እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የነፍስ ኄር አባ ገብረማርያም አጭር የሕይወት ታሪክ

የክቡር አባ ገብረማርያም አመንቴ የሕይወት ታሪክ (ገድል)

"ሩጫዬን እስከመጨረሻው ሮጫለሁ፣ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶ ይጠብቀኛል፡፡" (2 ጢሞ፣4፡7)

AGM6ክቡር አባ ገብረማርያም አመንቴ ከአባታቸው አቶ አመንቴ አባያና ከእናታቸው ወ/ሮ በክሳ ዳኧባ በ1913 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደር በነቀምቴ አውራጃ በዋዩ ጡቃ በኮምቶ ወረዳ ልዩ ስሙ ጃቦ በሚባል ቦታ ተወለዱ፡፡

ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ በዘመኑ ይሰጥ የነበረውን የቤተክህነት ትምህርት የተከታተሉ ሲሆን ወደ ደንቢዶሎ ሳኮ በሚገኘው የካቶሊክ ትምህርት ቤት በመግባት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡

ከጠላት ወረራ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እንደማንኛውም የአካባቢያቸው ወጣቶች ሃገራቸውን በውትድርና ለማገልገል ባላቸው ጽኑ ፍላጎትና ምኞት በተለያዩ ወታደራዊ  ተቋም ቀርበወ ለመግባት ባደረጉት ጥረት የተመኙት ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡

ክቡር አባ ገብረማርያም ከልጅነታቸው ጀምሮ  በጸሎተኛ ቤተሰብ በማደጋቸው ይህንን ባህሪያቸውን ሳይለቁ አዲስ አበባን ከረገጡበት ጊዜ ጀምሮ

ዛሬ የአርበኞች ትምህርት ቤት ያለበትን ቦታ በነበረው የካቶሊክ ቤተክርስቲያንና ት/ቤት በመመላለስ ላይ እያሉ የሕይወት አቅጣጫን የሚያስቀይር ጥሪ ቀረበላቸው፡፡

በጊዜው በኢትዮጵያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ የነበሩት አቡነ ኪዳነ ማርያም ካሣ ዘወትር ከቤተክርስቲያን የማይለየውን ወጣት ሞላ አመንቴን በማስተዋልና በመመልከት ብሎም በአካል በማስጠራት በዚያ ዕድሜው ለእምነቱ ባለው ፍቅር በመማረክ ከየት እንደመጣ በመጠየቅና የተፈጥሮ ልዩ ችሎታውን በማድነቅ ለዘርዓ ክህነት እጩነት ጥሪ ያቀርቡለታል፡፡

ወጣት ሞላም በመጀመሪያ የቀረበላቸውን ጥየቄ በመጠራጠርና ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ጳጳስ በማየታቸውና በመደነቅ በብፁዕ አቡነ ኪዳነ ማርያም ትህትናና ሥነ ምግባር በመማረክ በዚሁ ገዳም በንኡስ ዘርአ ክህነት ት/ቤት ገብቶ ለመማር ጥሪውን ተቀበሉ፡፡

በመቀጠልም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሮም ኢትዮጵያ ኮሌጅ ተልከው በፍልስፍናና በነገረ መለኮት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በመቀጠልም ወደ እንግሊዝ አገር በኬንብረጅ ዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ ትምህርት ለአንድ አመት ወስደዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ታህሳስ 1948 ዓ.ም. በሮም ቫቲካን በብፁእ ሞንሲኞር ባቲሊድ እጅ አባ ገብረማርያም ተሰይመው ምስጥረ ክህነት የተቀበሉ ሲሆን ታህሳስ 8 በሮም በምትገኘው እመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የመጀመሪያ ቅዳሴአቸውን አሳርገዋል።

በ1948 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሁለገብ ካህን ሆነው የመጀመሪያ ዓመታትን ሲያገለግሉ ብፁዕ አቡነ ኃይለማርያም ካሕሳይ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ለሚገኙ ለኢትዮጵያውያን ካቶሊካውያ ምእመናን የነፍስ አባት እንዲሆኑ ተመርጠው በቁምስናውን አግልግሎት መስጠት ይጀምራሉ፡፡ መኖሪያቸውን ካቴድራል ልደታ ለማርያም በማድረግ ዕለት ዕለት በመመላለስ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ቅዳሴ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲደረግ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡

ክቡር አባ ገብረማርያም አመንቴ ሁልጊዜ የሚናገሩትና የማይረሱት የብፁዕ አቡነ አስራተማርያም ወሳኝ አመራርና የመድኃኔ ዓለም ቁምስና ምእመን ጠንካራ የእምነት አቋም ለሐዋርያዊ አገልግሎታቸው መሠረት መሆኑን ነው፡፡

ክቡር አባ ገብረማርያም ከሐዋሪያዊ አገልግሎታቸው ጎን ለጎን ከ1952 ዓ/ም ጀምሮ በጎልማሶች የፊደል ሠራዊት አስተምሮ የጀመሩት መርሃግብር ቀስ በቀስ በማደግ ታዋቂና ዝነኛ የሆነውን የካቶሊክ ካቴድራል የማታ ትምህርት ቤት ለመመስረትና ለብዙ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን ታላቅ የእውቀት ዘር በመዝራት ሃገርንና ወገንን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመዋል፡፡

ከ1970 ጀምሮ ከ10 ዓመታት በላይ የልደታ ማርያም ወንዶች ት/ቤት የቀኑንና የማታውን ክፍለጊዜ ጋር በጣምራ በማስተዳደር ብቃት ያላቸውን መምህራንን በማሰባሰብ የትምህርትን ጥራት ደረጃ በማሳደግ እንዲሁም ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ጋር በማጣመር ከሕፃን እስከ አዋቂ ሁለንተናዊ እድገት እንዲኖረው ጥረዋል፡፡

ክብር አባ ገብረማርያም ሁለገብ አገልጋይ ቢሆኑም የኢትዮጵያ ካፑቺን አባቶች የመድኃኔ ዓለምን ቁምስና ከተረከቡ በኋላ ሐዋሪያዊ አገልግሎታቸውን ከ1970 ዓ.ም. ጀምሮ በልደታ ማርያም ካቴድራል በረዳትና በዋና ቆሞስነት እስከ 1999 ዓ.ም. አገልግለዋል፡፡

ክቡር አባ ገብረማርያም በተጨማሪ፡-

  • በኢትዮጵያ ቤተ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን ከፍተኛ የመማክርት ጉባኤ አባል
  • በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ም/ም/ቤት የቆሞሳት ሰብሳቢና አማካሪ
  • የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በመወከል በሃገርና በውጪ ሃገር ልኡክ በመሆንና በመሳሰሉት አገልግለዋል፡፡
  • የካህናትና የመእመናን አማካሪና የነፍስ አባት መሆን
  • ሕሙማንንና እስረኞችን መጠየቅ
  • ሐዘንተኞችን ማፅናናት
  • የተቸገሩትን መርዳት
  • ለሀገራቸው አንድነትና ዕድገት ያላቸው ራእይ
  • ከሕፃን እስከ ሽማግሌ እንደየ ዕድሜያቸው ያላቸው አቀባበል
  • የቋንቋ ልዩ ችሎታቸው (ከ7 በላይ ቋንቋ መናገራቸው)
  • ለእስፖርት ያላቸው ልዩ ፍቅር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ አባ ገብረማርያም ያልሠሩት ሐዋሪያዊ አገልግሎት አለ ብሎ መናገር ይከብዳል፡፡

ዋና ተግባራቸው ነበር፡፡ {jathumbnail off}

ወደ ግል ሕይወታቸው ስንመጣ ፍፁም ለገቡት ቃል ታማኝ በመሆን ሕይወታቸው በታዛዥነትና በድህነት አሳልፈዋል፡፡ ክቡር የሆነውን የክህነት ምስጢር እስከ መጨረሻው አክብረውት እንዲከበር አድርገዋል፡፡

እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት፡-

ሌላው መጠቀስ ያለበት የመጀመሪያ ቤተክርስቲያ ቤተሰብ ናት፡፡ የአባ ቤተሰብ 7 ወንዶችና 8 ሴቶች በአጠቃላይ 15 ልጆችን ያፈራች ስትሆን ከነዚህ ውስጥ 3ቱ ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ዛሬ ሁለቱ በሞት ተለይተውናል፡፡

ቤተክርስቲያናችን ዛሬ ታላቅ መካሪ፣ ልዩ ሀብትና ታማኝ አገልጋይ አጥታለች፡፡ ምንም በአካል ቢለዩንም ሕያው ሥራቸውንና የእምነት ተጋድሎአቸውን ለእኛ አስተላልፈውልናል፡፡ ዛሬም ሃይማኖታችንን አውቀንና ተረድተን እንድንጠብቃት አደራቸውን ትተው አልፈዋል፡፡

እኛም ይህንን ታላቅ አደራቸውን በማጠናከርና በማሳደግ የእምነት ብርሃናችንን ይዘን ከተጓዝን የእርሳቸውን አግልግሎት መቀጠላችንን አንዘንጋ፡፡ እንግዲህ የአባታችንን የሕይወት ገድል ብንዘረዝረው ጊዜ አይበቃንም፡፡ ከሁሉም በላይ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝና ደግ አገልጋይ ሆነው ተልዕኮአቸውን ፈጽመዋል፡፡

ዘወትር ረዳታቸውና ባልደረባቸው የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረጅሙ ጉዞአቸው የእርሷን ፈለግ ተከትለዋታል፡፡

ምንጭ፡ በሥርዓተ ቀብራቸው ላይ በክቡር አባ ምስጋና ተሾመ የተነበበው በአቶ ገብሩ ሀብተዮሐንስ የተዘጋጀ ጽሑፍ 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት