Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የናዝሬቱ ኢየሱስ ላንተ ማነው?

Independent Catholic News - ኢየሱስ መንገድን ሊያሳየን ያውም ወደ ሕይወት የሚያደርሰን መንገድን እንጂ ፍልስፍና ሊያስተምረን አልመጣም፤ ይህ መንገድ የእውነተኛ እምነት መገለጫ የሆነው ፍቅር ነው" በማለት ነበር ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው ከካስተልጋንዶልፎ ባለፈው እሑድ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አስተምህሯቸው መጀመሪያ ላይ የዕለቱን ወንጌል መልእክት ማካፈል የጀመሩት።

በመቀጠልም "የእግዚአብሔር ቃል ሁለት ወሳኝ ጥያቄዎችን ያቀርብልናል፦ የናዝሬቱ ኢየሱስ ላንተ ማነው? የሚልና እምነትህ ተግባራዊ ሆኗል ወይስ አልሆነም? የሚለው ናቸው።" ካሉ በኋላ ር.ሊ.ጳ.

ለተሰበሰቡት ምእመናን "ለመጀመሪያው ጥያቄ ጴጥሮስ አንተ መሲሕ ነህ፤ ማለትም ሕዝቡን ለማዳን ከእግዚአብሔር የተቀባና የተላከ ማለት ነው። ለጴጥሮስና ለተቀሩት ደቀመዛሙርት ከብዙኀኑ ሕዝብ በተለየ ሁኔታ ኢየሱስ አንድ ታላቅ መምህር ወይም ነቢይ ብቻ ሳይሆን ከዚህም በላይ ነው። እነሱ እግዚአብሔር በርሱ እንዳለና እንደሚሠራ እምነት አላቸው፤ ሆኖም ግን ኢየሱስ መሰቃየትና መሞት እንዳለበት በነገራቸው ጊዜ ራሱ ጴጥሮስ ይህን የስቃይና የሞት ጉዳይ ተቃወመ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ማመኑ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ነገር ግን በፍቅር ገፋፊነት እሱ በተጓዘበት ተመሳሳይ መንገድ ማለትም የመስቀል ጎዳና መጓዝ እንዳለበት ለማስረዳት ጴጥሮስ ገሰጸው። ኢየሱስ ፍልስፍናን ሊያስተምረን ሳይሆን መንገድን ያም ወደ ሕይወት የሚያደርሰውን መንገድ ሊያሳየን ነው የመጣው፤ ይህ መንገድ የእውነተኛ እምነት መገለጫ የሆነው ፍቅር ነው" ብለዋል።

ከሰንበት ንባባት ሁለተኛ ከሆነው ውስጥ "ከመልካም ሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው" የሚለውን የቅዱስ ያዕቆብን ትምህርት በመጥቀስ (ያዕ.2:17) "ሰው ባልንጀራውን በንጹሕና ለጋስ ልብ ካፈቀረ በእውነት እግዚአብሔርን አውቋል ማለት ነው። በአንጻሩ ሰው እምነት አለኝ ግን ወንድሜን አላፈቅርም ካለ እውነተኛ አማኝ አይደለም፤ እግዚአብሔር በርሱ አይኖርም" በማለት "አንድ ሰው በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ትክክለኛ እምነት ሊኖረው ይችላል፤ ነገር ግን በትክክለኛ አናኗር ካልተማላለሰ እምነቱ ብቻ ለደኅንነቱ ምንም አይጠቅመውም። ስለዚህ በወንጌል ውስጥ "የዘላለም ሕይወትም ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው።" (ዮሐ.17:3) የሚለውን ስታነቡ ከጠራ ሕይወትና አናኗር ጋር እንጂ ይህ አባባል ብቻ ለመዳናችን በቂ ነው ብላችሁ አታስቡ" የሚለውን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዚህ መልእክት ላይ ያተተውን ወስደው አብራርተዋል።

በመጨረሻም በዚህ ሳምንት ውስጥ የሚከበሩትን ክብረ መስቀልንና የኀዘንተኛዪቱ እመቤታችንን በዓሎች በማስታወስ በእግዚአብሔር ቃል ማመን...የትሕትና አገልጎሎት ሕይወትን ለስቃይ ዝግጁ በመሆን ለወንጌል ፍቅርና እውነት በታማኝነት የእምነታችን ምስክሮች ስንሆን ተግባሮቻችን ሁሉ ከንቱ እንደማይሆኑ እርግጠኞች መሆንንን ከእመቤታችን ማርያም እንድንማር በመጋበዝ ደምድመዋል።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።