እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel
× እንኳን ቤተኛ ሆኑን - Welcome to our forum!

ዘፈን_ኃጢአት_ነውን?

3 years 8 months ago #5 by Woldu101
በገላትያ 5፡21 “መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት” በሚለው ጥቅስ ላይ በመመርኰዝ ባሕላዊ ጨዋታና ማንኛውም ለእግዚአብሔር ክብር ከሚቀርብ መዝሙር ውጭ የሆነ ሙዚቃ ኃጢአት ነው የሚል አቋም አጋጥሞን ይሆናል፡፡
ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሃሳብ ከመጓዛችን በፊት ዘፈን በሚለው ቃል ላይ አንዳንድ ነጥቦችን ማንሳት ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡
1) ዘፈን በምንልበት ጊዜ በአአምሮአችን
የሚመጣው ምንድን ነው?
2) በቴሌቪዥን ወይም በሬዲዮ የሚቀርቡት
ድምጻውያንና የሚያጅባቸው የተወዛዋዦች
ቡድን እንደሁም የሚያጅባቸው የሙዚቃ
መሳሪያ ነውን?
3) ወይስ ወደ ሲኦል የሚወስድ አስፈሪ
ኃጢአት ነው?
4) በፊታችን የሚደቀነው የዚህስ ምክንያቱ ምን
ይሆን?
5) እንዳንዴ የሚከብዱ ወይም የሚዘገንኑ
ቃላት ወደ ጆሮአችን ሲደርስ
እንደሚያጋጥመን ዓይነት ነው ወይስ
ኃጢአት ነው ስለተባልን ብቻ ምሥጢሩን
ሳንረዳ እንዲሁ በመቀበለ የሚሰማን ነገር
ነው?
#በመሠረቱ_ባሕል_የሰው_ልጅን_ከእንስሳት_የሚለይ_ትልቅ_ስጦታ_ነው፡፡
ማንኛውም ባሕል በክርስቶስ ወንጌል ትምህርት የሚገመገምና የሚፈተን ሲሆን አስፈላጊነቱን ማመን ግን የግድ ይሆናል፡፡
ጌታችን ኢየሱሰ ክርስቶስም እኮ ወደ እኛ የመጣው በአይሁድ ባሕል ውስጥ ተወልዶና አድጎ ነው፡፡ በዚያ ባሕል የተቃወማቸው ነገሮች እንዳሉ ሁሉ የተቀበላቸውም ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በአይሁድ ሠርግ ላይ ባሕላዊ ውዝዋዜ እንደነበረ ይታወቃል፤ ብሉይ ኪዳንም ከሠርግ ጋር ስለሚገናኝ ሙዚቃና ጨዋታ ይናገራል፡፡
ጌታችንም በቃና ዘገሊላ ሠርግ ላይ ሲካፈል የሠርግ ዘፈን አልነበረም ለማለት የሚያዳግም ይሆናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃልን ስናነብ ስለአይሁድ ባሕል ብዙ ነገር እናገኛለን፡፡ ብሉይና አዲስ ኪዳንን ለመረዳትም ይህንኑ የአይሁድ ባሕል ማጥናት ሊጠቅመን ይችላል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር እራሱ በአንድ ዘመን በነበረ ባሕል፣ ቋንቋና ሥልጣኔ አማካኝነት መናገሩን አንዘንጋ፡፡
ወደ አገራችን ስንመጣ እንደ የጉራጌኛ፣ የኦሮምኛ፣ የትግርኛ፣ የአማርኛ፣ የወላይትኛ ወዘተ… ባሕላዊ ጨዋታን በመመልከት ወይም አብሮ በመሳተፍ ላይ ምን ክፋት አለ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡፡
1) በዚያ ውዝዋዜ ከአሥርቱ ትእዛዛት የትኛውን
እናፈርሳለን?
2) ከየትኛውስ በደል ሊመደብ ይችላል?
3) ከመግደል ወይስ ከመስረቅ በሐሰት
ከመመስከር ወይም ከማመንዘር?
አንዳንድ ጊዜ #ሙዚቃና_ድምጻዊነት_ለእግዚአብሔር_ክብር_ብቻ_መሆን_አለበት_የሚል_አባባል_አለ፡፡ ነገር ግን ቀጥታ ከእግዚአብሔር ክብር ጋር የማይገናኙ ሆኖም ኃጢአት የማንላቸው ብዙ ነገሮችም እንዳሉ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ #ለምሳሌ በቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ቃል ይነበባል ለእግዚብሔር ክበር ማለት ነው፤ ታዲያ እኮ በቤታችን የታሪክ ወይም የሳይንስ መጽሕፍትንም እናነባለን፡፡ #ንባብ_በሙሉ_በእግዚአብሔር_ክብር_መሆን_አለበት_ብለን_ከማንበብ_አንታቀብም_ወይም_ደግሞ በጋዜጣ፣ ታሪክ፣ ስነ-ጸሑፍ፣ የቋንቋ መጻሕፍት ሀጢኃአት ናቸው አንልም፡፡ ግብዣ፣ እሰፖርት፣ የተለያዩ ብሔራዊ በዓላት በቤተክርስቲያን ውስጥ አይከናወኑም፡፡ ነገር ግን ቁምነገር እንዳላቸው አምነን እናከብራቸዋለን እንጅ ኃጢአት ናቸው ብለን አናወግዛቸውም፡፡
#ታዲያ
1) ቅዱስ ጳውሎስ የሰው ልጅ ውበትን ጥበብን
የሚገልጽበትን ነገር ለምን አወገዘው?
2) እርሱ የተቃወመው እስካሁን
እየተነጋገርንበት ያለነውም ሙዚቃ ይሆን?
እሱን “ከመግደል፣ ከስካርና ከቅናት፣ ከመናፍቅነትና ከምቀኝነት” ጋር እንዴት ሊደምረው ይችላል፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶችም ሆኑ ሌሎች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በመጀመሪያ የተጻፉት በግሪክ ቋንቋ ስለሆነ “ዘፋኝነት” በሚል ቃል የተተረጐመው የትኛው የግሪክ ቃል መሆኑን ማየት ያስፈልጋል፡፡
#ቅዱስ_ጳውሎስ #በግሪክ_ቋንቋ “ #ኮማይ” ብሎ ያስቀመጠውም ቃል የአማርኛ መጽሐፈ ቅዱስ /የ1985 እና የ1972 ዓ.ም. ትርጉም/ በዘፋኝነት ይተረጉመዋል፡፡
እርግጥ ቅዱስ ጳውሎስ በሚያወግዘው ድርጊት ውስጥ ዘፈንና ሙዚቃ ይኖራል፡፡ ነገር ግን “ኮማይ” የሚለው ቃል ከላይ በተጠቀሰው ዘፈን የሚፈታ አይመስለንም፡፡ “ #ኮማይ” ከልቅ ግብረሥጋ ጋር የሚገናኝ ትርጉም አለው፡፡ ሰዎች ለጣዖት አምልኮ እየበሉና እየጠጡ የሚፈፅሙትን ሕገ ወጥ የዝሙት ኃጢአት ያመለክታል፡፡ ይህም በሮማውያንና በግሪካውያን ዘንድ ይፈፀም ነበር፡፡ እንግዲህ ቅዱስ ጳውሎስ “ይህንን የሚፈፅሙ የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም” ያለበትም ምክንያት አሁን መረዳት እንችላለን፡፡
ለዚህ ተጨማሪ ማረጋገጫ ከፈለግን ብዙ ሰዎችን የእንግሊዘኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን መመልከት እንችላለን፡፡ እንግሊዝኛው “ኮማይ” የሚለው ቃል “Orgy” ብሎ ይፈታዋል፡፡ በአንጻሩ በቴሌቪዥን ወይም በሬዲዮ የሚቀርበው ዘፈን “Song” የሚባል ይመስለናል፡፡
በመጨረሻም በአዎንታዊ ትርጉሙ በዘፈን ተፈጥሮን፣ ውበትን፣ፍቅርን፣ መልካም ነገሮችን ማድነቀ እንደምንችል እናውቃለን፡፡ ያን ደግሞ እግዚአብሔር የሚቃወመው አይመስልም፡፡
ስለ ወንድና ሴት ፍቅር መዝፈን ኃጢአት ከሆነ “መኃልይ ዘሰለሞን” የተባለውን መጽሐፍ ምን ልንለው ነው፤ እሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡
በየትኛውም ደረጃ ብንተረጉመው በቀጥታም ሆነ በተምሳሌነት የወንድና የሴት ፍቅር ይገልጻል፡፡
እንግዲህ አስቀድመን ከመፍረዳችን በፊት ምን ዓይነት ዘፈን ብለን መለየት ያስፈልገናል፡፡ ወደ ኃጢአት ይመራል ወይስ ትምህርታዊ መልእክት አለው? በለን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በ1879 ዓ.ም የታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በገላትያ 5፡21 ላይ “ #ዘፋኝነት” ተብሎ የተተረጐመውን ቃል “ #ማሶልሶል” በሚል ቃል ነው የሚተረጉመው፡፡ ሊፈጠር ከሚችለው የምሥጢር መዛባትና የትርጉም እሻሚነት የሚያድን ቃል ይሆን? ወይስ “መስከር” የሚለው ቃል ከሁሉም ይሻል ይሆን፡፡
#ምክንያቱም የግሪኩ ቃል ቅጥ ማጣትንና መስከርን ያሰማልና፡፡ በመሠረቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የግዕዙ አዲሰ ኪዳን ገላትያ ምዕራፍ 5 ላይ “ስክረት” እንጂ “ዘፈን” አይደለም፡፡
የቃላቱን ትርጉም ለማመዛዘን ይረዳን ዘንድ የተለያዩ መዝገበ ቃላት ስለ ዘፈን ወይም ስለመሶልሶል የሚሉትን እንመልከት፡፡
#ስለ_ዘፈን፦
የደስታ ተ/ወልድ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል “ዘፈን” “ቀነቀነ፣ አወረደ፣ ግጥም ገጠመ፣ አዜመ፣ አንጐራጐረ፣ ዘለለ፣ ተረገረገ”
የአማርኛ የመጽሐፍ ቅድስ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላይ (ገጽ. 2ዐ2-2ዐ3)
“በቅኔና በግጥም ከልዩ ልዩ መሣሪያ ጋር እየተቀነባበረ የሚቀርብ የደስታ ምልክት በልደት ቀን (ኢዮብ 21፡ 11-12፣ ማቴ. 14፡6) በሠርግ ቀን (ኤር 31፡4፣ ማቴ.11፡17) በድል በዓል ቀን (ዘጸ.2ዐ፡21፣ ምሳ. 11፡34፣ 1ሳሙ.18፡6) በመንፈሳዊ በዓል ቀን (2ሳሙ. 6፡14) የደረጋል፡፡ ከዚህም ሌላ በልዩ ልዩ የደስታ ቀን ይዘፈናል (ሉቃ. 15፡25)፡፡ (በእስራኤል የአምልኮት ሥርዓት ዘፈን (ማኀሌት) ትልቅ ቦታ ይይዝ ነበር (መዝ.149፡3/15ዐ፡4)፡፡ ነገር ግን#ባዕድ_አምልኮትንና_ዝሙትን_የሚያስከትል_ዘፈን_አልተፈቀደም (ዘዳ. 32፡6-19፣ማር. 6፡21-22)፡፡ “እዚሁ ላይ ሐዋርያት ዘፈን የማይገባ መሆኑን ተናግረዋል ይላል፡፡ ነገር ግን ሐዋርያት ምን ዓይነት ዘፈን እንደተቃወሙ አልገለጹም፡፡ አብዛኛዎቹ ጥቅሶች ተቀባይነት ስላለው ዘፈን እንደገለጹ እናስተውል፡፡
#ስለ_መሶልሶል፦
የደስታ ተ/ወልድ መዝገበ ቃላት (ገጽ 118ዐ) “ሶለሶለ - አንሶለሶለ፣ አዞር፣ አንቀዠቀዠ፣ አንቀለቀለ መንሶልሶል፣ መዞር፣ መንቀዥቀዥ (መጽሐፍ ግን መሶልሶለ ይላል ገላ. 5፡22)”
የአማርኛ እንግሊዘኛ መዝገበ ቃላትም እንዲህ ይላል፡፡ “ሶለሶለ - በማያገባ ጥልቅ ማለት፣ በማይሆን ሰዓት በምጣት፣ ሳይጠሩ መምጣት፣ መቀላወጥ፣ የሰው ምግብ ፍለጋ ወዲህና ወዲያ መዞር፡፡”
#ዝግጅት፦
ዶ/ር አባ ዳንኤል አሰፋ
(ዘማኀበረ ካፑቺን) - ፍቅርና ሰላም ጋዜጣ ጥር 2003 ዓ.ም።

Please Log in or Create an account to join the conversation.

Time to create page: 0.390 seconds

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት