Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የብ. አቡነ ብርሃነየሱስ የትንሣኤ መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

ክቡራን ምዕመናን፡-

በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የምትገኙ ክቡራን የቤተክርስቲያን አገልጋዮችና በጎ ፍቃድ ያላችሁ ወገኖች ሁሉ፣


Abatachin2ከሁሉም አስቀድሜ የ2004 ዓ.ም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በራሴ ስም እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ፡፡ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ምህረትንና ሰላምን ለአደረግልን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡

''በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያት ሕያው የሆነውን ተስፋ የሰጠን በታላቅ ምህረቱ በአዲስ ልደት ልጆቹ ያደረገን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነ አምላክ ይመስገን'' (1 ጴጥ 1፡ 3-4)፡፡

በጌታ ትንሣኤ የሕይወት ዘላዓለማዊነት ተረጋግጦዋል፡፡ ስለሆነም ለኛ ለክርስቲያኖች ከኃጢያት ቀንበር ተላቀን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ስናመራ የእግዚአብሔር ልጅ ብርሃን ይወዳልና የብርሃን ልጆች እንድንሆን "በእግዚአብሔር እመኑ ይለናል" (ዮሐ.14፡1)፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከዘለዓለም ሞት ለማዳን የተዋረደውን ሞት ተቀብሎ ከፍ ባለ ዋጋ ተቤዥቶናል፡፡ በመሆኑም የክርስቶስ ትንሣኤ የእኛ ትንሣኤ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ እኛ ወደ ሰዎች የእግዚአብሔርን ፍቅር ይዞ የመጣውን ኢየሱስ እናከብራለን፡፡ በእዚህም የአምላካችንን ፍቅር ስናይ በሕይወቱ ተካፋይ እንድንሆን እርሱ በኛ መከራ ተከፋይ ሆኗል፡፡

"እንዲሁም ኢየሱስ ሕዝቡን በገዛ ራሱ ደም ለመቀደስ ከከተማው በር ውጪ መከራን ተቀበለ ፡፡ እኛም ከሰፈር ወጥተን ወደ እርሱ እንሂድ፤ የውርደቱም ተካፋዮች እንሁን፡፡'' (ዕብ 13፡ 12-13)

የሞተው ኢየሱስ ጌታ ሆኖ በክብር እንደተነሣ ለደቀመዛሙርቱ የተነገራቸው ቃል "ሰላም ለእናንተ ይሁን'' (ሉቃ 24፡36) የሚል ነው፡፡ እኛም ይህን ሰላም ሁልጊዜ አጥብቀን ልንይዘውና ልንጠብቀው ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም በክርስቶስ ትንሣኤ ጥላቻ ሁሉ ከኛ ከሰዎች መወገድ ይኖርበታል፡፡ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተገኘውንም የክርስቶስን ሰላም እንያዝ፣ ኢየሱስ የሰላም ንጉሥ ነውና፡፡

ሐዋርያው ጰውሎስ ወደ ቆላስይስ በጻፈው መልእክት ላይ "እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ያለበትን በላይ ያለውን አስቡ'' (3፡1) ይለናል፡፡ እኛም ኢየሱስን ከመውደድ የበለጠ ነገር ሊኖረን አይገባም፡፡ በእምነታችን እርሱን አክብረን ማስከበር ይኖርብናል፡፡ እሱ ስለ ሁሉም ሞቶ ተነስቶአልና፣ እኛም በእርሱ ሕይወትን አግኝተናል፡፡

ለእኛም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መኖር ታላቅ ደስታ ነው፡፡ ከእርሱም ጋር መጓዝ ከፍያለ መጽናናት ነው፡፡ ሃይማኖታችን እውነት በሆነው፣ ሞትን በተጋፈጠው፣ በተቋቋመውና ድልም በነሣው በክርስቶስ ላይ ነው፡፡ በዚህም ቤተክርስቲያናችን የክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ደስታና መንፈሳዊነት ታከብራለች፡፡ በእምነትና በተስፋ ዓይንም የትንሣኤውን ብርሃን ታያለችና የሞትን ድል መመታት እያስታወሰች ጌታን ስታከብር፣ ምዕመናንም በጌታ ያገኙትን ክብር ተገንዝበው ልባቸውን ደስ አሰኝተው በዓሉን በጋራ ማክበር እንዲችሉ አደራ እላለሁ፡፡

የጌታችን ትንሣኤ የአንድ ቀን በዓል ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ በሕይወታችን ውስጥ በማድረግ ዘወትር በኑሮአችን መግለጽ ይኖርብናል፡፡ ምን አልባት እስካሁን የአምላካችንን ትክክለኛ መንገድ አላያዝንም ይሆናል፤ እናም ይህን ታላቅ በዓል ስናከብር በሥጋ ብቻ ሳይሆን በታላቅ የሃይማኖት መንፈስ እንድናከብረውና ሃይማኖታችንን አጠንክረን እንድንይዝ አሳስባለሁ፡፡

የተወደዳችሁ ወገኖች ሆይ!

በአሁኑ ጊዜ ከህጋዊ መንገድ ውጭ በሚደረጉ የውጭ አገር ጉዞ በከንቱ በሚጠፋውና እየጠፋ ባለው የዜጎቻችን ሕይወት ቤተክርስቲያናችን ከፍተኛ ሐዘን ይሰማታል፡፡ ለዚህም ጉዳይ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በአሁኑ ጊዜ ህብረተሰቡን በማስተማርና ዜጎችን ከጥፋት የመታደግ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ይህንንም ጥረት ቤተክርስቲያን እያመሰገነች ዜጎችም በአገራችው ያሉትን የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን ሳይንቁ በመሥራት ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲያሳድጉ በራሴና በቤተክርስቲያናችን ስም ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ በዓል ስናከብር ሞት ሐዘን ያደረሰባቸውን ወገኖች በማሰብ በትንሣኤው ለምናምን ሁሉ ሞት የሰው መደምደሚያ ወይም ፍጻሜ ሳይሆን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት መሸጋገሪያ መሆኑን ተገንዝበውና አምነው እንዲጽናኑ እንርዳቸው፡፡ "ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት የኖራል" (ዮሐ. 11፡25)፡፡

በመስቀሉ ሰላምን የሰጠን፣ በትንሳኤው እርቅን ያወርደልን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም ንጉሥ ነውና ሰላሙን ለቤተሰቦቻችን፤ ለማህበሮቻችን፤ ለአገራችን፣ ለጐረቤቶቻችንና እንዲሁም ለዓለም ሁሉ ይሰጠን ዘንድ እንጸልይ፡፡

በመጨረሻም ለመላው ክርስቲያኖች፣ በህመም ምክንያት በቤታችውና በሆስፒታል ለሚገኙ፣ በማረሚያ ቤት ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች፣ የአገር ድንበር ለማስከበር በአገር ጠረፍ በዳር ድንበር ለተሰማሩ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ በተለያዩ ሥራዎች ከቤተሰብ ርቀው ለተሰማሩትና ከአገር ውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በዓል አደረሳችሁ፡፡ በዓሉ የደስታ፣ የፍቅርና የሰላም ይሁንልን፡፡

+ ብፁዕ አቡነ ብረሃነየሱስ ሱራፌል

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

ምንጭ፡ ቫቲካን ራድዮ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።