እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ቅድስት ሪታ ዘካሺያ

ቅድስት ሪታ ዘካሺያ

St Ritaችግረኞችንና የተጠበቡትን በመርዳት የታወቀችው ቅድስት ሪታ እ.ኤ.አ. በ1367 ዓ.ም. ሮካ ፓሬና /ካሺያ/ ውስጥ ተወለደች። አባቷ እንጦንዮስ ሎትዮስ እናቷም አማታ ፌሪ የሚባሉ ጥሩ ክርስቲያኖች ነበሩ። የክርስትና ስሟም ማርጌሪት ነው።

ወላጆቿ በፈሪኀ እግዚአብሔር ስላሳደጓት፤ መልካም ጠባይና ሥነ ሥርዓት ያደረባት ነበረች። ጸሎት ማዘውተርን ትወድ፣ ችግረኞችንም ለመርዳትና ለማጽናናት ትተጋ ነበር። ከሁሉም በላይ የሆነውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክቡርና ቅዱስ ስም ስትሰማም የተለየ ልባዊ ደስታ ይሰማት ነበር።

ከፍተኛ የቤተሰብ ፍቅር ያደረባት ታዛዥዋ ሪታ ዕድሜዋ ለጋብቻ ሲደርስ በወላጆችዋ ፈቃደ ተዳረች። ይሁን እንጂ ፈርናንድ የተባለው ባለቤቷ በነበረው መጥፎ ጠባይና አጉል የመጠጥ ሱስ ብዙ ያሠቃያት ነበር። ቁጡ ስለነበረም ይደበድባት ነበር። እርስዋ ግን ያን ሁሉ በደል በትዕግሥት ትሸከመውና ባሏ መልካም ጠባይ እንዲኖረው በለሰለሰ አንደበት ትመክረውና ስለርሱም ትጸልይ፤ ብዙውን ጊዜም የቁጣውን እሳት በመልካም አንደበት ታበርደውም ትጸልይለትም ነበር። የሚደርስባትን ሥቃይና መከራ ከክርስቶስ ሥቃይና መከራ ጋር በማዋሃድ ለጌታ መስዋዕት እንዲሆን ታቀርብለት ነበር። ጸሎት ተአምር ያደርጋል እንደሚባለው ከጊዜ በኋላ ባሏ ወደ መልካም መንገድ ተመለሰ፤ ባለቤቷም ሪታም ጌታን አመሰገነች፤ በሰላም መኖር ጀመሩ ሁለት ወንዶች ልጆችም ወለዱ። በተለይ ቅድስት ሪታ ልጆችዋ በፈሪኀ እግዚአብሔር እንዲያድጉና ደግና ታዛዦች እንዲሆኑ ትተጋና ተመክራቸው ነበር። ክፉ ሥራ በመሥራት እግዚአብሔርን ከሚያሳዝኑ ይልቅ ሞተው ለማየት ትፈቅድ ነበር።

ባለቤቷ ፈርናንድ ጠላቶች ስለነበሩት ከዕለታት አንድ ቀን በሕይወቱ ላይ ከባድ አደጋ በማድረስ ገደሉት። ይህ በተለይ ለሪታ ልብ መሪር ኀዘንና ሥቃይ እንዲደርስባት ምክንያት ሆነ። ልጆችዋም ያለ አባት በመቅረታቸው በኀዘን ላይ ኀዘን ተጨመረባት። ልጆቹ ወላጅ አባታቸው በሰው እጅ በመገደሉ ኅሊናቸው በሥቃይ ተውጦ የማይረሳ መራራ ነገር ሆኖባቸው በመጥፎ ትዝታው ሲበሳጩ እርሷም ታጽናናቸውና ይቅርታን እንዲማሩ ትመክራቸው ነበር። ለባሉ ገዳዮችም ይቅርታን ያደረገች ሲሆን የታላቁ መለኮታዊ መምህር /ኢየሱስ/ ትምህርትና አርአያን  ለመከተል ትጥር ነበር።

ይህች ቅድስት ልጆችዋ የአባታቸውን ደም ለመበቀል ያስቡ ስለነበር ሳትጨነቅ አልቀረችም። የልጆቹ እጆች የሰው ደም እንዳያፈሱም ትጸልይና ትመክራቸውም ነበር። “ጌታ አምላኬ ሆይ! እነዚህ ልጆቼ የሰው ነፍስ ከሚያጠፉ ብትወስዳቸው ይሻላል” እያለች አጥብቃ ስትጸልይ የተመኘችው ደረሰ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቅድስት ሪታ ወደ ገዳም ገብታ በጸሎትና በተጋድሎ ተወስና ለመኖር ስላሰበች፤ ወደ ቅዱስ አውግስጢኖስ  የሴቶች ገዳም ለመግባት ጠየቀች። ነገር ግን የገዳሙ ኀላፊ /እመምኔት/ ለጊዜው ጥያቄዋን ሳትቀበል ቀረች። ይሁንና አንድ ሌሊት ቅድስት ሪታ ወደ ገዳሙ በመሄድ በሩ እንደተዘጋ በተአምር ገዳሙ ውስጥ ተገኘች፤ ይህም እመምኔቷን ከማስደነቁ የተነሣ ቅድስቲቱ የማኅበር አባል ለመሆን አበቃት።

ቅድስት ሪታ ባሳየችው ከፍተኛ መንፈሳዊነት ለባልንጀሮቿ መልካም አርአያ ነበረች። የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሕማማትም ዘወትር ታሰብና በኢየሱስ ስቁል ሥዕል ፊትም ብዙ ጊዜ በጋለ የፍቅርና የትሕትና ስሜት ጸሎቷን ታደረስ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ከሥዕሉ አንዲት እሾኽ ተነጥላ መጥታ ግንባሯን በኃይል ያቆሰለቻት ሲሆን፤ በቁስሉ ምክንያት ትሠቃይ ነበር። ይሁን እንጂ ይህንንም ከጌታ ሥቃይ ጋር በማስተባበር ስለ ነፍሶች ደኅንነት መስዋዕት በማድረግ ለጌታ ታቀርብ ነበር፤ በዚህም መንፈሳዊ ደስታ ይሰማት ነበር። ባልንጀሮቿንም ሁሉ ለጌታ ያላቸውን ፍቅር ያጸኑና ያዳብሩ ዘንድ ትመክራቸው ነበር።

ቅድስት ሪታ በመጨረሻ ዘመንዋ በብርቱ ሕመም ስለተያዘች ብዙውን ጊዜ የአልጋ ቁራኛ ለመሆን በቅታለች። በመጠኑ በመመገብ፤ በተለይ በቅዱስ ቁርባን በመወሰንና የኅሊና ጸሎት በማዘውተር ከታላቁ ፍቅሯ ጋር ፍጹም በሆነ ግንኙነት ጊዜዋን ታሳለፍ ነበር። ለባልንጀሮቿም “ክርስቶስን እጅግ አፍቅሩ፤ የቤተ ክርስቲያንንም ትእዛዛት አክብሩ፤ ባልንጀሮቻችሁንም ውደዱ” እያለች ዘወትር ትመክራቸው ነበር። ቅድስቲቱ ባደረባት በሽታ ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየቷ በፊት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያጽናንዋት እንደነበረና እ.ኤ.አ. ግንቦት 22 ቀን 1447 ዓ.ም. በሰላም ባረፈችበት ዕለትም የቤተ ክርስቲያኑ ደወል በተአምር በራሱ መደወሉ ይነገራል፤ በታላቅ አጀብም ተቀበረች። በአማላጅነቷ ከፍተኛ የሆኑ ድንቅ ጸጋዎችና ተአምራቶች ስለሚታዩ “ተአምራዊቷ ሪታ” ተብላ በምእመናን ዘንድ ትታወቃለች።

ምንጭ፡- "ሁለቱ ታላላቅ ተስፋዎች" በዮሐንስ ገብሩውበት 1972 ዓ.ም.

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት