እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

መግነጢሳዊው ቅዱስ (ቅ. በርናርዶስ)

ቅዱስ በርናርዶስወጣት በርናርዶስ ተሸሊን በ22 ዓመት ዕድሜው ማለት በ1112 ዓ.ም. ወደ ገዳመ ሲቶ ገባ፣ ከሦስት ዓመት በኋላም አበምኔት ተሾሞ አዲስ ገዳም እንዲመሠርት ወደ ክለርቮ ተላከ፡ ወጣቱ በርናርዶስ የንግግር፣ የስብከት እንዲሁም የመምራት የተለየ ስጦታና ችሎታ የነበረው ብዙዎችን ይማርክና ይስብ የነበር መግነጢሳዊ ስብእናን የተላበሰ ነበር፡፡ ከመንፈሳዊ ሕይወት ምስክርነቱ የተነሣም ብዙዎች እሱን መከተል ጀመሩ፡፡ በነበረው የተለየ ስጦታና ችሎታ፣ እንዲሁም በንግግሩ ጣፋጭነት ‹‹ከአፉ የማር ወለላ የሚያፈስ፣ የሚያወጣ ሊቅ ወይም ዶክተር›› ተባለ፡፡ በዚህ ላይም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘማሪ ፈረሰኛ ተብሎ ይጠራል፡፡ ምክንያቱም በጣም ከፍ ያለ የእመቤታችን ፍቅርና ክብር ስለነበረው ነው፡፡

አበምኔት በርናርዶስ "የ12ኛው ክፍለ ዘመን ሰው" ተብሎም ይጠራል፣ ይህ የተባለበትም ምክንያት በዚያን ጊዜ ሁሉም የሰው ልጆች፣ ከጳጳሳት እስከ ተራ ምእመን፣ ከነገሥታት እስከ ተራ ገበሬ ሁሉም ለምክር፣ ምሪትና መፍትሔ ለማገኘት ወደ እርሱ ይሮጡ፣ ይጠሩትም ነበር፡፡

የክለርቮው አበምኔት በርናርዶስ የአርእስተ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሊቃነ ጳጳሳት፣ የጳጳሳት፣ የአበምኔቶች፣ የካህናት፣ የመነኩሴዎች የደናግሎች፣ የነገሥታት፣ የመሳፍንት፣ የባለስልጣኖች እና የተራ ሕዝብ መካሪ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም ዕርቅንና ሰላምን ለማስፈነው መላ ኤውሮጳን ዞሮአል፡፡ በመንበረ ሮሜ ተነሥቶ የነበረው በጣም ከባድ ችግር ማለትም የመንበር ድርርቦሽ እንዲወገድ አድርጓል፡፡ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኤውጀንዩስ 3ኛ (መጀመሪያው ሲታዊ ር.ሊ.ጳጳሳት) ትእዛዝም ቅድስት ሃገርን ነጻ የሚያወጡ ሁለተኛ የመስቀላውያን ወታደሮች ቡድን አዘጋጅቶ ልኳል፡፡ መናፍቃንን ተቃውሞአል፣ ብዙ ተአምራትም አድርጓል፡፡


የአበው ምሥክርነት

(ቅ. ሮበርቶስ በላርሜን1542-1621) የተባለ ኢየሱሳዊ ሊቅ ስለ ቅ. በርናርዶስ ሲጽፍ ‹‹በርናርዶስ እውነተኛ ሐዋርያ ነበር፤ ብዙ ተአምራቶችንም ፈጽሞአል፣ ከምናውቃቸውና ታሪካቸው ከተጻፈላቸው ቅዱሳን የተአምራቶች ብዛት በተመለከተ ከሱ የሚወዳደርና ከሱ የሚበልጥ ማንም የለም›› ይላል

(ቅ. ቶማስ ዘአኩኖ 1225-1274) የተባለ የታወቀ ሊቅም ስለ ቅ. በርናርዶስ ሲናገር ‹‹እግዚአብሔር የመረጠው የሃይማኖት መስተዋትና አብነት፣ የቤ/ክ ምሰሶ፣ የተመረጠ የአምላክ ሠራተኛ፣ እንደ ጣፋጭ ወይን ጠጅ ማር በሚያፈሰው አፉ ዓለምን አጥግቦአል፣ ዓለምን አስክሮአል›› ይላል፡፡

(ማርቲን ሉተርም) ስለ ቅ. በርናርዶስ ሲናገር ‹‹ሁሉንም የቤ/ክ ሊቃውንት ይበልጣቸዋል፣ ከሁሉም መነኩሴዎች በላይ አድርጌ አየዋለሁኝ፣ አባት ተብሎ መጠራት የሚገባውና ሥራውም በጥንቃቄ መጠናት ያለበት እሱ ብቻ ነው›› እስከ ማለት ደርሷል፡፡ ስለ ቅዱስ በርናርዶስ የጻፉና የተናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሦስት ሰዎቨዋ ለማስረጃ ያህል የተጠቀሱ ናቸው፡፡


የሲታዊ ሕይወት

የሲታዊ ሕይወት ዓይነተኛ መንፈሳዊነት በነፃነትና በመንፈስ ቅዱስ ደስታ የሚቀበሉት ተጋድሎ በማድረግ ቀላልና ተራ የሆነ አኗኗር በመከተል፣ በክርስቶስ ትስብእት የተገለጠውን መለኮታዊ ፍቅር በማስተንተን ነው፡፡ በሲታዊ መንፈሳዊነት በጣም ጎልቶ የሚታየው ወይም ጎልቶ መታየት የሚገባው የቅዱስ ቁርባንና የቅዱስ ልብ ኢየሱስ መንፈሳዊነት ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ ለክርስቲያናዊ ፍጽምና መሠረታዊ ነገር ፍቅር ነው፡፡ ይኸውም አባቱንና የዳም ልጆችን እስከ መጨረሻ የወደደውን የክርስቶስን አርአያ በመከተል ተግባራዊ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህንን መለኮታዊ ፍቅር የሚመግብና ሕይወት የሚሰጥ ደግሞ ምልእተ ጸጋ የሆነችው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልዩ ፍቅርና መንፈሳዊነት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም የቤተክርስቲያን እናት ከመሆንዋም በላይ የማኅበራችን ባልደረባና ጠባቂ ሆና ትከበራለች፡፡ የዚህ ከፍተኛ የማርያም አክብሮትና ፍቅር ሕያው ምስክር የሆነ፣ ከዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ መንፈሳዊ ተግባር አለ፡፡ ይኸውም በሁሉም የሲታውያን ገዳማት የቀኑ ሙሉ የጸሎትና ሥራ ተግባር ፍጻሜ ማለትም በጸሎት ዘንዋም መጨረሻ ላይ ‹‹ሰላም ለኪ ኦንግስት›› የሚለው ወደ እመቤታችን በዜማ የሚደረግ ጸሎት ነው፡፡ ስለእመቤታችን ብዙ የጻፈና የሰበከው የማርያም መዘምር ተብሎ የሚጠራው ቅ. በርናርዶስ አባታችን የሲታዊ ሕይወትን መልክ እንዲህ በማለት ያብራራዋል፡-

‹‹ሕይወታችን የፍጹም ትሕትና፣ የነጻ ድሃነት፣ የተአዝዞና በመንፈስ ቅዱስ የሰላም ሕይወት ነው፡፡ ሕይወታችን ለአለቃ፣ ለአበምኔት፣ ለሕግና ለሥርዐት የመታዘዝ (ራስን ዝቅ የማድረግ) ሕይወት ነው፡፡ ሕይወታችን የጽሞና (የዝምታ)፣ የጾም፣ የንቃት፣ የጸሎት፣ የእጅ ስራ ከሁለም በላይ ግን የበለጠችውን የፍቅር ጎዳና የመከተል፣ ከቀን ወደ ቀን በፍቅር የመበልጸግና እስከ መጨረሻ በርሷ ጸንቶ የመኖር ሕይወት ነው›› (ከቅ.በርናርዶስ መልእክቶች ቁ.142)፡፡

ቅ.በርናርዶስ ከተናገራቸው ውስጥ

 • ከድንግል እንጂ ከሌላ አለመወለዱ ለእግዚአብሔር ልጅ ተገቢው ነው፤ ለድንግሏም እግዚአብሔርን እንጂ ሌላ አለመውለድዋ ተገቢዋ ነው፡፡ ስለዚህ፣ የሰው ፈጣሪ እንደ ሰው ለመሆን ከሰው ለመወለድ ሲዘጋጅ ከሁሉም ለራሱ የምትስማማና የምታሰደስተው እናት መምረጥ ማለትም መፍጠር ነበረበት፡፡
 • በአካልም ሆነ በአእምሮ ቅድስት፣ አዲስ በአጋጣሚ የተገኘች ሳትሆን በዘመናት ከሁሉ የተመረጠች፣ በልዑል እግዚአብሔር አስቀድማ የታወቀችና ለራሱ የተዘጋጀች፣ እንዲሁም በመላእክት የተከበበች፣ አበው አስቀድመው ያወቁአት፣ ነቢያትም ተስፋ ያደረጓት እርስዋ ናት፡፡
 • በአምላክ ቁስሎች ካልሆነ በስተቀር ደካሞች የሚያርፋበት ጠንካራ ምሽግ የት ይገኛል? በዚያ ደኅንነት የሚለካው ለማዳን ባለው ኃይል ነው፡፡ ዓለም ይቆጣል፣ ሥጋ ወደታች ይጎትተኛል፣ ሰይጣን ወጥመዶቹን ይዘረጋል ነገር ግን በጠንካራ ዓለት ላይ ስለተመሠረትኩ አልወድቅም፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ኃጢአት ሰርቻለሁ፣ ሕሊናዬ ይሸበራል ነገር ግን ተስፋ አይቆርጥም፣ ምክንያቱም የአምላክን ቁስሎች አስታውሳለሁና፡፡ በርግጥ ‹‹ለኛ ኃጢአት ቆስሏል›› በክርስቶስ ሞት የማይሰረዝ ኃጢአት ምን ያህል የከበደ ነው? እንግዲያ እንደዚህ ያለ ኃይለኛና ውጤታማ መፍትሄ ካስታወስኩ ምን ያህል ከባድና ሰቃይ የበዛበት ቢሆንም ማንኛውንም ዓይነት በሽታ አልፈራም፡፡
 • የርሱ ሃሣቦች የሰላም ሃሳቦች ነበሩ፣ እኔ ግን አላውቅሁም ነበር፡፡ ‹‹የአምላክን ሃሣብ ያወቀ ወይም የአምላክ አማካሪ የነበረ ማነው?›› ነገር ግን የተቸነከረበት ምስማር የአምላክን ፈቃድ እንዳይ ለኔ በር የከፈተልኝ ቁልፍ ሆነ፡፡ በዚህ ክፍት ቦታ ዘልቄ ማየት እንዴት አልችልም? እግዚአብሔር በእውነት በክርስቶስ ውስጥ ሆነ ዓለምን ከራሱ ጋር እንደሚያስታርቅ ምስማሩ ይጮሃል፣ ቁስሉም አፋን ከፍቶ ይናገራል፡፡ ደካማነቴን ለመረዳት ያስችለው ዘንድ ብረቱ ነፍሱን አልፎ ወደ ልቡ ተጠጋ፡፡
 • ጥበብን ካገኛችሁ በርግጥ ማር አግኝታችኋል፣ ብቻ እስክትታመሙ ድረስ አትብሉ፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ እንድትራቡ ብሉ፡፡ ጥበብ ራሷ ‹‹የሚበሉኝ የበለጠ ይራባሉ›› ትላለችና፡፡ ካላችሁ ነገር ብዙ አታከማቹ፤ ፍለጋውን በቶሎ ስላቋረጣችሁ አለን የምትሉት እንዳይወሰድባችሁና እስኪያስመልሳችሁ ድረስ እራሳችሁን ያለ ልክ አታጭቁ፡፡ ጥበብ በምትገኝበትም ሆነ ቅርብ በምትሆንበት ጊዜ እንኳን እርሷን መፈለጋችንንና መጥራታችንን ማቆም የለብንም፡፤ አለበለዚያማ ሰላሞን ‹‹ማር እንኳን ሲበዛ ይመራል›› እንዳለው ‹‹ሞገስን የሚፈልግ በክብሩ ይጠመዳል››
 • ከነፈራችሁ ጥበብን ወይም እውቀትን የሚያፈስሰው በሦስት መንገዶች፣ ይኸውም ኃጢአታችሁን በመናዘዝ፣ እግዚአብሔርን በማመስገንና በውዳሴ ድምጽ እንዲሁም በማበረታቻ ቃል መሆኑ እውቅ ነው፡፡ ‹‹ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል፣ በአፉም መስክሮ ይድናል›› የተባለው እውነት ነው፡፡ እንዲሁም ጻድቅ በንግግሩ ራሱን ይወቅሳል›› በንግግሩ መሃል እግዚአብሔርን ያመሰገናል፣ በመጨረሻም ጥበብ በሙላት እስከፈሰሰ ድረስ ባልንጀራውንም ደግሞ ያበረታታል፡፡
 • ነቢዩ ዕንባቆምም የሚለውን ስሙ፡፡ እርሱ የጌታን ሐሳብ ሳይደብቅ በጥንቃቄና በማስተዋል ሲያንፀባርቅ እንዲህ ያላል፣ ‹‹በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፣ በአምባ ላይም ላይም እወጣለሁ፤ እግዚአብሔርየሚናገረኝን ስለ ክርክሬም የምመልሰውን አውቅ ዘንድ እመለከታለሁ፡፡›› እንግዲህ፣ ወንድሞቼ ሆይ፣ የውጊያ ጊዜ አሁን ነውና የመጠበቂያ ቦታችንን እንድንይዝ እለምናችኋለሁ፡፡ ኑረችን ኢየሱስ በሚኖርበት በልብ ውስጥ ይሁን፤ በልባምነትና ተገቢ በሆነ ምክር እንኑር፤ ነገር ግን ዘወትር በዚህ አንመካ፡፡ በደካማ መከላከያ አንተማመን፡፡
 • መላው መንፈሳዊ ሕይወት በእነዚህ ሁለት ነገሮች ላይ ያተኩራል፤ ስለራሳችን በአንክሮ ሳናስብ እነታወካለን፤ ሃዘናችንም ደኅንነትን ያስገኝልናል፤ ስለ እግዚአብሔር ስናሰላስል ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ መጽናናትን እናገኝ ዘንድ እንታደሳለን፡፡ ስለ ራሳችን ስናስላስል ፍርሃትና ትሕትናን እናተርፋለን፤ ስለ እግዚብሔር ከማሰላሰል ግን ተስፋና ፍቅርን እናገኛለን፡፡
 • ኢየሱስ ‹‹ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል›› ሲለኝ ኃጢያት ማድረግ ካላቆምኩ ምን ዋጋ አለው? የቆሸሸውን ልብስ አውልቄዋለሁ ነገር ግን ምልሼ የለበስኩት እንደሆነ ምን ለውጥ አለው? ያጠብኩትን እግር ካቆሸሸኩኝ ማጠቤ ዋጋ ቢስ አይደለምን? ቀድሞ ያዳነኝ እንዲህ ይለኛል ‹‹ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደፊት ኃጢአት አትሥራ›› ዮሐ 5፡14
 • በዓመት አንድ ጊዜ ለሚደረገው ስብሰባ ካልሆነ በቀር በፍጹም ከገዳሙ ላለመውጣት ወስኛለሁ፡፡
 • በልግስና በእግዚአብሔር ፍቅር እና በወንደሞች ፍቀር የሚኖረው ሲታዊ እውነተኛ መነኩሴ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች በሌሉበት ግን ምንም ያህል ቢለፋ እርሱ እውነተኛ ሲታዊ መነኩሴ አይደለም፡፡

የቅዱስ በርናርዶስ ጥንካሬ ከትህትናው የመጣ ነው፤ በዚህም በራሱ ደካማነት ከመመካት ይልቅ ትምክህቱን ሁሉ በመለኮታዊው አዳኝ እና በቅድሰት እናቱ ላይ አደገ፡፡ (ቶማስ ሜርተን)

‹‹ቅዱስ በርናርዶስ ስለ እመቤታችን የፃፈውን ነገር ከማጥናታችን በፊት ስለ እርሷ በአጥጋቢ ሁኔታ መናገርም ሆነ መጻፍ አይቻልም›› (ቶማስ ሜርተን)


የክርስቶስ ፍቅር የግዴታ ወደ እናቱ ፍቅር ይጠቁመናል፡፡ እርሱን ስናከብር እርሷንም እንዲሁ እናከብራታለን፡፡ ስለዚህ የኢየሱስ እና የማርያም ፍቅር ሊነጣጠሉ አይችሉም ሁለቱም አንድ ናቸው፡፡ እርሷን ሳናፈቅር እርሱን ማፍቀር አንችልም፤ እርሷን የምናፈቅርበት ብቸኛው ምክኒያት የበለጠ እርሱን ለማፍቀር ነው፡፡


ጸሎት ወደ ቅዱስ በርናርዶስ

ቅዱስ አባት ሆይ!

መላ ልጆችህን ወደ ፍጹም ፍቅር የምትጠራና

የተወሰኑትን ደግሞ በቅርብ የልጅህን ፈለግ

ይከተሉ ዘንድ የምትጋብዝ፤

በቅዱስ በርናርዶስ አማላጅነት በሙላት

ያንተ እንዲሆኑ የመረጥካቸውን ለዓለምና ለቤተ ክርስቲያን

ያንተን መንግሥት ይገልፁ ዘንድ ኃይልን ስጣቸው፡፡ አሜን፡፡


ብርሃነ ሲቶ - ግጥም

ቤቱ ደካክሟል ሰው የለበትም

በር የሚያንኳኳ እንግዳ አልመጣም

በውስጥ የቀረው ተስፋ አይሰጥም

ለስንት ዘመን ለዓለም ያበራ

‹‹ሰው›› በጠፋበት በወና ሥፍራ

ሊለይ ደርሷል ጸሎት ከሥራ፡፡

የምታፅናናን አንዲት ቃል ጠፍታ

ከኛ ርቃ የተስፋ ጠብታ

የሲቶ ብርሃን ወጣ ወደ ማታ፡፡

የደብሩ ደውል እንዲህ ይጮሃል

የበርናርዶስ እጅ በሩን ይመታል

ይከፈትለት ያድሰን ገብቶ

ቅዱስ በርናርዶስ ብርሃነ ሲቶ፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት