Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የሊ. ጳ. ብርሃነየሱስ የ፳፻፮ ዓ.ም. የጌታችን ልደት መልእክት

ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳትና የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት የ2006 ዓ.ም. የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት

Gena2006 1በስመ አብ ወወልድ መንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

 "የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከልን" (ገላ 4፡4)

 የተወደዳችሁ ምዕመናን፣ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች፣ ካህናትና ደናግል፣ በጎ ፍቃድ ያላችሁ ሰዎች፣ እንደዚሁም መላው የአገራችን ህዝቦች፣ 

ከሁሉ አስቀድሜ ለካቶሊካውያን ምዕመናን በአገር ውስጥና በውጭ ላላችሁ ሁሉና ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን

ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መንፈሣዊ ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ፡፡

 እግዚአብሔር አምላካችን ሁላችንም የእርሱ ልጆች ሆነን በክርስቶስ አንድ ቤተሰብ እንድንሆን እርሱ የፈቀደው ዘመን በደረሰ ጊዜ ልጁን ሲልክልን አዲስ ሕይወትና ፀጋ ሰጥቶናል፡፡ ምክንያቱም ሰዎችን ሁሉ ለማዳን መጥቶአልና እኛም የእርሱን መንፈስ ተቀብለን ይህንን የልደቱን ቀን ስናከብር እርስበርሳችን ወንድማማቾችና እህትማማቾች ነን፡፡ እርሱ ድኃ ሆኖ ተወለደ በድኅነትም ኖረ የናዝሬት ቤቱ የደኃ ሰው ቤት ነበር፡፡ በዚህም ትሕትናን ለዓለም ሁሉ በማስተማር ሰዎችን ወደርሱ ሰብስቦአል፡፡ ስለዚህ የእርሱን ሕይወት ከምናስበው በላይ ቢሆንም ሐዋሪያው ጳውሎስ እንደሚለው "ክርስቶስ የማይታየው አምላክ እውነተኛ አምሳል ነው" (ቆላ 1፣15-20)፡፡

 የተወደዳችሁ ምእመናን ሁላችንም በክርስትና ሕይወታችን በረከት እንዲበዛልን ወደ ክርስቶስ በመጠጋት ልናፈቅረውና ልንከተለው ያስፈልገናል፡፡ እርሱ የኛ ጌታ በመሆኑ በትህትና እንቀበለው እንስገድለትም፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን በክርስቶስ መንፈስና ሕይወት ውስጥ ሲኖር ሰላምና ክብር ይጎናጸፋል፡፡

ሰው በኃጢአት እግዚአብሔርን ቢበድለውም እርሱን ለማዳን የሰማይ አባታችን አንድ ልጁን በመላክ ከእርሱ ጋር ታርቀን ምህረትን እንድናገኝ አድርጎናል፡፡ ዛሬም እኛ ይህንን ምህረት ክብርና ምስጋና ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ላንተ ታላቅ አምላክ ይሁን ብለን በንፁህ ልቦና እርሱን እንቀበለው፡

እኛ ክርስቲያኖች ዘወትር የምንጓዘው እርሱ በዘረጋልን የክርስትና መንገድ ነው፡፡ ያንን የእርሱን መንገድ ደግሞ ሁልጊዜ መከተል አለብን፡፡ ይኸውም እርሱን የሚያሳዝኑትን ነገሮች የክፋትና የኃጢአት ሥራዎች ሁሉ አውልቀን በመጣል ሊሆን ይገባል፡፡ ከእርሱ የልደት በዓል የምናገኘው ነገር መንፈሳዊ ፀጋ ነው፡፡ መንፈሳዊ ፀጋን ያገኘ ክርስቲያን ደግሞ በጣም የታደለ  ነው፡፡ ይኸውም ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚያስገባው እርሱ ስለሆነ ነው፡፡

 በመሆኑም ሁላችንም በእርሱ ፀጋንና ደግነት ተሞልተን መልካም ሥራ በመስራት እርሱ የሚፈልገውን  በማድረግ እውነተኛ የእርሱ ልጆች መሆናችንን በማረጋገጥ ምን ያህል ታላቅ በረከት እንደሰጠን በማሰብ እግዚአብሔር አምላካችንን እናመስግነው፡፡

 ሁላችንም ይህንን ታላቅ በዓል ስናከብር በቤታችንና በአካባቢያችን የሚገኙትን በመርዳት መንፈስ እንዲሆን ላሳስባችሁ እወዳለሁ፡፡ ይህንንም ስል አቅመ ደካሞችንና አረጋውያንን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችንና ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን ሳንረሳ ማለቴ ነው፡፡  እውነተኛ እምነት የእግዚአብሔርን ፍቃድ መፈፀም ሲሆን ታላቅ ፈቃደኝነትም የሚገለፀው ይህን በዓል ለማክበር አቅም የሌላቸውን ስንረዳ ነው፡፡ ስለሆነም እንደ ሁልጊዜው ሁሉ የተለመደውን የበጎ አድራጎት ሥራ በመሥራት መልካም ነገርን በማከናወን ደስታችሁን ደስታቸው ታደርጉና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ትፈፅሙ ዘንድ በማክበር እጠይቃችኋለሁ፡፡ እርሱ በቃሉ እንደሚለን ለድኃና ለችግረኛ የሚያስብ ሰው እርሱ ምስጉን ነው፡፡

 እንደ ከዚህ ቀደሙ ህብረተሰቡ ራሱን ከኤች.አይ.ቪ ኤድስና እና መሰል ከሆኑ በሽታዎች እንዲጠብቅ በማሳሰብ ማኀበረሰቡም ህሙማንን ከማግለል ይልቅ በእግዚአብሔር ስም በመንከባከብና በመጠበቅ ተስፋ ይሆኗቸው ዘንድ በቤተክርስቲያንችን ስም አደራ እላለሁ፡፡

 "በድንገት ብዙ የሰማይ መላእክት ከመላኩ ጋር አብረው ታዩ፣ እግዚአብሔርንም በማመስገን፣

በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን

በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው

ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን" ይሉ ነበር  (ሉቃ፡2፡13-14)፡፡

ይህንን ሰላም ለእያንዳንዳችን፣ለቤተሰባችን፣ለሕዝባችን እንዲሁም ለምንወዳት አገራችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይሰጠን ዘንድ ሁልጊዜ እንጸልይ፡፡

 በአሁኑ ጊዜ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰበት ያለውን የመልካም አስተዳደር እንቅፋት የማስወገድና የማስተካከል ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሁሉም ፍትሃዊ አስተዳደርና አገልግሎት ያገኝ ዘንድ የቤተክርስቲያናችን እምነት ሲሆን ለዜጎች ደኅንነትም እየተሰጠ ያለውን ትኩረት በማድነቅ በትምህርት፣ በጤናና በመሠረታዊ የልማት አውታሮች ግንባታ ተጠናክረው በመቀጠል አንድ ታላቅ እመርታ ላይ እንደሚደርሱ እምነታችን ነው፡፡ የተያዙትም የልማት አውታሮች ሥራ እንቅስቃሴዎች የዓባይ ግድብን ጨምሮ በዚህ ዓመት ተጠናክረው በመቀጠል ለአገራችን የህልውና ዕድገት ግልጋሎት ላይ እንደሚውሉ የሁላችንም እምነት ነው፡፡

  

መልካም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ይሁንልን!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

+ ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

ከ http://www.ecs.org.et የተወሰደ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።