እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘስብከት 2ኛ - ዘብርሃን

"...ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም"- ዘስብከት 2ኛ - ዘብርሃን - ዮሐ.1:1-18 /ሮሜ 13:11-14 /1ዮሐ.1:1-10 /ሐዋ.26:12-18

ለገና በዓል ዝግጅት በሚደረግበት በዚህ ሁለተኛ ሳምንት የዛሬው ወንጌል እግዚአብሔር በሕዝቡ መሐል ብርሃን ሆኖ ስለመኖሩና የሰውን ከብርሃን ይልቅ ጨለማን የመምረጥ ቀጣይ ዝንባሌ ግልጽ በሆኑ ቃላት ይነግረናል።

"ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም።" ይላል ወንጌላችን። ጨለማ በራሱ ያለ ነገር ሳይሆን የብርሃን ያለመኖር መሆኑን እናውቃለን። ጨለማን ስንፈልግ ማድረግ የምንችለው ነገር የብርሃን ምንጭን ማስወገድ ነው፤ በተቃራኒው ደግሞ ብርሃን እንዲሆን ከፈለግን የብርሃን ምንጭን ማግኘት ነው። ማንም ሰው በቀጥታ የክርስቶስ ተቃራኒ መሆን አይፈልግ ይሆናል፤ ነገር ግን ክርስቶስን በዕለታዊ ሕይወቱ ካልተቀበለ ሌላ ሦስተኛ ምርጫ የለምና ሊቀበል የሚችለው ጨለማን ብቻ ነው።

ክርስቶስን በብርሃን መስሎ በመናገርና ይህን ብርሃን ያልተቀበሉ ጨለማን እንደመረጡ ዮሐንስ ወንጌላዊው ያሳየናል። ብቸኛ የዓለም ብርሃን የሆነውን ክርስቶስን ያልተቀበለ ያለው ብቸኛ ምርጫ ወይም በተሻለና ግልጽ አባባል ብቸኛ ግዴታው ጨለማን መቀበል ነው። ይህን ጨለማ የሰው ልጅ በሕይወቱ ውስጥ እንዴት ይለማመደዋል ብለን የምናስብ ከሆነ እያንዳንዳችን ዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ ገብተን ከክርስቶስ ፈቃድ ጋር የማይሰማማ አናኗሮቻችንን መመርመሩ ጥሩ ነው። ሥጋዊ ብርሃን ውስጥ ብንመላለስም ውስጣዊ ብርሃናችንን ያጣን ልንሆን እንችላለንና ዛሬም ስለክርስቶስ ብርሃናዊነት ሲነገር ውስጣችንን በርሱ ማብራት ይጠበቅብናል።

ቁ.18 ላይ "እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ያለው አንድ ልጁ ብቻ ገልጦታል" ይላል። እግዚአብሔር እንደ ሰው በቦታና በጊዜ ተገድቦ ሊታይ ባህርይው ወይም ተፈጥሮው አይደለም። ግን ሁሉን ቻይ ነውና ራሱን በሚገባን መልክ ለመግለጥ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በአንድ ልጁ ሥጋን ለበሰ። ይህን እውነት በዘወትር ሕይወታችን ካሰብነው ደግሞ ብዙ ትርጉም ይኖረው ይሆናል። ማለትም እግዚአብሔር ራሱን የሚገልጥበትን መንገድና እኛን የሚጠራበትን ሁኔታዎች እንድናስተውል ያግዘናል። ማንም እግዚአብሔርን በቀጥታ አይቶ በሕይወት ሊኖር የሚቻለው ሥጋ ለባሽ የለም፤ ክርስቶስ ግን አባቱን ተረከልን፣ በተለያየ መልክም እንደሚገለጥ አሳየን።

እንዲሁም "እርሱም ወደ ወገኖቹ መጣ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም" ሲል ቶሎ ብለን ልናስብ የምንችለው ነገር ካልተቀበሉት ምኑን ወገኑ ሆኑ የሚል ሊሆን ይችላል። በርግጥ እነርሱ አድርገውታል ማለትም አልተቀበሉትም፤ ጥያቄው ግን ዛሬ ለኛ ነው፤ የጥምቀት ጸጋን ተቀብለን ክርስቲያኖች በመባል የእርሱ ወገን ሆነን ለደኅንነት ማለትም ሕይወታችንን ለርሱ እንድናስገዛ ሲጠራንና ሲጋብዘን ላለመቀበል በቀጠሮ የምናሰለቸው ከሆነ አንድ ዓይነት ታሪክ እንደግማለን:- ወገኑ ነን ግን አልተቀበልነውም።

ክርስቶስ በአካል በየዕለት ሕይወታችን ውስጥ እኛ በምንፈልገው መልክ ቢገለጥ ኖሮ ለመቀበሉ እንሽቀዳደም ነበር። ግን በተለያየ መልክ ዛሬም ወደ ወገኖቹ ማለትም ወደ እኛ በስሙ ወደተጠራነው መምጣቱን አላቋረጠም እኛም እርሱን ካለመቀበል አልሰነፍንም። ይህ ነገር በቀጣይነት እንዳይጠናወተንና ከውስጣዊ ጨለማ ጋር መኖርን እንዳንመርጥ የዛሬው ወንጌል ለውሳኔ ያነቃቃናል።

"ይሁን እንጂ ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን መብት ሰጣቸው" ሲል ይህ ለሁላችን የተደረገ ግብዣና ጥሪውን ተቀብለን ስንመልስ የብርሃን ልጆች የመሆን መብታችንን መኖር እንደምንችል ያሳያል። ብርሃን ወይ ጨለማን፤ የእርሱ ልጅነትን ወይም የጨለማው ባላባት (የሰይጣን) ልጅነትን መምረጥና መለማመድ ከኛ በኩል በሚደረገው ምርጭ ስለሚወሰን ምርጫችንን መኖር በእጃችን ነው። ይህ ምርጫ አንዴ ተደርጎ በቃ የሚባል ዓይነት ሳይሆን በቀን ውስጥ በሚቀርቡልን ተደጋጋሚ ምርጫዎች ይወሰናል።

እግዚአብሔር የኛን ዝቅተኝነት በመካፈል የእርሱን ክብር ሊያካፍለን ይህን የገና ጊዜ እንጠቀምበት ዘንድ ሰጥቶናል፤ ሰው ሆኖ በመወለዱ ብዙዎች ሊለዩትና ሊቀበሉት እንዳልፈለጉ ሁሉ ዛሬም በተለያየ መልኩ በመካከላችን ተገኝቶ እኛን ሊያከብረንና ከአእምሮ በላይ የሆነ ሰላሙን በድካም ለታጠረው ማንነታችን ሊሰጠን ይጠብቀናል።

አንድ ታሪክ እንዲህ ይላል፦ ዙፋኑን የሚወርስለት ልጅ ያልነበረው አንድ ንጉሥ ነበር፤ እናም እንደ ልጁ የሚሆንና የሚወርስ ካለ ሙሉ የልጅነት መብት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን የሚገልጽ ማስታወቂያ በግዛቱ ላሉት ወጣቶች በሙሉ አወጣ። ይህ እንዲሆን ግን ሁለት መስፈርቶችን ማሟላት እንዳለባቸውም አሳወቀ። እነዚህም መስፈርቶች ልጁ መሆን የሚፈልግ ሁሉ እግዚአብሔርንና ሰውን በጣም የሚወድ መሆን አለበት የሚሉ ናቸው። አንድ ድኻ እረኛ ልጅ ይህንን ሰማና ማመልከቻ ማስገባት አሰበ፤ ሆኖም ግን ይህን ለማድረግና በንጉሡ ፊት ለመቅረብ የሚመጥን ልብስ የለኝም ብሎ አሰበና ለተወሰነ ጊዜ ገንዘብ አጠራቅሞ ያሰበውን ልብስ በመግዛት ወደ ቤተ መንግሥቱ በመሄድ ላይ ሳለ በብርድ እየተንቀጠቀጠ ልብስ የሚለምን አንድ ሽማግሌን በመንገድ አገኘና ልጁ በጣም ከማዘኑ የተነሣ የሽማግሌውን ልመና ረግጦ ማለፉ ስለከበደው አዲሱን ልብሱን ሰጣቸው። ከዚህም በኋላ ከነድሮው ቡቱቱ ልብሱ ይሳካለት መሆኑን በጣም እየተጠራጠረ በቤተ መንግሥቱ ቃለ መጠይቁን አደረገና ተቀባይነትን አግኝቶ ተሳካለት። ከዚያም ዙፋኑ ወዳለበት ክፍል እንዲሄድ ተደረገ እናም በዚያ ያየውን ነገር ማመን ተሳነው። በዙፋኑ ላይ የነበረው ንጉሥ ያ በመንገድ ላይ በብርድ ሲንቀጠቀጥ የነበረው ሽማግሌ ሆኖ አገኘው። ንጉሡም ወጣቱን ሲያይ በልዩ ፈገግታ "ልጄ ሆይ! እንኳን በደህና መጣህ!" አለው።

ይህ ታሪክ ክርስቶስ ድኻ ከሆነው ሁሉ የበታች ሆኖ በመወለድ ለኛ ለደካሞቹ የእርሱ የሆነውን ሰላምና ፍቅር ወርሰን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን እንድንኖር በየቀኑ አጠገባችን ባሉ ሰዎች እንደሚጋብዘንና ሰውን ሁሉ በርሱ አምሳል እንድናይ ያሳስበናል። ዘመነ ገናም መልእክቱ "ለተቀበሉት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን ሰጣቸው" ነውና መብታችንን ችላ አንበለው።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት