እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ቅድስት ቴሬዛ ቤኔዲክታ ዘመስቀል

ቅድስት ቴሬዛ ቤኔዲክታ ዘመስቀል

St. Teresa Benedicta of the Crossኤዲት ስቴይን ከአይሁዳውያን ወላጆቿ በ1883 ዓ.ም. በብሬስላው ጀርመን ውስጥ ተወለደች። አሥራ አንደኛ ልጅ ነበረች፤ በተወለደችበትም ወቅት ቤተሰቧ የአይሁድ <<የሥርየት ቀን በዓል>> ያከብሩ ነበር። ይህ ክስተት ወደፊት ከሚሆነው ሕይወት ታሪኳ ጋር ሲያያዝ ባለ ትልቅ ዓላማ ሴት መሆኗን ትርጉም ይሰጠዋል።

አስተማሪዋ ያንፀባርቅ በነበረው የድፍን አይሁዳውያን ጥላቻ ምክንያት ገና በ14 ዓመቷ በእግዚአብሔር ማመን የሚባለውን ነገር እንደተወችው እንዲህ ስትል ጽፋ ነበር <<የሆነኝ ብዬ በፈቃደኝነት መጸለይን አቆምኩ>>። ከዚህም በኋላ ለዓመታት እምነት የለሽ ሆና ተመላለሰች። ሆኖም ግን ስል አእምሮዋ እውነትን ከመፈለግ ባተሌ ሆኖም አያውቅም ነበር። ይህን እውነት ክርስቲያን ከሆነች በኋላ ስትገልጸው <<እውነትን ፍለጋ እንከራተት የነበረው በራሱ ጸሎት ነበር>> ብላለች።

በዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዓመታት ተማሪ በነበረችበት ጊዜም በወቅቱ ይፈለጉ ለነበሩት የሴቶች መብት ብዙ ትጥር ነበር ኋላ ላይ ግን በነዚህ መሰል እንቅስቃሴዎች ሁሉ የመሳተፍ ፍላጎቷ እንደጠፋና ወደ ሌላ አቅጣጫ መቀየሩን ጽፋለች።

በ1906 ዓ.ም. ኤዲት ጎበዝ የፍልስፍና ተማሪ በመሆኗ በታወቀው ፈላስፋ ኤድመንድ ኸሰርል ሥር ለመማር ከብሬስላው ወደ ጎትንገን ዩኒቨርስቲ አመራች። በዚያም የኸሰርል ብቸኛ ሴት ተማሪ ሆነች፤ ግን ልዩ የሚያደጋት ይህ ሳይሆን ጎበዝና ግንባር ቀደም ተማሪ መሆኗም ነው። በስተመጨርሻ ላይ የዶክትሬት መመረቂያ ሥራዋን የተቆጣጠረላት መምህሯም እሱ ነበር። ትኩረቷን ወደ ካቶሊክነት እንድታደርግ ያገዛትን ፈላስፋ ማክስ ሼለርን ያገኘችው በነዚህ ዓመታት ነበር።

የነርስነት ኮርስም አድርጋ ስለነበር የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ሲጀምር በአውስትሪያ ውስጥ ይገኝ ወደ ነበረ አንድ ሆስፒታል ሄደች። በዚያም የብዙ ወጣቶች ሕይወት ስታልፍ ታስተውል ነበር።

በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሳለች አንድ ቀን በፍራንክፈርት ውስጥ ወደሚገኝ አንድ የካቶሊክ ካቴድራል ስትሄድ ውስጧን የነካ አንድ ክስተት አስተዋለች። አንዲት ሴት የገበያ ዘንቢሏን ይዛ በዚያ ካቴድራል ውስጥ ገብታ ተንበርክካ አጭር ጸሎት አድርጋ ስትወጣ ኤዲት እዚህ ምን ወይም ማን አለ የሚል ዓይነት ሃሳብ በውስጧ ተነሣ… እንዲህም ገልጸዋለች <<ይህ ነገር ለኔ ፍጹም አዲስ ነው፤ ሰዎች ወደ ምኩራቦችና ወደ ፕሮቴስታንቶች ቤተ ክርስቲያናት ሲሄዱ አውቃለሁ ነገር ግን በዚህ ካቴድራል ያየሁት ይህን ነው:- አንዲት ሴት ልክ ቅርብ ከሆነ ሰው ጋር እንደሚወያይ ሰው ሁሉ ከግርግር ገበያ በቀጥታ ወደዚህ ባዶ ቤተ ክርስቲያን መጣች፤ ይህ መቼም የማልረሳው ነገር ነበር…>>።

ሌላም ልቧን የነካው ነገር አለ። ኤዲት የኸሰርል ረዳት ፕሮፌሰር የነበረው ሰውና ባለቤቱ ወዳጅ ነበረች። ይህ ሰው በ1910 ዓ.ም. ሲገደል ኤዲት ባለቤቱን መጎብኘት ነበርባት ሆኖም ግን ይህን በመሰለ ኀዘን ምን እላታለሁ በማለት እየተጨነቀች ነበር። በደረሰች ጊዜ ግን ሁኔታው እንዲህ አልነበረም ይህች ባሏ የተገደለባት ክርስቲያን ኀዘንተኛ በጣም የእምነት ሴት ሆና በርትታ አገኘቻት፤ ኤዲት እንዲህ ትገልጸዋለች <<መስቀልና መለኮታዊ ጸጋ ለሚቀበሉት ኃይልን እንደሚሰጥ ለመጀመሪያ ያየሁበት ጊዜ ነው። እምነተ ቢስ መሆኔ በዚህ ክስተት አከተመ፤ ክርስቶስ በመስቀሉ ምሥጢር በኔ ላይ ማብራቱን ጀመረ>>።

ኤዲት በጽሑፏ ስለ ሕይወቷ <<እኔ ፍጹም አስቤ የማላውቃቸው ነገሮች ሁሉ በእግዚአብሔር እቅድ ነበሩ፤ ሕይወቴ በሙሉ በጣም ዝርዝር በሆኑ ሁኔታዎች ሁሉ ሳይቀር በእግዚአብሔር መለኮታዊ እቅድ ውስጥ የተነደፉና ከርሱ ምንም በማይሰወር ሁኔታ የተከናወኑ እንደሆኑ በእሱ አሠራርም አጋጣሚ የሚባል ነገር እንደሌለ በጣም ማመን ችያለሁ>> ብላለች።

ኤዲት ወደ ብሬስላው ከተመለሰች በኋላ የሥነ ልቦናን ፍልስፍናዊ መሠረቶች (phiolosophical foundation of psychology) የሚገልጹ ሥራዎችን መጻፍ ጀመረች። ጎን ለጎንም አዲስ ኪዳን፣ የኪርከጋርድን ሥራዎችና የቅዱስ ኢግናጽዮስ ዘሎዮላውን Spiritual Exercises ታነብ ነበር። ወዲያውም ሰው እነዚህን መሰል ጽሑፎች በማንበብ ብቻ ማለፍ የለበትም በሕይወቱ መኖር አለበት ብላ ደመደመች።

በ1914 በአንድ የበጋ ምሽት የቅድስት ተሬዛ ዘአቪላን የሕይወት ታሪክ (Autobiography) መጽሐፍ ለማንበብ አነሣች፤ በጣም ስለሳባትም ሌሊቱን ሙሉ አነበበችው። አንብባ ስትጨርስም እንዲህ ስትል ጻፈች <<ለራሴ እንዲህ አልኩኝ:- እውነቱ ይህ ነው!>>። ይህ እንግዲህ ካለማመን በክርስቶስ ወደማመን ያደረገችው መዳከር ድምዳሜ ሆነላት። ስለዚህም ምሥጢረ ጥምቀትን ለመቀበል ጠየቀች እናም በ1914 ዓ.ም. አዲስ ዓመት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተጠመቀች።

ቅድስት ተሬዛ ቤኔዲክታ ዘመስቀል ሕይወቷ ከመለወጡ በፊትና ኋላም ለጥቂት ጊዜ መመንኮስ ማለት ምድራዊ ነገሮችን ሁሉ መተውና አእምሮን ወደ መለኮታዊ ነገር ብቻ ማተኮር አድርጋ ታስብ ነበር። ነገር ግን ቀስ በቀስ ይህ እይታዋ ተቀየረ። <<በዚች ዓለም ከኛ ሌላም ነገር እንደሚጠበቅብን አወቅክሁ፤ እንደውም አንድ ሰው ይበልጥ ወደ እግዚአብሔር በቀረበ መጠን ይበልጥ ከራሱ መውጣት አለበት፤ ማለትም መለኮታዊውን ሕይወት ወደ ዓለም ማድረስ አለበት>>።

EdithStein2ለተከታዮቹ ጥቂት ዓመታት ካርዲናል ኒውማን ካቶሊክ ከመሆናቸው በፊት የጻፉትን ግለ ታሪክ (diary)፣ አንዳንድ ደብዳቤዎችና የቅዱስ ቶማስ ዘአኩይናስን አንዳንድ ሥራዎች በመተርጎም በፍልስፍና ጥናቷ በጣም ቀጠለችበት።

ክርስቲያን ከሆነች ስምንት ዓመታት በኋላ ነበር መምህሯንና ፈላስፋውን ኸርሰልን አግኝታ ስለ እምነቷ ያጫወተችውና እሱም ክርስቲያን ቢሆን ደስ እንደሚላት የገለጸችለት። ከዚህ በኋላ እንዲህ ብላ ጽፋ ነበር <<ሰዎች ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተፅእኖ መፍጠር ያለመቻል ድክመቴና ችሎታ ቢስ መሆኔ ሁል ጊዜ ይታወቀኛል፤ በዚህም እኔ ራሴ መሰዋት እንዳለብኝ ይበልጥ ይሰማኛል>>።

በ1924 ዓ.ም. ኮለኝ በሚገኘው የቀርሜሎሳውያን ገዳም በመግባት ተሬዛ ቤኔዲክታ ዘመስቀል በሚል ስመ ምንኩስና መጠራት ጀመረች። በ1925 ዓ.ም. በጀርመን ላይ ጨለማ ማንጃበብ ጀመረ። በዚህም ጊዜ <<በአይሁዳውያን/እስራኤላውያን ላይ ጨካኝ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ሰምቼ ነበር፤ አሁን ግን እግዚአብሔር ከባድ እጁን በሕዝቡ ላይ አድርጓል። የዚህ ሕዝብ እጣ ፈንታም የኔም ይሆናል>> በማለት የወገኖቿ ስቃይ የርሷም መሆኑን ገልጻ ነበር። ይህ አባባሏ ዝም ብሎ የሀገራዊነት ስሜት ወኔ ግፊት ብቻ ሳይሆን ክርስቶስ በግፍ ከሚሰቃይ ሕዝብ ጋር አብሮ እንደሚሰቃይ ተገንዝባ የርሱ ሕማም ተካፋይ ለመሆን ያደረገችው ትልቅ የጸጋ ውሳኔ ነው። ይህንንም ከቀጣይ ንግግሮቿ በግልጽ ማየት ይቻላል። በዚያው ዓመት ከገዳማቸው ኀላፊ ተገናኝታ ነበር፤ እንዲህም በማለት ስለ ሁኔታው ሃሳቧን ጠቆመቻቸው <<የክርስቶስ ስቃይ ብቻ እንጂ የሰው ጥረቶች ሊያግዙን አይችሉም። እኔም ስቃዩን መካፈል ምኞቴ ነው>>።

በኅዳር 1931 ዓ.ም. የናዚ ጸረ አይሁዳዊነት አቋም ለመላው ዓለም ግልጽ ሆነ። ምኩራቦችን ማቃጠልና አይሁዳውያንንም ማሰቃየት ተጀመረ።

 

በኮለኝ ያለው ገዳም ኀላፊ እህት ተሬዛ ቤኔዲክታን (ኤዲት) ከጀርመን ለማስወጣት ብዙ ጥረው ነበር። ተሳካና በ1931 ዓ.ም. ኤዲት አዲስ ዓመት ዋዜማ በኔዘርላንድ ወደሚገኝ ሌላ ገዳማቸው ድንበር በማቋረጥ ተሻገረች። በዚያው ዓመት በኔዘርላንድ ሳለች ይህን ጽፋ ነበር <<አሁንም ቢሆን እግዚአብሔር ለኔ ያዘጋጀውን ሞት የርሱ ቅዱስ ፈቃድ አድርጌ በፍጹም ታዛዥነትና ደስታ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ። ፤ የእርሱ ሕዝብ በጌታ ያምኑ ዘንድ፣ የርሱም መንግሥት በክብር ይመጣ ዘንድና ይህም ለጀርመን ሕዝብ ደኅንነት ለዓለም ሰላምን በመመኘት ጌታ ሕይወቴንና ሞቴን እንዲቀብለኝ እጸልያለሁ>>።

edithstein01በ1933 ለአንድ የገዳሟ አባል መነኮሳይት <<አንድ ሰው ሙሉ የመስቀል እውቀት ሊኖረው የሚችለው ሙሉ ለሙሉ መስቀልን በሕይወቱ ሲለማመደው ብቻ ነው። ይህንንም ስለማምን ከመጀመሪያው ጀምሬ በሙሉ ልቤ ብቸኛ ተስፋችን መስቀል ሆይ! ሰላም! እላለሁ>> በማለት ስቃይዋን ሁሉ በክርስቶስ መስቀል በኩል ትቀበለው እንደነበር ገልጻለች።እንዲሁም በ1934 የቅዱስ ዮሐንስ ዘመስቀል 400ኛ ልደት ሲዘከር የርሱ ሕይወትና ሥራዎቹ ላይ ጥናት በማድረግ The Science of the Cross የሚል ሥራዋን ጽፋ አቀረበች።

የአይሁዳውያንን ያለምክንያት በጅምላ መጨፍጨፍና መባረር በመቃወም የኔዘርላንድ ካቶሊክ ጳጳሳት ለጻፉት የተቃውሞ መልእክት እንደአጸፌታ ኤዲት ስቴይንን ከሌሎች መንኮሳይት እህቶቿ ጋር በቤተ ጸሎት ሳለች በናዚ ምሥጢራዊ የደኅንነት ፖሊሶች (ጌስታፖ) ተይዛ ሐምሌ 26 1934 ዓ.ም. ወደ እስር ቤት ተወሰደች። <<ነይ! ለሕዝባችን እንሄዳለን>> የሚሉት የኤዲት የመጨረሻ ቃላት እዚያው ኔዘርላንድ ውስጥ ለነበረች ካቶሊክ ሆና ኋላም ለመነኮሰችው ለእህቷ ሮዛ ነበር።

ነሐሴ 3 1934 ዓ.ም. በአውሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ ኤዲትና እህቷ ከሌሎች ብዙ ወገኖቻቸው ጋር በመሆን በጋዝ እንዲቃጠሉና እንዲሞቱ ተደረገ።

ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሚያዝያ 24 1979 ዓ.ም. ጀርመንን ሲጎበኙ በኮለኝ ከተማ << በናዚ ጭፍጨፋ ወቅት ኤዲት የእስራኤል ልጅ ለተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ በመሆን እንደ አይሁዳዊነቷም ለሕዝቧ በፍቅርና ታማኝነት እስከመጨረሻ የጸናች >> ብፅዕናዋን ማለትም ለመላዪቱ ቤተ ክርስቲያን አብነት የምትሆን መሆኗን በማለት በይፋ አወጁ። በ1990 ዓ.ም. ደግሞ ቅድስናዋ ታውጆ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ነሐሴ 3 ቀን ታከብራታለች።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት