እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ስንመጻደቅ እንዳንወድቅ

ስንመጻደቅ እንዳንወድቅ

በኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ በመከራ እንደምንፈተን ሁሉ እንደ ክርስቲያን መፈተናችን ግድ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ፈተና የሚመጣው ከሩቅ ሳይሆን ከምናየው፣ ከምንሰማውና ከምንመኘው ነገር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ፈታኞቻችን ዓለም፣ ሰይጣንና ሥጋችን እንደሚዋጉን ይነግረናል፡፡

ካርዲናል ፉልተን ሺን በአንድ ወቅት ባስተላለፉት ትምህርት ሰዎች ከምንፈተንባቸው ነገሮች አንዱ የራሳችን ፍላጐት መሆኑንና እንዴት ነፃነትን እንደምንቀዳጅ የሰጡትን ቃል እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡

በሰው አዕምሮ ውስጥ በቀላሉ የሚነሳሱ ሦስት ፍላጎቶች አሉ፡፡ የወሲብ ፍላጐት፣ የስልጣንና ንብረት የመያዝ ፍላጐት ናቸው፡፡ ሥጋችን ወሲብን መሻቱ፣ አዕምሮአችን ስልጣንን፣ ነፍሳችን ደግሞ ንብረትን መፈለጉ መጥፎነት የለውም፤ እነኚህ ሦስት ፍላጐቶች ጥሩ ናቸው ምክንያቱም የወሲብ ፍላጐት ባይኖር ቤተሰብ ባልተፈጠረ ነበር፤ ስልጣን የመሻት ምኞት ባይኖር እውነትን ባልፈለግናት ነበር፤ ተሪማዎችም ባልነበሩን፤ ንብረትን መፈለጋችን ለውስጣዊ ነፃነታችን ውጫዊ ዋስትና ነው፡፡ እኔ በውስጤ ነፃ ሰው ነኝ፤ ነፍሴን የራሴ ብዬ መጥራት እንዲሁም በውጭ ነፃ ነኝ፤ አንድን ነገር የራሴ ብዬ መጥራት እችላለሁና፡፡ እነኚህን ሶስት ፍላጐቶች መጥፎ የሚሆኑበትም ጊዜ አለ፡፡ ይኸውም ያለቦታቸው በተቀመጡ ጊዜ ነው ምክንያቱም ቆሻሻ ሆነዋልና፤ ቆሻሻ ማለት ያለ ቦታው የተቀመጠ ነገር ማለት ነው፡፡

ሦስቱ ፈላጐቶች መጥፎ የሚያሰኛቸው የወሲብ ፍላጐት ወደ ነብርነት ከቀየረን፣ የስልጣኑም እንደ አንበሳ ካልሆንን ካሰኘንና ንብረት መሻታችንም አላስፈላጊ ነገሮችን ወደ መሰብሰብ ምክንያት ከሆነን ነው ምክንያቱም ያለ ቦታቸው ተገኝተዋልና፡፡

መጥፎ ተግባሮች ልማድ ከመሆናቸው በፊት በሀሳባችን ይጸነሳሉ፡፡ ሰዎች ወሲብ ሲፈጽሙ ስናይ እኔስ ለምን አላደርገውም ወደሚል ሀሳብ እንገባለን፡፡ ስለ ስልጣን ስናስብ ይህንን አድርጉ፤ ያንን አታድርጉ የሚሉንን በመጥላት በራሳችን መንገድ መሄድ እንመርጣለን፤ ራስገዝ መሆን ያምረናል፡፡ ንብረት እንዲኖረን የመፈለጋችን ሀሳብ ሰርተን አልሆን ቢለን እንኳ አቋራጭ መንገድ እንፈልጋለን፤ ሰርቄ ባደርግ በሚል ሀሳብ እንፈተናለን፡፡ ከሀሳብ ጋር ከተስማማን በኋላ ወደ ድርጊቱ እንገባለን፡፡ ድርጊቱን ስንደጋግመው ወደ ልማድ ይለወጣል፡፡ ልማዱ እኛን ይቆጣጠረናል፤ ነገር ግን ነጻነታችን ተገደበ እንጂ መቶ በመቶ ጠፍቷል /ተወስዶብናል/ ማለት አይደለም፡፡

ብዙ ሰዎች ከታሰሩበት መጥመድ ውስጥ ሆነው ራሳቸውን ሲያዩት ተስፋ ይቆርጣሉ፤ መውጫው ይጠፋቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ራሳቸውን ያጠፋሉ፡፡ በሱስ ከተጠመድን ሕመምተኞች ነን፤ ከዚያ ነፃ ለመውጣትና ፈውስ ለማግኘት ሱሳችንን ማስወጣትና በምትኩ ሌላ ጥሩ ነገር ማስገባት ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ከማንም በላይ አስበልጠን የምንወደውን ነገር ፈልገን ማስገባትና ሱሳችንን /መጥፎ ልማዳችንን/ ማባረር ያስፈልጋል፡፡ በሰው አቅም ከሱስ መላቀቅ ከባድ ነው፤ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ግን ሁሉን ማድግ ይቻላል፡፡ የወሲብ፣ የስልጣንና የንብረት ፍላጐታችን ከአምላካችን ፍቅር አይበልጥብንም፡፡ የፍቅር አምላክ ነፃ የሚያወጣ ጌታ ነው፡፡

ስለ ፈተና ሲወሳ በብዙዎቻችን አዕምሮ የሚመጣው ወደ መጥፎ አቅጣጫ ለመሄድ መፈተንን ነው፤ ነገር ግን መጥፎ ከመሆን ይልቅ ጥሩ እንድንሆን የሚፈትኑን ብዙ ነገሮች እንዳሉን እናስታውስ፡፡ ለምሳሌ፡- አንድን ኳስ ብንወረውረው ሌላ ሰው በእግሩ መትቶ አቅጣጫ እስካላስቀየረው ድረስ በቀጥታ ይሄዳል፡፡ በአልኮል መጠጥም ሆነ በየትኛውም ሱስ የተጠመደ ሰው እንዲሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱ ጣልቃ ገብቶ፣ ካልገላገለውና አቅጣጫ ካላስቀየረው በቀር ባለበት መጓዝ የግድ ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሔር አቅጣጫ ማስቀየት በጐ ለመሆን መፈተን ብለን ልንጠራው እንችላለን፡፡

ከሕይወት ልምዳቸው ሲናገሩ ካርዲናል ሺን እንዲህ ይላሉ “ሴትዮዋ የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ ናት፡፡ አንድ ቀን ወደ እኔ መጥታ እንዲህ አለችኝ፡- አባ ሆይ! ለመጠጥ የማወጣው ገንዘብ በዓመት ወደ ሰማንያ ሺህ የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡ ከመጠጥ ሱስ ለመላቀቅ በተለያዩ ሆስፒታሎች ለአራት ጊዜ ተመላልሻለሁ ግን ለውጥ አላየሁም፤ በዚህ ሀሳብ መፍትሔ ሳፈላልግ እርስዎ ትዝ አሉኝና ወደ እርስዎ መጥቻሉሁና እባክዎን ይርዱኝ” አለችኝ፡፡ ልጄ ሆይ ከምንም ከማንም በላይ መጠጥን ስለምትወጂ ልረዳሽ የምችል አይመስለኝም፡፡ የመጠጥ ሱስሽን ከውስጥሽ ማስወጣት እንችላለን ካልኳት በኋላ አንድ ሰዓት ተኩል ይህል ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ነገርኳትና በመቀጠልም የምትጠጣበትን ቦታ ጠየኳትና ስትነግረኝ እንዲህ አልኳት፡- ነገ ወደ መጠጥ ቤቱ ሂጂ፣ ስትደርሺ በሩ አጠገብ ቁሚና ከጌታዬ ከኢየሱስ ይበልጥ ይህንን መጠጥ እወዳለሁን? ብለሽ ራስሽን ጠይቂ፤ ካማረሽ ትንሽ ጠጪ፡፡ በዚያ በኋላ ነይና ስለ ሁኔታው አጫውቺኝ አልኳት፡፡ እንዳልኳት አደረገች፡፡ መጠጥን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አቆመች፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማነው? የዓይን አምሮት፣ የወሲብ ፍላጐት፣ የስልጣን፣ የንብረት ወይስ የገንዘብ ጥማት እነኘህ ሁሉ ከክርስቶስ ፍቅር ሊለዩን አይችሉም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ትክክለኛው  አቅጣጫ የሚመልሰን አምላክ ነው፡፡ በየትኛውም ሱስ እንጠመድ ተስፋ መቁረጥ አይገባንም ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጥምና፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን ኢየሱስን “ጌታ ሆይ ኃጢአተኛ ስለሆንኩ ወደ እኔ አትቅረብ” ሲለው ጌታችን ኢየሱስም “አዎን ኃጢአተኛ መሆንህን አውቃለሁ፤ ለዚህም ነው የምፈልግህ” አለው፡፡ እኛን ከነኃጢአታችን የሚወደን አምላክ በምንፈተንበት ጊዜ ከፈተና የምንወጣበትን መንገድ የሚያዘጋጅ አምላክ ነው፡፡

