እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

5. ቅናት (ምቀኛነት)

5. ቅናት (ምቀኛነት)

በትንሹ እሳት ስር ከተጠቃለሉት ብዙ የሥጋ ተግባሮች መካከል ምቀኛነትም ሳይጠቀስ ሊታለፍ የማይገባው እሳት ነው፡፡ ቅናት ወይም ቅንአት ዓይነቱ ሁለት ነው፡፡ አንደኛው ትክክለኛውና ወደ ጽድቅ የሚመራው መንፈሳዊ ቅናት ሲሆን፣ ሌላኛውና የኃጢአት መተግበርያው ቅንአት ደግሞ ከምቀኝነት ጋር የተቆራኘው ነው፡፡ ትክክለኛ መንፈሳዊ ቅናት ከሌለን መሻሻልንና ማደግን የማይፈልጉ ሐኬተኞችና፣ የማይሠሩ የማያሠሩም ጋሬጣዎች ያደርገናል፡፡ የእግዚአብሔር ቤት ቅንአት የማያቃጥለን ከሆንን፣ ቅጥረኛ እረኞች እንጂ መልካም እረኞች አንሆንም፡፡ እውነተኞቹን የአምላክ ወዳጆችን ግን የቤቱ ቅንአት እንደ እሳት ያቃጥላቸዋል፡፡ "ለቤትህ ያለ መንፈሳዊ ቅንአት በውስጤ እንደ እሳት ይነድዳል፤ በአንተ ላይ የተሰነዘረው ስድብ በእኔ ላይ ዐረፈ፡፡" (መዝ. 69፡9) ዳዊትን ይህ መንፈሳዊ ቅንአት ይፈጀው ነበር፤ በመዝሙሩም ላይ ትክክለኛ ስሜቱን ገልጿል፡፡ ከብዙ ዘመናት በኋላም ይኸው የእግዚአብሔር ቤት ቅንአት፣ ጌታ ኢየሱስን እያጋለው በቤቱ ውስጥ ይሸቅጡ የነበሩትን የገንዘብ ባሪያዎች በጅራፍ እየገረፈ አስወጥቷቸዋል፡፡ "‹ይህን ሁሉ ወዲያ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት› አላቸው፡፡ በዚያ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ‹ስለ ቤትህ ያለኝ ቅንአት እንደ እሳት አቃጠለኝ› ተብሎ እንደተጻፈ አስታወሱ፡፡" (ዮሐ. 2፡13-17 ተመልከት)

 

ጥጋችንን ይዘን ‹እኔ ምን አገባኝ አይመለከተኝም› የምንል ዳተኞች እንድንሆን የእግዚአብሔር ፍቃድ አይደለም፡፡ የቤቱ ቅንአት የሚበላን (የሚያቃጥለን)፣ የቤቱ ጉዳይ የሚመለከተን፣ ቤቱ ሲፈርስ የሚገደን እንጂ እጃችንን አጣምረን ትከሻችንን አወዛውዘን ዝም ብለን የምንመለከት እንድንሆን ጌታ አይሻም፡፡

 

በሌላ በኩልም የሌሎች ወገኖቻችን መሻሻል አስቀንቶን ለመሻሻል እንድንነሣሣ የጌታ ፍቃድ ነው፡፡ "እኔ የምደወዳቸውን ሁሉ እገስጻቸዋለሁ፣ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ፡፡" (ራዕይ. 3፡19) የወገኖቻችን በጎ ነገር በመንፈሳዊነት እንድንነሣሣ እስካደረገን ድረስ መልካም ቅንአት ነው፡፡ ‹ወንድሜ ለምን በለጠኝ?› ‹ለምን ከኔ ተሻለ?› ወዘተ... በሚል አጉል ቅንአት ከተነሣሣን ግን ምቀኝነት እንጂ እውነተኛ ቅንአት በልባችን የለም ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ቅንአትን ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚነቅፈው፡፡ ቅ.ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ ላይ ከዘረዘራቸው የሥጋ ሥራዎች መካከልም የሥጋ ቅንአት ይገኝበታል፡፡ (ገላ. 5፡19-21 ተመልከት)፡፡ የምቀኝነት እሳት አደገኛና ጠንቀኛ ነው፡፡ ሳኦልን ከመንፈስ ቅዱስ ማደሪያነት ወደ ክፉ መንፈስ ማደሪያነት የለወጠው ይኸው መዘዘኛ ቅንአት (ምቀኝነት) ነበር፡፡ በሳሙኤል እጅ የተቀባ ዕለት የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል የወረደበትና አዲስ ልብን የተቀበለው ሳኦል በጌታ መንፈስ ስር ሆኖ ትንቢትንም ይናገር ነበር፡፡ ኋላ ግን ዳዊት ጎልያድን ገድሎ ሲመለስ፣ የአገሩ ሴቶች "ሳኦል ሺህ፣ ዳዊትም እልፍ (አሥር ሺህ) ገደለ" እያሉ እየተቀባበሉ በመዝፈናቸው ምክንያት፣ ሳኦል እጅግ ተቆጣ፡፡ "እርሱም፡- ለዳዊት እልፍ (አሥር ሺህ) ሰጡት፣ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ ሰጡኝ፤ ከመንግሥት በቀር ምን ቀረበት? አለ፡፡ ከዚያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ተመቅኝቶ ተመለከተው፡፡" (1ሳሙ. 18፡6-9) የምቀኝነት መጨረሻው ክፉ ነው "በነጋውም ሳኦልን ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው፣ በቤቱም ውስጥ ትንቢት ተናገረ፡፡" (1ሳሙ. 18፡10) የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል የወረደበት ዕለት ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ክፉ መንፈስ የያዘው ጊዜ ትንቢት ተናገረ፡፡ በሁለት ተቃራኒ ዓለሞች ውስጥ እንዲኖር ያደረገው መዘዘኛው የምቀኝነት እሳት ነው፡፡ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስም ቢሆን ይህ የምቀኝነት መንፈስ አልተለየውም ነበር፡፡

 

እሺ እኛስ የትኛው እሳት ይንደድብን? አሁንም ነገም ለዘላለምም የሚፈጅና የሚያቃጥለው ትንሹ እሳት፣ ወይስ አሁን የሚያጠራው የሚባርከው የሚቀድሰውና ነገና ለዘላለምም በማያቋርጥ ብርሃን ውስጥ የሚያኖረን የአርያሙ እሳት? በፍላጎት በኩል ትክክለኛውን ምርጫ እንደምናደርግ አልጠራጠርም፤ በሕይወት ጉዞ በኩልስ? እዚህ ላይ ሁሉም ለየራሱ በግሉ ይመልሳል፡፡ የመጨረሻው ቀን ሁሉንም ግልጽ ያደርገዋል፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት