እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ሲታዊነት

የሲታውያን ማኅበር አጀማመርና የአቡን ቡርክ ደንብ

የሲታውያን ማኅበር ሲታዊ (Cistercians) የሚለውን ስያሜ ያገኘው ከ900 ዓመታት በፊት ከተመሠረተበት ሲቶ ከሚባል ፈረንሳይ ውስጥ ከሚገኝ የቦታ ስም ነው ነው። የሲታውያን ምንኩስና እንዴት እንደተጀመረ ታሪኩን የምናገኘው ከሁለት ሰነዶች ነው፡፡ እነሱም ኤክሶርዲዩም ማኙም (Exordium Magnum) እና ኤክሶርዲዩም ፓርቩም የተባሉ ናቸው። እነዚህ ሰነዶች የተጻፉት በ12ኛ ክ.ዘ. መጨረሻ ሲሆን ጸሐፊው ኮንራድ የተባሉ የክለርቮ መነኩሴ ናቸው። እኚህ ጸሐፊ ለምን እንደተመሠረተ ሲገልጹ “የአቡነ ቡሩክን ሕግ ቃል በቃል ለመፈጸምና በገዳማዊ ሕይወት እግዚኣብሔርን ለማገልገል ነው” ይላሉ። የአቡነ ቡሩክ ሕግ የተጻፈው በ6ኛ ክ.ዘ. ኣጋማሽ ላይ ሲሆን፡ እንደ አቡነ ቡሩክ አገላለጽ “ገዳም የእግዚአብሔር ትምህርት ቤት ነው”። ደግሞም በገዳም ውስጥ ለእግዚአብሔር ምስጋና/መለኮታዊ ሥራ (Divine Praise – Opu Dei) መንፈሳዊ ንባብ (Spiritual Reading – Lectio Divina) የጉልበት ሥራ (Physical Work – Laboro Manum) የእርሻና ሌሎች ሥራዎች ይኖራሉ። ስለዚህ የሲቶ መመሥረት ዋና ዓላማ መነኮሳን የቅዱስ አቡነ ቡሩክን ሕይወት እንዲከተሉ ነው ስንል የመነኮሳኑ ሕይወት በመለኮታዊ ምስጋና፣ በሥራ፣ በእግዚአብሔር ቃል ንባብና አስተንትኖ ይገለጻል ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ''ሥራሕ ወጸሊ'' (Ora et Labora) የሚል መፈክር የገዳሙ መገለጫ የሆነው።

ሌላው ሦስተኛ ሰነድ ኤክሶርድዩም ቺስተርቺ (Exordium Cistercii) ስለ ሲቶ መነኮሳን የመጀመሪያ አሰፋፈር ሲገልጽ “ሰው በማይኖርበት ጫካና በረሃም ቦታ ሰፈሩ። ይህንንም የመረጡበት ምክንያት በሐሳባቸው የነበረውን የመስዋዕትነት ሕይወት ለመኖር ነው” ይላል። ኤክሶርድዩም ፐርቩም (Exordium Parvum) የሚባል ሰነድ ደግሞ “ሲቶ የተመሰረተበት ቦታ በሻሎን (Chalon) ሃገረ ስብከት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ጫካና ሰው የማይኖርበት ቦታ ነበር። ገዳሙን የመሠረቱት ጫካውን በመመንጠርና በማጽዳት ነው።” ይላል። አንዳንድ የጊዜያችን ጸሓፊዎች ግን ቅ.ሮቤርቶስ በሞለዝም ገዳም ተቀምጦ ሳለ ለእሱ የሚሆን ቦታ ይፈልግ ነበር። በመሆኑም ራይነልድ የተባለ የመሬት ባላባት ለቅ.ሮቤርቶስ ይህን ቦታ ከትንሽ ቤተ ጸሎት ጋር ሰጥቶታል። ስለዚህ ሲቶ የተመሠረተበት ቦታ ዛፍ የበዛበት እንጂ ሙሉ በሙሉ ሰው የማይኖርበት ጫካ አልነበረም። ስለሆነም ከዚህ በፊት የተጻፉት የሲቶ መረጃዎች የተጋነኑና መረጃ የሌላቸው ናቸው የሚል ሐሳብ አለ። ይህም ማለት እውነተኛ ጫካ አይደለም እንደ ማለት ነው። የሆነ ሆኖ የመጀመርያ የሲታውያን ተክል የሲቶ ገዳም መሆኑን ሁሉም ይስማሙበታል።

የሲታውያን ማኅበር መሥራቾች - ቅዱስ ሮቤርቶስ፡ ቅዱስ አልቤሪኮስና ቅዱስ እስጢፋኖስ

ቅዱስ ሮቤርቶስ

በ11ኛው ክ.ዘ. የምንኵስና ሕይወት የመቀዝቀዝ መንፈስ አሳይቶ ስለነበር፡ ብዙ ቅዱሳን መነኮሳን የምንኩስና ሕይወትን ለማደስ ብዙ ተንቀሳቅሰው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። ከነዚህም መነኮሳን መካከል አንዱ ቅዱስ ሮቤርቶስ ነው። ቅዱስ ሮቤርቶስ ቅዱስ ሮቤርቶስ በፈረሳይ ሃገር ሻምፓኝ በሚባል ቦታ በ1028 ዓ.ም. ተወለደ። በወጣትነቱ ሞንተር ዳ ሳሌ (Montier da salle) በሚባል የአቡነ ቡሩክ ገዳም ገባ። እ.ኤ.አ. በ1053 የዚሁ ገዳም ኣበምኔት ሆኖ ተመረጠ። ከ 1068 – 1072 ዓ.ም. የገዳም ቅዱስ ሚካኤል ዴቶነረ (St. Michael de Tonnerre) አበምኔት ሆኖ አገለገለ። ቅዱስ ሮቤርቶስ የዚህ ገዳም መንፈሳዊ ሕይወት ደካማ በመሆኑ ሊስማማው ስላልቻለ ወደ ጥንት ገዳሙ ሞንትየር ዴ ሳሌ ተመለሰ። ቅዱስ ሮቤርቶስ በ1074 ዓ.ም. እንደገና ገዳሙን ትቶ ኩሉኒ (Collun) ወደሚባለው ገዳም ሄዶ፡ ከአንዳንድ ባሕታውያን ጋር ተገናኝቶ እዚያ በመቀመጥ ሞለዝም (Moleseme) የሚባል ገዳም መሠረተ፡፡ ይህንን ገዳም በጥሩ የገዳማዊ መንፈስ ማካሄድ ጀመረ። ብዙ ቅዱሳን መነኮሳን ተከታዮችን አፈራ። ከጊዜ በኋላ ግን ብዙ ምቾትና ሃብት ስለበዛ እንደሌሎቹ ገዳማት የመንፈስ መቀዝቀዝና የሕይወት ውድቀት ስላስከተለ፡ ቅ.ሮቤሮቶስ በዚህ ጉዳይ በጣም ኣዝኖ በተደጋጋሚ መነኮሳንን ጠርቶ የአቡነ ቡሩክን ሕግ ሙሉ በሙሉ መፈጸም እንዳለባቸው አሳሰባቸው። መነኮሳኑ ግን ሕጉን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም አልፈለጉም። እሱንም አልሰሙትም፤ ባሉበት ሁኔታና የምቾትን ኑሮ ለመኖር ፈለጉ።

በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሮቤቶስ የእነርሱን የሕይወት አቋም ትቶ ቅ. አልቤሪኮስንና ቅዱስ እስጢፋኖስን በመያዝ የሞለዝምን ገዳም ትቶ ወጣ። ሃያ አንድ የሚሆኑ መነኮሳንም ተከትለውት ጥቅጥቅ ወዳለው ጫካና ሰው ወደማይኖርበት ቦታ ሄዱ። እንደተመኙትም ለእነርሱ የሚሆን ቦታ አገኙ። ቦታውም ቡርጉንዲ በሚባል አውራጃ ውስጥ ሲሆን ልዩ ስሙም ሲቶ (Citeaux) ይባል ነበር። ይህን ቦታ የአውራጃው ሹም ራይፕልድ የሰጣቸው ሲሆን በዚህ ቦታ እ.ኤ.አ. መጋቢት 21 ቀን 1098 ዓ.ም. ገዳም መሠረቱ። ቅዱስ ሮቤርቶስና ልጆቹ የአቡነ ቡሩክን ደንብ ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ከባዱን የምንኩስና ኑሮ በሥራና በጸሎት ታጥቀው መኖር ጀመሩ። በዚህ በሲቶ ገዳም መነኮሳን በጥሩና በአስተደሳች ሁኔታ ሲኖሩ ሳለ በሞለዝም የቀሩት መነኮስን ግን አንዳንድ ችግሮች ስለገጠማቸው፡ መጀመርያ መሪያቸውን ቅዱስ ሮቤርቶስን በማጣታቸውና አንዳንድ በአካባቢያቸው የሚኖሩ ሰዎች የንቀትና የዛቻ ቃላት በመወርወር ኣስቸገሯቸው። በዚህ ጊዜ መነኮሳኑ ይቅርታ በመጠየቅ መሪያቸው እንዲመለስላቸው ጠየቁ። ቅ.ሮቤርቶስ ግን ጠባያቸውን ያውቅ ስለነበር ልመናቸውን አልተቀበለም። እነሱም በዚህ ሳይተዉ ልመናቸውን ወደ ር.ሊ.ጳ. ኡርቢኖስ 2ኛ ስላቀረቡ፡ ር.ሊ.ጳ. ኡርቢኖስም የሚነኮሳኑን ሁኔታ በመልእክተኞቻቸው አድርገው በደንብ ካጠኑ ቅ.ሮቤርቶስ ወደ ሞለዝም እንዲመለስ ወሰኑ። እሱም የሲቶ ገዳም መነኮሳን ወደ ሞለዝም ገዳም መመለስ ወይም ደግሞ በሲቶ ገዳም መቅረት እንደሚችሉ ነገራቸው። አንዳንዶቹ ሐሳቡን ተቀብለው ከሱ ጋር ሲሄዱ አንዳንዶቹ ግን በሲቶ ገዳም መቅረት እንደሚፈልጉ ገለጹለት። በዚህ ሁኔታ ቅ.ሮቤርቶስ በቤተክርስትያን ትእዛዝ ወደ ሞለዝም ገዳም ተመለሰ። የሲቶ ገዳም አበምኔታቸው ሲሄድ በጣም ሲያዝኑ፡ የሞለዝም ግን በጣም ተደሰቱ። ቅ.ሮቤርቶስ በሞለዝም ገዳም ሲያገለግል ኖሮ በ1110 ዓ.ም. በቅድስና አረፈ። በ1220 ዓ.ም. በቤተከርስትያን ፈቃድ ቅዱስ ተባለ።። ክብረ በዓሉም ሚያዝያ 29 ቀን ይከበር ነበር። በኋላ ግን በ1970 ዓ.ም. ከሁለቱ ቅዱሳን (አልቤሪኮስና እስጢፋኖስ) ጋር ጥር 18 እንዲከበር ተወሰነ።

ቅዱስ አልቤሪኮስ

ቅዱስ ሮቤርቶስ ወደ ሞለዝም ገዳም ከተመለሰ በኋላ የሲቶ መነኮሳን ሐምሌ 1099 ተሰብስበው ቅዱስ አልቤሪኮስን የሲቶ ገዳም አበምኔት አድርገው መረጡት። ቅ.አልቤሪኮስ የቅዱስ ሮቤርቶስ ምክትል፡ እንዲሁም በጣም መንፈሳዊ ስለነበር፡ የሲቶ መንፈሳዊና ስጋዊ ሕይወት እንዲጠናከር አደረገው። በተለይም ቅ.አልቤሪኮስ ከቤተ ክርስትያን ወገን ከአቡናት፣ ከመነኮሳንና ከካህናት ጥቃትና ተጽዕናኦ እንዳይደርስበት ገዳሙ ጳጳሳዊ ጥበቃ (Papal protection) ሥር እንዲሆን አድርጓል። በትውፊት (Tradition) እንደሚገኘው “አንድ ቀን ቅ.ኣልቤሪኮስ በእርሻ ቦታ ሲሠራ ሳለ እመቤታችን ድንግል ማርያም ተገለጠችለትና ጥቁር ስካፒለር ከመታጠቂያው ሥር ኣድርጋ አስታጠቀችው” ይላል። ሌላ ትውፊት ደግሞ “ቀሚሱ ነጭ ስካፒለሩ ጥቁር አንዲሆን” ነገረች ይላል። የሆኖ ሆኖ የአቡነ ቡሩክና የሲታውያን አለባበስ በቅ.አልቤሪኮስ ጊዜ እንደተለያየና ጥቁር ቀሚስ የሚለብሱትን ቤኔዲክንቲን (Benedictine) ነጭ ቀሚስ የሚለብሱት ደግሞ ሲታውያን (Cistercians) እንደተባሉ የተረጋገጠ ነው። ቅ.አልቤሪኮስ በዚሁ ገዳም እ.ኤ.አ ጥር 26 ቀን 1119 ዓ.ም. በሰላም አረፈ።

ቅዱስ እስጢፋኖስ ሃርዲንግ

እስጢፋኖስ ሃርዲንግ እ.ኤ.አ. በ1060 ዓ.ም. በእንግሊዝ ሃገር ተወለደ። በወጣትነቱ በአካባቢው ወደ ነበረው የአቡነ ቡሩክ ት/ቤት ገብቶ ትምህርቱን ሲከታተለ ቆይቶ በጦርነት ምክንያት ከአገሩ ወደ ፈረንሳይ በመሄድ በፓሪስ ትምህርቱን ጨረሰ። ከዚህ በኋላ ለጉብኝት ወደ ሮማ ሄደ። በዚህ ጊዜ በሮም ያያቸው መንፈሳዊ ቅርሶችን እንዲሁም በቅ.ጴጥሮስ ቤተ ክርስትያን ገብቶ ሲጸልይ በልቡ የአምላክ ጥሪ አድሮበት ከዚህ ወጥቶ በቀጥታ ወደ ሞለዝም ገዳም እንደገባ ይነገራል። ቅ.እስጢፋኖስ በሲቶ ገዳም ሦስተኛ አበምኔት ነው። በአካባቢው ከሚኖሩት ሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ስለነበረው፡ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎችን አግኝቶ የእርሻ ቦታዎችን አቋቋመ። በፓሪስ፣ በእንግሊዝና፡ በኢጣልያ ሃገርም የተመለከታቸውን ሁኔታዎችና ልምድ ገዳሙን ለማስተዳደር በጥሩ ሁኔታ አገዘው። በተጨማሪም አንዳንድ ወንዶችና ሴቶች መሬታቸውን ለገዳም እንደ ገጸ በረከት ያበረክቱ ነበር። ከእነዚህም የእርሻ ቦታዎች የወይን ፍሬዎችን በብዛት በማምረት ገዳሙ ከፍተኛ ገቢ እንዲያገኝ አድርገው ነበር።

ቅ. እስጢፋኖስ በአካባቢው የታወቀው በእርሻ ብቻ ሳይሆን በሥርዓተ ሊጡርጊያም ጭምር ነበር። በዚህ ረገድም የላቲን ዜማ (Gregorian Chant)ና ምልክቱን በማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎም ቩልጋታ (Vulgata) የተባለውን ከእብራይስጥ ወደ ላቲን በመተርጎም ከፍተኛ ማሻሻል አድርጓል። በዚህም የአይሁድ ሊቃውንትን ጭምር በመሰብሰብ ለትርጉሙ ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። የጥሪ ፈተና ቅ.እስጢፋኖስ በሕይወቱ እያለ በገዳሙ ላይ ከባድ የጥሪ ፈተና ያጋጥመው ነበር። ይኸውም ተላላፊ በሽታ ገዳም ውስጥ ገብቶ በከባድ ሁኔታ ላይ ወደቁ። መነኩሴዎቹ አንድ በአንድ ወደ መቃብር ወረዱ። ይህም ሁኔታ በገዳሙ ላይ ከፍተኛ ጥፋትን በማስከተሉ ለመነኮሳን መታጣት ከፍተኛ ሥጋት ሆነ። የቀሩት መነኮሳንም የያዝነው ጥሪ የተሳሳተ ይሆን ወይ? እያሉ ወደ ጥርጣሬ ገቡ። እግዚአብሔርም ይህን የመሰለ ችግር ወደ ደብረ ሲቶ ያመጣው የእነርሱ እምነት ለመፈተን ብሎ ነበር። ነገር ግን ከመነኮሳኑ አብዛኞቹ በሞት ቢለዩአቸውም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይሁን እያሉ በእምነት ጸኑ። የማኅበሩ ዳግም ትንሣኤ እግዚአብሔር የሲታውያንን መነኮሳን ብርታትና እምነት አይቶ ይፈሩት ከነበሩት ጥፋት አዳናቸው። ሞትና በሽታም ቆመላቸው። ለመጀመርያ ጊዜ ፈርተ (Ferte) የተባለውን ገዳም መሠረቱ። በዚህም ተስፋ ከመቁረጥ ድነው ወደ መጽናናት ወደ ትልቅ መንፈሳዊ ብርሃን ተሻገሩ። ቀጥሎም ገዳሙ ወደተለያዩ አቅጣጫዎች እየተስፋፋ ሄደ። በመልካም ሕይወቱና በመንፈሳዊነቱም በሕዝቡ ዘንድ ዝናና ፍቅርን አሳደረ። በዚህ ጊዜ ቅ.በርናርዶስ የገዳሙን መንፈሳዊነትና ዝና ሰምቶ ሠላሳ ወጣቶችን ይዞ ወደ ገዳም ገባ። ጥሪውም እንደገና ተስፋፍቶ የማኅበሩ ትንሣኤ ሆነ። በ1114 ሌላ ፐንቲኚ (Pantigny) የሚባል ገዳም ተተከለ። በዚህ ጊዜ በርናርዶስ ተመክሮ ገብቶ ነበር። በዓመቱ በ1115 ዓ.ም. ተመክሮ ጨርሶ ክለርቮ የሚባል ገዳም ተከፍቶ በቅ.እስጢፋኖስ ተመርጦ የዚህ ገዳም አለቃ ሆኖ ማስተዳደር ጀመረ። ከዚህም ቀጥሎ ሌላ ሞርሞንድ (Morimond) የሚባል ተጨማሪ ገዳም ተከፈተ። ሲቶ፣ ፐንቲኚ፡ ክሌርቮና ሞርሞንድ አራቱም ገዳማት የሲታውያን የመጀመርያ ገዳማት ተብለው ተጠሩ። እያንዳንዱም ገዳማት የየራሳቸው አበምኔት ተመረጠላቸው። አበምኔቶቹም ከሲቶ አበምኔት ገዳም ጋር ሆኖ ገዳሙን በከፍተኛ ሐላፊነት ይመሩ ነበር። ከዚህ በኋላ ቀስ በቀስ ሌሎች ገዳምት ተከፈቱ። ማኅበሩም ከነበረበት የጥሪ ስቃይ ተገላግሎ በተረጋጋ መንፈስና ጸሎት ሕይወታቸውን መምራት ጀመሩ። ቅ. እስጢፋኖስም በጣም ተደስቶ በጊዜው ለነበሩት ር.ሊ.ጳ. ክላቶስ 2ኛ መልካም ፍቃድቸው ከሆነ ገዳሙን (ሲቶን) እንዲጎበኙ ጋበዛቸው። እርሳቸውም ሐሳቡን በመቀበልና ድጋፍ በመስጠት ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገው የማኅበሩን መተዳደርያ ደንብ አጸደቁላቸው። የሲታውያን ማኅበር መሠረታዊ ሕጎች ቅ.ሮቤቶስ ከሞለዝም ገዳም ወጥቶ የሲቶን ገዳም ሲያቋቁም የቅ.አቡነ ቡሩክ ሕግና ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ነበር። በዚህም ምክንያት በአቡነ ቡሩክ ገዳም ከኩሉኒ ጋር ከፍተኛ ግጭት ነበራቸው።

የሲቶ መነኮሳን የአቡነ ቡሩክን ደንብ ቀጥ አድርገው በመያዝ ሌላም ከአካባቢው ጋር የሚስማማ ሌላ አዲስ ውሳኔዎችን መሥርተው ነበር። ይህም ውሳኔ የፍቅር ወረቀት (Charter of Charity, Charta Caritatis) ተብሎ ተጠራ። የፍቅር ወረቀት ጀማሪው እራሱ ቅ. እስጢፋኖስ ሲሆን ሥራውን የቀጠሉትና ወደ ተግባር ያሸጋገሩት የእርሱ ተከታዮች ናቸው። በዚህ በፍቅር ወረቀት አማካኝነት እንደገና በኩሉኒና በሲቶ መካከል ከፍተኛ አለመግባባት ተፈጠረ። የኩሉኒ መነኮሳን የሲቶን መነኮሳንን “እናንተ ፈሪሳውያን የሕግ ፈጣሪዎች” በማለት ተቃወሟቸው። የሲቶ መነኮሳንም በበኩላቸው የአቡነ ቡሩክን ደንብ የሚፈጽሙበት መሣርያ እንጂ ከአቡነ ቡርክ ሕግ ውጪ ሌላ ሕግ እንዳላወጡ የፍቅር ጥሪ ወረቀት ወይም መንገድ እንደሆነ የአቡነ ቡሩክን ደንብ እየጠቀሱ አስረዱዋቸው። የፍቅር ወረቀት የአቡነ ቡሩክን ደንብ ከጊዜ ጋር የሚያስማማ መመርያ ነው (የአ.ቡ.ደንብ ምዕ.72)። በዚህም ላይ መነኮሳኑ ጠንካራ ዓላማ በመያዝ ከዓለም ለመራቅ ወሰኑ። ይህ የመነኮሳን ጠንካራ ውሳኔ ለኩሉኒ መነኮሳን ከፍተኛ እንቅፋት ሆነባቸው። ምክንያቱም የኩሉኒ መነኮሳን የምቾት ኑሮ ለምደው የሲቶን መነኮሳን ኑሮ እንደ መጥፎ ጎን በማየት ወቀሱዋቸው። በተለይም የፍቅር ወረቀትን በመጻፋቸው፡ የአቡነ ቡሩክን ደንብ እንደተዉ አድርገው በመቁጠር አምርረው ተከራከሩዋቸው። ቅ. በርናርዶስም በዚህ ነገር በጣም ተቸገሮ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል።

የፍቅር ወረቀት ዋናዋና ይዘቶች

1. ከዚያ በፊት ያልተለመዱትን ለምሳሌ፡- የመነኮሳን በእርሻ ሥራ መሰማራት፡ አርድዕት (ወንድሞች) በገዳም ውስጥ መያዝ

2. አዲስ ገዳም ሲገደም አባላቱ አሥራ ሁለት እንዲሆኑ

3. አዲስ ገዳም ሲመሠርቱ በእመቤታችን ድንግል ማርያም ስም እንዲሰየም፡ ገዳም በሚመሠረትበት ጊዜም ከከተማ ውጭ እንዲሆንና መነኩሴዎች ከገዳም ውጭ እንዳያድሩ።

4. የሊጡርጊያ ሥርዓት የያዙ መጻሕፍትን በሙሉ በማኅበር እንዲዘወተሩ፡ በተለይም የአቡነ ቡሩክ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም፡

5. አለባበስ፡ የምግብ ዓይነቶችና ሌሎችም አንድ ዓይነት መሆን እንዳለባቸው፡ ሥጋ በገዳም ውስጥ እንዳይበላና መነኩሴዎች ደግሞ በእርሻ በሚያገኙት ፍሬ መተዳደር እንዳለባቸው፡

6. መነኩሴዎች የድህነት ኑሮ መኖር ስላለባቸው፡ ቁምስና መያዝ፡ የቤተክርስትያን ግብር መቀበል፡ ከበድ ያሉ ዓለማዊ ጉዳዮች አለማካሄድ፡ መሸጥና መለወጥ፡ በዓለማዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ አለመግባትና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጌጣጌጥ አለማድረግ፡

7. ስለ ማኅበሩ ጉባኤ (General chapter) ስለ መብት፡ ስለ ዓመታዊ ጉብኝት፡ ስለ በደለኞች ቅጣት፡ ስለ አበምኔት ምርጫ፡ ስለ አቡናት ግንኙነት፡ ስለ እንግዶች አቀባበል፡ ስለ ስሹመትና የመሳሰሉት

8. ስለ አስተዳደር (Administration)፡ የሲቶ አጠቃላይ ማኅበር አባት ወይም ማኅበሩን የሚመሩ መሆኑን፡ የመጀመርያዎቹ አራቱ ገዳማት እናት ገዳም እንዲባሉ መደረጉ፡ በዓመት አንድ ጊዜ (መስከረም 14) እንዲሰበሰቡ፡ የአቡነ ቡሩክ ደንብ በተግባር መዋሉና አለመዋሉን መገምገም የመሳሰሉት ናቸው። በተጨማሪ ስለማኅበሩ ታሪክ ኤክሶርዲዩም ፓርቩም ኤክሶርዲዩም ቺስተርቺ (Exordium Cistercii) ኤክሶርዲዩም ማኙም (Exordium Magum) እና የመሳሰሉት የፍቅር ወረቀት ውስጥ ይገኛሉ።


አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት