የካልካታዋ ቅድስት ተሬዛ (ማዘር ተሬዛ)
- Category: አጫጭር ገድለ ቅዱሳን
- Published: Tuesday, 01 November 2016 06:45
- Written by Super User
- Hits: 10978
- 01 Nov
የካልካታዋ ቅድስት ተሬዛ (ማዘር ተሬዛ)
“በደም አልባናዊት፣ በዜግነት ህንዳዊት፣ በእምነቴ ካቶሊክ መነኩሲት ነኝ፡፡ በዚህ ጥሪዬ እኔ የዓለም ሁሉ ነኝ፤ ልቤ ግን ሙሉ በሙሉ የኢየሱስ ልብ ዘላለማዊ ንብረት ሆኖ ተሰጥቷል”
እማሆይ ተሬዛ ነሐሴ 26 ቀን 1910 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ.) ስኮፕጄ ተብላ በምትጠራ መንደር በሜቄዶንያ ግዛት ተወለዱ፡፡ ከሶስት ወንድሞችና እኅቶች የቤቱ መጨረሻ ልጅ ነበሩ፡፡ አባታቸው አቶ ኒኮላ ታዋቂ ነጋዴ የነበሩ ሲሆን እናታቸው ወ/ሮ ድሬን (Drane) ለእግዚአብሔርና ለባልነጀሮቻቸው ትልቅ ፍቅርና አክብሮት የነበራቸው መንፈሳዊት የቤት አመቤት ነበሩ፡፡ እማሆይ ተሬዛ ዕድሜያቸው አምስት ዓመት ተኩል ሲሆን የመጀመርያ ቅዱስ ቊርባን የተቀበሉ ሲሆን በ1916 ዓ.ም. ደግሞ ምሥጢረ ሜሮን ተቀብለዋል፡፡ እማሆይ ተሬዛ የመጀመረያ ቊርባን ከተቀበሉበት ጊዜ አንስቶ ታላቅ የነፍሳት ጥማት በውስጣቸው ነበረ፡፡ እማሆይ ተሬዛ ዕድሜያቸው ስምንት ዓመት ሲሆን ወላጅ አባታቸው በድንገት ስላረፉ ቤተሰቡ ኢኮኖሚያዊ እክል ገጠመው፡፡ እናታቸው ወ/ሮ ድሬን እንደ አባትም እንደ እናትም ሆነው ልጆቻቸውን በጠንካራ ስብዕና፣ በግብረገብና በፈሪሃ እግዚአብሔር አሳደጓቸው፡፡ እኚህ እናት የልጆቻቸውን ሁለንተናዊ ስብዕና እና የጥሪ አቅጣጫ ያነጹ ትልቅ እናት ናቸው፡፡ እማሆይ ተሬዛ በመንደራቸው ከሚገኘው ከኢየሱስ ቅዱስ ልብ ደብር አይጠፉም ነበርና በጊዜው የነበሩት የደብሩ ቆሞስ እማሆይን ስለጥሪያቸው በጥልቀት እንዲያሰላስሉ ያግዟቸው ነበር፡፡
እማሆይ ተሬዛ ዕድሜያቸው 12 ዓመት ሲደርስ ሚሲዮናዊት ሆነው የክርስቶስን ፍቅር ለዓለም ማዳረስ እንደሚፈልጉ ወሰኑ፤ በመሆኑም በ18 ዓመት ዕድሜያቸው የወላጆቻቸውን ቤት ለቅቀው በህንድ ሀገር ሚሲዮናዊ አገልግሎት ይሰጡ ከነበሩት አየርላንዳውያን የሎሬቶ ደናግን ማኅበርን ተቀላቀሉሉ፡ በዚህ ማኅበር ውስጥ ሳሉ እኅት ማርያ ተሬዛ የሚል የምንኩስና ስም ተሰጣቸው፡፡
