላይ ሲገልፅልን የእግዚአብሔር ሥራ በደህንነት ታሪካችን የፈጸማችው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ያገኘነው ደህንነት ነው። ሆኖም ግን ሰነዱ በቁጥር 7 ላይ ሥርዓተ አምልኮ ስንፈፅም የሥርዓቱ ማሳረግ ሥራ ራሱ "የክርስቶስ ተግባር ነው" ይለናል። በእርግጥም ሁለቱ ትርጉሞች የተሳሰሩ ናቸው። ዓለምና ሰውን የሚያድነው ማን ነው ብለን የጠየቅን እንደሆነ ያለን ብቸኛ መልስ በመስቀል ላይ የሞተውና ከሙታን ተለይቶ የተነሣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህን ደህንነት ያመጣ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ምሥጢር፣ ዛሬ ለእኛ ለኔ እንዴት እውን ይሆናል? መልሱ በክርስቶስ ሥራ በቤተክርስቲያን አማካኝነት ይህም በሥርዓተ ዓምልኮ በተለይም የእግዚኣብሔር ልጅ መሥዋዕት የሆነበት የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሕያው በሚያደርግ በምሥጢረ ቅዱስ ቁርባን እውን ይሆናል። እንዲሁም ከኃጢአት ሞት ወደ አዲስ ሕይወት የምንለወጥበት ምሥጢረ ንስሐና ወደ ቅድስና በሚያደርሱን ሌሎችም ምስጢራት እውን ይሆናሉ። እንዲህ ባለ መንገድ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የያዘ ምስጢረ ፋሲካ የጉባኤው ሥርዓተ አምልኮአዊ ትምህርተ መለኮት ማእከል መሆኑን ያሳያል።

ወደፊት አንድ እርምጃ እንራመድና፤ ይህ የክርስቶስ ምሥጢረ ፋሲካ እውን እንዲሆን የሚያደርገው ምን ይሆን? ብለን እንጠይቅ፣ ር.ሊ.ጳ ብፁዕ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቅዱስ ጉባኤ የሚለው የሁለተኛ ቫቲካን ሰነድ ከታወጀ በ25ኛው ዓመት ዝክር የሚከተለውን ጽፈዋል፣ "ክርስቶስ ምሥጢረ ፋሲካን ውብ እና እውን ለማድረግ ሁሌ በቤተ ክርስቲያኑ ሕያው ነው፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ በሥርዓተ አምልኮ ተግባር፣ ስለዚህም ሥርዓተ አምልኮ ክርስቲያኖች ከእግዚብሔርና እሱ ከላከው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚገናኙበት ልዩና የተከበረ ቦታ ነው (ዮሐ 17.3 )፣" በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስም የሚከተለውን እናነባለን፣ "እያንዳንዱ የሥርዓተ አምልኮ ክንውን የእግዚብሔር ልጆች ከአባታቸው ጋር በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ የሚገናኙበት መንገድ ነው። ይህም ግንኙነት በቃላትና በድርጊት አማካይነት የሚገለጽና የውይይት መልክ ያለው ነው።" (ቁ.1153) ይሁን እንጂ በመጀመሪያ ሥርዓተ አምልኮን ለማክበር የሚያስፈልገው በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገርና በተለይም ድምፁን በማዳመጥ መልስ መስጠት ነው።

አቡነ ብሩክ በሕገ ገዳሙ መዝሙረ ዳዊትን ስለመድገም ለመነኩሴዎች ሲያስተምሩ "ሃሳባችን (ልባችን) ከድምፃችን ጋር መስማማት" እንዳለበት ይናገራሉ፣ ቅዱሱ የመዝሙረ ዳዊት ጸሎት ቃላቶች አሳባችንን መቅደም እንዳለባቸው ያስተምራሉ፣ ሁል ጊዜ ግን በዘልማድ እንዲህ አይደለም፣ መጀመሪያ ማሰብ አለብን ከዚያ በኋላ ያሰብነውን በቃላት እንናገራለን፣ በሥርዓተ አምልኮ ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ ይቀየራል የሚቀድመው ቃሉ ነው፣ እግዚአብሔር ቃልን ቅዱስ ሥርዓተ አምልኮ ደግሞ ቃላትን ያበረክቱልናል፣ እኛም በቃላቱና በትርጉማቸው ውስጥ በመግባትና በመቀበል ከእርሱ ቃል ጋር በመስማማት የእግዚአብሔር ልጆችና እሱንም መምሰል እንችላለን፣ የቅዱስ ጉባኤ ሰነድ እንደሚያስታውሰን "ሥርዓተ አምልኮውን ውጤት እንዲኖረው፤ምእመናን በቅን መንፈስ ተዘጋጅተው ሐሳባቸው ከአፋቸው ከሚወጣው ቃል ጋር በማስማማት መለኮታዊውን ጸጋ ለከንቱ እንዳይቀበሉ ከእርሱ ጋር በመተባበር መሥራት አለባቸው" (ቍ.11)፣ በሥርዓተ አምልኮ ከእግዚአብሔር ጋር በምናከናውነው ውይይት መሠረታዊና ተቀዳሚ ነገር ከአፋችን በሚወጡ ቃላትና በልባችን በምናስበው መካከል ሙሉ ስምምነት መኖር አለበት፣ በታላቁ የጸሎት ታሪክ ቃላት ውስጥ በመግባት ራሳችንን በእነዚህ ቃላት መንፈስ እናስማማለን በዚህም ከእግዚአብሔር ጋር መናገር እንችላለን።

ከዚሁ መስመር ሳልወጣ በሥርዓተ አምልኮ ጊዜ ከሚፈጸሙ ነገሮች ስለአንድ ጉዳይ መጥቀስ እፈልጋለሁ፣ ሥርዓተ አምልኮው ራሱ ከምንሰማው ቃለ እግዚአብሔር በምንናገረውና በምንፈጽመው ስምምነት እንዲኖረን ይጠራናል ይረዳናልም፣ መሪው ሠራዒ ካህን ጸሎተ አኰቴተ ቍርባንን ሲጀምር "አልዕሉ አልባቢክሙ" - ልባችሁን አንሡ - የሚለውን ነው፤ ይህም ማለት ከሚያስጨንቁንና ከሚያሳስቡን፣ ፍላጎቶቻችን፣ ጭንቀቶቻችንና ሐሳባችን ከሚሰርቁ፣ ነገሮች ልባችንን ከፍ እናድርግ ማለት ነው፡፡ ከሁሉም ነገር እጅግ ቅርባችን የሆነው ልባችን በትሕትና በእግዚአብሔር ቃል ዝግጁ በመሆን ከሚሰማቸውና ከሚደግማቸው ቃላት ትኩረቱን ወደ እግዚአብሔር እንዲያደርግ በቤተ ክርስቲያን ጸሎት መሳተፍ አለበት፣ የልባችን ትኩረት ሁሌ በመካከላችን በሚገኝ በእግዚአብሔር ማነጣጠር መሠረታዊ ዝግጅት ነው፣

እንዲህ ባለ ጥልቅ ስሜት ሥርዓተ አምልኮን የፈጸምን እንደሆነ ልባችን ወደ ታች ከሚስበው ስበት ከፍ ብሎ በኅሊና እውነትና ፍቅር ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ወደ ላይ ይወጣል፣ የቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ በቁ. 2655 "በሚጸልይ ልብ ውስጥ የሚቀጥለውን የድኅነት ምሥጢር የክርስቶስና የመንፈስ ቅዱስ ተልእኮ የሚያውጀው፤ የሚያቀርበውና የሚያስተላልፈው በቤተ ክርስትያን ምሥጢራታዊ ሥርዓተ አምልኮ አማካኝነት ነው፣ መንፈሳውያን ጸሐፍት አንዳንድ ጊዜ ልብን ከመሠዊያ ጋር ያነጻጽሩታል" እንዳለው ሁሉ የእግዚአብሔር መንበረ ታቦት ልባችን ነው።

ውዶቼ! ሥርዓተ አምልኮን በሚገባ የምናሳርገውና የምንኖረው በጸሎት መንፈስ ስናደርገው ነው፤ እንድንታይ ወይንም ሌላ ነገር ለማድረግ ካልፈለግን ነገር ግን የልባችን ትኵረት ወደ እግዚአብሔር በማድረግ ከክርስቶስ ምሥጢር ጋር እና ከአባቱ ጋር ባለው የልጅነቱ ውይይት በመተባበር መንፈሳችን በጸሎት ስንቆጣጠረው ብቻ ነው፣ ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚያረጋግጥልን እንዴት እንደምንጸልይ እግዚአብሔር ያስተምረናል፣ (ሮሜ 8፡26) ወደ እርሱ እንድናተኩር እርሱ ራሱ ቃላትን ይሰጠናል፣ እነኚህን ቃላት በመዝሙረ ዳዊት እና በሌሎች ትላልቅ የሥርዓተ አምልኮ ጸሎቶች እንዲሁም በመሥዋዕተ ቅዳሴ ሥርዓት እናገኛቸዋለን፣ ከመንፈስ ቅዱስና ከእኛ የሚፈልቀው የሥርዓተ አምልኮ ጸሎት፤ ሰው በሆነው ልጁ አማካይነት ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር አብ ያቀና እና የእግዚአብሔርና የሰው ልጅ ተግባር መሆኑን መረዳት እንድንችል ዘንድ እግዚአብሔርን እንለምነው።

ምንጭ፡- ራድዮ ቫቲካን

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።