የር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ ስብከት ዘሆሳዕና 2005 ዓ.ም.

የር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ ስብከት ዘሆሳዕና 2005 ዓ.ም.

triumphal-entry-zoom1. ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በርካታ ተከታዮቹ ታላቅ በዓል አደረጉለት፤ ልብሶቻቸውን በፊቱ አነጠፉለት፣ እርሱ ስላደረገላቸው ተዓምራት በብዙ ይነጋገሩ ነበር፣ "በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተመሰገነ ነው፤ ምሥጋና በሰማይ ለእግዚአብሔር ይሁን ሰላምም በምድር በጎ ፈቃድ ላላቸው ይሁን" የሚል ታላቅ የምሥጋና ድምፅ ይሰማ ነበር፡፡ (ሉቃ 19፡38)

ተከታዮቹም በምሥጋና፣ በታላቅ በዓል፣ በበረከት እና በሰላም ተሞሉ፤ የደስታ መንፈስ ሰፈነ፡፡ ኢየሱስ በተለይ በድሆች እና በሚስኪኖች፣ በትሑታን እና በተረሱት ሰዎች ልቦና ውስጥ ትልቅ ተስፋ ቀሰቀሰ፡፡ እነዚህ ሰዎች በዓለም ፊት ለዓይን የማይሞሉ ነበሩ፡፡ እርሱ የሰው ልጆችን ስቃይ ያውቀዋልና የእግዚአብሔርን የምሕረት ፊት አሳያቸው፤ ነፍስን እና ሥጋን ለመፈወስ ሲል ዝቅ አለ፡፡

ይሄ ኢየሱስ ነው፡፡ ይህ ድካማችንን፣ ኃጢአታችንን እንዲሁም እያንዳንዳችንን የሚመለከተን ልቡ ነው፡፡ የኢየሱስ ፍቅር ታላቅ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ፍቅር ወደ ኢየሩሳሌም በመግባት አኛን ይመለከተናል፡፡ በጣም ውብ የሆነ ገጽታ ነው፤ በኢየሱስ ልብ ፍቅር ብርኃን የተሞላ ነው፤ በደስታ እና በበዓል መንፈስ የተሞላ ነው፡፡

በቅዳሴያችን መጨረሻ ላይ እኛም ይህንኑ እንደግመዋለን፡፡

ዘንባባችንን እና የወይራ ቅርንጫፎቻችንን እናውለበልባለን፡፡ አኛም ኢየሱስን በቤታችን እንቀበለዋለን፤ ከእርሱ ጋር በመንገዱ ላይ በመገኘታችን የተነሳ ደስታችንን እንገልፃለን፡፡ ቅርባችን መሆኑን በምናውቅበት ጊዜ፣ በማንነታችን ውስጥ በመገኘቱ፣ ጓደኛችን ሆኖ በመቅረቡ፣ ወንድማችን በመሆኑ እና በንጉሥነቱ እንደሰታለን፤ ይህም ለሕይወታችን የሚያበራ በተራራ ላይ ያለ መብራት ነው፡፡ ኢየሱስ አምላክ ነው ነገር ግን ዝቅ ብሎ ከእኛ ጋር ለመጓዝ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡ እርሱ ጓደኛችን እና ወንድማችን ነው፡፡ እርሱ መንገዳችንን ከዚህ ጀምሮ ያዘጋጀዋል፡፡ እናም በዚህ መልኩ እኛም ዛሬ ተቀብለነዋል፡፡ እንግዲህ ከሁሉ አስቀድሜ የምነግራችሁ ቃል እነሆ፤ ደስታ! የሃዘን ሰዎች አትሁኑ፣ ክርስትያን በፍጹም በሃዘን ውስጥ አይኖርም! ለተሥፋ መቁረጥ እጁን አይሰጥም! የእኛ ኃብት የቁሳዊ ነገሮች ባለቤትነት ሳይሆን አንድ ግለሰብን ማግኘት ነው፤ እርሱም ኢየሱስ ነው፡፡ ደስታችን ኢየሱስ በመካከላችን መገኘቱ ነው፣ ከእርሱ ጋር ስንሆን መቼም ቢሆን ብቻችንን እንደማንሆን በማወቅ እንደሰታለን፤ በአስቸጋሪ ጊዜያቶች፣ የሕይወት ጉዟችን ሁሉ ወደ ችግር እና ወደ ፈተና ሲገባ እና እነዚህ ችግሮች እና ፈተናዎች የሚታለፉ ሳይመስሉን በላይ በላይ ሲደራረቡ እንኳን ብቻችንን አይደለንም፤ በእነዚህ ጊዜያት ጠላት ዲያብሎስ ይመጣል፣ ብዙ ጊዜ የበግ ለምድ ለብሶ ተኩላው ይመጣል የእርሱን ሃሳቦች በጆሮአችንን በሹክሹክታ ይነግረናል፡፡ እርሱን እንዳትሰሙት! ይልቁንም ኢየሱስን እንከተለው! ከእርሱ ጋር እንጓዛለን! ኢየሱስን እንከተላለን ከሁሉም በላይ ደግሞ እርሱ ራሱ ከእኛ ጋር እንደሚመላለስ እና በትክሻው ላይ ተሸክሞን እንደሚዞር እናውቃለን፡፡ ይህ ነው የእኛ ደስታ፤ ለዚህ ዓለም የምናበረክተው ተሥፋ ይሄው ነው፡፡ ተስፋችሁ ከእናንተ ይወሰድባችሁ ዘንድ ዝም አትበሉ! ተሥፋ እንዲሰረቅባችሁ አትፍቀዱ! ይህም ተሥፋ ኢየሱስ የሰጠን ነው፡፡

2. ሁለተኛው ቃል፡፡ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ስለምን ገባ? ወይም ኢየሱስ ወደ ኢየሩሣሌም የገባው እንዴት ነው? ሕዝቡ እንደ ንጉሥ ተመለከተው፤ እርሱም መሆኑን አልካደም፣ ዝም እንዲሉም አልነገራቸውም (ሉቃ 19፡ 39-40) ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ምን አይነት ንጉሥ ነው? እስቲ እንመልከተው፤ በአህያይቱ ጀርባ ላይ ተቀምጧል፤ በሠረገላ አልታጀበም፤ ኃይሉን ለማመልከት በሠራዊት አልተከበበም፤ ወደ ምስኪኖች እና ወዳልተማሩ ነገር ግን በኢየሱስ ውስጥ አንዳች ትልቅ ነገር ወዳስተዋሉት ትሑት ሕዝቦች መጣ፤ እነርሱም እነሆ መድኃኒታችን ለማለት የሚያስችል እውቀት ነበራቸው፤ ይህም በልባቸው ያለው እምነት ነው፡፡ ኢየሱስ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ወደ ኢየሩሣሌም የገባው ለምድራዊ ነገሥታት የተዘጋጀውን ክብር ለመውረስ፣ የኃይለኞችን ሥልጣን ለመጋራት፣ የገዢዎችን መንግሥት ለመሻማት አይደለም፡፡ ነገር ግን ኢሳያስ በትንቢቱ እንዲህ ብሎ እንደሚናገረው "ለሚገርፉኝ ጀርባዬን፣ ጢሜንም ለሚነጩኝ ጉንጬን ሰጠኋቸው፣ ከሚሰድቡኝ እና ከሚተፉብኝ ፊቴም አላዞርኩም" (ኢሳ 50፡6) ለመገረፍ፣ ስድብና ንቀትን ለመቀበል፣ የእሾህ አክሊል ለመቀዳጀት፣ ቀይ ካባ ለመልበስ፣ በዘንግ ለመገረፍ ሲሆን ንግሥናውም ሊፌዝበት መጣ፡፡ ወደ ኢየሩሣሌም የገባው የጎልጎታን ተራራ ለመውጣት የእንጨቱን ሸክም ለመሸከም ነው፡፡ ይህም ወደ ሁለተኛው ቃል ያደርሰናል፣ እርሱም መስቀል ነው፡፡ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለመሞት ነው፡፡ የእርሱ ንግሥና እንደ አምላካዊ ገጽታው ጎልቶ የሚያበራው እዚህ ላይ ነው፤ የንግሥናው ዙፋን የእንጨቱ መስቀል ነው! ይህም ቤኔዲክቶስ 16ኛ (Pontiff Emeritus) ለካርዲናሎች ያሉትን ነገር የስታውሰኛል፡- "እናንተ የተሰቀለ ንጉሥ ልዑላን ናችሁ፡፡ ያ የኢየሱስ ዙፋን ነው፤ ኢየሱስ ወደ ራሱ አስጠግቶታል፣ ለምን መስቀል አስፈለገ? ኢየሱስ ክፋትን፣ ውድቀትን እና የዓለምን ኃጢአት ሁሉ የእኛውንም ኃጢአቶች ጨምሮ ተሸክሞበታል፤ እርሱም ይህንን ሁሉ ንጹሕ አድርጎታል፤ ያነጻውም በደሙ፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ምሕረት እና ፍቅር ነው፡፡ ዙርያችንን እንመልከት እስቲ፡- በክፋት የተነሳ በሰው ልጅ ላይ ምን ያህል ቁስሎች ተቀብረዋል! ጦርነት ጭኮና፣ ደሃውን የሚገድሉ የኢኮኖሚ ውጥረቶች፣ ትተነው ለምንሄደው ገንዘብ ያለን ስግብግብነት ወዘተ፡፡ ሕፃናት ልጆች እያለን አያታችን "ወጥ ሆኖ የተስፋ ልብስ ኪስ የለውም" ትለን ነበር፡፡ የሥልጣን ፍቅር፣ ሙስና ፣መከፋፈል፣ በሰው ሕይወት እና ባጠቃላይ በፍጥረት ላይ የሚፈጸመው ወንጀል! ሁላችንም እንደምናውቀው የግል ኃጢአቶቻችን፣ እግዚአብሔርን፣ ባልንጀራችንን እና መላውን ፍጥረት ለማፍቀር እና ለማክበር አለመቻላችንን ሁሉ ኢየሱስ በመስቀል ላይ መላውን ክፋትን ኃጢአት ተሸክሞ ተሰቅሏል፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል ይህንን ሁሉ አሸንፎ በትንሣኤው ድሉን አረጋገጠ፡፡ ዙፋኑ በሆነው መስቀል ላይ ለእኛ ያደረገልን መልካም ነገር እነሆ ይህ ነው፡፡ የክርስቶስ መስቀል ሲያቅፈን ወደ ደስታ እንጂ በፍጹም ወደ ኀዘን አያደርሰንም፤ ደስታችንም ስለ መዳናችን እና በሞት እርሱ እንደሰራው የሥራው ተካፋዮች የመሆን ጥሪ ነው፡፡

3. ዛሬ በዚህ ቦታ ተሰብስባችሁ ያላችሁ ወጣቶች ሆይ፤ ላለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት የሆሳዕና በዓል የዓለም ወጣቶች ቀን በዓል ሆኖ ሲከበር ቆይቷል! ሦስተኛው ቃል ይሄ ነው፡- ወጣት! የተወደዳችሁ ወጣቶች ሆይ ዘንባባችሁን ይዛችሁ ስትዘምሩ ኢየሱስን ከብባችሁ እንደምታከብሩት አድርጌ አያችኃለሁ፡፡ ስሙን ከፍ ባለ ድምፅ እንደምትጠሩት እና ከእርሱም ጋር በመሆናችሁ ያላችሁን ደስታ በዓል በማድረግ እንደምትገልፁ አማኞች አድጌ አስባችኋለሁ፡፡ እምነትን በማክበር ውስጥ እናንተ በጣም ወሳኝ ሥፍራ አላችሁ! የእምነትን ደስታ ታመጣላችሁ፤ በሰባ እና ሰማንያ ዓመት ዕድሜ ላይ ሆነን እንኳን እምነታችንን በወጣት ልብ እንድንኖረው ትጋብዙናላችሁ፡፡ የተወደዳችሁ ወጣቶች ሆይ ከክርስቶስ ጋር ስትሆኑ ልባችሁ አያረጅም! ደግሞም እናንተ ሁላችሁ እንደምታውቁት የምንከተለው እና አብሮን የሚጓዘው ንጉስ ከሌሎቹ የተለየ ነው፤ እርሱ እስከ መስቀል ድረስ የሚያፈቅር እና አኛም እንድናፈቅር እና ሌላውን እንድናገለግል የሚያስተምር ንጉሥ ነው፡፡ እናንተም በእርሱ መስቀል አላፈራችሁም! ይልቁንም ታቅፉታላችሁ ምክኒያቱም ከራሳችን ውስጥ በመነሳት እና ራሳችንን ለሌላው አሳልፈን በመስጠት እውነተኛ ደስታ እንደሚገኝ አውቃቹኋል፤ እግዚአብሔር ክፋትን ሁሉ በፍቅር አሸነፈ፡፡ የንግደትን መስቀል በየአህጉራቱ አደባባዮች ከፍ አድርጋችሁ ይዛችሁ ትዞራላችሁ፤ የምትሸከሙትም ለኢየሱስ ጥሪ መልስ ለመስጠት ነው"እንግዲህ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ የእኔ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው" (ማቴ 28፡19) ፡፡ በዚህ ዓመት የሚከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን የዓመቱ መሪ ቃል ይህ ነው፡፡ የምትሸከሙት መስቀል ሕዝቦችን እና ሃገራትን የከፋፈለውን የጥል ግድግዳ ኢየሱስ ስላፈረሰበት ነው፤ በመስቀሉ እርቅ እና ሰላም መጣልን፡፡ የተወደዳችሁ ወጣቶች ጓደኞቼ ሆይ እኔም ከዚች ዕለት አንስቼ በብፁዕ ዮሐንስ ጰውሎስ ዳግማዊ እና ቤነዲክቶስ 16ኛ እግር ተተክቼ ከእናንተ ጋር ጉዞዬን ጀምሬያለሁ፡፡ የዚህ መስቀል ቀጣዩ ታላቅ ንግደት በጣም ወደ እኛ ቀርቧል፡፡ በሚቀጥለው ሐምሌ በብራዚል አስደናቂ ከተማ ሪዮዲ ጄኔሮ የሚኖረንን የእምነት ሥብሰባ በደስታ እጠባበቃለሁ፡፡ በሚገባ ተዘጋጁ! ከሁሉ በላይ በመንፈሳዊ ህንጸት በርቱ፤ በሪዮ በሚኖረን የእምነት ስብሰባ ለመላው ዓለም የእምነት ምሥክር ይሆን ዘንድ ተዘጋጁ፡፤ ወጣቶች ሆይ ለዓለም ሁሉ ተናገሩ፡- ክርስቶስን መከተል መልካም ነው! ከክርስቶስ ጋር መጓዝ መልካም ነው! የክርስቶስ የምሥራች ቃል መልካም ነው! ከራሳችን ጀምረን ወደ ዓለም ሁሉ፣ ወደ ፍጥረት ሁሉ ክርስቶስን መውሰድ መልካም ነው! ስለዚህ ሦስት መሠረታዊ ነጥቦች አሉ፡- ደስታ፣ መስቀል፣ ወጣቶች፡፡

የድንግል ማርያምን አማላጅነት እንጠይቅ፡፡ ከክርስቶስ ጋር መገናኘት ያለውን ደስታ ታስተምረናለች፤ የመስቀሉን እግር የምንመለከትበት ፍቅር፣ በዚህ የተቀደሰ የሕማማት ሳምንት እና በሕይወታችን ሙሉ ኢየሱስን የምንመለከትበትን የወጣት ልብ ወኔ ታሳየናለች፡፡ አሜን እንዲሁ ይሁንልን!

ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ይባርካችሁ እና ይጠብቃችሁ፡፡

መልካም በዓል!

ትርጉም በወጣት ሳምሶን ደቦጭ - ቅ. ዮሴፍ ዘሲታውያን

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።