Map St Joseph Cistercians

Top Panel

በክርስቶስ ትምህርት ዛሬም ሰዎች ይደናቀፋሉ

ከካስተል ጋንዶልፎ የበጋ ማረፊያቸው ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው የዕለቱን ወንጌል ማለትም ኢየሱስ በቅዱስ ቁርባን ሥጋውና ደሙ እንደሚገኝ ሲነግራቸው አይሁዳውያንና ደቀ መዛሙርቱ እንዳልተቀበሉት የሚገልጸውን የዮሐንስን ወንጌል ምዕ.6 ተመርኩዘው የተለመደው የእሑድ መልአከ እግዚአብሔር አስተምሯቸውን አስተላልፈዋል። የክርስቶስ ተከታዮች ትምህርቱን ለዘመኑ በሚመች ሁኔታ ከማስማማት ይልቅ ፈታኝ ለሆነው ለርሱ ትምህርት በሙሉ ሕይወታቸው መመለስ አለባቸው ብለዋል።
"አራተኛው ወንጌላዊ በጌታ ቃል በመደናገጥ ይህ ንግግር ከባድ ነው፤ ማን ሊቀበለው ይችላል እስከማለት የደረሱትን ሰዎችና ደቀመዛሙርት ሁኔታ ይነግረናል፤" ካሉ በኋላ "በዚህም ምክንያት ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ኢየሱስን መከተል ተዉ።" የሚለውን ከወንጌል አነበቡ። በመቀጠልም "ይህ ቢሆንም ቅሉ ኢየሱስ ንግግሩን ቀለል ሊያደርገው አልፈለገም። እንደውም በቀጥታ ወደ 12ቱ ሐዋርያት ዞሮ እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁን? አላቸው። ይህ ለማሰብ የሚጋብዝ ጥያቄ በዚያን ዘመን ለነበሩት ሰዎች ብቻ የተሰነዘረ አይደለም፤ ለዘመናት ሁሉ ለሰው ልጅ የሚቀርብ ጥያቄ ነው። የኢየሱስ ትምህርትን መቀበሉና መተግበሩ ከባድ መስሎ ስለሚታይ ዛሬም ቢሆን እውነት በማይመስለው ነገር ግን እውነት በሆነው በክርስትና እምነት ብዙዎች ይደናገጣሉ። በዚህም ምክንያት ክርስቶስን የማይቀበሉና የሚተዉ፣ ዕሤቱንና ትርጉሙን በማጣመም ትምህርቱን ለጊዜው ሁኔታ የሚመች ለማድረግ የሚሞክሩ ብዙዎች ናቸው።" ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ አስተምህሮዋቸውን ሲቀጥሉ " እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁን? የሚለው ጋባዥ ጥያቄ የያንዳንዳችንን ምላሽ በመጠበቅ በልባችን ውስጥ አሁንም ያስተጋባል፤ ርግጥ ነው ኢየሱስ ወጋዊና ውጫዊ በሆነው ሃይማኖተኛነት ደስተኛ አልነበረም። የመጀመሪያ ሰሞንና ስሜታዊ የሆነው ተከታይነትም ለርሱ በቂ አልነበረም። በተቃራኒው በዕድሜያችን ሙሉ በቀጣይነት የርሱ ሃሳብና ፈቅድ ተካፋዮች መሆን አለብን" ብለዋል ቅዱስነታቸው።
ወደ አስተምሯቸው መደምደሚያም ሲቃረቡ "እምነት እግዚአብሔር ለሰው የሚሰጠው ስጦታ ሲሆን የሰውም በነጻነትና በምልአት ለእግዚአብሔር መሰጠት ነው። እምነት  ለእግራችን መብራት ለጉዟችንም ብርሃን የሆነውን  የጌታን ቃል መስማት ነው።... ናዝራዊት አገልጋይ የሆነችውን እሷን የአምላክ እናትና የአማኞች ሁሉ አብነት ያደረጋትን በፍቅር የሆነው ይህ እምነት ሕያው ሆኖ በውስጣችን ይኖር ዘንድ ድንግል ማርያምን እንለምናታለን።" ካሉ በኋላ በዚያ ተሰብስበው ለነበሩ የምእመናን አንዳንድ የመንፈሳዊ ንቅናቄ ቡድኖች "እውቀት ሁልጊዜ አዲስ ነገር ነው፤ ትምህርት የሚታይና የሚዳሰስ ቁሳዊ ነገር ብቻ አይደለም፤...በያንዳንዱ የሰው ልጅ የማወቅና የማፍቀር ሂደት የሰው ልጅ ነፍስ ገና ልትቀበለው የሚገባት፣ ከፍ ብላ ልትደርስበት የሚገባት ከርሷ በላይ የሆነ ነገር እንዳለ ይታወቃታል" በማለት አጠቃለዋል። አጭር ቪዲዮ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።