የቅዱስ ጴጥሮስና የመጀመሪያዎቹ ር.ሊ.ጳ. አጭር ታሪክ
- Category: የቅዱሳን ሕይወት ታሪክ
- Published: Friday, 29 November 2013 16:00
- Written by Super User
- Hits: 15312
- 29 Nov
የቅዱስ ጴጥሮስና የመጀመሪያዎቹ ሁለት ክ. ዘመናት ር.ሊ.ጳ. አጭር ታሪክ
ቅዱስ ጴጥሮስ
ከሞቱ ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ ኢየሱስ በፊሊጶስ ቂሣርያ ሀገር ሳለ ጴጥሮስን እንዲህ አለው ‹‹አንተ ጴጥሮስ ነህ በዚህችም አለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም፡፡ የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰትሃለሁ፡፡ በምድር የምታሰረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈታው ሁሉ በሰማያት ተፈታ ይሆናል›› (ማቴ 16፡14-20)።
የጴጥሮስን አስፈላጊና ዋነኛ ሚና ለማወቅ በአዲስ ኪዳን ለ195 ጊዜ ያህል ብቻውን መጠቀሱን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ሌሎቹ ሐዋርያቶች በድምሩ 130 ጊዜ ብቻ በተለያየ ቦታ ተጠቅሰዋል፡፡ ኢየሱስ በፊሊጶስ ቂሣርያ በገባው ቃል መሠረት በቤተክርስቲያን ላይ ጴጥሮስ መሪነቱን ተረክቧል፡፡ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከማረጉ አስቀድሞ ኢየሱስ ለጴትሮስ፣ ለቶማስ፣ ለናትናኤ፣ ለዮሐንስ፣ ለያዕቆብ እና ለሌሎች ሁለት ደቀ መዛሙርት በጥብርያዶስ ባህር አጠገብ ተገለተላቸው፡፡ እዚህ ላይ በስድስቱ ሐዋርያት ፊት ጴጥሮስ ቤተክርስቲያንን እንዲመራ ሥልጣን ተሰተው፡፡ ነገር ግን ጴጥሮስ እና ተከታዮቹ ይህንን ሥልጣናቸውን እንከ አስጨናቂ ገዢ ያለ ፍቅር ይጠቀሙበት ዘንድ አልፈለገም፡፡ ስለዚህ ይህንን ሥልጣን ለጴጥሮስ ከመሥጠቱ በፊት ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ያለውን ፍቅር ሦስት ጊዜ ደጋግሞ እንዲያ ረጋግጥለት ጠይቆት ነበር፡፡ ጴጥሮስ የተጠየውን በፈጸመ ጊዜ ‹‹ግልገሎቼን መግብ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሰማራ›› በሚሉት ቃላት የቤተ ክርስቲያን መሪነት ሥልጣን ተቀበለ፡፡ {jathumbnail off}
ስለ ጴጥሮስ የቀድሞው ሕይወት የሚታወቀው በጥቂቱ ነው፡፡ በገሊላ ሀገር ቤተሳይካ ከምትባል ከተማ አሳ በማጥመድ ሥራ ከሚተዳደር ቤተሰብ የተገኘ ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ ላይ የተማረ ሰው እንዳልነበረ ተጠቅሷል፤ ምናልባት በጊዜው በአይሁድ መምህራን (ረቢ) የሚሰጠውን ትምህርት አልተከታተለም ይሆናል፡፡ አማቹ በወንጌል ውስጥ ተጠቅሳ እንደምናገኛት ጴጥሮስ ባለትዳር ነበር፡፡ በቅፍርናሆም ከአባቱ እና ከወንድሙ ጋር በዓሳ ማጥመድ ተግባር ላይ ተሰማርቶ ይሠራ ነበር፡፡ ከኢየሱስ ጋር የተገናኘውም እዚያ ነበር፡፡ ‹‹ሰው አጥማጅ ትሆናለህ›› በሚል ቃልኪዳን የኢየሱስ ሐዋርያ ለመሆን ተጠራ፡፡
