ከቅዱስ ዮሴፍ ምን እንማራለን?
- Category: ቅዱስ ዮሴፍ
- Published: Tuesday, 02 November 2010 15:01
- Written by Super User
- Hits: 23550
- 02 Nov
ከቅዱስ ዮሴፍ ምን እንማራለን?
ስለ ቅዱስ ዮሴፍ በምናነሳበት ጊዜ ስሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ጋር ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡
አበው ጸሐፍት ይህን ምንጭ በመጠቀም ስለቅዱስ ዮሴፍ ብዙ ጽፈዋል፣ ብዙ ብለዋል፡፡ እና በዚህ አጭር ጽሑፌ የአበውን አባባል ለመዘርዘር ባልሞክርም፤ ትልቁ የሕይወት መዝገብ የሆነው ቅዱስ መጽሐፋችን ስለቅዱስ ዮሴፍ ደግነት፣ ትጋት… ወዘተ ያስቀመጠውን በመጠኑም ቢሆን ለመነካካት እሞክራለሁ፡፡
ስለ ደግነቱ፡ ማቴ. 1፡18 ላይ በአዲስ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ በተገኘች ጊዜ፣ ዮሴፍ “ደግ” ስለነበር ሊያጋለጣት አልፈለገም ይላል፡፡ በሌላ ትርጉም ደግሞ “ጻድቅ” ስለነበር ይለዋል፡፡ ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠው ስያሜ በከንተ ያገኘው አይደለም፡፡ ከባህላቸውና ከነበረው በጊዜ ሁኔታ ሲታይ ትልቅ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ነገር ነበር፡፡ እጮኛው በድብቅ ፀንሳ ስለተገኘች አጋልጦ በእስራኤላውያን ሕግ መሠረት መወገር ነበረባት፡፡ ነገር ግን ይህ እንዳይደረስባት ብሎ ቅዱስ ዮሴፍ በስውር ሊተዋት አሰበ ይላል የእግዚአብሔር ቃል፡፡
ስለ ታማኝነቱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ እንደ ምናገኘው ቅዱስ ዮሴፍ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን መልአክት ሁሉ በእምነት ፈጽሟል፤ የታዘዘውንም ሁሉ ያለምንም መጠራጠር አድርጓል፡፡ በዚህም ታማኝነቱና ታዛዥነቱን አስመስክሯል፡፡ ለምሳሌ ያህል እመቤታችን ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በፀነሰች ጊዜ ቅዱስ ዮሴፍ በስውር ሊተዋት አሰበ፡፡ እጮኛህን ውሰዳት በመንፈሰ ቅዱስ ነው የፀነሰችው አለው፡፡ ዮሴፍም እንደተባለው አደረገ ይለናል ቅዱስ መጽሐፍ፡፡ ታዲያ እኮ ይህ ነገር በቅዱስ ዮሴፍ ዘመን አምኖ ለመቀበል ትልቅ መስዋእትነት የሚጠይቅ ነገር ነበር፡፡ ምክንያቱም የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በግልጽ የታወቀበት የታመነበት ዘመን አልነበረም፤ እዚህ ላይ መንፈስ ቅዱስ አይሠራም ነበር ማለት ሳይሆን፣ በግልጽ በሰዎች ዘንድ እንደ አንድ አምላክ አያውቁትም ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ ግን ከፍጥረት ዓለም ጀምሮ በነቢያት፣ በነገሥታት በአበውና በጻድቃን ሲሰራ ነበር አሁንም እየሠራ ነው ወደፊትም ይሠራል፡፡ እና ቅዱስ ዮሴፍም በዚህ ኃይልና ሕይወት ሰጭ በሆነው መንፈስ ተመርቶ ለማመን አስቸጋሪ የነበረውን ነገር አምኖ ተቀበለ በዚህም ምክንያት የእምነት በአባት ሲባል ስሙ አይበዛበትም፡፡
ስለ ትጋቱ፡ መጽሐፍ ቅዱስ በመንደሩ የታወቀ ጠራቢ፣ ትጉህ ሠራተኛ እንደነበር ይነግረናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም የእንጨት ጠራቢው ልጅ እያሉ የሚሠራውን ድንቅ ታምራትን ሁሉ ያጣጥሉበት ነበር፡፡ እና ቅዱስ ዮሴፍ ይህን ዝቅተኛና የተናቀ ሥራ በትሕትና ይሠራ ነበር፡፡ ከቤተሰቦቹም ጋር በሰላምና በመግባባት ይኖር እንደነበርና በስደትም ሆነ በሰላም ጊዜ ቅዱስ ዮሴፍ ከኢየሱስና ከማርያም እንዳልተለየ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ የእግዚአብሔር መልእክትም ለቅዱሰ ዮሴፍ ነበር በሕልም የሚነገረው፤ እርሱም ለቤተሰቡ ደኀንነት የተላለፈውን መልእክት ምንም ሳይዘገይ በተግባር ያውለው ነበር፡፡ በዚህም መልካም የቤተሰብ አባልነቱን አስመስክሯል፡፡
ለምሳሌ፡ ሕፃኑ ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ ከሄሮድስ ግድያ ለማስመለጥ ወደ ግብጽ አገር ሽሽ በተባለ ጊዜ ምንም ሳያመነታ ወደ ማያውቀው አገር ተነሥቶ ሄደ፡፡ ሄሮድስ ከሞተ በኋላም የእግዚአብሔር መልአክ ባዘዘው መሠረት ከስደት ሕይወት ወደ ትውልድ አገሩ ተመለሰ፡፡ እና ይህ ሁሉ ቅዱሰ ዮሴፍ ምን ያህል ታዛዥነትና እምነት እንደነበረው ያሳያል፡፡ ዛሬም እኛ ባለንበት ዘመን እንደ ቅዱስ ዮሴፍ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተን አምነን ታዘን ብንፈጽመው ምን ያህል ፀጋና በረከት ባገኘን ነበር ነገር ግን እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ቃል እያጣመመ ደስ እንደው እየተረጐመ የአንድነት ሳይሆን የመለያየት፣ የፍቅር ሳይሆን የጥላቻ ምንጭ አድርጐታል፡፡ በመሰረቱ የእግዚአብሔር ቃል ለሁከትና ለመለያየት በፍጽም የማይሆን የማይመች ቃል ነው፡፡ በአንፃሩ ግን የእግዚአብሔር ቃል የፍቅር፣ የሰላም፣ የደስታ፣ የደግነት፣ የበጐነት፣ የታማኝነት… ወዘተ ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ እና ከኛ የሚጠበቀው እንደ ቅዱስ ዮሴፍ በታማኝነትና በእምነት ለእግዚአብሔር ቃል መገዛት ነው፡፡ ትህትናን በህይወታችን እንድትነግስ መፍቀድ ነው፡፡ ትዕቢት ባለበት ምንም መልካም ነገር የለም፤ ከእግዚአብሔር የራቅነው ከመጀመሪያ ጀምሮ በትዕቢት ነው፡፡ አዳምና ሄዋን በትዕቢት የተሰጣቸውን ፀጋ አጠፋ፡፡ ለራሳቸውና ለሰው ዘር በሙሉ ቅጣትን አመጡ፡፡ በአንፃሩ በትህትና የጥላቻ የሞት ቅጣት ተደመሰሰ፤ በእመቤታችን ድንግል ማርያም እና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም ትህትና ደህንነታችን ተመሰረተ፡፡ ቅዱስ ዮሴፍም የዚህ ትህትና ተካፋይ ነው በናዝሬት ይኖሩ የነበሩት ድሀና ትሁት ቤተሰብ መሪያቸውና የቤቱ አባት ቅዱስ ዮሴፍ ነበር፡፡ ከእግዚአብሔር የሚተላለፈው መልእክት ሁሉ ተቀባይ እርሱ ነበር፡፡ በዚህም ታማኝና ታዛዥ የቤተሰብ መሪ መሆኑ በእግዚአብሔር ተመስክሮለታል፡፡ ታዲያ እኛ ከቅዱስ ዮሴፍ የምንማረው ነገር ካለ በተጠራንበት ጥሪ ታማኞችና ታዛዥች ሆነን መልካመ ፍሬ ለማፍራት መጣር ይሆናል፡፡ ቅዱስ ዮሴፍ በጌታ ምንጭ በቅድስት ቤተሰብ መሪ ሆነ፣ እኛም ዛሬ እያንዳንዳችን በጌታ ምንጭ በጋብቻ ሆነ በድንግልናዊ ህይወት ለምንገባበት መንገድ ታማኞች እና የተቀበልነውን ተልእኮ፣ የገባነውን ቃልኪዳን በተገቢው ሁኔታ ለመወጣት መጣር ይጠበቅብናል፡፡
ጌታ ደግሞ ማረሻና የሚታረስ ቦታ ሳይሰጥ እረሱ አይለንም፡፡ ለቅዱስ ዮሴፍም ኃይልና ጸጋውን ሳይሰጠው የቤተሰቡ ጠባቂ አድርጐ አልሾመውም፡፡ ለኛም ዛሬ ጸጋውንና በረከቱን ሳያፈስልን መስቀሉን ተሸክመን እንድንከተለው አይጠራንምና የተሰጠንን ጸጋ በተገቢው መንገድ እንድንጠቀምበት መንፈስ ቅዱስ አእምሮአችንና ልቦናችንን ያብራልን፡፡
በቅዱስ ዮሴፍ አማላጅነት ለሀገራችንና ለዓለም ሁሉ ጌታ ሰላሙን ይስጠን፡፡ አሜን፡፡
የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን፡፡
ምንጭ፡ መልካም ዜና መጽሔት 1991 ዓ.ም
አባ ወልደ ገብርኤል /ባዘዘው/ ግዛው - ሲታዊ