እማሆይ ተሬዛ በዱብሊን በሚገኘው በእመቤታችን ድንግል ማርያም ስም በተሰየመው የመንፈሳዊ ሕንጸት ማዕከል ውስጥ ለጥቂት ወራት ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ እ.ኤ.አ. በጥር 6 ቀን 1929 ዓ.ም. ወደ ህንድ ሀገር ተላኩ፡፡ በግቦት 24 ቀን 1931 ዓ.ም. የመጀመርያ የምንኩና መሐላቸውን በህንድ ሀገር አደረጉ፡፡ ከ1931-1949 ዓ.ም. እማሆይ ተሬዛበካልካታ በሚገኘው የቅድስት ማርያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በጂኦግራፊ እና በትምህርተ- ክርስቶስ መምህርትነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ግንቦት 24 ቀን 1937 ዓ.ም. ዐብይ የምንኩስና መኃላቸውን ለማድረግ ለዘላለም የኢየሱስ ሙሽራ ለመሆን ቃል ገቡ፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶ እማሆይ ተሬዛ እየተባሉ መጠራት ጀመሩ፡፡ በዚያው በቅድስተ ማርያም ት/ቤት በመምህርትነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በ1944 ዓ.ም. የት/ቤቱ ርዕሰ መምህርት በመሆን አገልግሎታቸውን ቀጠሉ፡፡ በገዳሙ ውስጥ ለነበሩት መነኮሳትና ለተማሪዎች ልዩ ፍቅር የነበራቸው እማሆይ ተሬዛ በሎሬቶ ገዳም በቆዩቸው 20 ዓመታት በደስታ የተሞሉ ዓመታት ነበሩ፡፡ የነበራቸው ልግሥና፣ ራስን አሳልፎ መስጠት፣ የአገልግሎት፣ ከባድ ኃላፊነቶችን የመሸከም መንፈስ እና አስተዳደራዊ ተሰጥኦ በገዳሙ እኅቶች መካከል የኢየሱስ እውነተኛ ሙሽራ የመሆንን ሕይወት በታማኝነት እና በደስታ ለመኖር ይችሉ ዘንድ ረድቷቸዋል፡፡
እማሆይ ተሬዛ ስለራሳቸው ሲናገሩ “በደም አልባናዊት፣ በዜግነት ህንዳዊት፣ በእምነቴ ካቶሊክ መነኩሲት ነኝ፡፡ በዚህ ጥሪዬ እኔ የዓለም ሁሉ ነኝ፤ ልቤ ግን ሙሉ በሙሉ የኢየሱስ ልብ ዘላለማዊ ንብረት ሆኖ ተሰጥቷል” ይላሉ፡፡ በአካላዊ ገጽታቸው እጅግ ትንሽ ቢሆንመ ከድንጋይ የጠጠረ እምነት ነበራቸው፡፡ “ተጠማሁ” የሚለውን የኢሱስን ጥያቄ ተከትለው ለሰው ልጆች ስቃይና መከራ ልባቸውንና ዐይኖቻቸውን በመክፈት የድኃ ድኃ የሆኑትን የሰው ልጆች በሁለንተናቸው ለመርዳት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ እማሆይ ተሬዛ በክርስቶስ ብርኀን የተዋበች ነፍስ ነበረቻቸው፤ ስለ ኢየሱስ ያላቸው ፍቅር አንድ የሚቃጥል ፍላጎት በውስጣቸው አኑሯል፤ ይህም ፍላጎት “ኢየሱስ ፍቅርን በማጣቱ እና ነፍሳት ወደ እርሱ በፍጥነት ባለመመለሳቸው የሚሰማውን የሚያቃጥል ጥማት ማርካት ነው”፡፡
እ.ኤ.አ. በመስከረም 10 ቀን 1946 ዓ.ም. ከካልካታ ወደ ዳርዬሊንግ ግዛት ዓመታዊ ሱባዔ ለማድረግ በባቡር ጉዞ ላይ ሳሉ መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው አዲስ ድምጽ አሰማቸው፡፡ እርሳቸውም ይህንኑ ሲናገሩ “በጥርዬ ውስጥ ሌላ ጥሪ ተቀበልሁ” ይላሉ፡፡ በዚያች ዕለት እርሳቸው ሊገልጹት በማይችሉበት መልኩ “ተጠማሁ!” የሚለው የኢየሱስ ጥማት ማርካት መሆኑን ተገነዘቡ፡፡ በቀጣዮቹ ሳምንታትና ወራት ኢሱስ ምሥጢራዊ በሆኑ ግልጠቶች ይበልጥ ስለዚህ ጥሪ በልባቸው ተናገራቸው፡፡ እሱ “ነይ የእኔ መብራት ሁኚ” በሚል ግብዣ ለተናቁት፣ ለታመሙት፣ ለተጠሉትና በልዩ ልዩ ምክኒያቶች ማኅበረሰቡ አንቅሮ ለተፋቸው የሰው ልጆች እናት እና እውነተኛ የመለኮታዊ ጥበቃ ብርኀን ይሆኑ ዘንድ አነሳሳቸው፡፡
በካልካታ የነበረው እጅግ አሰቃቂ ድህነት፣ ረሃብ እና በሽታ በእጅጉ ልባቸውን ስለነካቸው ይህንኑ ጉዳይ ከኢየሱስ አዲሱ ጥሪ ጋር በማስተሳሰር ለሎሬቶ ደናግላን ገዳም እመምኔት ሃሳባቸውን ገልጸው አዲስ አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችላቸውን ፈቃድ አገኙ፡፡ በነሃሴ 17 ቀን 1948 ዓ.ም. ሰማያዊ ዘርፍ ያለውንና “ሳሪ” ተብሎ የሚጠራውን ነጭ ቀሚስ ለብሰው የሎሬቶን ገዳም ለቅቀው ወደ ካልካታ ድሆች መንደር ገቡ፡፡
ፓንት በምትባል ግዛት ከሕክምና ተልዕኮ እኅቶች ገዳም ዘንድ ለጥቂት ወራት ቆይተው አጫጭር የሕክምና ስልጠናዎችን ወስደው ወደ ካልካታ በመመለስ በድሆች አገልጋይ እኅቶች ገዳም ተጠግተው በመቀመጥ ድሆችን የመንከባከብ አገልግሎታቸውን በካልካታ ጀመሩ፡፡ ቤት አልባ ሕፃናትን በአንድ ዋርካ ሥር በማሰባሰብ ማስተማር፣ በመንገድ ዳር የወደቁትን ህሙማን በማንሳት፣ በረሃብና በበሽታ የሚሞቱ እናቶችና ህፃናትን በመንከባከብ ቀኑን ያሳልፉ ነበር፡፡
ቀስ በቀስ የበጎ ፈቃድ አገልጋዮችን ጥቂት እርዳታ ከቤተክርስቲያንና ከአካባቢው ባለሥልጣናት ለማግኘት ቻሉሉ፡ በዚህ ወቅት እጅግ አሰቃቂ የኑሮ ሁኔታ ወደነበረበት የመንደሩ ክፍል ዘልቀው በመግባት በቃላት ሊገለጹ ከማይችሉት ጋር ተጋፈጡ፡፡ በጥቅምት 7 ቀን 1950 ዓ.ም. እማሆይ ተሬዛ ለድሆች አገልግሎት የሚሰጥ ማኅበር ለማቋቋም ከቅድስት መንበር ፈቃድ አገኙ፡፡ ይህ ማኅበር ለጥቂት ጊዜ የካልካታ ሀገረስብከት ሐዋርያዊና ማኅበራዊ አገልግሎት አንድ ቅርንጫፍ ሆኖ ከቆየ በኋላ ራሱን ችሎ የፍቅር ሥራ ልዑካን ማኅበር (Missionaries of Charity) ተብሎ ተጠራ፡፡ የዚህ ማኅበር ተቀዳሚ ዓላማ ማንም ሰው ሊያገኛቸውና ሊያያቸው የማይፈልጋቸውን የሰው ልጆች መንከባከብ እና ቤተሰብ መሆን ነው፡፡
እማሆይ ተሬዛ ከተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን በካልካታ መንደር ቤት ለቤት እየዞሩ የደከሙትን በመደገፍ፣ ቁስለኞችን በማከምና ገላቸውን በማጠብ፣ በመንገድ ዳር የወደቁትን በማንሳት አገልግሎታቸውን ቀጠሉ፡፡ በጥዋት በቅዱስ ቊርባን ከሚገኘው ኢየሱስ ጋር በጸጥታ ጸሎት ቆይታ ካደረጉ በኋላ እማሆይ ተሬዛ ዘወትር ከእሳቸው የማትለየውን መቁጠርያቸውን ይዘው በተናቀው፣ በተጠላው በወደቀው፣ በተጎቆለውና በታመመው የሰው ልጅ ውስጥ ኢየሱስን ያገለግሉ ነበር፡፡ “ከእነዚህነ ከታናናሾች ለአንዱ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው” (ማቴ 25፡40) በሚለው የወንጌል ቃል በመመራት በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ኢየሱስን ለመመልከት ችለዋል፡፡
ከ1960ዎቹ ጀምሮ እማሆይ ተሬዛ የገዳሙን መነኮሳን ወደሌሎች የህንድ ግዛቶች መላክ ጀመሩ፡፡ ር.ሊ.ጳ. ጳውሎስ 6ኛ በየካቲት 1965 ማኅበሩ እያከናወነ የሚገኘውን ታላቅ ሥራ በማድነቅ ማበረታቻ መላካቸው ለእማሆይ ተሬዛ ትልቅ መጽናናትና ኃይል ስላስገኘላቸው ማኅበሩ ወደሌሎች የዓለም ክፍሎች መስፋፋት ጀመረ፡፡ በዚህም መሠረት ከህንድ ግዛቶች ውጪ የመጀመርያው ዓለም አቀፍ ቤት እ.ኤ.አ. በ1965 ዓ.ም. በቬንዝዌላ ተከፈተ፡፡
የማኅበሩ አገልግሎት አድማስ እየተስፋፋ በመምጣቱ እማሆይ ተሬዛ እ.ኤ.አ. 1963 ዓ.ም. የፍቅር ሥራ ልዑካን ወንድሞች ማኅበር፣ በ 1976 ዓ.ም. የፍቅር ሥራ ልዑካን ገዳማውያን ወንድሞችን እና በ1984 ዓ.ም. የፍቅር ሥራ ልዑካን አባቶችን ማኅበራት ለመመሥራት ችለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር እማሆይ ተሬዛ ዘር፣ ጎሳ፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ልዩነት ሳያደርጉ የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል ኢየሱስን በሰው ልጆች ውስጥ ለማገልገል፣ ለፍትሕና ሰላም ግንባታ በርካታ በጎ ፈቃደኛ አገልጋዮችንም በመላው ዓለም ለማፍራት ችለዋል፡፡
እማሆይ ተሬዛ ላበረከቱት ታላቅ የሕይወት ዘመን አገልግሎት የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ሽልማቶችን ተቀብለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በ1962 ከህንድ መንግሥት የተበረከተላቸው የህንድ መንግሥት የመጨረሻው ደረጃ የክብር ሽልማት (Padmashri Award)፣ በ1979 ዓ.ም. የዓለም የኖቤል ሽልማት ፤ ይጠቀሳሉሉ፡ እነዚህን ሁለት ሽልማቶች ሲቀበሉ በተደጋጋሚ ከመገኛኛ ብዙኀን ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ “እነዚህ ሽልማቶች ለእግዚአብሔር ክብር በድሆች ስም የቀረቡ መሠዋዕቶች ናቸው” ብለው ነበር፡፡ ከእነዚህ ባሻገር የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የሰላም ሽልማት (1971)፣ የኔሄሩ ዓለም ዓቀፍ የሰላምና የጋራ መግባባት ሽልማት (1972)፣ የባልዛን ሽልማት (1978) እና የባህራት ራትና ሽልማት (Baharat Ratna, 1980) መጥቀስ ይቻላል፡፡
የእማሆይ ተሬዛ ሕይወትና አገልግሎ በሙሉ የእያንዳንዱን የሰው ልጆች የሕይወት ክቡርነት ያረጋገጠ ተግባራዊ ምሥክር ነው፡፡ በትልልቅ ፍቅር የሚሠሩ ትንንሽ ተግባራትን እግዚአብሔር እጅግ አስገራሚ ለሆነ ፍሬአማነት እንደሚያበቃቸው ከእማሆይ ተሬዛ ሕይወትና አገልግሎት መረዳት ይቻላል፡፡ በመጋቢት 13 ቀን 1997 ዓ.ም. እማሆይ ተሬዛ ከፍቅር ሥራ ልዑካን እኅቶች ማኅበር አስተዳደር የለቀቁ ሲሆን በመስከረም 5 ቀን 1997 ዓ.ም. ከ87ኛ ዓመት ልደታቸው ዘጠኝ ቀናት በኋላ በብዙ ፍቅር፣ በስቃይና በተጋድሎ በታማኝነት ሲያገለግሉት ወደነበረው ሰማያዊው አባታቸው ቤት በሰላም ተመልሰዋል፡፡
እማሆይ ተሬዛ “ነይ የእኔ መብራት ሁኚ!” ለሚለው የኢየሱስ ጥሪ የሰጡት የእሺታ መልስ “ተጠማሁ!” የሚለውን የኢየሱስን ፍላጎት ለማርካት የፍቅር ሥራ ልዑክ እና የድሆች እናት ይሆኑ ዘንድ አበቃቸው፡፡ ለጥሪው የሰጡት “እሺታ” የቅድስና አክሊል ሥጦታ አመጣላቸው፡፡ እነሆ ከሞታቸው 19 ዓመታት በኋላ እንደ ቅድስት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነትና አስተምህሮ ሁለት ተዓምራት በእርሳቸው አማላጅነት መገኘቱ በመረጋገጡ በመስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ር.ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ በሮም ቅድስት መንበር የእማሆይ ተሬዛን ቅድስና በታላቅ ደስታና ምሥጋና አውጀዋል፡፡
እማሆይ ተሬዛ ወደ ቅድስና ደረጃ ከፍ ይሉ ዘንድ ያስቻላቸው ሁለቱ የፈውስ ተዓምራት በሞኒካ ቤስራ እና ማርቺሊዮ ሀዳድ አንድሪኖ ላይ የታዩ ሲሆን የመጀመርያዋ ህንዳዊት ከማሕፀን ካንሰር የተፈወሰች ሲሆን ሁለተኛው ብራዚላዊ ሰው ደግሞ ከጭንቅላት ካንሰር ተፈውሷል፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው በብፅዕት እማሆይ ተሬዛ አማላችነት ፈውስ ለማግኘት በእምነት ይጸልዩ ነበር፡፡ መፈወሳቸው በሕክምና ቢረጋገጥም የፈውሱን ሁኔታ በየትኛውም የህክምናም ሆነ የሳይንሳዊ ዘዴ ለማረጋገጥ አልተቻለም!
የካልካታዋ ቅድስት ተሬዛ ሆይ ለምኝልን!
ወጣት ሳምሶን ደቦጭ ከቅ. ዮሴፍ ቁምስና ዘሲታውያን አ.አ.