ጴጥሮስ ጥንታዊቷን ቤተ ክርስቲያን የመምራት ተግባሩን የጀመረው ልክ ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ነበር፡፡ በይሁዳ ምትክ የሆነውን የማትያስን ምርጫ በበላይነት የመራው እርሱ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስን በተቀበለ ጊዜ አይሁዳውያንን በመስበክ በአንድ ቀን 3000 ሰዎችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ማኅበር ጨመረ፡፡ በቤተ መቅደስ መግቢያ ላይ ተቀምጦ የነበረውን ሽባ በመፈወስ ተዓምር አደረገ፡፡ የኢየሱስ ተከታዮች መሪ እንደመሆኑ መጠን ከዮሐንስ ጋር በወኅኒ ቤት ታሰረ፡፡ ውሸት በመናገራቸው በአናንያ እና በሰጲራ ላይ ቅጣት አሳለፈባቸው፡፡ መለኮታዊ ኃይልን በገንዘብ ለመግዛት የሞከረውን ስምኦን ገሰፀው፤ በሮም ቆረኔሊዎስ በኩል የመጀመርያዎቹን ክርስቲያን በቤተክርስቲያን ተቀብሏል፡፡
የአህዛብ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሔጄ ጴጥሮስን ማግኘት አለብኝ በማለት ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያን መሪ ስለመሆኑ ዕውቅና ይሠጣል፡፡ በሔሮድስ ትዕዛዝ ቢታሰርም በመላዕክ እርዳታ አመለጠ፡፡ እንደገናም ደግሞ በኢየሩሳሌም ጉባኤ ላይ አሕዛብ መገረዝ ሳያስፈልጋቸው የቤተ ክርስቲያን አባላት መሆን እንደሚችሉ ሲያውጅ እናገኘዋለን፡፡
የቤተክርስቲያን ትውፊት እንደሚናገረው ጴጥሮስ ከኢየሩሳሌም ወደ ሮም ከሔደ በኋላ በንጉሥ ኔሮ ዘመን በሰማዕትነት እንደተሰዋ እናምናለን፡፡ ይህ የንጉሥ ኔሮ ጭፍጨፋ የተካሄደው ሮም ከተቃለጠች በኋላ በ64 ዓ.ም. ገደማ ነው፡፡ ኔሮ ራሱን ያጠፋው በ68 ዓ.ም. ነበር፡፡ ስለዚህ የቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕትነት የተፈጸመው ከ64-68ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ መሆኑ ነው፡፡
በአፈታሪክ እንደምናውቀው የንጉሥ ኔሮ ጭፍጨፋ በተፋፋመበት ጊዜ የሮም ክርስቲያኖች ጴጥሮስን ከሥፍራው አሸሽተውት ነበር፤ ጴጥሮስም ወደ ጥንታዊቷ የአፒያን (Appian) ከተማ በወረደ ጊዜ ኢየሱስ ወደ ሮም ሲወጣ በመንገድ አገኘውና ‹‹Quo Vadis Domine›› ጌታ ሆይ ወዴት ትሄዳለህ? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም መልሶ ‹‹በጎቼን እንዲጠብቅ ያዛዝኩት እረኛ ጥሏቸው ጠፍቷልና ዳግመኛ እሰቀል ዘንድ ወደ ሮም እየሄድኩኝ ነው›› አለው፡፡ ጴጥሮስም መልእክቱ ገባውና ወደ ሮም ተመለሰ፣ ጌታ እንደነገረው በመስቀል ተሰቃይቶ ሞተ፡፡ በቫቲካን ጉብታ ላይ ታላቁ የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን የታነጸው በእርሱ መቃብር ላይ ነው፡፡
ቅዱስ ሊኑስ
የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ነበር፡፡ የቤተክርስቲያን ትውፊት እንደሚያስረዳው ቅዱስ ሊኑስ ቤተ ክርስቲያንንን ከ67 ዓ.ም. እስከ 76 ዓ.ም. ድረስ የመራ ነው፡፡ ስለርሱ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም ለማለት ይቻላል፡፡ ቅዱስ ኤሬንዮስ (Ireneus) ከፃፋቸው መፅሐፍቶች በአንዱ ውስጥ እንደጠቀሰው ቅዱስ ሊኖስ በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ጢሞቴዎስ በተላከችው ሁለተኛይቱ መልእክት ምዕራፍ 4፡21 ላይ የተጠቀሰው የሐዋርያት ረዳት ነበር፡፡ ‹‹ኢዮቡሉስ፣ ጱዴስ፣ ሊኖስ፣ ቅላዲያና አማኞችም ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል›› (ጢሞ 4፡21)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን መልእክት የፃፈው ለሁለተኛ ጊዜ በሮም እሥር ላይ በነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ሊኖስ በሮም ታዋቂ እና ጥሩ ክርስቲያን እንደ ነበር በጳውሎስ ስሙ መጠቀሱ ይመሰክራል፡፡ ሊኖስም በሰማዕትነት ተሰውቷል፡፡ ንጉሥ ቬስፓስያን (Vespasian) ከ70 ዓ.ም. እስከ 79 ዓ.ም. ለነገሠበት ዘመን ይህ ተፈጽሟል፡፡ እርሱም በቫቲካን ውስጥ ከቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር አጠገብ ተቀብሯል፡፡
ቅዱስ አናቅሌጦስ
ሦስተኛው ር.ሊ.ጳጳሳት ቅዱስ አናቅሌጦስ ነበር፡፡ እርሱ አስቀድሞ ከጴጥሮስ ጋር ከዚያም በኋላ ከሊኖስ ጋር አዲሲቷን ቤተ ክርስቲያን በሚመለከት ይሰራ ነበር፡፡ ሊኖስ ከሞተ በኋላ እርሱ ር.ሊ.ጳ ሆኖ ከ76 እስከ 88 ዓ.ም ካገለገለ በኋላ በዶሚሻን (Domitian) ዘመን እንደ ቀዳሚዎቹ ሁሉ በሰማዕትነት ተሰዋ፡፡
ቅዱስ ቀለሜንጦስ 1ኛ
አናቅሌጦስ በ88 ዓ.ም. በቀለሜንጦስ 1ኛ ተተካ፡፡ ይህ ሰው ፍላቪዮስ ክሌመንስ በተባለ እና የንጉሥ ዶሚሻን አጎት በነበረ ሰው ቤተ ውስጥ በባርነት ይሠራ ነበር፡፡ የክሌመንስ ባለቤት ፍላቪያ ክርስቲያን የነበረች ብትሆንም በገዛ ወንድሟ ትዕዛዝ ከሮም እንድትሰደድ ተደረገች፡፡ ባለቤቷ ክሌመንስ ደግሞ ቀለሜንጦስን ከባርነቱ ነፃ ካወጣ በኋላ ስለ እምነቱ አንገቱ በሰይፍ ተቀላ፡፡ ቀለሜንጦስ የቅዱስ ጴጥሮስ ወዳጅ ነበር፡፡ ር.ሊ.ጳ. ቀለሜንጦስ 1ኛ በስፋት የሚታወቁት ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በፃፉት መልእክት ነው፡፡
በቆሮንቶስ ወንጌልን የሰበከው ቅዱስ ጳውሎስ ነበር፡፡ በቆሮንቶስ የሚኖሩ አያሌ ክርስቲያኖች በግል ሕይወታቸው ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ጥያቄ የማንሳት መብት የላትም ብለው ያስቡ ነበር፡፡ እነዚህ ኃብታሞች ክርስቲያኖች የግለሰብ ግብረገባዊ ሕይወት በቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ሥር መሆኑን አልተቀበሉም ነበር፡፡ ሴተኛ አዳሪነት በቆሮንቶስ በሠፊው ይንጸባረቅ ነበር፡፡ በተለይ በቤተመቅደስ ውስጥ ይህ አጸያፊ ተግባረፍ ይዘወተር ስለነበር የቆሮንቶስ አንዳንድ ክርስቲያኖች ር.ሊ.ጳ. ቅዱስ ቀለሜንጦስ 1ኛ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብተው እንዲያስቆሙላቸው ደብዳቤ ላኩባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በቆሮንቶስ አቅራቢያ በምትገኘው በኤፌሶን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በሕይወት የነበረ ቢሆንም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ወደ እርሱ አቤት አላሉም፡፡ ይልቁንም የቤተ ክርስቲያን ራስ የነበረው ቅዱስ ቀለሜንጦስ 1ኛ እንዲረዳቸው ጠየቁት፡፡
ቅዱስ ቀለሜንጦስ 1ኛ በ97 ዓ.ም. ሞተ፡፡ የሞተውም ንጉሥ ትራጃን (Trajan) ቆሮሴኔሱስ ወደ ምትባል በድኝ ምርት የበለጸገች ከተማ በግዞት ከወሰደው በኋላ ድንጋይ በአንገቱ ዙርያ ወደ ባህር ተወርውሮ ነው፡፡
ቅዱስ ኢቫሪስቶስ (Evaristus)
ቅዱስ ኢቫሪስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የመራው ከ97 ዓ.ም. እስከ 105 ዓ.ም. ነው፡፡ ሮምን በተለያዩ ቁምስናዎች በመከፋፈል ለእያንዳንዱ ቁምሥና ጳጳስ ሾሞ ነበር፡፡ ንጉሥ ትራጃን እርሱም በ105 ዓ.ም. ገደለው፡፡
ቅዱስ አሌክሳንደር 1ኛ
ቅዱስ ኢቫሪሲቶስ ከሞተ በኋላ የሮም ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ አሌክሳንደር 1ኛ ስድስተኛው ር.ሊ.ጳ. አድርጋ መረጠች፡፡ ለአሥር ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን ከመራ በኋላ በ115 ዓ.ም. በሰማዕትነት አረፈ፡፡
ቅዱስ ሲክስቱስ 1ኛ
በትውልድ የሮም ዜጋ ነበር፡፡ በቅዳሴ የምንገለገልባቸውን የተቀደሱ ጽዋዎች በሚመለከት ለኹላዊቷ ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ አውጥቷል፡፡ እነዚህ የተቀደሱ ጽዋዎች መያዝ የሚችሉት ካህናት ብቻ ነበሩ፡፡ እንዲሁም ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› የሚለው የቅዳሴ ክፍል በካህናት እና በምዕመናን በመቀባበል መባል እንዳለበትም ደንግገዋል፡፡ በንጉሥ ሀርድያን (Hadrian) ዘመን በ125 ዓ.ም. በሰማዕትነት ሞተዋል፡፡
ቅዱስ ቴሌስፎረስ (Thelesphorus)
ቅዱስ ኤሬኔዎስ እንደፃፈው ቴሌስፎረስ ግሪካዊ ነበር፡፡ ለ11 ዓመታት ስለዘለቀው አመራሩ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ እንደ ቅዱስ ሊክስቱስ ሁሉ በንጉሥ ሀድርያን ዘመን በ136 ዓ.ም. በሰማዕትነት አረፉ፡፡
ቅዱስ ሂግነስ (Hyginus)
ግሪካዊ የነበሩ ሲሆኑ በ140 ዓ.ም. በሰማዕትነት አረፉ፡፡
ቅዱስ ፒዮስ 1ኛ (Piusi)
ቅዱስ ፒዮስ 1ኛ ር.ሊ.ጳ. የነበሩት ከ140 ዓ.ም. እስከ 155 ዓ.ም. ድረስ ነበር፡፡ ኢጣሊያዊ ዜግነት ነበራቸው፡፡ በ155 ዓ.ም. ንጉሥ አንቶኒዮስ በሞት ፍርድ አስገደሏቸው፡፡
ቅዱስ አኒሴቱስ (Anicetus)
አኒሴቱስ የመጣው በሮም የግዛት ሥር ከነበረው የሶርያ ክፍል ነው፡፡ በእርሷቸው ዘመን ሁለት መናፍቃን ተነስተው ነበር፤ እነርሱም ቫለንታይን (Valentine) እና ማርቺያን (Marcian) ሲሆኑ ቫለንታየን የሰው ልጅ በሦስት ደረጃ የተመደበ ነው በዚህም ቁሳዊው ሰው (Material Men)፣ ለጥፋት የተፈጠረው ሰው፣ አዕምሮ ያለው ሰው ተብሎ ይታወቃል ሲል አስተማረ፤ በእርሱ ትምህርት እነዚህ ሰዎች መዳን የሚችሉት በጌታ ምህረት ወይም በራሳቸው ሲፈጠሩ መንፈሳዊያን እና ፍጹሞች ሆነው አስቀድመው ለመንግሥተ ሰማያት የታጩ እንደሆነ ነው፡፡ የዚህ ኑፋቄ ትምህርት ተከታዮች ራሳቸውን ለመንግሥተ ሰማያት የታጩ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ር.ሊ.ጳ. ከዚህ ትፈምህርት ጋር ለመዋጋት የቅዱስ ኤሬኒዮስን ዕርዳታ ጠይቀዋል፡፡
ማርሺያን በበኩሉ የአይሁዳውየን አምላክ ከክርስቲያኖች አምላክ የተለየ ነው ብሎ አስተምሯል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን የተገለጠው የያህዌ ልጅ አይደለም ብሎ ተናገረ፡፡ ብዙ ተከታይ አልነበረውም፡፡ ስለዚህ ማርሺያን በሞተ ጊዜ ይህ የኑፋቄ ትምህርትም አብሮ ተቀበረ፡፡ ቅዱስ አኒስቱስ በንጉሥ ማርኩስ ኤውሬሊዮስ ዘመን በግፍ ጭፍጨፋ በሚያዝያ 7 ቀን 166 ዓ.ም. በሰማዕትነት አረፉ፡፡
ቅዱስ ሶተር (Saint Soter)
በቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ላይ የተቀመቱ 12ኛው ር.ሊ.ጳ. ናቸው፡፡ የኢጣልያ ዜግነት አላቸው፡፡ በረኃብ ወቅት በቆሮንቶስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ቁሣቂ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በ175 ዓ.ም. በማርኩስ ኤውሬሊዮስ ትዕዛዝ በመገደላቸው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡
ቅዱስ ኤሌውቴሪዮስ (Eleutherius)
ለ14 ዓመታት ቤተክርስቲያንን መርተዋል፡፡ ር.ሊ.ጳ. ሆኖ ሲመረጥ ዲያቆን ነበር፡፡ በዜግነቱ የግሪክ ሰው ነበር፡፡ በእርሳቸው ዘመን የሊዮን ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ኤሬኒዎስ ወደ ሮም በመምጣት ለሞንታኑስ (MOntanus) ኑፋቄ ትምህርት ምላሽ ለመስጠት ከር.ሊ.ጳ. ፈቃድ ጠየቀ፡፡ ር.ሊ.ጳ. ለዚህ ኑፋቄ ትምህርት ምላሽ ሲሰጥ በርኅራኄ እንዲሆን ጠየቁት፡፡ ኤሌውቴሪዮስ በ189 ዓ.ም. አረፉ፡፡
ቅዱስ ቪክቶር 1ኛ (Victor I)
ንጉሥ ኮሞዱስ (Commodus) የክርስቲያኖች ወዳጅ ነበሩ፡፡ ስለዚህም ንጉሥ ኮሞዶስ በንጉሥ ማርኩስ ኤውሬሊዮስ ዘመን በሰርዲኒያ (Sardinia) ግዛት በማዕድን ቁፋሮ ዘርፍ በባርነት ያገለገሉ የነበሩትን ክርስቲያኖች ነፃ የሚያወጣ አዋጅ እንዲያወጡ ለቅዱስ ቪክቶር ፈቃድ ሰጧቸው፡፡ በትውልዱ አፍሪካዊ ስለሆነ ብዙ ግሪክ መናገር አይችልም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ በእርሳቸው ዘመን በሮም ከግሪክ ቋንቋ ይልቅ የላቲን ቋንቋ ይዘወተር ነበር፡፡ የፋሲካ በዓል ቀንን በተመለከተ ተነሥቶ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት ችለዋል፡፡ በ199 ዓ.ም. በንጉሥ ሴፕቲሙስ ሴቨንስ እጅ ሰማዕትነትን ተቀብለው አረፉ፡፡
ከመ/ር ሳምሶን ደቦጭ - ቅ. ዮሴፍ ቁምስና ዘሲታውያን - አ.አ.