እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘአስተምሕሮ 3ኛ

በእግዚአብሔር ፊት የመገኘት ፍቅር-ማቴ.8:23-34 ዕብ.12:25-29 ያዕ.3:4-12 ሐዋ.21:27-40

እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ?የዛሬው ወንጌል ውስጥ የተካተቱት ሁለት ክንዋኔዎች ማለትም፤ ኢየሱስ የማዕበልን ሞገድ ጸጥ ማስባሉና በአጋንንት የተያዙ ሰዎችን ማዳኑ፤ ነገሮች ሁሉ ከምናመልከው አምላክ ኃይል በታች መሆናቸውን በማሳየት የክርስቶስ ተከታይነታችን በነገሮች ገደብ ሳይሆን በርሱ ህላዌ ስለመሆኑ ያለንን እምነት እንድንመረምር ያግዙናል።

ለሰው ልጅ ህልውና ወሳኙ ነገር የእግዚአብሔር ህልውና በሕይወታችን ያለው ቦታ ነው። ደቀ መዛሙርቱና ኢየሱስ በባሕር ላይ ሳሉ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ ታላቅ መናወጥ በሆነበት ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደርሱ ቀርበው። "ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን" እያሉ ሲያስነሡት "እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ?" በማለት ከማዕበሉ በፊት እነርሱን የገሰፃቸው ምናልባት ከርሱ ህልውና ወይም በመካከላቸው መገኘት በላይ የርሱን ሥራ ስለፈለጉ ይመስላል።

ይህ ዓይነት ግንዛቤ በመንፈሳዊ ጉዟችን ላይ መዘዝ የሚያስከትል ነገር ነው። ክርስትናችን በእግዚአብሔር ሥራ ወይም እሱ በሚያደርግልን ብለን በምናስባቸው ነገሮች መጠን ከሆነ፤ በተወሰነ ደረጃ ላይ ነገሮች በራሳቸው መሳካት የጀመሩልን ሲመስለን እግዚአብሔርን ከሕይወታችን የማስወጣት ድምዳሜ ላይ ልንደርስ እንችላለን። ወይም በተቃራኒው አላደረገልንም ብለን ስናስብ ሌላ "አምላክ" ፍለጋ እንሄዳለን። በጠባብ እቅዳችን ውስጥ እግዚአብሔር የገባ ሲመስለን እውነተኛውን አምላክ አገኘን ብለን እናውጃለን። እውነቱ ግን ያገኘነው አምላክን ሳይሆን  የፈለግነውን ነገር ነው ። በርሱ ሰፊ እቅድ ውስጥ ራሳችንን ማስገባት ሲከብደን እሱን በኛ ደካማ እቅድ ውስጥ ለማስገባት እንጥራለን።

ስለዚህ ክርስቶስ የተኛ በመሰላቸው ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ተረበሹ። የእርሱ በመሃላቸው መገኘት ማመንን ሳይሆን እሱን "ቀስቅሰው" ተአምር ማድረግ መጠየቅን ወሰኑ። ማዕበሉን ጸጥ ማሰኘቱ የኢየሱስ ህልውና ማረጋገጫ እስኪመስል "ቀሰቀሱት"። እሱ ስለነርሱ የሚያስብ ሳይሆን እሱን ስለነርሱ አሳስበውት የሚያስብ አስመሰሉት። ክርስትናን በእግዚአብሔር ፊት የመገኘትን ፍቅርና እውቀት ማስፋፋትና መኖርን ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት መጮህ አስመሰሉት።

የእግዚአብሔር ህልውና በሕይወቱ መተከሉን የማያምን ሰው እግዚአብሔር "ጸጥ" ያለ ሲመስለው የመኖሩ መሠረት የተናወጠ ይመስለዋል። በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር መኖሩን ለማረጋገጥ የማስረጃ ውጫዊ ምልክትን ይሻል። ይህንንም በማድረጉ ሳይታወቀው ለእምነት እንደ ሳይንስ አካላዊና ግዙፍ ማስረጃ መሰብሰብን ይጀምራል። ቶማስ ሜርተን "እግዚአብሔርን በደንብ የማናውቀው ከሆነ እሱ የሌለ በሚመስለን ሰዓት ይበልጥ በሕይወታችን እንደሚገኝ አንገነዘብም" ይላል። የእምነት ሰው እግዚአብሔር አለ ብሎ በሚያስብበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን የሌለ በሚመስልበትም ሰዓት ሁሉ የአምላኩን ህልውና የሚይምን ነው።

ደቀ መዛምርቱ ጥያቄያቸው በራሱ ምንም ክፋት ያለው አይመስልም "ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን" ነው ያሉት። እንደዚህ ብሎ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ የእምነት ሰው መሆን ምልክት እንጂ እንዴት የእምነተ ቢስነት ወይም ጎዶሎነት ሊሆን ይችላል? "ጌታ ሆይ! ይህን አድርግልኝ፤ ያን ስጠኝ..." ብለን የጸለይናቸውና የምንጸልያቸው ሁሉ ትርጉም የለሽ ሊሆኑ ይችል ይሆን የሚል ስጋት ይፈጥራል። ክርስቶስ ግን "እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ?" ብሎ ሲመልስላቸው የሚያስተላልፈው መልእክት የኔ ይህን ወይም ያን ማድረግ ሳይሆን የእኔ ከናንተ ጋር መኖር ትልቅ ነገር መሆኑን አታውቁምን የሚል ነው።

ስለዚህ የርሱ ከኛ ጋር መኖር የምንፈልጋቸው ነገሮች ከመሆናቸው ወይም ካለመሆናቸው በላይ በሕይወታችን ትልቅ እፎይታን መስጠት አለበት። ስላደረገልኝ የማምነው ከሆነ "እምነት" የምንለውን ትርጉማችንን እናጢነው። ኢየሱስ ሆይ እኔ ያልኩትን ማግኘት ሳይሆን በሕይወቴ ውስጥ የአንተ ህልውና፤ ያንተ መገኘት ለኔ በቂ ነው እንበለው።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት