እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የሲታውያን ማኅበር አመሠራረት በኤርትራና በኢትዮጵያ

የሲታውያን ማኅበር አመሠራረት በኤርትራና በኢትዮጵያ

አባ ፍስሐ ገብረ አምላክ የመጀመሪያው ሲታዊ ሓበሻ

አባ ፍሥሐ ገ/አምላክ ሰኔ 16/1887 ዓ.ም. በኤርትራ በከረን አካባቢ “ዓዲ በሃይማኖት” በምትባል መንደር ተወለዱ። በከረን ቅ.ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተጠምቀው ኃይለማርያም ተባሉ። ከልጅነታቸው ጀምሮ ክፋትን የሚጠሉና ሰብአዊ ርኅርኄ ያላቸው ሰው ነበሩ። አባ ኃይለማርያም ዕድሜያቸው 12 ዓመት ሲሆን የከረን ዘርአ ክህነት ት/ቤት ገቡ። ዘርአ ክህነት ከገቡ በኋላም መንፈሳዊ ሕይወታቸውን በሚገባ ያካሂዱ ስለነበሩ አለቆች መንፈሳዊ ሕይወታቸውን አይተው የዘርአ ክህነት ተማሪዎች መሪ አደርጉዋቸው። እሳቸውም ነፍሳትን ለማዳን ከፍተኛ ቅናት ስለነበራቸው በእረፍታቸው ጊዜ በከረን አካባቢ እየዞሩ ትምህተ ክርስቶስ ያስተምሩ ነበር። የዘርአ ክህነት ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የፍልስፍናና የትምህርተ መለኮት ትምህርታቸውን ቀጠሉ። ከዚያም በከረን ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስትያን በአቡነ ካሚሎ ካራራ ክህነት ተቀበሉ። ለሁለት ዓመት ያህል በከረን አካባቢ ክህነታዊ አገልግሎታቸውን አበረከቱ። ነፍሳትን ለማዳን የነበራቸው ምኞት እየበረታ ስለሄደ የሃገራቸውን ሕዝብ በእውነተኛ መንገድ ለመምራት ይመኙ ነበር። ይህ ምኞታቸው ብቻቸውን እንደማይፈጽሙት ተረድተው ካቶሊካዊ ምንኩስና በሃገራቸው እንዲመሠረት ብዙ ይጥሩና ይመኙ ነበር። ይህ ምኞታቸው ብቻቸውን እንደማይፈጽሙት ተረድተው ካቶሊካዊ ምንኩስና በሃገራቸው እንዲመሠረት ብዙ ይጥሩና ይመኙ ጀመር። ሓሳባቸው ለብዙ ሰዎች አካፈሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ልዑል ካርዲናል ኤንሪኮ አለክስዮስ ለፒስየ በቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ለሐዋርያዊ ጉብኝት በ1914 ዓ.ም. ወደ ሃገራችን በመጡበት ወቅት አባ ኃይለማርያም ይህንን ፍላጎታቸውን ገለጹላቸው። አቡነ ለፒስየም ወደ ሮም በተመለሱ ግዜ ይህን የአባ ኃይለ ማርያም ፍላጎት ለሌሎች የቤተክርስቲያን መሪዎች አካፈሉ።

የእግዚአብሔር ፍቃድ ሆኖ አባ ኃይለማርያም በቫቲካን ለሚማሩት የኢትዮጵያ ኮሌጅ ተማሪዎች የነፍስ አባት ለመሆን ተመርጠው 1918 ዓ.ም. ወደ ሮም ሄዱ። ሮም እንደደረሱ ጥቅምት 20/1918 ዓ.ም. የምሥራቃውያን ቤተክርስቲያ ኃላፊ ወደ ሆነችው ይህንኑ ሐሳባቸውን አቀረቡ። በጥቂት ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ልመናቸውን አቀረቡ። በኢትዮጵያ ኮሌጅ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እያካሄዱ በቫቲካን የተጻፉትን መጻሕፍት ያነቡ ነበር። ጠቃሚ የሆኑትን ይጽፉ ነበር። አንዳንዶችን በመግዛት ያስቀምጡ ነበር። አባ ኃይለማርያም በአቡነ ቡሩክ ገዳም አባ ኃይለማርያም ሁለት ዓመት ያህል በሮም ካሳለፉ በኋላ በሮም የአቡነ ቡሩክ ገዳም ለመግባት ጠይቀው ፍቃድ አግኝተው ከአቡነ ቡሩክ ገዳም ገቡ። ከዚያም ፋርፋ ወደሚባል ገዳም ወሰዷቸው። ለሁለት ዓመት ያህል በዚያ አሳለፉ። ምንም እንኳን በቅዱስ አቡነ ቡሩክ ገዳም ቢደሰቱም የነበራቸው ፍላጎት አልሰመረላቸውም። ምክንያቱም እሳቸው የኢትዮጵያ (የግዕዝ) ሊጡርጊያ እዲፈቀድላቸው ነበር። የአቡነ ቡሩክ መነኮሳን ግን ይህን አልፈቀዱላቸውም። ካርዲናል ሹስተር በጥናታቸው እንደገለጹት ትልቁ ችግር የሊጡርጊያ ችግር መሆኑን ይገልጻሉ። በዚህም ምክንያት ከልብ በማዘን ኅዳር 1 ቀን 1921 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ኮሌጅ (ቫቲካን) ለመመለስ ተገደዱ። በቀድሞ ሥራቸው ለተማሪዎቹ የነፍስ አባትና መምህር ሆነው ቀጠሉ። ከፋርፋ ወደ ሮም እንደተመለሱ ምንም እንኳን ሐሳባቸው ያልተሳካላቸው ቢመስልም የአባ ኃይለማርይም ቅዱስ ዓላማ ሊወገድ አልቻለም። አንዳንድ የቤተክርስትያን ኃላፊዎች የአባ ኃይለማርያምን ሐሳብ ከጎናቸው ሆነው መደገፍ ጀመሩ። የምሥራቃውያን ቤተ ክርስትያን ቅድስት መንበር ኃላፊ ለአቡነ ቸልስቲኖ ካታላዮ የኤርትራ ሐዋርያዊ እንደራሴ ኢትዮጵያ በሃገሯ ካቶሊካዊ ምንኩስና ሥርዓት ብትከተል መልካም ነው ወይ? ብላ መልእክት ጻፈችላቸው። እርሳቸውም በወገናቸው ከትላልቅ ቆሞሳትና ሚስዮናውያን ጋር ከተማከሩ በኋላ በመጋቢት 14 ቀን 1921 ዓ.ም. በመለሱት መልስ “ካቶሊካዊ ምንኩስና በኢትዮጵያ ቢጀመር የምንኩስና ሕይወት ለሚፈልጉት የሃገር ልጆች እንዲሁም በግዕዝ ሊጡርጊያ ለመመራትና ለስብከተ ወንጌል በጣም ጥሩ ነው” ብለው በቅድስት ወንበር ለምሥራቃውያን ኃላፊ ገለጹላቸው። ነገር ግን በዚህ ላይ የሚከተሉት ሁለት ሐሳብ ነበራቸው።

1. ምንኩስናዊ ሕይወት በጣሊያን ሃገር ከሚጀመር በኢትዮጵያ ቢጀመር ጥሩ ነው። ይህም አንድ የሃገርን ልምድና ባህል በሚያውቅ መነኮስ ቢመራ የሚል ነበር። ለዚህም አባ ኃ/ማርያም የዚህ ማኅበር አባል ቢሆኑ የሚል ሐሳብ ለአቡነ ካታናዮ ተላከ።

2. የምንኩስና ፍላጎትና ዓላም ያላቸውን ወጣቶች ሰብስቦ ወደ ሮም መላክና እዚያ የኢትዮጵያ ባህልና ሥርዓት በሚያውቅ መነኮስ በሥነ ሥርዓት ቢኮተኮቱ ይሻላል። ከዚያ ተመልሰው የሃገራችውን ምንኩስናና ሥርዓት በሚፈቅደው መሠረት በኢትዮጵያ ምንኩስናዊ ሕይወት ሊያስፋፉ ይችላሉ፤ የሚል ሓስብ ነበር።

ሌላው ምን ዓይነት መነኮሳን በየት ቦታ የሚል አንዱ ችግር ነብር። ይህም አቡነ ቸልስቲኖ ከቆሞሳት፣ ከሚስዮናውያን፡ ከአቡናት ጋር በአሥመራ ከተማ ተሰብስበው ተማከሩ። የነዚህ አማካሪዎች ሐሳብም ትላልቆችን ከመቀበል ፈንታ ትናንሾች ወጣቶችን ተቀብለው ሰብስበው ማሳደግ ይሻላል የሚል ነው። ይህ በኢትዮጵያ የሚመሠረት ምንኵስና ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት የቤተ ክርስትያን ኃላፊዎች በኤርትራና በኢትዮጵያ ያሉ አቡናት ላይ ብቻ ሳይተዉ በሮምም በቅድስት መንበር የምሥራቃውያን ቤተ ክርስትያን ኃላፊ ክፍል መሠረት ይህንኑ ጥናት ማካሄድ ጀመሩ። በዚህ ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ የሚተከለው የካቶሊካዊ ምንኩስና ሕግ ከቅዱስ አንጦንዮስና ከቅዱስ ጳኩሚስ ሕግ የተውጣጣ መሆን አለበት የሚል ሐሳብ ጸደቀ። ይህም የምሥራቃውያን ሕግ ማስወገድ እንዳይሆንና ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ እንዳይኖር በሚል የቤተክርስትያን ኃላፊዎች ከሚስዮናውያን ጋር ምክክራቸውን ቀጠሉ። ከእነዚህ መካከል አባ ማውሮ ለዮናሳ (ካፑቺናዊ) የተባሉት በሃገራችን ብዙ ዓመታት የተቀመጡ የኢትዮጵያውያንን ታሪክና ዝንባሌ የሚያውቁ ስለዚህ ጉዳይ ጥያቄ ቀርቦላቸው ጥር 20/1930 ዓ.ም. ለቅድስት ወንበር በመለሱላቸው መልስ ላይ፡-

1. የካቶሊካዊ ምንኩስና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚስማማና አስፈላጊ ነው።

2. ይህ ምንኩስና በሌሎች ማኅበራት ከሚቋቋም ይልቅ የሃገር ልጆች ከልጅነታቸው ተኮትኩተው ምንኩስናዊ ሕይወት በሃገራቸው ሥርዓትና ባሕል ቢመሠርቱ መልካም ነው።

3. ከኢትዮጵያ ምንኩስና ሕይወት ጋር የሚስማማ “ጸሎትና ሥራ” የሚል የአቡነ ቡሩክ ደንብ ነው።

4. ከጣሊያን ከሚመጡ ይልቅ ምንኩስናዊ ሕይወት በኢትዮጵያ ቢጀመር ይሻላል የሚሉ ሐሳብ ነበር።


ካዛማሪ

ከብዙ ጥረት በኋላ ካርዲናል ለፒስየ የአቡነ ቡሩክን ደንብ ከሚከተሉት አንዱ ከሆኑት የሲታውያን ማኅበር ጋር ተወያይተው ተስፋ አገኙ። በዚህም መሠረት ካርዲናል ለፒስየ ከአቡነ ኪዳነ ማርያም ካሣ ጋር ወደ ካዛማሪ ሄደው፡ ከካዛማሪ ገዳም አበምኔት ጋር ውል አደረጉ። በተደረገው ውል መሠረትም በኢትዮጵያ ሥርዓተ ሊጡርጊያ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ምንኩስና በካዛማሪ ቢመሠረት ተቀባይነት ይኖረዋል በማለት ለምሥራቃውያን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቅድስት መንበር ሐሳብ አቀረቡ። በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያንን በጣም ያፈቅሩ የነበሩ ር.ሊ.ጳ. ፒዮስ 11ኛ ነሐሴ 25 ቀን 1923 ዓ.ም. ፈቃዳቸውንና ቡራኬያቸውን ሰጡ። ይህም ፍቃድ ከቤተክርስትያን መሰጠቱን በሰሙ ጊዜ ኣባ ኃይለማርያም በጣም ደስ አላቸው። በዚህም ውለው ሳያድሩ ጥቅምት 8 ቀን 1923 ዓ.ም. ወደ ካዛማሪ የሲታውያን ገዳም ገቡ። ኅዳር 28 ቀን 1923 ዓ.ም. ልብሰ ምንኩስና ተቀብለው አባ ፍሥሐ ዘማርያም ተብለው ተመክሮ ጀመሩ። ታኅሣሥ 16 ቀን 1922 ዓ.ም. አባ ክፍለ ጊዮርጊስ ገብረማርያም የሚባሉ ካህን በአቡነ ኪዳነ ማርያም ተመርተው ወደ ካዛማሪ ገቡ። እሳቸውም አባ ፍሬምናጦስ ዘማርያም ተብለው ተመክሮ ጀመሩ። በዓመቱ ተመክሮ ጨርሰው የሲታውያን ልብሰ ምንኩስና ለበሱ። በዚህ ጊዜ አባ ፍሥሐ በጣም ይታመሙ ስለነበር በብዙ ሥፍራ ሕክምና አድርገው በመጨረሻ ሕመማቸው በቀላሉ የማይድን የሣንባ በሽታ (ነቀርሳ) መሆኑ ተነገራቸው። አለቆቻቸው ከእመቤታችን ጸጋ እንዲለምኑ ወደ ፈርንሣይ አገር ሉርድ ማርያም ወደ ሚባለው መካነ ንግደት ላኩዋቸው። እሳቸው ግን ስለጤንነታቸው ጸጋ በመለመን ፈንታ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም የሚያስችል ጸጋ ለምነው ተመለሱ። አባ ፍስሐ ታዛዥ በሕይወታቸው ሁልጊዜ ደስተኛና የጸሎት ወዳጅ በመሆናቸው መነኮሳን ጓደኞቻቸውና አለቆቻቸው በሚያንጽ ፀባያቸው ይደነቁ ነበሩ። ሕመማቸውም እየበረታ ሲሄድ በካዛማሪ ገዳም አካባቢ ወደሚገኘው ሶራ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምናቸውን መከታተል ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ሰዎች ጻድቅ መሆናቸውን አወቁ። ሕመማቸው እየበረታ ሄዶ ሰኔ 1 ቀን 1926 ዓ.ም. ቅዱስ ልበ ኢየሱስ እንደታያቸውና እንደ ጠራቸው እሳቸውም “ዝግጁ ነኝ” ብሎ እንደመለሱለት ለነፍስ አባታቸው ነገሩ። በዚሁ ቀን ከፊታቸው የነበረውን መስቀል አትኩረው እየተመለከቱ በፊቱ ሰው ከሰው ጋር እንደሚነጋገር እራሳቸውን ቀና አድርገው “ኢየሱስ ሆይ እወድሃለሁ፡ ለዘወትርም እወድሃለሁ” እያሉ የሚያንቀላፉ መስለው በሰላም አረፉ። የእረፍታቸው ወሬ እንደተሰማ ያውቋቸው የነበሩና ዝናቸውን የሰሙ ሰዎች “ቅዱሱ መነኩሴ አረፉ” እያሉ አንዳንዶቹ አበባ ተሸክመው ሌሎች ደግሞ የልብስ ቁራጭ ወይ ሌላ ትሩፋት ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ ይሽቀዳደሙ ነበር። አባ ፍሥሐ በሆስፒታል ከአረፉ በኋላ አስከሬናቸው ወደ ካዛማሪ ተወስዶ ተቀበሩ። አሁንም በካዛማሪ ቤተክርስትያን ውስጥ መቃብራቸው ይገኛል። ቤተክርስትያን የሕይወታቸውን ታሪክ አጥንታ “የእግዚአብሔር አገልጋይ” ብላ ሰይማቸዋለች። አሁን ለብጽዕናቸው ጥናት ጨርሳ አንድ ተአምር ብቻ ትጠብቃለች።


በመንዲዳ (ሰሜን ሸዋ) የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት

የመንዲዳ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተቆረቆረችው በ1916 ዓ.ም. በማኅበረ ልኡካን (ላዛሪስት) ካህናት አባ ተስፋሥላሴ ወልደገሪማ (አሊቴና) አባ ገብርዬና አባ ዮሴፍ ባትማን-ፈረንሣዊ (እንደ አካባቢው መጠሪያቸው አባ ዝናሙ) ነበር። ወደዚህ ቦታ ሊመጡ የቻሉበት ምክንያት ከ56 ዓመታት በፊት በ1860 ዓ.ም. ከመንዲዳ በስተሰሜን ምሥራቅ አማን ጉልት (ጅለጎብ) አካባቢ የነበረውን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ለማወቅና ተበታትነው የነበሩትን ምዕመናን ለመፈለግ ነበር።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ካህናት ከመንዲዳ በስተሰሜን ምሥራቅ የሚገኘውን የጅለጎብ ሁኔታ ለማጥናት በ1915 ዓ.ም. መንዲዳ አካባቢ ገዢ ከነበሩት ከቀኝ አዝማች መትፈሪያ ጋር ተገናኝተው ቀኝ አዝማቹ ፈረንጅን ይዛችሁ እንዴት ትዘዋወራላችሁ? ማንስ ፈቀደላችሁ? ብለው ጠየቋቸው። እነሱም በአማን ጉልት ያለውን ሁኔታ ለማጥናትና እዚያ ስብከተ ወንጌል ማካሄድና ት/ቤት መሥራት እንደሚፈልጉ ገለጹላቸው። ቀኝ አዝማች መታፈሪያም ት/ቤት መሥራት የሚፈልጉ ከሆነ በመንዲዳ ሁሉም ነገር እንደሚሰጣቸውና ወደ አማን ጉልት ቢሄዱ የሚማር እንደሚያገኙ ነግሯቸው አሁን የመንዲዳ ገዳመ ሲታውያን ተግባረ እድ በሚገኝበት አካባቢ ቦታ ሰጧቸው። ካህናቱም በዚህ ሃሳብ ተስማምተው ከአለቆቻቸው ጋር ለመመዳደር ወደ አዲስ አበባ ተመልሱ። በዓመቱ በ1916 ዓ.ም. ከአለቆቻቸውና ከቤተ ክርስቲያን ፈቃድ በማውጣት ከአዲስ አበባ ተመልሰው በመምጣት በተሰጣቸው ቦታ አገልግሎታቸውን ጀመሩ። ይኸውም ሱቅ በመክፈት፤ ለተማሪዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በነፃ በመስጠት፤ ለት/ቤት የሚሆነውን ድንኳን በመሥራት 30 የሚሆኑ ተማሪዎችን ማለትም በአዳሪነት 15 ተማሪዎችን እንዲሁም በተመላላሽነት የሚማሩትን በመቀበል ማስተማር ጀመሩ። ቀስ በቀስ አገልግሎታቸውን በማስፋፋት ከስድስት ዓመት በኋላ በ1922 ዓ.ም. አሁን የሲታውያን ማኅበር ያለበትን ገዳምና የመድኃኔዓለም ቤ/ያን ሥራ በመጀመር በ1926 ዓ.ም. ሥራው ተጠናቆ በጥቅምት 27 ቀን 1927 ዓ.ም. ተመረቀ።


ከአንድ ዓመት በኋላ በ1928 ዓ.ም. የጣልያን ፋሺስቶች ኢትዮጵያን በወረሩበት ጊዜ እነዚህ አባቶች አግሎታቸውን አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ ልምሄድ ተገደዱ፤ ት/ቤቱም ተዘጋ። ወራሪዎቹም ገዳሙን ወርሰው መኖሪያቸው አደረጉ። ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ የነበሩ አንዳንድ ምዕመናን በገዳሙ አካባቢ በመሆን በተቻላቸው ሁሉ የቤተ ክርስቲያንን ንብረት በመጠበቅና እንዲሁም ካህናት እንዲሰጣቸው ወደ አቡን አቤቱታ በማቅረብ ለመላዋ ካቶሊካዊት ቤ/ያን ለመንዲዳ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል። ከነዚህ ምዕመናን መካከል በ1916 ዓ.ም. በመንዲዳ የመጀመሪያ ካቶሊክ ቤ/ያን ስትቆረቆር ከመጀመሪያ ካቶሊኮች ከነበሩት አንዱ አቶ አሰግድ ፋሪስ ናቸው። የሃይማኖት መድልዎ፣ ብቸኝነትና ችግርን ሁሉ በመታገስ ጊዜያቸውን ከመድኃኔዓለም ጋር ያሳለፉ ናቸው። እንዲሁም ካህን እንዲላክላቸው ወደ አቡነ ኪዳነማርያም አቤቱታ ካቀረቡትና በሕይወታቸውም ጭምር የካቶሊክ እምነት ከሰሜን ሸዋ እንዳይጠፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉት ጠንካራ ምዕመናን መካከል አንዱ ናቸው። ወደ አቡኑም አቤቱታ እንዳቀረቡም አባ ገብረሥላሴ የተባሉ ካህን ወደ መንዲዳ ተልከው ጣልያን እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ደብረ መድኃኔዓለምን አገልግለዋል።

ከዚህ በኋላ እንደገና በ1934 ዓ.ም. ገዳሙ ተጠናክሮ አገልግሎቱን ጀመረ። ተዘግቶ የነበረው ት/ቤትም አባ ገብረሥላሴ ት/ርት ሚኒስቴር ዘንድ ሄደው በማስፈቀድ ተከፍቶ ሥራውን ጀመረ። በዚህ ዓይነት ሁኔታ የተለያዩ ካህናት በተለያዩ ጊዜ ተመድበው አገልግለዋል። ከነዚህም ካህናት መካከል በኋላ አቡን የሆኑት አባ አሥራተማርያም የምሩ ይገኙበታል። ይህ በላዛሪስት አባቶች የተጀመረ ገዳም በቤተ ክርስቲያን ፈቃድ በ1948 ዓ.ም. ወደ ሲታውያን አባቶች እንዲዘዋወር ተደረገ።

የመጀመሪያዎቹ ሲታውያን መነኮሳን ታሪክ በመንዲዳ ይቀጥላል

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት