እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፴፪-፴፫ የትንቢተ ሶፎንያስ እና ትንቢተ ሐጌ ጥናት

ክፍል ሦስት (ትምህርት ሠላሳ ሁለት) - የነቢያት መጽሐፍት ጥናት

ትንቢተ ሶፎንያስ እና ትንቢተ ሐጌ

  • ሶፎንያስ ተወልዶ ያደገው፣ ለነቢይነት አገልግሎት የተጠራውና አገልግሎቱ የተወጣው መቼና የት ነው?

Zephaniahሶፎንያስ የሚለው ስም “ሶፎን” እና “ያህ” የሚሉት የሁለት ቃላት ጥምረት ሲሆን ሶፎን “መሸሸግ” “መሰወር” “መጠበቅ” ወይም “መደበቅን” ሲያመለክት “ያህ” የሚለው ቃል ደግሞ የእግዚአብሔር መጠሪያ ስሞች ከሆኑት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ሶፎንያስ ማለት “እግዚአብሔር ሰውሯል” ወይም “እግዚአብሔር ይሸሽጋል” ወይም “እግዚአብሔር ይጠብቃል” በሚለው ይተረጐማል፡፡ የስሙ ትርጓሜ በሚታይበት ጊዜ ምንአልባትም ሶፎንያስ ጭካኔ በተሞላበት በአስከፊው በምናሴ ጊዜ(ከ680-642 ዓ.ዓ) እንደተወለደ ይታመናል፤ በመሆኑም ከምናሴ የጭካኔ ተግባር እግዚአብሔር የሸሽገናል የሚለውን በማሰብ “እግዚአብሔር ይሸሽጋል” ብለው ሰይመውት ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ ምናሴ በነገሠ ጊዜ አስጸያፊ ልማድ በመከተል በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ የገዛ ልጁን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ መተተኛና ጠንቋይ ሆነ፤ ሙታን አነጋጋሪዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን ምክር ጠየቀ፤ እግዚአብሔርን ለቁጣ የሚያነሣሣው ክፉ ድርጊት ፈጸመ(2 ነገ 211-9)፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “ሶፎን” በጥንት ጊዜ ከከናናውያን አማልክት አንዱ ስለነበር በሰሜናዊ ከነዓን የነበረውን ተራራ የአማልክት መኖርያ እንደነበር ስለሚታመን ተራራውም ሶፎን ተብሎ ተጠራ፡፡ በኋላ ግን ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ እግዚአብሔር በደንብ ማወቅ ሲጀምሩ “ሶፎን” ወይም እውነተኛው አምላክ “ያህ” ነው ብለው እግዚአብሔርን ለማመልከት መጠቀም ጀመሩ፡፡ ሶፎንያስ የሚለው ስም በብሉይ ኪዳን ውስጥ ዐሥር ያህል ጊዜ ሲጠቀስ አራት የሚያህሉ ሰዎች ደግሞ በዚህ ስም ተጠርተዋል፡፡ እነዚህም ነቢዩ ሶፎንያስ (ሶፎ11)፣ ካህኑ ሶፎንያስ(ኤር 211)፣ የካህኑ ልጅ ሶፎንያስ(2925)፣ ኩሻዊው የታሐት ልጅ ሶፎንያስ(1 ዜ.መ 636) እና የኢዮስያስ አባት ሶፎንያስ ናቸው(ዘካ 610)፡፡

ነቢዩ ሶፎንያስ የኩሺ ልጅ ሲሆን የኖረውም ይሁዳ ውስጥ በሰባተኛው ምዕተ ዓመት ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ንጉሥ ኢዮስያስ ሃይማኖታዊ ተሐድሶ ከማድረጉ ዐሥር ዓመታት ቀደም ብሎ ይሁዳ ለባዕዳን አማልክት ትሰግድበት በነበረበት ወቅት ነው፡፡ ይህም ማለት ሶፎንያስ ከ640 እስከ 609 ዓ.ዓ መኖሩንና የነቢይነት ተግባሩን ማከናወኑን ያሳያል፡፡ በእርግጥ ነቢዩ ሶፎንያስ የጣኦት አምልኮን በተለይም ባኣል የተባለውን አማልክት በጽኑ እያወገዘ ተናግሯል (ሶፎ 1፡4-12፤ 3፡1-4)፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከነቢዩ ኤርምያስና ዕንባቆም በተመሳሳይ ወቅት ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን መኖራቸውን ያመለክታል፡፡ ሶፎንያስ የዘር ሃረጉን ሲቈጥር እስከ ንጉሥ ኢዮስያስ ስለሚደርስ ምንአልባትም ከንጉሥ ኢዮስያስ ቤተሰብ ወገን ሊሆን እንደሚችልም ይገመታል(ሶፎ 11)፡፡ በእርግጥ መጽሐፉ ገና ሲጀምር የራሱ የሶፎንያስ የዘርሃረግ ከአባቱ ከኩሺ ጀምሮ እስከ የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ኢዮስያስ ይደርሳል፡፡ በተለምዶ ነቢያቶች ቢበዛ የአባታቸው ስም ብቻ ይጠቅሳሉ እንጂ የዘር ሃረጋቸው አይቈጥሩም፡፡ ለምሳሌ ኢሳይያስ የአሞጽ ልጅ ከማለት አያልፍም(ኢሳ 11)፡፡ ትንቢተ ሶፎንያስ የዘር ሃረጉን እስከ አራት ትውልድ ድረስ በመቁጠሩ ከሌሎች ነቢያቶች አቈጣጠር ለየት ይበል እንጂ ስለ ቤተሰባዊም ሆነ ስለ ግል ሕይወቱ ለማወቅ የሚረዳ ምንም ዓይነት መረጃ ከመጽሐፉ ስለሌለ ማንነቱን የበለጠ ለመረዳት ያስቸግራል፡፡ 

  • የትንቢተ ሶፎንያስ ጥንቅር፣ ይዘትና ዋና ትኩረት ምን ይመስላል? እንዴት ይገለጻል?

መጽሐፉ የተጠናቀረው ወይም የተጻፈው ኢየሩሳሌም ውስጥ ሲሆን ነቢዩ አብዛኛው ትምህርቱን ያስተማረውደግሞቤተመቅደስውስጥነው(14110-12፤3፡1፤3፡11-20)፡፡መጽሐፉገና ከጅማሬው እግዚአብሔር የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ እንደሚቀጣ፣ እንዲያውም እግዚአብሔር መብራት ይዞ ኢየሩሳሌምን በመፈተሽ እንደሚያጸዳት ከተናገረ በኋላ በእስራኤል ዙሪያ ስለሚኖሩ አሕዛብ አወዳደቅ፣ ኢየሩሳሌም ወደፊት ስለምታገኘው ቤዛነትና የእስራኤል ሕዝብ በእልልታ ለእግዚአብሔር ስለሚያቀርቡት ዝማሬ ላይ ይደመድማል፡፡ በመደምደሚያው ክፍል የእስራኤል ሕዝብበመከራውስጥስለነበሩበትስደት ጊዜ እንዲሁም ወደአገራቸውስለመመለሳቸውተስፋይተርካል(314)፡፡ ነገር ግን ይህንን ስደት የትኛውና በየትኛው ወቅት የተከሰተው እንደሆነ በትክክል ለማወቅ  በቂ የሆነ መረጃ መጽሐፉ ውስጥ የለም፡፡ በመጽሐፉ ጅማሬ ይሁዳ በተለይም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በጣዖት አምልኮ ውስጥ ተሳታፊ እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ ጣዖት አማላኪነታቸው የተገለጸውም ባዓል የተባለውን የባዕዳን አምላክ ስላመለኩ፣ ለፀሐይና ለጨረቃ ለከዋክብትም ስለሰገዱ ነው፡፡ ስለዚህ መሪዎችዋ፣ ዳኞችዋ፣ ነቢያቶችዋና ካህናቶችዋ በዚህ ጉዳይ ቅድሚያ ተጠያቂዎች ስለሆኑ በብርቱ እንደሚቀጡ ከገለጸ በኋላ ወዲያውኑ የአሕዛብን መንግሥታት እንደሚያጠፋ፣ ምሽጎቻቸው እንደሚያፈራርስና ከተሞቻቸው እንደሚደመስስ ያረጋግጣል፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፉ ወደፊት ስለሚመጣው ጥፋት በስፋትና በዋናነት እየተነበየ ይህም ጥፋት በመጀመሪያ ምድርን በሙሉ(ሶፍ 1፡2-3)፣ ቀጥሎም ኢየሩሳሌምን(1፡4-6 እና 14-18፤ ሶፎ 3፡1-8)፣ በመጨረሻም አጐራባች አገራትን ይመለከታል(ሶፎ 2፡4-15)፡፡ በተጨማሪም ወደፊት ስለሚገኘው ቤዛነትና በሕይወት ውስጥ መከናወን ስላለባቸው ደግ ተግባራት መመሪያ ይሰጣል(ሶፎ 1፡7፤ 2፡1-3)፡፡

ስለዚህ መጽሐፉ ቅደም ተከተል በጠበቀና ወጥነት ባለው መልኩ የተዋቀረ ሳይሆን ከአንድ ርዕስ ወደ ሌላ ርዕስ ባልተጠበቀ ሁኔታ በመሸጋገር ስለ ይሁዳና በእስራኤል ዙርያ ስለሚኖሩ አሕዛብ ጥፋት በማፈራረቅ ይናገራል፡፡ በዚህም የመጽሐፉ አብዛኛውን ክፍል ስለ ቅጣት ሆኖ የመጨረሻው ጥቂት ክፍል ግን ከእንግዲህ ወዲህ በእስራኤልም ሆነ በጽዮን ላይ ጥፋት እንደማይመጣ፣ የተበተኑትም እንደሚሰበስብ፣ ሐፍረታቸውንም በማስወገድ ወደ ክብር እንደሚለውጥና ዝነኞችም እንደሚያደርጋቸው ይናገራል(ሶፎ 3፡14-20)፡፡ በሌላ መልኩ ነቢዩ የቃላት አጠቃቀሙ እንዲሁም የነገሮች አገላለጹ ሲታይ ጸሐፊው ከግብርና፣ ከቤት እንስሳትና በአጠቃላይ ከተፈጥሮ ጋር በደንብ የተዋወቀ መሆኑን እነሱን በመጠቀም ከሚያብራራቸው ነገሮች በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በእርግጥ ጽሑፉ ውስጥ ፀሐይና ጨረቃ እንዲሁም ከዋክብት፣ ጨለማና ጭጋግ፣ ጉምና ደመና፣ የበግና የፍየል መንጋዎች፣ ከብቶችና የምድር አራዊቶች፣ ቁራዎች፣ ጉጉቶች፣ ዝግባዎች እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ ፍጥረታት ተካተው መልእክት ማስተላለፍ በሚችሉ መልኩ ተገልጸዋል፡፡ እነዚህን ነገሮች በአብዛኛው የሚጠቀምባቸውም ጥፋት ወደፊት እንደሚመጣ ለመተንበይና የወደፊቱ የሕዝቡን ሕይወት አስቸጋሪነት ለመግለጽ ነው፡፡

  • ነቢዩ ሶፎንያስ እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለሚፈርድበት ቀን ይናገራል፤ እንደ ነቢዩ ሶፎንያስ አገላለጽ ይህየፍርድ ቀን ምን ዓይነት ቀን ይሆናል?

ነቢዩ ሶፎንያስእግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ የሚፈርድበት ቀንመቃረቡንደጋግሞይገልጻል(ሶፎ 114-16)፡፡ከሌሎችነቢያቶችአገላለጽለየትየሚያደርገውይህቀንእግዚአብሔርሁሉንነገርከምድርላይፈጽሞየሚያጠፋበት ቀን መሆኑን ነው(ሶፎ 12)፡፡ በዚህም መሠረት ሰውንናእንስሳት፣የሰማይወፎችንናየባሕርዓሣዎችንሁሉይደመስሳል፤ዐመፀኞችንሁሉ ይገለባብጣል፤ አንድስ እንኳ ሳይቀር የሰውን ዘር ከምድር ላይ ያጠፋል(ሶፎ 1፡3)፡፡ነቢዩበእግዚአብሔርየፍርድቀንየሰውንዘርከምድርየሚያጠፋበትቀንመሆኑንቢገልጽምዋናውትኩረቱግንእግዚአብሔርየይሁዳንጠላቶችየሚቀጣበትቀንመሆኑንለማስገንዘብእንደሆነነው፡፡ እነዚህም ጠላቶች የተባሉትም በሰሜን በኩል የሚገኙት አሦራውያን ሲሆኑ ዋና ከተማቸው የሆነችው የነነዌንም ውሃ በሌለበት ምድረ በዳ እንደፈረሰች ከተማ ባድማ እንደሚያደርጋት ይገልጻል(ሶፎ 2፡13)፡፡

በመጽሐፉ መጨረሻ ክፍል ግን ኢየሩሳሌምን ከእንግዲህ ወዲህ ጥፋት እንዳይደርስብሽ አደርጋለሁ፤ ሐፍረትሽንም አስወግዳለሁ፤ ሲያስጨንቁሽ የኖሩትንም ሁሉ በዚያን ጊዜ እቀጣለሁ እያለ ወደፊት ስለምትድንበት ሁኔታ ተስፋዋን ይገልጽላታል(ሶፎ 318-20)፡፡ ይህንን ፍርድ እግዚአብሔር በሕዝቡ በይሁዳና በአጐራባች አገራት ላይ የሚያመጣበት ምክንያት ነቢዩ በግልጽ ይዘረዝራል፡፡ በዚህም መሠረት የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ሕዝብ እንዲሁም ካህናቶቻቸው ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት አምልከዋልና ይቀጣሉ፡፡ ከዚህም በላይ እግዚአብሔርን እያመለኩና በስሙ እየማሉ ዘወር ብለው ደግሞ ሚልኮም ተብሎ በሚጠራው ጣዖት ስም የሚምሉ፣ ጣራ ላይ ወጥተው ለፀሐይ፣ ለጨረቃና ለከዋክብት የሚሰግዱትን በሙሉ ይደመሰሳሉ(ሶፎ 1፡4-6)፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔርን መከተል በመተው ከእርሱ የራቁትንና እርሱም እንዲመራቸው ያልጠየቁትን ያጠፋቸዋል(ሶፎ 1፡6)፡፡ ከዚህም በላይ ኢየሩሳሌም የማንንም ትእዛዝ ስለማትቀበል፣ ተግሣጽንም ስለማትፈልግ፣ በእግዚአብሔር መታመንዋንም ስለተወችና ወደ እርሱም ቀርባ እርዳታውን ስለማትጠይቅ በብርቱ ትቀጣለች(ሶፎ 3፡1-2)፡፡

ኢየሩሳሌም መሪዎችዋ፣ ዳኞችዋ፣ ነቢያትዋና ካህናትዋ በፈጸሙት መጥፎ ሥራቸው ምክንያት ይቀጣሉ (ሶፎ 3፡3-5)፡፡ በተለይም ካህናቶችዋ የተቀደሰውን በማርከሳቸውና የእግዚአብሔርን ሕግ ለራሳቸው እንደሚስማማ አጣምመው በመተርጐማቸው ምክንያት ይቀጣሉ (ሶፎ 3፡4)፡፡ በአጠቃላይ ዋናው የቅጣት ምክንያት የሚሆነው “ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን ስለ በደሉ” መሆኑን ከገለጸ በኋላ ውጤቱም እንደ ዕውር እስኪደናበሩ ድረስ በሰው ዘር ሁሉ ላይ ታላቅ መከራ ያመጣል፤ ደማቸው እንደ ጐርፍ ውሃ ይፈስሳል፤ ሬሳቸውም እንደ ፋንድያ የትም ይጣላል በማለት የቅጣቱ አስከፊነት ይናገራል፡፡ ከዚህም በላይ ያ የመጨረሻው ዕለት የቁጣ፣ የመከራና የጭንቀት፣ የጥፋትና የመፍረስ፣ የጨለማና የጭጋግ፣ የጉምና የደመና ቀን ይሆናል በማለት ያረጋግጣል(ሶፎ 1፡15)፡፡

በሌላ መልኩ እግዚአብሔር የይሁዳ አጐራባች አገራት ለማጥፋት የወሰነበት ምክንያት ይዘረዝራል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የሞአብና የዐሞን ሕዝቦች በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ እያፌዙና እያላገጡ ምድራቸውን ለመንጠቅ በዛቻ ስለሚናገሩ ይቀጣሉ፤ እንደ ሰዶምና ገሞራ ይደመሰሳሉ፤ የጨው ጉድጓድና በዳዋ የተሸፈነ ጠፍ ቦታ ይሆናሉ(ሶፎ 2፡8-9)፡፡ ከዚህም በላይ በእልኽና በትዕቢት ተሞልተው የሠራዊት ጌታ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሕዝብ እየሰደቡ በማዋረዳቸው ምክንያት በብርቱ ይቀጣሉ(ሶፎ 2፡10)፡፡ ከተሞቻቸውም በተለይም ነነዌን ፈርሳ ምድረበዳ ትሆናለች፤ የበግና የፍየል መንጋዎች፣ የከብቶችና የምድር አራዊት መሠማሪያ ትሆናለች(ሶፎ 2፡13)፡፡

በአጠቃላይ በዚያች የፍርድ ቀን እግዚአብሔር አሕዛብንና መንግሥታትን በአንድነት ሰብስቦ በቁጣው እሳት ያነዳቸዋል፤ መላዋ ምድር ትቃጠላለች(ሶፎ 3፡8)፡፡ የፍርድ ቀን ስለቀረበ አሕዛብ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመሥዋዕት እንደሚታረድ እንስሳ ለማረድ እየተዘጋጀ መሆኑን በማረጋገጥ ስለዚያች ቀን አስፈሪነትና አስጨናቂነት ይተነብያል(ሶፎ 1፡7)፡፡ በተለይም እግዚአብሔር በጎም ሆነ ክፉ ነገር ከቶ አያደርግም የሚሉትን በብርቱ ይቀጣቸዋል፤ ሀብታቸው ሁሉ ይዘረፋል፤ ቤቶቻቸውም ይፈርሳሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ቤት ይሠራሉ ነገር ግን አይኖሩበትም፤ ወይን ይተክላሉ ነገር ግን የወይኑን ጠጅ አይጠጡም በማለት ነቢዩ መልእክቱን ያስተላልፋል(ሶፎ 1፡12-13)፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ወደ እርሱ ተመልሰው፣ ራሳቸውን በፊቱ ዝቅ አድርገው፣ ትእዛዛቱን በመፈጸም ደግ ሥራ እየሠሩ የሚኖሩ ትሑታን እግዚአብሔር ቁጣውን በሚገልጥበት ቀን ከቅጣት ያመልጣሉ(ሶፎ 2፡3)፡፡

ትንቢተ ሐጌ

  • ነቢዩ ሐጌ ተወልዶ ያደገው፣ ለነቢይነት የተጠራውና የነቢይነት አገልግሎቱ የተወጣው የትና መቼ ነው?

ሐጌ የሚለው ቃልሐግ” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውምክብረበዓልማለት ነው፡፡ሐጌ ምንአልባት በአንድ የአይሁድ ክብረ በዓል ወቅት በመወለዱ ምክንያት ወላጆቹ ሐጌ ብለው ሰይመውት ሊሆን ይችላል፡፡ ከትንቢተ ሐጌ ውጭ ሐጌ የሚለው ስም በብሉይ ኪዳን ውስጥ በሁለት ቦታዎች ተጠቅሶ ይገኛል(ዕዝ 51፤ 614)፡፡ መጽሐፉ ውስጥ ስሙ ከመጠቀሱ ውጪ ስለራሱምሆነስለቤተሰባዊሕይወቱምንምዓይነት ተጨማሪ መረጃ የለም፡፡ ሐጌ አገር ወዳድ፣ ፖለቲከኛና የሕዝብ እንቅስቃሴ መሪ እንደነበር ሊቃውንት ይገልጻሉ፡፡ የዚህም ዋና ምክንያታቸው ሐጌ ኢየሩሳሌም እንድትገነባ ቤተ መቅደስዋም እንድትታነጽ ሕዝቡን በተለያየ መልኩ እያስፈራራ ብዙ ቅስቀሳ አድርጓል፤ ይህ ደግሞ በወቅቱ ኢየሩሳሌም የሃይማኖታዊና የፖለቲካዊ አስተዳደር ዋና ማዕከል እንድትሆን የወቅቱ መሪዎች በተለይም የፖለቲካ ሰዎች ጽኑ ምኞት ስለነበር ነው፡፡

ነቢዩ ሐጌ የኖረውና የትንቢት ቃሉን ያስተላለፈው በ520 ዓ.ዓ በኢየሩሳሌም ውስጥ ለነበሩት አይሁዶች ነው፡፡ በዚህ ወቅት አይሁዳውያን ከባቢሎን የስደት ሕይወት ተመልሰው ኑሮአቸውን በመመሥረትና በማጠናከር ሂደት ላይ ነበሩ፡፡ በእርግጥ በ539 ዓ.ዓ የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ባቢሎናውያንን በማሸነፍ ምርኮኞች ሆነው በስደት ይኖሩ የነበሩትን ወደ አገራቸው ወደ ይሁዳ እንዲሁም ወደ ዋና ከተማቸው ወደነበረችው ኢየሩሳሌም መመለስ ለሚፈልጉ አይሁዳውያን ፈቃድ ሰጥቶ ነበር፡፡ ከስደት ተመላሾቹ ምንም እንኳ በደንብ ያልተደራጁና ብዙም ሀብት ባይኖራቸውም በባቢሎናውያን ፈርሶ የነበረውን ቤተ መቅደስ ዳግመኛ መገንባትና ማነጽ ጀምረው ነበር፡፡ ነገር ግን ሳምራውያኖች በብርቱ ስለተቃወምዋቸው እነርሱም በሞራልና በገንዘብ የአቅም ደረጃ በደንብ ካለመጠናከራቸው የተነሣ ተቃዋሚዎቻቸውን የመቋቋም ኃይል ስላልነበራቸው ሥራውን ለማቋረጥ ተገደዱ፤ ወደ ፍጻሜም ሳያደርሱት ለ16 ዓመታት ያህል የግንባታ ሥራው በእንጥልጥል ተቋርጦ ቀረ(ዕዝ 3-4)፡፡

  • የትንቢተ ሐጌ ጥንቅር፣ ይዘትና ዋና ትኩረት እንዴት ይገለጻል?

መጽሐፉ ከዐሥራ ሁለቱ ታናናሽ ነቢያቶች መካከል ከትንቢተ ዕንባቆም ቀጥሎ በትንሽነቱ የታወቀ እጥር ምጥን ብሎ በሁለት ምዕራፎች የተጠቃለለ መጽሐፍ ነው፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ በሌሎች ዳግመኛ ተከልሶ ወይም ከጅማሬው በተለያዩ ሰዎች አማካይነት ተጠናቅሮ ሊሆን እንደሚችል የተለያየ አቀራረብ ካለው የአጻጻፍ ስልቱ መረዳት ይቻላል፡፡ መጽሐፉ ጅማሬው ላይ እግዚአብሔር በቀጥታ ለሕዝቡ ሕዝቤ ሆይ እያለ ሲናገር(ሐጌ 14) በቀሪው የመጽሐፉ ክፍል ግን በነቢዩ ሐጌ አማካኝነት እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ ይላል እግዚአብሔር(ሐጌ 113) በሚለው የሦስተኛ አካል አባባል የተገለጸ ነው፡፡             

መጽሐፉ ከጅማሬው ግልጽ በሆነ የዘመን አቆጣጠር ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ ስድስተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን፣ እግዚአብሔር በነቢዩ ሐጌ አማካኝነት ተናገረ በማለት ስለሚገልጽ መጽሐፉ የተጻፈው  በ520 ዓ.ዓ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በእርግጥ ይህ ዓይነት የዓመታት፣ የወራትና የቀናት አገላለጽ መጽሐፉ ከሚታወቅባቸው የአጻጻፍ ስልቶች አንዱ ነው፡፡ ነቢዩ ታላላቅ ክስተቶችን ሲጠቅስ በተለያዩ ቦታዎች ይህንን የወቅቶች አገላለጽ ይጠቀማል፡፡ የመጽሐፉም የመጀመሪያውና ዋና ትኩረት የሆነውም ሕዝቡ ቤተ መቅደሱ የመገንባት ሥራ እንዲጀምሩ የተደረገ ጥሪና ሙግት ነው(ሐጌ 1፡1-15)፡፡ ሕዝቡ ቤተ መቅደሱ ታድሶ የሚሠራበት ጊዜ ገና አልደረሰም ይላል(ሐጌ 1፡2)፤ ነቢዩ ሐጌ ግን በዚህ አይስማማም፡፡ ግንባታው አሁኑኑ መጀመር እንዳለበት ካልሆነ ግን ድርቅ በምድር ሁሉ እንደሚመጣ ያስጠነቅቃቸዋል፡፡ ቀጥሎም ተገንብቶ ስላለቀው ስለ አዲሱ ቤተ መቅደስ ውበትና ግርማ ይገልጻል(ሐጌ 2፡15-2፡9)፡፡ ከቤተ መቅደሱ ግንባታ መጠናቀቅ በኋላ ቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናቶች ነቢዩ ስለሰጣቸው ምክር ይተርካል፡፡ በመጨረሻም እግዚአብሔር ለዘሩባቤል የሰጠውን ተስፋ በመግለጽ መጽሐፉ ምዕራፉን ይደመድማል፡፡

ከዚህ ውጪ መጽሐፉ አንባቢው ሊረዳ በሚችለው መልኩ ግልጽ የሆነ ቋንቋና አገላለጽ እንዲሁም ከዕለታዊ ሕይወት ጋር በተያያዘ መልኩ ጠቀሜታ ላይ የሚውሉት ምሳሌዎችን እየተጠቀመ ትንቢቱን ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት በወቅቱ ከነበረው የግብርና አኗኗር ዘይቤ በመከተል ዘሮች፣ ምርቶች፣ የመከር ጊዜያት፣ የእህል ማሣዎች፣ የእህል ጎተራ፣ የወይን ቦታዎች፣ የወይራ ተክሎች፣ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የብስን የመሳሰሉትን በመጠቀም ሕዝቡ በቀላሉ ሊረዳው በሚችልበት መንገድ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

  • ነቢዩ ሐጌ በትንቢት ቃሉ ውስጥ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ስለ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ መታነጽ ነው፤ ነቢዩሐጌ በምን ምክንያት ነው ስለ ቤተ መቅደስ መታነጽ ሰፋ ባለ መልኩ የሚናገረው?

በትንቢተ ሐጌ ውስጥ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ቤት ወይም የእግዚአብሔር ማደሪያ ቦታ እንደሆነ በተደጋጋሚ በእግዚአብሔር በራሱ ተገልጿል፡፡ ሁለት ጊዜ እግዚአብሔር እራሱ የእኔ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ተሸላልመው በተሠሩ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን?”፤ ከእናንተ ቤቱን አስጊጦ እየሠራ የእኔ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ ሆኖ በመቅረቱ ነው፤ እያለ የቤተ መቅደስ ባለቤትነቱና የሚመሰገንበት ቦታ መሆኑን በተለያየ መልኩ ይገልጻል(ሐጌ 1፡4፤ 1፡8-9)፡፡ በመጀመሪያው ዙር ከስደት የተመለሱ አይሁዳውያን ምንም እንኳ የቤተ መቅደሱ ዳግም ግንባታ ቢጀምሩም በተለያዩ ምክንያቶች አቋርጠውት ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው ሕዝብ በእርግጥ ከስደት የተመለሰና በአቅምም ደረጃ ገና ያልተደራጀ ነበር፤ በዚህም ምክንያት ያለነገሥታቶች ድጋፍ ቤተመቅደሱን ማደስ እጅግ በጣም ከባድ ተግባር አድርጎ ይወስደው ነበር፤ ነቢዩ ሐጌ ግን ሕዝቡ አመለካከቱ እንዲቀይርና ቤተመቅደሱ ለማደስ እንዲነሣሣ ይቀሰቅሳል፡፡እንደ ነቢዩ ሐጌ አገላለጽ የቤተ መቅደሱ መታደስ ወደፊት ሕዝቡ ለሚኖረው የኑሮ ብልጽግና እጅግ በጣም ወሳኝ ስለሆነ ሕዝቡ ስለወደፊቱ የኑሮ መሳካት በማሰብ እንዲገነባውና እንዲያድሰው ይገፋፋዋል፡፡ እንደ ነቢዩ ሐጌ አገላለጽ እስካሁን ድረስ ቤተመቅደሱ ባለመታደሱ ሕዝቡ በኑሮው እርካታ አጥቶ እየተንከራተተ ነው፡፡

  • ነቢዩ ሐጌ የቤተ መቅደሱ የመታነጽ ሥራ በምን ዓይነት ሁኔታ፣ መቼና በማን መከናወን አለበት ይላል?

ነቢዩ ሐጌ ይህንን ግንባታ አሁኑኑ መጀመርና ፍጻሜ ማግኘት እንዳለበት ሕዝቡንና መሪዎቻቸውን ይቀሰቅሳል፡፡ ለቅስቀሳ ከተጠቀመባቸውም መንገዶች አንዱ በወቅቱ የነበረው የሕዝቡን የኑሮ ችግር ነበር፡፡ እንደ ነቢዩ አገላለጽ በወቅቱ በሕዝቡ የደረሰው ችግር በሙሉ ቤተ መቅደሱ ካለመገንባቱ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ነቢዩ ለሕዝቡ የደረሰባችሁ ሁሉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ! ካላቸው በኋላ ምን እንደደረሰባቸው ሲገልጽላቸው እነሆ ብዙ ዘርታችሁ ጥቂት ሰበሰባችሁ፤ ትበላላችሁ ነገር ግን አትጠግቡም፤ ትጠጣለችሁ ነገር ግን አትረኩም፤ ደራርባችሁ ትለብሳለችሁ ነገር ግን አይሞቃችሁም፤ ሠርታችሁ የምታገኙት ደመወዝ ስለማይበረክትላችሁ በቀዳዳ ኪስ ውስጥ የማኖር ያህል ይሆናል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ልብ ብላችሁ ተመልከቱ ይላቸዋል(ሐጌ 1፡6-8)፡፡ በተጨማሪም ያቺኑ የሰበሰብዋት ትንሽዋ መከር እንኳ ወደ ቤት ባስገቡት ጊዜ እኔ እፍ ስላልሁበት ጠፋ፤ የጠፋውም ቤተ መቅደሱ ፍርስራሽ ሆኖ እያለ እያንዳንዱ ሰው ቤቱን አስጊጦ ይሠራል በማለት እግዚአብሔር እራሱ ስለ ቤቱ ቀንቶ ለሕዝቡ ይናገራል(ሐጌ 1፡9)፡፡

ሕዝቡ ብዙ መከር ለመሰብሰብ አቅደው ቢዘሩም መከሩ በጣም እንዳነሰባቸው ይናገራል፡፡ ከዚህም በላይ ዝናብ የማይዘንምበት፣ ቡቃያ የማይበቅልበትና የወይን ቦታዎች፣ የወይራ ተክሎች፣ የእህል አዝመራ፣ ሰውንና እንስሳ የሚጐዳ ድርቅ በምድራቸው የተከሰተበት ዋናው ምክንያት ከቤተ መቅደሱ አለመገንባት ጋር የተያያዘ መሆኑን ያስገነዝባቸዋል(ሐጌ1፡9-11)፡፡ ስለዚህ ይህንን ሁሉ ችግር እንዲወገድና ሕዝቡ በረከት አግኝቶ እንዲኖር ዋና መፍትሔው የቤተ መቅደሱ መገንባት ስለሆነ ሕዝቡን አሁኑኑ ወደ ኮረብታዎች ውጡ፤ እንጨትም ቈርጣችሁ አምጡ፤ ቤተ መቅደሱንም እንደገና አድሳችሁ ሥሩ በማለት ይቀሰቅሳቸዋል(ሐጌ 1፡8)፡፡

ይህንን የነቢዩ የጥሪ ቃል የሰሙት ከባቢሎን ስደት የተመለሱት አይሁዳውያን በዘሩባቤልና በሊቀ ካህናቱ ኢያሱ እየተመሩ የቤተ መቅደሱን ግንባታ ጀመሩ፡፡ በእርግጥ ለጅማሬው ዋና ምክንያት የሆነው ፍርሃት እንደሆነ እግዚአብሔር አምላካቸው ያዘዛቸውን ሁሉ አደረጉ፤ እጅግ በመፍራትም እግዚአብሔር በላከው በነቢዩ ሐጌ አማካይነት ለተናገረው ቃል ታዛዦች ሆኑ በማለት ይገልጻል(ሐጌ 1፡12)፡፡ በዚህም መሠረት ቤተ መቅደሱን መሥራት ጀመሩ(ሐጌ 1፡15)፡፡ ነቢዩ ሐጌ ሕዝቡንም ሲያበረታታ ምንም እንኳ አሁን ለዘር የሚሆን እህል በጎተራ ባይኖር፣ የወይንናየ በለስ፣ የሮማንና የወይራም ተክል ሁሉ ገና ፍሬ ባይሰጥ ከዚህ ቀን ጀምሮ እኔ በረከትን እሰጣችኋለሁ ይላል እግዚአብሔር በማለት በቤተ መቅደሱ የመታደስ ሥራ ጅማሬ በማበረታታት ይናገር ነበር(ሐጌ 2፡19)፡፡

  • እንደ ነቢዩ ሐጌ አገላለጽ ቤተ መቅደሱ ከታነጸ ሕዝቡ ሊያገኘው የሚችለው በረከት ምንድን ነው?

ነቢዩ ሐጌ በትንቢቱ የመጨረሻው ክፍል ላይ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለሕዝቡ መሪ ለሆነው ለዘሩባቤል ስለሚሰጠው የወደፊቱ ተስፋ ይናገራል፡፡ በዚህም መሠረት የበረከት ሁሉ አምላክ እንደሆነና ይህንንም በረከት ለሕዝቡ እንደሚሰጥ ቃል ይገባል፡፡ ይህ የተስፋ ቃል ግን የተያያዘው ከቤተ መቅደሱ መታነጽ ጋር እንደሆነ የተረጋገጠ ነው፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ከአሁን ጀምሮ ወይም ከዚህ ቀን ጀምሮ እኔ በረከትን እሰጣችኋለሁ በማለት ስለወደፊቱ ተስፋ ይገልጽላቸዋል፡፡ ይህ ቀን የተባለውም ቤተ መቅደሱን መሥራት የጀመሩበት ዕለት እንደሆነ ነቢዩ ያስገነዝባል(ሐጌ 2፡15)፡፡ የቤተ መቅደሱን ሥራ ቸል ብለው ወደ እርሻ ሥራቸው በገቡ ጊዜ የምትደክሙበትን አዝመራ ሁሉ ለማጥፋት በሽታ፣ የሚያቃጥል ነፋስና በረዶ ላክሁባችሁ፤ እናንተ ግን ይህ ሁሉ ደርሶባችሁ እንኳ ንስሓ አልገባችሁም በማለት እግዚአብሔር ሥራቸው ፍሬ እንዳያፈራ ይከለክላቸው እንደነበር አሁን ግን ምንም እንኳ ለዘር የሚሆን እህል በጐተራ ባይኖር፣ የወይንና የበለስ፣ የሮማንና የወይራም ተክል ሁሉ ገና ፍሬ ባይሰጥ ከዚህ ቀን ጀምሮ እኔ በረከትን እሰጣችኋለሁ በማለት በረከትን እንደሚያዘንምላቸው ነቢዩ ሐጌ ያረጋግጥላቸዋል፡፡

  • ነቢዩ ሐጌ ቤተ መቅደስ እንዲታነጽ ብዙ ሲቀሰቅስ ነበር፤ በቅስቀሳውም ሂደት ስለሚታነጸው ቤተ መቅደስየወደፊት ውበትና ግርማ ይገልጽላቸው ነበር፡፡ ይህንን የሚያደርገው ከምን አኳያ ነበር?

የነቢዩ ሐጌ የቅስቀሳ ዘመቻ ሰምተው፣ መንፈሳቸውን አጠናክረው የቤተ መቅደሱን ግንባታ የጀመሩ አይሁዳውያን በድካም ወይም በመሰልቸት መንፈስ ዳግመኛ ወደ ኋላ እንዳይመለሱ ነቢዩ ሐጌ እየተከታተለ ያበረታታቸው ነበር፡፡ ነቢዩ ሕዝቡን ያበረታታበት ከነበረበት መንገዶች አንዱ እግዚአብሔር በግንባታ ሥራቸው እንደተደሰተና ከእነርሱም ጋር እንደሚገኝ ማረጋገጥ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ ይላል እግዚአብሔር እያለ ነቢዩ ሐጌ ለሕዝቡ የማሳመኛ መልእክቶች ያስተላልፍ ነበር(ሐጌ 1፡13፤ 2፡4)፡፡ የይሁዳ ገዥ የነበረውን ዘሩባቤል፣ ሊቀ ካህናቱ ኢያሱና ከባቢሎን ምርኮ የተመለሱትም ቤተ መቅደሱ ዳግመኛ መገንባቱ ብቻ ሳይሆን ውበቱና ግርማው ላይ ትኩረት በመስጠት የበለጠ ተነቃቅተው ማነጽ ጀመሩ(ሐጌ 1፡14)፡፡ ይህ ቤተ መቅደስ ውበቱ ከቀድሞው ቤተ መቅደስ እጅግ በጣም የበለጠና ከቀድሞ ክብሩም እጅግ በጣም የላቀ፣ በሀብትም የተሞላ እንደሚሆን ነቢዩ ጨምሮ ያረጋግጥላቸዋል(ሐጌ 2፡3-6)፡፡  እግዚአብሔር ራሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደገና ሰማይንና ምድርን ባሕርንና የብስን አናውጣለሁ፤ መንግሥታትን እገለብጣለሁ፤ ሀብታቸውን ሁሉ ወደዚህ እንዲመጣ አደርጋለሁ፤ ስለዚህም ቤተ መቅደሱ በሀብት የተሞላ ይሆናል በማለት ያረጋግጥላቸዋል(ሐጌ 2፡6)፡፡ በአጠቃላይ አዲሱ ቤተ መቅደስ በውበት፣ በክብርና በሀብት ከቀድሞው እጅግ በጣም የተሻለና ወደር የማይገኝለት እንደሚሆን ነቢዩ እያረጋገጠ ሕዝቡን የበለጠ ይቀሰቅሳል፡፡ ስለዚህ የነቢዩ ሐጌ ዋና ዓለማ የነበረው የቤተ መቅደሱ መታነጽ እስከ ሚጠናቀቅ ድረስ ሕዝቡ እንዳይሰለችና እንዳያፈገፍግ ነው፡፡ በመሆኑም ሕዝቡን በተለያየ መልኩ ያነቃቃዋል፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

  1. የነቢዩ ሶፎንያስ የአገልግሎት ሕይወት፣ የመጽሐፉ ጥንቅርና ዋና ትኩረት በተመለከተ ትክክል የሆነው የትኛውን ነው?

ሀ) የመጽሐፉ የቃላት አጠቃቀምና የነገሮች አገላለጹ ሲታይ ጸሐፊው ከግብርና ከቤት እንስሳት ጋር ቅርበት ያለው ይመስላል፡፡ ለ)መጽሐፉ ቅደም ተከተል በጠበቀና ወጥነት ባለው መልኩ የተዋቀረ ነው፡፡ ሐ) የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ምናሴ በነገሠ ጊዜ ብዙ በጎ ተግባራት አከናውኖአል፡፡ መ)ሶፎንያስ የዘር ሃረጉን እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ ይቈጥራል፡፡ ሠ) በመጽሐፉ ጅማሬ ይሁዳ በተለይም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ከጣዖት አምልኮ የራቁ እንደነበር ይገልጻል፡፡

2. በነቢዩ ሶፎንያስ ከተካተቱት የትንቢት ቃል ውስጥ ትክክል የሆነውን የትኛውን ነው?(ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ትንቢተ ሶፎንያስ ሦስቱም ምዕራፎች መነበብ ይኖርባቸዋል)፡፡

ሀ)ገና ከጅማሬው እግዚአብሔር የሰውን ዘር በሙሉ ከምድር እንደሚያጠፋ፤ እንስሳት ግን እንደሚተው ይናገራል፡፡ ለ)ከምርኮ የተረፉት የእስራኤል ሕዝብ በማንም ላይ ክፉ አያደርጉም፤ በልጽገው በሰላም ይኖራሉ፡፡ ሐ) የኢየሩሳሌም ነቢያት በተገቢው ሁኔታ በትሕትና ተግባራቸው እየተወጡ ነበር፡፡ መ) የሞአብና የዐሞን ሕዝቦች የእግዚአብሔር ሕዝቦችን ያከብሩ ነበር፡፡ ሠ) የኢየሩሳሌም ካህናት በትጋት ያገለግሉ ነበር፡፡

3. በትንቢተ ሶፎንያስ ውስጥ “የጽዮን ልጅ ሆይ ! ዘምሪ ! የእስራኤል ሕዝብ ሆይ ዘምሩ ! እልልም በሉ ! የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ ! በሙሉ ልብሽ ደስ ይበልሽ” ይላል፡፡ የዚህ የደስታና የዝማሬአቸው ዋና ምክንያት ምንድን ነው? ለምንድንድ ነው እልል እያሉ እንዲዘምሩ የሚነግራቸው?

4. የነቢዩ ሐጌ ሕይወት፣ የመጽሐፉ ጥንቅርና ይዘት እንዲሁም ስለ ቤተ መቅደስ መታነጽ ከተናገረው ውስጥ ትክክል የሆነውን የትኛውን ነው?

ሀ) ነቢዩ ሐጌ የትንቢት ቃሉን ያስተላለፈው ባቢሎን ውስጥ ለነበሩት አይሁዶች ነው፡፡ ለ)ሳምራውያኖች የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እንዲታነጽ ሲተባበሩ ነበር፡፡ ሐ) ቤተ መቅደሱ ዳግመኛ ሲታነጽ ውበቱና ግርማው ላይ ትኩረት በመስጠት የበለጠ ተነቃቅተው ይሠሩ ነበር፡፡ መ)በወቅቱ በሕዝቡ የደረሰው ችግር ከቤተ መቅደሱ አለመገንባቱ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ሠ)ሕዝቡ የቤተ መቅደሱን ሥራ ቸል ብለው ወደ እርሻ ሥራቸው በገቡ ጊዜ ብዙ ምርት መሰብሰብ ቻሉ፡

5. በትንቢተ ሐጌ ውስጥ እግዚአብሔር “አገልጋዬ” ብሎ በመጥራት “አንተን ወስጄ በእኔ ስም መግዛት እንድትችል አነግሥሃለሁ፤ እኔ አንተን መርጨሃለሁ፤ እንደ ማኅተም ቀለበቴ አደርግልሃለሁ” የሚለው ለማን ነው?

6. ነቢዩ ሐጌ የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያና የቃል ኪዳን ታቦቱ መቀመጫ የነበረው ቤተ መቅደስ እንዲታነጽ ሕዝቡን በተለያየ መልኩ ይቀሰቅሳል፡፡ ይህ ቤተ መቅደስ በናቡከደነፆር በተመራው በባቢሎናውያን ጦር በ587 ዓ.ዓ አካባቢ ፈርሶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ራሱ “ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ቤት አስጊጦ እየሠራ የእኔ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ ሆኖ ቀረ፤” ይላል(ሐጌ 1፡ 9)፡፡ ቤተ መቅደሱ እንዲታነጽ የእግዚአብሔር ጽኑ ፍላጎት ነበር፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆናችሁንና የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ መኖሩን ታውቁ የለምን? እንግዲህ ሰው የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነው፤ ይህም ቤተ መቅደስ እናንተ ናችሁ” ይላል(1 ቆሮ 3፡ 16-17)፡፡ ስለዚህ የዛሬው ቤተ መቅደስ የእያንዳንዳችን ሰውነት መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህ ሰውነት ሁሌም መታነጽ እንዳለበት ደግሞ ሐ.ጳውሎስ ይነግረናል፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግ በመጀመሪያ ፦1 ቆሮ 6፡ 12-20 ያለውን ክፍል እና 1 ቆሮ 3፡ 16-17 በደንብ እናንብብ፡፡ ቀጥሎም የሚከተለው ጥያቄ ለመመለስ እንሞክር፡፡

-    ዛሬ ለእኛ ቤተ መቅደስ ማነጽ ማለት ምን ማለት ነው? በቤተ መቅደሱ ውስጥ መኖር ወይም መደረግ ያለበት ተግባር ምንድን ነው?     

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት