እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ካቶሊካዊነት

በልጅነታችን በአንድ ወቅት እንደተነገረን ወይም በቤተሰብም ይሁን በሆነ አጋጣሚ ብለን በምንተረጉመው፤ ነገር ግን እውነቱ በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንነውን ክርስቲያንነት እንደ ካቶሊክነታችን መኖር ካለብን ቆም ብለን ካቶሊክነት ለኛ ምን ትርጉም አለው ብለን መጠየቅ የግድ ነው፤ ምክንያቱም ወንጌልን ከጌታዋ ተቀብላ የሰጠችንን ቤተ ክርስቲያናችንን ለይቶ ማወቅ ራሷ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ እውቀት እንደሚያደርሰን እሙን ነው። እንደው በድፍኑ ሁሉም አንድ ነው የሚል የዘመኑ አባዜን በዋዛ ወስደን ማስተጋባት ትተን ሁሉም ያው ነው ማለትና ሁላዊነት ልዩነት ስላለው ማንነታችንን ማወቁ ተገቢ ነገር ነው።

ካቶሊክ የሚለው ስም ሁነኛ ትርጉሙ ጠቅላላ፣ ሁላዊነት፣ ሁሉን አቀፍ... የሚል ጽንሰ ሃሳብ የሚያስተላልፍ ሲሆን መሠረቱም ከግሪክ ካቶሊኮስ የሚል ቃል የተወረሰ ነው። ቤተ ክርስቲያን በጥንታዊው ዓለም በኃያልነት ተንሰራፍቶ በነበረው የሮማ ግዛት ሙሉ ለሙሉ ተሰራጭታ ትገኝ ስለነበረ ካቶሊክ የሚል ስያሜን በዚያን ዘመን አገኘች። በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ለመጀመሪያ ጊዜ ካቶሊክ የሚለው ቅጽል ለቤተ ክርስቲያን ተሰጥቶ የምናገኘው በ110 ዓ.ም. ገደማ በቅዱስ ኢግናጽዮስ ዘአንጾኪያው ጽሑፍ ውስጥ ነው።

በክርስትና ታሪክ ውስጥ ካቶሊክ የሚለው ቃል የተለያዩ አጠቃቀሞች አሉት። ከነዚህም ውስጥ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል:-

1. በአቅራቢያ ወይም በአካባቢ ከምትገኘው የክርስቲያን ማኅበር ወይም ቤተ ክርስቲያን በተለየ ሁኔታ በሁሉ አካባቢ የምትገኘዋን ሁሉን አቀፍ ቤተ ክርስቲያንን ለማመልከት ሲሆን በዚህም አጠቃቀም የመላዪቱ ቤተ ክርስቲያንን እምነት ያመለክታል።

2. የሐሰት ትምህርትን አንግበው ይነሡ ከነበሩ መናፍቃን እና ከቤተ ክርስቲያን የተነጠሉ ቡድኖች (Schismatical) ለመለየት ሐቀኛ -  orthodox - ትምህርትን የያዘች ቤተ ክርስቲያንን ለማመልከት፤

3. በታሪክ ጸሐፊያን አገላለጽ ቤተ ክርስቲያን በ1054 ዓ.ም. በምሥራቅና በምዕራብ ሳትከፋፈል በፊት የነበረችውን አንዲት ቤተ ክርስቲያን ለመግለጽ ሲጠቀሙበት፤ ቤተ ክርስቲያን ግን ለሁለት ከተከፈለች በኋላ በምሥራቅ ያለችው ኦርቶዶክስ በምዕራቡ ደግሞ ካቶሊክ የሚለውን ስያሜ ይዘው ቀጥለዋል።

4. ከ16ኛው ክ.ዘ. ወዲህ ደግሞ የምዕራቧ ቤተ ክርስቲያን በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በስዊዘርላንድ... በተሐድሶ - Reformation - ዘመን በተለያየ ምክንያቶች ስትከፋፈል እነዚህ የተለያዩ ወገኖች የየራሳቸውን ስያሜ ሲያገኙ አሁንም ከነርሱ የተቀረችው ቤተ ክርስቲያን ካቶሊክ በሚለው ስያሜ ቀጠለች፤ ከዚህ እንቅስቃሴም በኋላ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ስያሜ በተወራራሽ መልኩ ቀጠለ። ምክያቱም እነዚህ የተለዩ ወገኖች ከጴጥሮስ ወንበር ማለትም በቫቲካን ከምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ኅብረት በመውጣት የየራሳቸውን አስተዳደር ስለጀመሩ ነው።

5. በአሁኑ ዘመናችን አጠቃቀም ደግሞ ካቶሊክ የሚለው ስያሜ ለሁለት ሺህ ዓመታት ቀጣይ የታሪክ፣ የእምነት፣ የመጽሐፍ ቅዱስና የትውፊት ሀብትን ይዛ የምትጓዝ ቤተ ክርስቲያንን ያመለክታል። ይህም ከክርስቶስ ልደት በኋላ 1600 ዓመታት እና ከዚያ በኋላ የተነሡ ከፕሮቴስታንቶች ልዩ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ያመለክታል

በ325 ዓ.ም. በኒቅያ በጊዜው የነበረችውን ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ያካተተ የመጀመሪያው ጉባዔ ሲካሄድ የተሰበሰቡት አባቶች የወሰኑት አንቀጸ ሃይማኖት ለመላዪቱ ቤተ ክርስቲያን የእምነት መገለጫ ይሆን ዘንድ ወሰኑ። ይህም በአጭር መልኩ ዘወትር በቅዳሴ ጊዜ የምንደግመው ጸሎተ ሃይማኖት ነው።

ዛሬም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊ እምነትና እይታ መለያዎቿ ናቸው። ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሃገራዊት ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፤ ፖለቲካዊም ሆነ ሀገራዊ ማንነትንና ልዩነትን ወደ ጎን በማድረግ ዘወትር ቅድሚያ ለሰው ልጅ እንደ ሰውነቱ ትሰጣለች። ይህን ሐቅ እውን ለማድረግ በዘር፣ በፖለቲካ ወይም በሃይማኖትና መሰል ነገሮች የሰው ልጅን ክብርና ስብእና የማያስከብሩ ሁኔታዎችን፣ የፍትሕና የሰላም መረገጥን...ወዘተ እንደታዛቢ አትመለከትም። በቃሏና በጸሎቷ አጽንዖት ሰጥታ የሰው ልጅን ሕይወት ተቀዳሚነት ታውጃለች።

የቤተ ክርስቲያናችን ሁላዊነት ታሪክ ያወረሳት ክስተት ሳይሆን ክርስቶስ የተሰዋበትና ያወረሳት የፍቅር እውነተኛ መገለጫ ልዩ ተፈጥሮዋ ነው። ሰው ራሱ እንዲመቸው በሠራቸው ድንበርና ወሰን የክርስቶስን ፍቅርና የማዳን ኃይል መወሰን ክርስቲያናዊ ትምህርት ሊሆን አይችልም። ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በጥሩ ቃላት እንደገለጹት <<ወገንተኝነት/ዘረኝነት ክርስቶስን ያቆስለዋል>>።

ካቶሊካዊነት ማለት ዓለም አቀፋዊነት መሆኑን ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ትመሰክራለች። በየትኛውም የዓለም ጫፍ ቢኬድ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን በሥርዓቷና በጸሎቷ፤ ያለምንም መሠረታዊ ለውጥ በቅዳሴና በምሥጢራቷ ትገኛለች።

ከመረጃ መለዋወጫና ከመጓጓዣ ዘዴዎች እድገት አኳያ ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበችና መንደር እየሆነች በመጣችበት ሰዓት ለክርስቲያንነት ብሎም ለካቶሊካዊነት የወንድማማችነትን ስሜት ለማሳደግ ይበልጥ ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ቢመስልም ቅሉ በዘመናችን ያለው የአስተሳሰብ ጫና ራስ ወዳድነት ዘወትር እንዲያድግ የሚያግዝና ግላዊነት ላይ ያተኮረ ስለሆነ እንደ ስማችን ካቶሊክ ክርስቲያን ማለትም የክርስቶስና የሁሉም ሆነን መገኘት ዛሬም የቤተ ክርስቲያን ጥሪ ነው።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት