Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለማኝ ነው - ለድሆች ያለንን አመለካከት እንቀይር!

የ፳፻፮ ዓ.ም. የር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ መልእክተ ሆሣእና ለወጣቶች

የተወደዳችሁ ወጣቶች ሆይ!

papa-francesco2014በዚህ ዓመት ከማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 5፡1-12 ላይ ስለ ብፅዕና የሚዳስሰውን የክርስቶስ የተራራ ላይ ስብከት እናስተነትናለን፡፡ ይህ ስብከት ውብ በሆነው በገሊላ ባሕር አጠገብ በሚገኘው ተራራ ላይ የተደረገ ዘለዓለማዊ ደስታን የሚሰጥ ስብከት ነው፡፡ ከዚህ ማራኪ እና ልብ የሚነካ የክርስቶስ አስተምሕሮ መካከል ዛሬ የመጀመርያ ላይ እንድናስተነትን እጋብዛችኋለሁ፡፡

“በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው…”

በርካታ ሰዎች በኢኮኖሚ ቀውስ እየተናጡ ባሉበት በዚህ ጊዜ ድህነትን ከብፅዕና ጋር እና ከደስተኞች ጋር ማያያዝ እንዴት ይቻላል? ድህነትን እንደ ቡራኬ ልንቆጥረው እንችላለንን? በመጀመርያ “በመንፈስ ደኃ” መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋ ለብሶ ለሰው በሆነ ጊዜ የድህነትን መንገድ በመምረጡ ራሱን ባዶ አደረገ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለፊሊጵስዮስ ሰዎች እንደነገራቸው “በዚህ ዓይነት ኢየሱስ ክስቶስ ያሳየው የትሕትና ጠባይ በእናንተም ሕይወት ሊኖር ይገባል፡፡ እርሱ የመለኮት ባሕርይ አለው፤ ይሁን እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የሚያደርገውን የመለኮት ባሕርይ እንደያዘ መቅረት አልፈለገም፡፡ ይልቁንም ያለውን ክብር በገዛ ፈቃዱ ትቶ አገልጋይ መሆንን መረጠ፤ በሰው ምሣሌም ተገለጠ፡፡” (ፊል 2፡5-7) እዚህ ላይ የአምላክን ደኃ የመሆን ምርጫ እናያለን፤እርሱ ሁሉ ነገር ያለው ባለጠጋ ሆኖ ሳለ በእርሱ ድህነት ውስጥ እኛን ለማበልጸግ(2ቆሮ 8፡9) ራሱን ደኃ አደረገ፡፡ የሰው ልጅ በበረት ውስጥ ተኝቶ ስንመለከተው፣ በኋላም በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ስናየው ራሱን ባዶ የማድረጉን ፍፃሜ ተንተርሰን ድህነቱን እናሰላስላለን፡፡ በግሪክ ቋንቋ ተጽፎ የሚገኘው Ptocho’s (ደኃ) የሚለው ቃል ትርጓሜ ቁሳዊ ድህነትን የሚያመላክት ሳይሆን ለማኝ የሚል አንድምታ ያዘለ ነው፡፡ ይህም ከሌሎች ዝቅ ማለትን፣ የአንድን ሰው የተገደበ ማንነት እና አብሮ ሕያው የሆነ ድህነትን ያመለክታል፡፡ በአይሁዳውያን ዘንድ anawim የሚለው ቃል የእግዚአብሔር ደኃ የሚል አንድምታ ያለው ሲሆን አይሁዳውያን እነዚህን ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ የተደገፉ እና እርሱም የሚያሳፍራቸው እንደሆኑም ያምኑ ነበር፡፡ ቅድስት ተሬዛ ዘኢየሱስ ህፃን (St. Therese of the child Jesus) በግልፅ እንደተመለከተችው ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ እንደ እኛ በመሆኑ ፍቅራችንን የሚጠይቅ ምስኪን ለማኝ ሆኗል ትላለች፡፡ {jathumbnail off}

የካቶሊክ ቤተክርስትያን ትምህርተ ክርስትያን በቁጥር 2559 ላይ “ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለማኝ ነው” ይላል፡፡ እንዲሁም በቁጥር 2560 ላይ “ጸሎት የእግዚአብሔር ጥማት እና የእኛ የራሳችን ጥማት የሚገናኙበት ነው” በማለት ይገልፃል፡፡ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከብፅዕና አስተምህሮዎች መካከል በመንፈስ ድኃ ስለመሆን የሚናገረውን ክፍል በፍጹም ምልዓት ተረድቶታል፡፡ እግዚአብሔር በለምፃሙ ሰው በኩል እና በመስቀሉ በኩል ባነጋገረው ጊዜ ቅዱስ ፍራንቸስኮስ የእግዚአብሔርን ታላቅነት እና የእርሱን ኢምንትነት ተረዳ፡፡ በጸሎቱም ለረዥም ሰዓታት “ጌታ ሆይ አንተ ማነህ?” እያለ ይጠይቀዋል፡፡ ደግሞም “እኔስ ማን ነኝ?” እያለ የራሱን ክብር በመተው እመቤት ድህነትን አግብቶ የወንጌልን እሴት በሕይወቱ ተርጉሞ ለመኖር ታላቅ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ ቅዱስ ፍንቸስኮስ በድህነት እና ለድሆች ባለው ፍቅር የክርስቶስን ምሳሌ በተግባር ኖሯል፡፡ ለቅዱስ ፍራንቼስኮስ ድህነትና ለድሆች ከልብ የመነጨ ፍቅር መስጠት በፍጹም ሊነጣጠሉ የማይችሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡

ምናልባት በመንፈስ ድኃ መሆንን የሕይወታችን መንገድ ለማድረግ ምን ብናደርግ ይሻላል? ብላችሁ ትጠይቁኝ ይሆናል፤ እኔም ሦስት ነገሮችን በማለት እመልሳለሁ፡፡ ከሁሉ በማስቀደም ቁሳዊ ነገሮች ላይ አትጣበቁ፡፡ ጌታ በወንጌል የሕይወት መንገድ እንድንኖር ሲጠራን መጠንን በማወቅ የስግብግብነት ጉዞን እንድንቃወም ይጋብዘናል፡፡ ይህም ማለት መሠረታዊ እና አስፈላጊ የሆነውን ነገር በልኩ በመጠቀም አላስፈላጊ እና ተጨማሪ የሆነውን ነገር እና ወደ እርሱ የሚያሰጥመንን ነገር መቃወም ማለት ነው፡፡ ሁሉን ነገር በአልጠግብ ባይነት ከመሰብሰብ እና ከአጉል አባካኝነት ባህል ራሳችንን እንጠብቅ፡፡ ገንዘብ ጣዖት ሆኖ በእኛ ላይ እንዳይነግስ እንጠንቀቅ፡፡ ኢየሱስን እናስቀድም፡፡ ባርያ አድርጎ ከሚገዛን የጣዖት አምልኮ ያድነናል፡፡ ውድ ወጣቶች ሆይ! በእግዚአብሔር ታመኑ፣ እርሱ በስማችሁ ያውቃችኋል፣ ከቶ አይረሳችሁም፡፡ በሜዳ ላይ የሚበቅሉት አበቦችን እንደሚመግብ(ማቴ 6፡28) ለእኛም የሚያስፈልገንን አያሳጣንም፡፡ በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ሳለን አካሔዶችንን እንለውጥ፣ አባካኝ ከመሆን እንቆጠብ፡፡ ደስተኞች ለመሆን እንደምንጣጣረው ሁሉ ቀላል ሕይወት ለመኖር እንጣር፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ብፁዓን ሆነን መኖር ከፈለግን ለድሆች ያለንን አመለካከት እንቀይር፡፡ ለእርሱ በመጠንቀቅ ለቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎታቸው ጊዜ እንስጥ፡፡ ወጣቶች ሆይ በተለይ ለእናንተ በሕዝቦች መካከል ትልቅ የወንድማማችነትን መንፈስ እንድታድሱ ዐደራ እጥልባችኋለሁ፡፡ በድህነት፣ በሥራ አጥነት፣ ስደት እና በተለያዩ ሱሶች መጠመድ እና ግዴለሽንትን ሁሉ ከእኛ ወዲያ ለማራቅ ንቁ መሆን አለብን፡፡ ፍቅር ያጡትን፣ ተስፋ የጨለመባቸውን፣ በተሸናፊነት ስሜት ከሕይወት ጎዳና ውጪ የወደቁትን፣ ያዘኑትን፣ በፍርሃት የተከበቡትን በመመልከት ከድሆች ጎን መቆምን መማር አለብን፡፡ ፊት ለፊት ዐይናቸውን ልንመለከት እና ልናዳምጣቸው ይገባል፡፡ ድሆች በቀጥታ ራሱን ክርስቶስን እንድናገኛቸው እና የሚያሰቃየውን ቁስሉን እንድንዳስስ ዕድሉን ይሰጡናል፡፡

ከዚህ ሁሉ በኋላ ሦስተኛው ነጥቤ እነሆ፡፡ ድሆች ያለንን የምንወረውርላቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ የምንቀበለው እና የምንማረው ብዙ ነገር አለ፡፡ ከድሆች ጥበብ ምን ያህል እንማር ይሆን! አስቡበት፤ ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ቅዱስ ቤኔዲክት ጆሴፍ ላብሬ በሮም ጎዳናዎች ላይ በሚመጸወተው ምፅዋት ብቻ እየኖረ የብዙኃን መንፈሳዊ አባት እና አስተማሪ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በዚህ ተመሳሳይ ተግባር ድሆች እውነተኛ መምህራኖቻችን ናቸው፡፡ የሰው ልጆች ሰብዓዊ ማንነት እና ክብር ባላቸው ጥሪት እና በባንክ ባካማቹት ኃብት እንደማይመዘን ይነግሩናል፡፡ ድሆች ትህትናን እና በእግዚአብሔር መታመንን ያስተምሩናል፡፡ በፈሪሳዊው እና በቀራጩ ምሳሌ (ሉቃስ 18፡9-14) ጌታ ቀራጩ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን በማመኑ እና በትህትናው የከበረ ሰው መሆኑን ያሳየናል፡፡ የነበሯትን የመጨረሻ ሁለት ሳንቲሞች ለቤተ መቅደስ የሰጠችው መበለት ያላቸው ሁሉ ሰጥተው ለነገ የሚሉት የሌላቸው ነገር ግን ከመስጠት የማይቆጠቡ ሁሉ ምሳሌ ነች (ሉቃ 21፡1-4)፡፡

መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና

የወንጌል ማዕከላዊ መልዕክት የእግዚአብሔር መንግሥት ነው፡፡ ኢየሱስ የዚህ መልእክት ተግባራዊ ምልክት ነው፡፡ እርሱም አማኑኤል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፡፡ መንግሥቱ ሥጦታ እና ቃልኪዳን ነው፡፡ በኢየሱስ በኩል ይህ መንግሥት ተሰጥቶናል ነገር ግን ገና በምልዓት አልወረስንም፡፡ “መንግስትህ ትምጣ” እያልን ወደ እግዚአብሔር በየዕለቱ የምንፀልየው ለዚሁ ነው፡፡ በድህነት እና በስብከተ ወንጌል መካከል ትልቅ ትሥሥር አለ፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልጋት ደሃይቱን ቤተክርስትያን ነው፡፡ ደሃ ቤተክርስትያን የድሆች ሰባኪ የሆነች የክርስቶስ ቤተክርስትያን፡፡ ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል ሥራ በላካቸው ጊዜ “ወርቅ ወይም ብ ር ወይም ናስ በኪሳችሁ አትያዙ፡፡ ከረጢትም፤ ትርፍ እጀ ጠባብም ትርፍ ጫማም በትርም ለመንገዳችሁ አትያዙ፤ምክንያቱም ለሠራተኛ የሚያስፈልግ ምግብ ይሰጠዋል፡፡” (ማቴ10፡9-10)

በሕይወቴ እውነተኛ ደስታን ያየሁት ምንም የሚይዙት ነገር በሌላቸው በድሆች ላይ ነው፡፡ ስለዚህ በመንፈስ ድሆች መሆናችን ከእግዚአብሔር ጋር፣ ከቁሳዊ ነገሮች ጋር እና ከድሆች ጋር ያለን ግንኙነት መልክ እንደሚሰጠው አይተናል፡፡ የብፅዕናን ሕይወት በተመለከተ ቅዱሳን ያግዙናል፡፡ ከፋሲካ ሁለተኛ ሰንበት የሚታወጀው የር.ሊ.ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቅድስና ታላቅ የደስታ አጋጣሚ ይሆንልናል፡፡ እርሳቸው የወጣቶች ትጉህ ጠባቂ ናቸው፡፡ ከቅዱሳን ሱታፌ ጋር እርሳቸው የእናንተ ወዳጅ እና አባት ሆነው ይቀጥላሉ፡፡

ይህ የሚያዝያ ወር የሚሊኒየሙ አዳኝ መስቀል ለወጣቶች የተሰጠበት ሰላሳኛ ዓመት ዝክር የሚከበርበት ነው ይህ የር.ሊ.ጳ. የሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ተግባር በአምስቱ ክፍለ ዓለማት በወጣቶች በዓል ላይ እየዞረ የሚባርከን ዑደት ሆኗል፡፡ 

በ1984 ዓ.ም. በትንሳኤ በዓል ዕለት እርሳችሁ የተናገሩት አይረሴ ንግግር እነሆ፡- “የተወደዳችሁ ወጣቶች ሆይ! በዚህ የተቀደሰ ዓመት መዝጊያ ላይ የሚሊኒየሙን ምልክት ለእናንተ አደራ እሰጣለሁ፤ ይህም የክርስቶስ መስቀል ነው! በዓለም ሁሉ እርሱን በመሸከም ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር መሥክሩ፤ መዳንም በሞተው እና ከሞት በተነሳው በክርስቶስ ብቻ የሚገኝ መሆኑን ተናገሩ፡፡”

በርግጥም ብዙ ፈተናዎች፤ ብዙ መስቀሎች አሉባችሁ፡፡ ድህነት፣ጭንቀት፣ መገለል፣ ለዕለት እንጀራ መታገል፣ በሽታ፣ ጦርነት፣ የፍትህ እጦት፣ ስለ ቅድስና ጥሪያችን ጽናት ያለብን ፍጥጫ፣ በየዕለቱ ለመለወጥ የምናደርገው ትግል ወዘተ… ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን በሩን ከፍተን ወደ ውስጥ ካስገባነው እና ከእኛ ጋር እንዲኖር ካደረግነው፣ ደስታችን እና ኃዘናችንን ከእሱ ጋር ከተካፈልን፤ ፍጹም ማብቂያ የሌለው ፍቅር የሆነው አምላክ የሚሰጠውን ሰላም እንወርሳለን፡፡ በዚህ ዓለም ፍርድ ኢየሱስ ስለ ብፅዕና ያስተማረውን የሚከተሉ ሁሉ ጅሎች እና ተሸናፊዎች ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡ ነገር ግን እኛ ቅዱስ ጴጥሮስን ተከትለን እንዲህ ማለት ይገባናል “ጌታ ሆይ! ወደ ማን እንሔዳለን? አንተ የዘለዓለም ሕይወት ቃል አለህ” (ዮሐ 6፡68) ፡፡ ስለዚህ ለኢየሱስ ጥሪ መልሳችን እሺ ከሆነ ሕይወታችን ፍሬያማ እና ትርጉም ያለው ይሆናል፡፡  

የተወደዳችሁ ወጣቶች! የማርያም የምሥጋና መዝሙር በመንፈስ ደኃ ሆኖ የብፅዕና ሕይወት ለመኖር የሚፈልግ ሁሉ ሰው መዝሙር ነው፡፡ የወንጌል ውስጥ ነው፡፡ ይህ ልብ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ብለው የሚጠሯትን (ሉቃ 1፡48) የማርያም ልብ ይመስላል፡፡ የድሆች እናት እና የአዲሱ ስብከተ ወንጌል ኮከብ የሆነችው እመቤታችን የብፅዕና ደረጃዎችን እንድንለማመድ እና ዘወትር በወንጌል ደስተኞች ለመሆን እንድንችል ታብቃን!

ለበዓለ ሆሣእና 2006 ዓ.ም. - ከቫቲካን መንበረ- ጴጥሮስ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።