እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ቅዱስ በርናርዶስ ዘክሌርቮ

ቅ. በርናርዶስ የገዳም ኃላፊና የቤተክርስቲያን ሊቅ

San Bernardo

ቅዱስ በርናርዶስ እ.ኤ.አ. በ1090  ዓ.ም. ፈረንሳይ ውስጥ ዲጀን /Dijon/ በሚባል አካባቢ ፎንተን መንደር ውስጥ ከትልቅ ቤተሰብ ተወለደ፡፡ አባቱ ቴስሊን /Tescelin/ ሲሆን እናቱ ደግሞ አሌታ /Aletha/ ትባል ነበር፡፡ እርሷም በጣም መንፈሳዊ ነበረች፡፡ እነዚህ ወላጆች ሰባት ልጆች ሲኖሯቸው ቅዱስ በርናርዶስ ሦስተኛ ልጅ ነበረ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1111 ዓ.ም.  ወደ ሲቶ ገዳም ገባ፡፡ በወቅቱ የሲቶ ገዳም አዲስ ከመሆኑም ባሻገር በዚያ የነበሩ መነኮሳን በሕመምና በእርጅና ምክንያት እየሞቱ ገዳሙ ለመዘጋት ተቃርቦ ነበር፡፡ እነዚህ መነኮሳን እራሳቸውን ሞለዝም በሚባል ገዳም ከሚኖሩት የአቡነ ቡሩክ መነኮሳን ለመለየት ዋናው ምክንያታቸው በሞለዝም የአቡነ ቡሩክ ደንብን መነኮሳኑ በምልአት ስለማይኖሩት ነበር፡፡ ስለዚህም በአበምኔት ሮቤርቶስ አማካይነት ሃያ አንድ መነኮሳን የአቡነ ቡሩክ ደንብን ሙሉ በሙሉ ለመኖር ወደ ሲቶ /Citeaux/ ጫካ በመሄድ ገዳም መሥርተው መኖር ጀመሩ፡፡ በኋላም በሞለዝም የነበሩ መነኮሳን ‹‹አበምኔታችን (ሮቤርቶስን ማለት ነው) ጥለውን ሄዱ›› በማለት ለቅድስት መንበር አቤቱታ ስላቀረቡ አበምኔት ሮቤርቶስ ወደ ቀድሞ ገዳማቸው ወደ ሞለዝም ተመለሱ፡፡ በቦታቸው በሲቶ የሚኖሩ መነኮሳን እስጢፋኖስን አበምኔት አድርገው መረጧቸው፡፡

እንግዲህ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ነበር ቅዱስ በርናርዶስ በመዘጋት ላይ ወደ ነበረው ገዳም ያመራው፡፡ ወደ ሲቶ ገዳም የመጣውም ብቻውን ሳይሆን ሰላሳ ወጣቶችን በማስከተል ጭምር ነበር፡፡ ይህ ለመነኮሳኑ እግዚአብሔር የያዙት መንገድ ትክክል መሆኑን የገለጸበት ተአምርም ጭምር አድርገው ነው የተቀበሉት፡፡ የቅዱስ በርናርዶና የወጣቶቹ አስገራሚ የጥሪ ሂደት እንደሚከተለው ነው፡፡

 የቅዱስ በርናርዶስ የምንኩስና ሕይወት አጀማመር

 በቅዱስ መጽሐፍ ኢየሱስ እርሱን በምልአት መከተል ለሚፈልጉት እንዲህ ይላል፡- ‹‹… ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል፡፡›› (ማቴ 19፡29) ቅዱስ በርናዶስ ግን ቤተሰብንና ጓዳኞችን ወደ አዲሱና ቀጥተኛ ወደ ሆነው የቅድስና መንገድ መመለስ እንደሚችል አሳየ፡፡ ለቅዱስ በርናርዶስ የለውጥ ሂደት የቤተሰብ ጉዳይ ነበርና ነው፡፡ ቅዱስ በርናርዶስ የምንኩስና ሕይወት ይህንን እውነታ ያሳያል፡፡ ቅዱስ በርናርዶስ ወደ ሲቶ /Citeaux/ ገዳም ለመግባት በብርቱ ይፈልግ ነበር፡፡ ይህንን ፍላጎቱን እውን ያደረገው ወንድሞቹንና ጓደኞቹንም በማስከተል ጭምር ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ የአንድ ቀን የሥራ ውጤት እንጂ የብዙ ጊዜ ሂደት አልነበረም፡፡ መጀመሪያ እርሱ ራሱ ምንኩስናዊ ሕይወትን ለመኖር ወሰነ፡፡ ከዚያ ሌሎችን ማለትም ወንድሞቹን፣ የቅርብ ዘመዶቹን እና ጓደኞችን አብረውት ገዳም እንዲገቡ ማሳመን ጀመረ፡፡ እናም እነዚህ ሰዎች ቁጭ ብለው በቤተሰቦቻቸው ንብረት ዙሪያና በሌሎች ነገሮች ከመከሩ በኋላ ለትልቁ የሕይወት ጉዞ እራሳቸውን አዘጋጁ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ቅዱስ በርናርዶስ፣ ወንድሞቹና ጓደኞቹ የሲቶን በር ያንኳኩት (ደጅ የጠኑት)፡፡ በወቅቱ የነበሩት አበምኔትም (አባቴ እስጢፋኖስም) በእነዚህ ባልተጠበቀ ሁኔታ አንድ ላይ በገቡት ወጣቶች ምንም አልተቸገሩም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ወጣቶች ገዳም ከመግባታቸው በፊት እራሳቸውን በምንኩስናዊ ሕይወት ለመኖር አሳምነውና ተዘጋጅተው ሰለ ነበረ ነው፡፡ በገዳም ውስጥም የወንድማማችነትና የጓደኝነታቸው ሕብረት በምንኩስናዊ ሕይወት በመታነጽ ይበልጥኑን አጠነከሩት፡፡

የቅዱስ በርናርዶስ አስተዋጽኦ በቤተከርስቲያን

ብዙዎች ቅዱስ በርናርዶስ ‹‹የ12ኛው ክፍለ ዘመን ቁጥር አንድ ሰው››! ‹‹Man of the 12th century!››  ይሉታል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት በቤተክርስቲያን ውስጥ የተጫወተው ዘርፈ ብዙ ሚና ነው፡፡ ቅዱስ በርናርዶስ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አማካሪ (መካሪ) ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. 1146 እና 1147 በነበነረው 2ኛው የመስቀል ጦርነት ቅዱስ በርናርዶስ እየዞረ በመስበክ እንዲቀሰቅስ በቅድስት ቤተክርስቲያን በይፋ ተመርጦ አገልግሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በየወቅቱ ተነስተው የነበሩት መናፍቃንን እነ አብላርድ /Abelard/, ጀልበርት ዴላ ፖሬ /Gilbert dela Porree/,  እና የብሬሽያው አርኖልድን /Arnold of Brescia/ በመርታት ሃይማኖትን ጠብቋል፡፡ ቅዱስ በርናርዶስ እ.ኤ.አ. በ1130 ዓ.ም.  በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ  ሁለት ር.ሊ.ጳጳትን ማለትም ኢኖስንት ዳግማዊና አናክሌቱስ ዳግማዊ በአንድ ጊዜ በመመረጣቻው ምክንያት የተፈጠረውን ክፍፍል ለመፍታት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ ቅዱስ በርናርዶስ ምስጉንና ጠንካራ መነኩሴ ከመሆኑም ባሻገር ትልቅ ሰባኪና የነገረ መለኮት ምሁር ነበር፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስም ሊቅ ነበር፡፡

ቅዱስ በርናርዶስ የማርያም ዘማሪ

ቅዱስ በርናርዶስ ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ጥልቅ ፍቅር ነበረው፡፡ ሌሎች መነኮሳንም ይህንን ፍቅር እንዲያድርባቸው ይሰብካቸው ነበር፡፡ በእመቤታችን ስምም ብዙ ተአመራትን አድርጓል፡፡ በማርያም ዙሪያ የጻፋቸው መጽሐፍቶችና ስብከቶቹ ዛሬም ድረስ ለነገረ ማርያም /Marian Theology/ መመሪያዎች ናቸው፡፡ ‹‹በአደጋ ጊዜ፣ በጥርጣሬ ጊዜ፣ በአስቸጋሪ ወቅት ማርያምን አስቧት እርሷንም ጥሩ፡፡ ስሟ ከአፋችሁ አይለይ፣ የእርሷን እግር ተከተሉ፡፡ እርሷ ትምራችሁ ከመንገድ አትወጡምና … እጃችሁን ከያዘች በፍጹም አትወድቁም፡፡ በእርሷ ጥበቃ ምንም የምትፈሩት ነገር አይኖርም፡፡ እርሷ ከፊት ፊታችሁ ከሄደች በፍጹም አትደክሙም፡፡ በእርሷ ፊት ሞገስን ካገኛችሁ ወደ ግባችሁ ትደርሳላችሁ›› በማለት ይሰብክ ነበር ቅዱስ በርናርዶስ፡፡ የቅዱስ በርናርዶስ ሕይወት በቤተክርስቲያን ውስጥ ዛሬ ላይ ሆነን ማሰብ ከምንችለው በላይ ነው፡፡ ጥረቶቹም እጅግ ብዙ ፍሬ አፈሩ፡፡ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በብዙ ጸሎትና አስተንትኖ ምክንያት ነው፡፡ ቅዱስ በርናርዶስ በተወለደ በ63 ዓመቱ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 20/1153 ዓ.ም. በሰላም አረፈ፡፡ ቅዱስ በርናርዶስ ምን ያህል ቤተክርስቲያንን እንዳሳደገና ሕይወቱን በቅንነት እንዳኖረ ከሚያሳዩ ነገሮች አንዱ በሞተ በ21 ዓመቱ 1174 ዓ.ም. ቅዱስ ሲባል እ.ኤ.አ. በ1830 ዓ.ም.  ደግሞ በይፋ የቤተክርስቲያ ዶክተር /Doctor of the Church/ ማለትም የቤተክርስቲያን ዋና አስተማሪ መባሉ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች በጣም ብዙ ዓመታት የሚፈጁ ናቸውና ነው፡፡

 ቅዱስ በርናርዶስ በመኃልየ መኃልየ ዘሰለሞን ላይ ካደረገው ስብከት የተወሰደ ንባብ

 ‹‹ፍቅር ስላለኝና ስለምወድ እወዳለሁ››

 ፍቅር ራሱን የቻለ ነው፤ ራሱንም እርሱን የሚመለከቱትን ሁሉ ያስደስታል፡፡ ፍቅር የራሱ ክፍያና ሽልማት ነው፡፡ ፍቅር ውጫዊ የሆነ ምክንያት ወይም ውጤት አያስፈልገውም፡፡ ፍቅር የፍቅር ውጤት ነው፤ በተፈጥሮ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለምወድ እወዳለሁ፤ ለመውደድም እወዳለሁ፡፡ ፍቅር ዋጋማ የሚሆነው ወደ መነሻ ምንጩ ሲመለስ፣ መነሻውን ሲያማክርና ወደ ምንጩ ተመልሶ ሲፈስስ ነው፡፡ ዘወትር ከዚያ ማቆሚያ ከሌለው ምንጭ መቅዳት አለበት፡፡ ፍጡር ብቁ ባልሆነ መንገዱ ፈጣሪውን የሚወድበትና ወሮታውን ሁሉ የሚከፍልበት የነፍስ እንቅስቃሴ፣ ስሜትና መውደድ ፍቅር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሲወድ፣ እኛም እንድንወደው ይፈልጋል፡፡ ለመወደድ እንጂ ለሌላ ምክንያት እንደማይወድ የተረጋገጠ ነው፡፡ የሚወዱት በዚህ ፍቅር ደስተኞች እንደሆኑ ያውቃል፡፡

የሙሽራው ፍቅር የሙሽሪቷን ፍቅርና ታማኝነት ብቻ ይፈልጋል፣ ይህ ሙሽራ ራሱ ፍቅር ነው፡፡ የምትወደደው መልሳ ልትወድ ይገባታል፡፡ የፍቅር ሙሽሪት እንዴት ልትወድ አትችልም? ፍቅር ራሱ እንዴት ሊወደድ አይችልም?

ሙሽሪቷ፣ ለሌሎች ያላትን ፍቅር በሙሉ በተገቢ ሁኔታ በመካድ፣ አንዱን ብቻ ለመውደድ ቃል ከገባች መልሳ በመውደድ ፍቅርን መመለስ ትችላለች፡፡ በፍቅር መላ አካሏን ስትሰጥ ይህ ጥረቷ የፍቅር ምንጭ ከሆነው ከሚፈሰው ማቆሚያ ከሌለው ፍቅር ጋር የሚወዳደረው እንዴት ነው? በርግጥ ፍቅር ከአፍቃሪው፣ ቃል ከተፈጠረው ነፍስ፣ ሙሽራው ከሙሽሪቷ፣ ፈጣሪ ከፍጡሩ የበለጡ ናቸው፡፡ የነዚህን መበላለጥ ለማሳየት የተጠማ ሰውን ጥሙን ከሚያረካለት ምንጭ ጋር ማወዳደር ይበቃል፡፡

በጣፋጭነት ከማር ጋር፣ በየዋህነት ከበግ ጋር፣ በንጣት ከሙሽራ አበባ ጋር፣ በድምቀት ከፀሐይ ጋር፣ በፍቅር ከፍቅር ጋር መወዳደር ስለማይቻል የሙሽሪቷ ፍቅር፣ እዚህ ምድር ያለው ፍጥረት ናፍቆት፣ የአፍቃሪው ስሜት፣ የአማኙ እምነት፣ ሊጠፋና ከንቱ ሊሆን ይችላልን? ይህ ፈጽሞ አይሆንም፡፡ ምንም እንኳን የፍጡሩ ተፈጥሮ ሆኖ ከፈጣሪው ባነሰ ደረጃ ቢወድም ቅሉ በሙሉ ኃይሉ የሚወድ ከሆነ ምንም ነገር አያጣም፡፡ ስለዚህ እንዲህ አድርጋ የምትወድ በርግጥ ሙሽራ ሆናለች፣ ምክንያቱም እንዲህ ያለ ፍቅር እያቀረበች በዚሁ መጠን ትወደዳለችና፡፡ በነዚሁ ሁለት ሰዎቸ ስምምነት የጋብቻ ሙሉነትና ፍጹምነት ይገኛል፡፡ ቃል ለነፍስ ያለው ፍቅር ነፍስ ለርሱ ካላት ፍቅር እንደሚበልጥና እንደሚቀድም ማን ይጠራጠራል? ሙሽሪት የተባለችው ቤተ/ያን ናት፤ ሙሽራው የተባለው በደሙ የዋጃት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው፡፡

የቅዱስ በርናርዶስ በረከቱና አማላጅነቱ አይለየን፡፡ አሜን!

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት