እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ጎሕ ሳይቀድ፤ ገና ጨለማ ሳለ ኢየሱስን ፍለጋ!

ጎሕ ሳይቀድ ኢየሱስን ፍለጋ!

Fasika 2010ecከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች።” /ዮሐ 20:1/።

የሰው ልጅ ሕይወት በመፈለግ የተሞላች ናት። ብዙ ዓይነት ፍላጎቶች እንዳሉን እናውቃለን፤ ፍጥረታችን በራሱ ብዙ ነገር የተዋቀረበትና የተቀነባበረበት ነውና ማንነታችንን በተለያየ መልክ የሚጎነትሉ፣ ወዲህ ወዲያ ሁን የሚሉ ፍላጎቶች አሉን፤ ሁሉንም ፍላጎት በአንድ ጊዜ መከተል ስለማንችልም ፍላጎታችንን ቅደም ተከተል ማስያዝ ግድ ይለናል። አንዳንድ ፍላጎታችን ባልሆነ ጊዜ አይለው ሊሰሙን ይችላሉ እናም አሁን ጊዜው አይደለም በምንልበት ሰዓት ሲሆን ደግሞ ይቅርብኝ ብለን እናስባለን፤ ከራሳችንና ከሁኔታዎች ጋር ቀጠሮ ይዘን እናስረዝመዋለን። ግን በሁሉ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ሁሉ የሚያስፈልገንና መፈለግም የሚቻል የፍላጎት ዓይነት ይኖር ይሆን ብለን መጠየቅም ይኖርብናል።

ማርያም መግደላዊት ኢየሱስ ሞቷል፣ ተቀብሯል ከተባለ በኋላ በሦስተኛው ቀን ያን ጊዜ እርሱ በሕይወት ሳለ ስለኢየሱስ ከሰማችበትና የልብሱን ዘርፍ እንኳ ብነካው ለዘመናት ካሰቃየኝ፣ ከሰው ተራ ውጪ ካደረገኝና በመኖርና በመሞት መካከል ከመደበኝ በሽታዬ ሊያድነኝ ይችላል ብላ አስባና ወስና በብዙ ሰዎች መካከል ተከብቦና ብዙ መገፋፋት በነበረበት አጀብ መካከል በምድር ተንፋቃና ተስባ የክርስቶስን ልብስ ከነካችባት ቅፅበት አንሥቶ እስከ ሞቱ ኢየሱስን መከተል፣ እርሱ ባለበት መሆንና ዞር ሲልባትም መፈለገ ሕይወቷ ነበር። ስለዚህም ኢየሱስ በግፍ ሞቶ፣ ተቀብሮ፣ ትልቅ ድንጋይ ተንከባሎ መቃብሩ ላይ ተደፍኖ እንኳ መፈለጓን አላቋረጠችም። ምክንያቱም መፈለጓ የበረታ ሲሆን ኢየሱስን እንደማታጣው ከፈውስ ታሪኳ ታውቃለችና ነው!

ሕይወት ወይም ኑሮ በእምነታችን፣ በተስፋችን፣ በደስታችን፣ በፍቅራችን... ላይ ድንጋይ አንከባሎ ሊደፍንብን ሲሞክር ቶሎ ብለን እጅ የመስጠትና እምነት እንደሌላቸው፣ ለዛሬ ብቻ እንጂ ቋሚ ተስፋ እንዳልተሰጣቸው፣ ደስተኛ መሆን ፍጹም እንዳልታደሉና በልዩ ፍቅር እንዳልተፈቀሩ እንደው ዝም ብሎ ቀን እየቆጠሩ ለመኖር እንደተፈጠሩ እያሰብን ለመኖር እንፈተን ይሆናል። መሆን ያለበት እውነታ ግን በምንም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን መፈለጋችንን ያለማቋረጥ መሆኑን ማርያም መግደላዊት ታስተምረናለች።

እሷ በብርሃንም ያይደለ “ገና ጨለማ ሳለ” ኢየሱስን ፍለጋ ወጣች። ጨለማ ለሥጋዊው ዓይናችን የማየት ብቃታችንን የሚያዳክም ተፈጥሯዊ ሁኔታ ነው፤ በሕይወታችንም የእምነት ሕይወታችንን የሚጋርዱን፣ የክርስትና ዓይናችንን የሚያዳክሙና በነገሮች ሁሉ ክርስቶስን እንዳናይ የሚፈትኑን ነገሮች ሊከሠቱ ይችላሉ፤ ሆኖም ግን በነዚህ ሆኔታዎች ውስጥም ብንሆን ሌላ ምርጫ መውሰድ የለብንም - ገና ጨለማ ሳለም ቢሆን ኢየሱስን መፈለግ!

የተነሣውን ክርስቶስ በሕይወታችን ማየት የምንችለው በአናኗራችን እርሱን መፈለግ ምርጫችን ስናደርግ ነው፤ እርሱን ሊጋርዱን፣ ክርስቶስን ሳይሆን ሌሎች ነገሮችን ብቻ እንድንሻ የሚያደርጉን ነገሮች ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን በሁሉም ሁኔታዎችና ጊዜ እርሱን ከፈለግን እርሱን ማግኘት እንችላለን፤ እርሱ ለሚፈልጉት ሁሌም የሚገኝ አምላክ ነው።

በአናኗራችን ልኬት መጠን የሆነ ክርስቶስን ከመፈለግ ይልቅ ክርስቶስን በራሱ ማንነት መፈለግ እንዳለብን መግደላዊት ማርያም ታስተምረናለች፤ ሥጋዊ ፈውስን መፈለግ ጥሩ ነው ነገር ግን ክርስቶስ እኛ በፈለግነው ፈውስ መጠን አይለካም፤ እርሱ እኛን ደስ ያሰኙናል ከምንላቸው ነገሮች በላይ የገዘፈ ጌታ ነው! እርሱ ከእኛ ነገሮችና ጊዜያዊ ፍላጎቶች በላይ ወደርሱ የሚስበን አምላክ ነው፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ እርሱ ሥጋውን ከሥጋችን ጋር ሊያዋህድ የሚጠራ፣ ለዘለዓለማዊ የሚበጀንን የሚነግረንና የሚያደርግ አምላክ ነው ስለዚህም እንዲህ አለን፡- “ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።” /ዮሐ 6:51/።

ስለዚህም ማርያም መግደላዊት በተደረገላት ሥጋዊ ፈውስ ብቻ ወይም እቅዷን ከእርሱ በማግኘት ብቻ ሳትገደብ የክርስቶስን ሥጋ ፍለጋ በጨለማ ገሰገሰች! እኛም ለሕይወታችን ምልአት ከእርሱ ሥጋና ደም ጋር መተሳሰርን በማስበለጥ ከጊዜያዊ ነገሮች ባሻገር እርሱን መራብና መጠማትን መምረጥ ይበጀናል። ቅዱስ ቁርባን ለእኛ ይህንን እውነት ያጎላልናል፤ በምንም በማንም የማይተካ የክርስቶስ መገኘት በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ አለን! ይህ ምስጢር ከውስጥ ሊነካን ይገባል፤ ሌሎች ነገሮችን ከመፈለግ ይልቅ ይህንን መፈለጋችን መበርታት አለበት፤ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ አግኝተን ለዘለዓለም ሕይወት ክርስቶስ የሚሰጠንን እንጀራ ሥጋውን ብናጣ ምን ይበጀናል! ሌሎች ነገሮች ባይታዩንም እንኳ፣ “ጎሕ ሳይቀድ፣ ገና ጨለማ ሳለ” ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም እንሂድ!

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት