Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጅ ተስፋ ኃይልና ትርጉም ይሰጣል

ቅ.አባታችን ር.ሊ.ጳ ቤኔዲክቶስ 16ኛው በበዓለት ትንሣኤ ምክንያት በየዓመቱ እንደሚያደርጉት ሁሉ ትናንትና በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ለተሰበሰቡት ከ100 ሺ በላይ ለሚሆኑ ም እመናን ‘ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ የነጻነት የፍትሕና የሰላም ጐዳና ከፈተልን’ ሲሉ ስለትንሣኤ ምሥጢር ካስተማሩ በኋላ ኡርቢ ኤት ኡርቢ ማለትም ለከተማዋና ለመላው ዓለም የተሰኘውን የትንሣኤ መልካም ምኞት በተለያዩ ቋንቋዎች ገልጠዋል።

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን ሲከፍቱ ‘ክርስቶስ ተንሥኣ እሙታን፤ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ’ የሚለው የሰው ልጅ ታሪክን ለአንዴና ለመጨረሻ የለወጠው መልካም ዜና ዛሬም ከሁለት ሺ ዓመታት በኋላ በመላው ዓለም እያስተጋባ ነው። የዕለቱ መዝሙር እንደሚለው

‘ይትፌሣሕ ሰማይ ወትትሐሰይ ምድር፤ ማለትም ሰማይና ምድር ደስ ይበላቸው’ ይህም የሰው ልጅ የመዳን ጎህ መቅደዱን የሚያመለክት ትልቅ ደስታ በኢየሱስ መዳኑን ነው።
ዛሬ የምንኖርባት ዓለም በመገናኛ ብዙኃን እጅግ ወደፊት መጥቃ ብትገኝም የክርስትና እምነታችን የሚመሠረተው ከሙታን ተለይቶ የተነሣውን ክርስቶስ ያዩ ሰዎች በሰጡን ምሥክርነት ነው።
የክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ መነሣት የአስተንትኖ ውጤት አሊያም የሰቂለ ኅሊና ውጤትም ኣይደለም። ከታሪክ ባሻገር የሚጓዝ ፍጻሜ ነው፤ ሆኖም ግን እርግጠኛ በሆነ ወቅት የተከናወና በሰው ልጅ ታሪክ የማይደመሰስ ማኅተም ያኖረ ፍጻሜ ነው። የጌታ ኢየሱስ መቃብርን በመጠበቅ ላይ የነበሩት ወታደሮች ዓይኖችን ያጭበረበረ ብርሃን ጊዜና ቦታን ተሻግሯል፤ የተለየ ብርሃን ነው፤ መለኮታዊ ብርሃን ነው። ይህ ብርሃን የሲኦልና የሞት ጨለማን ጥሶ የእውነትና የርኅራኄ ጮራ የሆነውን የእግዚኣብሔር ጮራ ለዓለም ያስገኘ ብርሃን ነው።
የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጅ ተስፋ ኃይልና ትርጉም ይሰጣል፡ ሆኖም ግን በዘመናችን ከትንሣኤ ሃሌ ሉያ ዜማ በትይዩነት የሚሰማ አሰቃቂ የሥቃይ እሪታ የድህነት፣ የረሃብ፣ የሕመም፣ የውግያና የዓመጽ እሮሮ እየተሰማ ነው። ክርስቶስ የሞተው ይህንን ለማቃለል ቢሆንም ቅሉ የሰው ልጅ ልቅሶ ገና አላበቃልም። ስለዚህ ለሁሉም የሰው ልጆች ከሁሉ በላይም በአሁኑ ግዜ የቀራንዮ ሕማማት - ስቃይን - በሚያሳልፉ ሕዝቦች ዘንድ ይህ መልእክቴ እንደ ትንቢታዊ መልካም ዜና እንዲደርስ እፈልጋለሁ፤ ‘ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ የነጻነት የፍትሕና የሰላም ጐዳና እንዲከፍትላቸው’ ምኞቴ ነው።
ቅዱስነታቸው ለመላው ዓለም ዕርቅና ሰላም እንዲወርድ ምኞታቸውን ሲግለጡ በተለይ በቅድስት መሬት በመካከለኛው ምሥራቅና በአይቮሪ ኮስት የሰላምና የሰው ልጅ ክብር ብርሃን የሆነው የትንሣኤ ብርሃን በሃገራቱ ላይ ነግሦ ባለው የመለያየት የጥላቻና የዓመጽ ጨለማን ድል እንዲነሣ፤ እንዲሁም በሊብያ የብዙ ሰዎች ሕይወት በመቅሰፍ ላይ የሚገኘው ጦርነት እንዲወገድ፤ መፍትሔውም ከጦርነትና ከጦር መሣርያ ሳይሆን ከውይይትና ከስምምነት መሆኑን በመረዳት በግጭቱ መሃከል ታጉረው ላሉ ደግሞ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደረግላቸው አደራ ብለዋል።
የጦርነት፣ የረሃብና የአምባገነን ጨቋኝ መንግሥታት ሰለባ በመሆን በስደት ላይ ስለሚገኙት አውስተውም እንዲህ ብለዋል:- ‘ባለ በጎ ፍቃድ ሰዎች እነኚህን ችግረኞች ለመቀበል ልባቸውን እንዲከፍቱ ጌታ በትንሣኤው እንዲያበራላቸውና ለስደተኞች ወንድሞቻችን አጋርነት በማሳየት ተጨባጭ እርዳታ እንዲያደርጉ ኣሳስባለሁ፤ አብነታዊ በሆነ መንገድ ምስክነታቸውን ለሚሰጡ በለጋስነት እነዚህን ችግረኞች በመርዳት ለሚገኙት ደግሞ የሚያደርጉትን በጎ ሥራ በልብ እንደምናደንቀውና እንደምናመሰግናቸው ለመግለጥ እወዳለሁ’ ሲሉ ሁላቸው የተቻላቸውን እንዲያበረክቱ አደራ ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ማገባደጃ ላይ በተፈጥሯዊ ኣደጋ ለተጐዱ ወገኖች በተለይም ብዙ ሕይወትና ንብረት የወደመባቸው የጃፓን ሕዝብን በማስታወስ ጽናትና ተስፋ እንዲያገኙ ምኞታቸውን ገልጠዋል።
በመጨርሻም በእምነታቸው ምክንያት በስደትና በሥቃይ የሚገኙ ክርስትያኖችን በማስታወስ ‘የጌታ ትንሣኤ መልካም ዜና ጽናትና እምነት ይስጣቸው’ ብለዋል።
በልባችን ውስጥ ደስታና ኃዘን አለ፤ እፊታችን ላይ የደስታ ፈገግታና የሥቃይ እንባ አለ፤ በዚህ ዓለም እስካለን ድረስ ሕይወታችን እንዲሁ ነው፤ ሆኖም ግን ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ በመካከላችን ይገኛል፤ ከእኛ ጋር ይራመዳል። ስለዚህ ለተልእኳችን ታማኞች በመሆን ፊታችንን ወደ ሰማይ በማዞር እየዘምርን እንራመድ’፤ ካሉ ብኋላ በ65 ቋንቋዎች የመልካም ትንሣኤ ምኞት ገልጠዋል፤ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝብም ብሩክ ፋሲካ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጠዋል።
ምንጭ፡- ራድዮ ቫቲካን

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።