አንድ ተማሪ በርትቶ በማጥናት ፈተናውን በጥሩ ውጤት ሲያልፍ ይደሰታል፣ ክብርም ያገኛል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ጥረት አድርጐ የተጠበቀውን ያህል ውጤት በተለያዩ ምክንያቶች ሳያመጣ ቢቀር ወድቀሃልና ትናንት የሰጠንህን ክብር መልሰን እንወስድብህና እናዋርድሃለን አይባልም፡፡ እንደዚሁም በክርስትና ሕይወታችን ከንግግራቸው እስከ ተግባራቸው ለመንፈሳዊ ሕይወታችን መታነጽ ምክንያት የሆኑን ሰዎች ጥሩ አብነት በመስጠታቸው ከውስጥና ከውጭ የሚገጥሙአቸውን ፈተናዎች በማሸነፋቸው ክብር እንዳልሰጠናቸው ሁሉ አንድ ቀን ወድቀው ስናያቸው ዓይናችሁን ላፈር ያድርገው ብለን እነርሱን ካከበርንበትና ባደነቅንበት አንደበት ዝቅ ዝቅ ልናደርጋቸው ልናዋርዳቸው አይገባም፡፡ ሁልጊዜ እንፈተናለን ነገር ግን ሁልጊዜም እናልፋለን ማለት አይደለም፤ በመቆማችን ስንኩራራ መውደቅም ይመጣልና፡፡ ስለዚህ ተፈትኖ የወደቀ ከውድቀቱ እንዲማር መርዳት፣ ማበረታታትና መጸለይ የክርስትናችን አንዱ ሃላፊነት ነው፡፡ በመቆማችን የምንመፃደቅ፣ በሌሎችም ተፈትኖ መውደቅ የምንሳለቅ ከሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ሲመክረን የቆመ የሚመስለው ሰው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ ይለናል፡፡

ዛሬ ቆመን መታየታችን ሌሎች ደግሞ መውደቃቸው ሁላችንም በአንድ ጀልባ ውስጥ መሆናችንን /ኃጢአተኛነታችንን/ ያሳየናል፡፡ ታዲያ በየዕለቱ የሚጥሙንን ፈተናዎች ለማሸነፍ ወደ ፈተና እንዳንገባ ሰውረን ብለን ከመጸለይ ባሻገር ምን ማድረግ እንችላለን ለመልሱ ከድረ-ገጽ ያገኘኋቸው የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

1. ሽልማትን ማስታወስ

ልክ እንደ ሙሴ ወደፊት የሚጠብቀንን ሽልማት እንመልከት፡፡ ሙሴ ካደገ በኋላ “የፈርዖን የልጅ ልጅ ተብሎ መጠራትን ያልፈቀደው በእምነት ነው፤ ስለዚህም እርሱ በሃጢአት ከሚገኘው ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ወደፊትም የሚቀበለውን ዋጋ ስለተመለከተ ከግብፅ ሀብት ይልቅ መሲሁ መዋረድ የበለጠ መሆኑን አሰበ” /ዕብ 11፡24-26/

2. የኃጢአትን መጥፎነት ማመን

ኃጢአት ጌታችን ኢየሱስ እንዲሞት ያደረገ መጥፎ ነገር ነው፡፡ እግዚብሔርን መውደድ ማለት ክፋትን መጥላት ያካትታል “ዑፅ ተብላ  በመትጠራ አገር ኢዮብ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ከክፉ ነገር ሁሉ ርቆ እግዚአብሔርን የሚፈራ ምንም ነውር የሌለበት ቅን  ሰው ነበር” /ኢዮብ 1፡1/፡፡ “ከሕግህ ማስተዋልን አግኝቻለሁ፤ ስለዚህ የሐሰት መንገድን ሁሉ እጠላለሁ” /መዝ 119፡1ዐ4/

3. ገንዘብን አለማፍቀር

ጠንክሮ መስራትና ገንዘብ ማጠራቀም ኑሮን ማሻሻል ተገቢ ነው፤ ነገር ግን ገንዘብ አምላካችን እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ምንጭ ነውና፡፡ “ሀብታሞች ለመሆን የሚፈልጉ በፈተና ይወድቃሉ፤ ሰዎችን በሚያበላሽና በሚያጠፋ ከንቱና አደገኛ በሆነ በብዙ ምኞት ወጥመድ ይያዛሉ” /1ጢሞ 6፡9-1ዐ/፡፡ አንድ ሰው ለሁለት ጌቶች አገልጋይ ሊሆን አይችልም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሌላውንም ይወዳል፤ ወይም አንዱን ያከብራል፤ ሌላውን ይንቃል፤ እንዲሁም አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ አገልጋይ መሆን አይችልም፡፡ ልባችን ያለው ገንዘባችን ላይ ከሆነ ከእግዚአብሔር ጋር ሊሆን አይችልም፡፡ ማቴ 6፡21-24

4. ፈተናን ማሸሽ /መራቅ/

ወደ ፈተና ከሚያስገቡ ሁኔታዎች፣ ጊዜያት፣ ቦታዎችና ሰዎች መራቅ /መሸሽ/ ጠቃሚ ነው፡፡ ዮሴፍ ከጶጢፋር ሚስት በመሸሽ ከፈተናው አመለጠ /ዘፍ 39፡12/ ፈተና የሚመጣው በከፈትንለት በር በመግባት ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ፤ እርሱም ወደ እኛ ይቀርባል /ያዕ 4፡8/፤ ከፈተና መሸሽ የጅልነት ሳይሆን የብልጥነት ምልክት ነው፡፡

5. ብዙኃኑን አለመከተል

ትክክል ያልሆነውን ነገር ብዙዎች ስላደረጉት ብቻ ትክክል ነው ብሎ ብዙኃኑን መከተል ወደ ፈተና ከሚያስገቡን ነገሮች አንድ ነው፡፡ ሁሉም ሰው እያደረገው ነውና ትክክል ነው ማለት ትክክል አይደለም፡፡ ሌሎች ሲያደርጉ አይቶ እንደ ትክክለኛ ነገር በመቁጠር ነው ጴጥሮስም ኢየሱስን የካደው፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ከአንተ ጋር እሞታለሁ እንጂ አልክድህም፤ ሌሎች እንኳ ቢክዱህ እኔ ከቶ አልክድህም ይል የነበረው ጴጥሮስ ነው የካደው /ማቴ 7፡13/፡፡

ሌሎች በሬ ወለደ ስላሉን በሬ ይወልዳል ማለት አይደለም፤ እንደ ቦይ ውሃ በሚመሩን አቅጣጫ ጨፍኖ መሄድ የክርስትናችን መገለጫ አይደለም፡፡ የሚያሰሙንና የሚያሳዩን ሁሉ እውነተኛና ትክክለኛ ነው ብለን መቀበል የለብንም፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች ውሸትን እንደ እውነት ቢቀበሉት እንኳ ዛሬም ውሸት ነው፡፡

6. በሥራ መጠመድ

ጣሊያኖች አንድ አባባል አላቸው “የሚሰራ ሰው በአንድ ሰይጣን ይፈተናል፤ የማይሰራ ሰው ግን በአንድ ሺህ ሰይጣኖች ይፈተናል”፡፡ ሥራ መፍታታ በፈተና ለመውደቅ በር እንደሚከፍት መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ “እነሆ የእህትሽ የሳዶም ሃጢአት ይህ ነበር፤ ትዕቢት፣ እንጀራን መጥገብ፣ መዝለለና ሥራ መፍታት በእርስዋና በሴት ልጆችዋ ነበር … ስለዚህ ባየሁ ጊዜ አጠፋኋቸው” ሕዝ 16፡49-5ዐ፡፡

ሥራ መፍታት አይደለም እንዴ የሰውን ስም እንድናጠፋ፣ ሰውን እንድናማ፣ ያለ ሥራችን ጣልቃ እንድንገባ የሚያደርገን ሥራ ለመፍጠር ብንሞክር ሲያንስ ከሀሜት ኃጢአት እንድን ነበር፡፡ በስንፍናችን ሰይጣንን እንፈታተነውና በኋላ ሰይጣን ፈተነን እንላለን፡፡

“ እንግዲህ እንዴት እንደምትኖሩ በጥንቃቄ አስተውሉ፤ እንደ ጥበበኞች እንጂ እንደ ሞኞች አትኑሩ፡፡ ይህ ዘመን ክፉ ስለሆነ በማናቸውም አጋጣሚ ጊዜ ተጠቀሙ” ይለናልና ኤፌ 5፡15-16፡፡

በመልካም ሥራ በመጠመድ ከፈተና እንጠበቅ፡፡

ምንጭ፡ ፍቅርና ሰላም መስከረም 2ዐዐ1

በአባ አብነት አበበ ዘማኀበረ ልኡካን /ላዛሪስት/

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት