በወንጌል የሕይወት ጎዳና በክርስቶስ መኖር
- Category: ዜናዎች
- Published: Tuesday, 14 April 2015 10:26
- Written by Super User
- Hits: 2327
- 14 Apr
በጥሩ ሁኔታ የታነጸ የምንኩስና ጥሪ በቁጥር ብዙ ከሆነው ጥሪ የበለጠ ጠቃሚ ነው ሲሉ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ባለፈው ቅዳሜ በቫቲካን ለተሰበሰቡ የምንኩስና ጥሪ ላይ በኀላፊነት ለሚያገለግሉ ተጋባእያን አሳሰቡ።
“የምንኩስናን ሕይወት ውበት በሕይወት ማስተላለፍ ስኬታማነት ባለበት ቦታ የጥሪ መቃወስ የለም፤ የምንኩስና ሕይወት በተዳከመበት ቦታ ቢሆንም እንኳ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር እጩዎችን ማብዛት ሳይሆን የአያያዙ ጥራት ላይ መሆን አለበት” ብለዋል ር.ሊ.ጳ.።
“በወንጌል የሕይወት ጎዳና በክርስቶስ መኖር” በሚል ርእስ ከመጋቢት 9 እስከ ሚያዝያ 3 በተደረገው የአምስት ቀናት ኮንፈረንስ 1300 የሚሆኑ የምንኩስና ጥሪ ኀላፊዎች ተገኝተው ተሳታፊ ሆነዋል። ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ለነዚሁ ተሳታፊዎች በሥራቸው እንክብካቤ ለሚገኙት ወጣት እጩዎች ያላቸውን ልዩ ፍቅርና የዚህን አገልግሎት ወሳኝነት ገልጸዋል።
“የምንኩስና ሕይወት ውብ ነው። በጥምቀት ጥሪ ውስጥ የተተከለ የቤ/ያን የከበረ ሀብት ነው” በማለት ስለ ምንኩስና ሕይወት ምንነት ተናግረዋል። አያይዘውም በዚህ የምንኩስና ጥሪ ላይ በኀላፊነት የሚያገልግሉ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በጠራቸው ውስጥ የልጁን ልብ ከሚያትመው ከእግዚአብሔር አብ ሥራ ጋር በልዩ መብት ተሳታፊ መሆናቸውን አስታውሰዋል። እንዲሁም እነዚሁ ኀላፊዎች በሥራቸው ለተሰጡ ወጣቶች እውነተኛ እናቶችና አባቶች እንዲሆኑና የሰፊ ልብ ባለቤት በመሆን ሀሉንም መቀበል የሚችሉ ልበ ሰፊ የሆኑ መነኮሳትን ማዘጋጀት እንዲችሉም አደራ ብለዋል።
በስተመጨረሻም ር.ሊ.ጳ. ለምንኩስና የማዘጋጀት ኀላፊነት ከሌላ ተግባራት ቢገታቸውም ኀላፊዎቹ ይህ አገልግሎት ሸክም እንደሆነ እንዳያስቡ አስገንዝበው፤ “ቤተ ክርስቲያን እናንተን ትወዳችኋለች፣ ትጸልይላችኋለችም፤ ያለእናንተ አገልግሎት የምንኩስና ሕይወት አይኖርም” በማለት ደምድመዋል።
ምንጭ፡- http://www.catholicnewsagency.com/news/pope-francis-vocations-are-about-quality-not-quantity-20907/