መላዪቱ ቤተ ክርስቲያንና ር.ሊ.ጳ. ከስደተኞች ጎን
- Category: ዜናዎች
- Published: Saturday, 09 April 2011 19:30
- Written by Super User
- Hits: 2099
- 09 Apr
Zenit.org - ከሊቢያ ተሰድደው ወደ ጣልያን ሲያመሩ በነበሩት 250 ስደተኞች ድንገተኛና ዘግናኝ ሞት ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ ጥልቅ ልባዊ ኀዘን የተሰማቸው መሆኑን ቫቲካን ቃል አቀባይ ገለጹ።
ረቡዕ መጋቢት 29 ቀን 2003 ዓም ማለዳ 300 ሰዎችን ያጎረች ጀልባ በሊቢያ ያለውን ግጭት ለማምለጥ ወደ ጣልያን በማምራት ላይ ሳለች የመስመጥ አደጋ የደረሰባት ሲሆን በጀልባይቱ ውስጥ ከነበሩት ተጓዦች በሙሉ 50 ሰዎችን ብቻ በሕይወት መታደግ ሲቻል ከሞቱት ውሰጥም ሕፃናት ይገኙበት እንደነበር ታውቋል።
ኢየሱሳዊው ካህን አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ የቫቲካን ማስታወቂያ ቢሮ ኀላፊ አሳዛኙ አደጋ የር.ሊ.ጳ.ን ልብ በእጅጉ እንደነካ ለጋዜጠኞች ጠቅሰው
በዚህ በተለየ ሁኔታ ለስደተኞች አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ቅዱስ አባታችን የስደተኞችን ጉዳይ ከቅርብ በመከታተል ላይ መሆናቸውን አሳውቀዋል። በዚህ የሜዲትራንያን ባሕር አደጋ ሰለባዎች መካከልም የተወሰኑት በሊቢያ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ኤርትራውያን ካቶሊኮች ይገኙበት እንደነበረም ተገልጿል።
የድኽነትን ወይም የኢፍትሐዊነትን፤ የአመፅን ወይም የጥቃትን ሁኔታዎች በመሸሽ የሚቀበላቸውን፣ የሚከላከላቸውንና የበለጠ ሰብአዊ ሕይወትን ለመፈለግ ሲሉ በአስቸጋሪ ጉዞ ሕይወታቸውን የሚያጡትን የዚህን ዓይነት አደጋ ሰለባዎች፤ የማንኛውንም አገር ዜጎች ሕፃናትንና ሴቶችን ሁሉ ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስና መላዪቱ ቤተ ክርስቲያን በጸሎት እንደሚያስታውሷቸውም አሳውቀዋል።