ካቶሊካዊ ምልክቶችና ትርጉማቸው
- Category: እምነታችን
- Published: Monday, 27 June 2011 00:00
- Written by Super User
- Hits: 13965
- 27 Jun
ካቶሊካዊ ምልክቶችና ትርጉማቸው
ምልክቶች ከጥንት ጀምሮ በባህል፣ በማኅበራዊ ሕይወትና በሃይማኖት ውስጥ ልዩ ቦታ የነበራቸውና ያላቸው ናቸው። ምልክቶች በእምነት ውስጥ ልዩ ቦታ ሲኖራቸው፤ የሐሳብና ጸሎት ትኩረት ማረፊያ ናቸው። በካቶሊካዊት ቤተክርሰቲያናችንም ውስጥ ከጥንታዊው የክርስትና ዘመን ጀምሮ እስከጊዜያችን ድረስ ሁላችንም በጋራም ይሁን እንደየባህላችንና ትውፊታችን የምንጠቀምባቸው የተለያዩ እምነታችንን ገላጭ ምልክቶች አሉን፤ ከነዚህም ውስጥ የጥቂቶቹን ትርጉሞች ባጭር መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ክርስቶስ በመስቀል ላይ
መስቀል፦ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሚያሳይ ነው። ይህ የተለመደ ካቶሊካዊ ምልክት ሲሆን፣ ቅዳሴ በሚቀደስበት መንበረ ታቦት ላይ ወይም ከመንበረ ታቦቱ ፊት ለፊት ይሰቀላል። መስቀሉ ላይ በምሕጻረ ቃል በላቲን የተጻፈ ”INRI” (Iesus Nazareno Rex Iudae) የሚል ጽሑፍ ሲገኝ “ኢየሱስ ናዝራዊ የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ትርጉም ነው ያለው። እነዚህ ቃላቶች የይሁዳ አስተዳዳሪ የነበረው ጲላጦስ ከመስቀሉ በላይ እንዲጻፍ ያዘዘው ጽሑፍ ነው። መስቀል የመስዋዕት ምልክት ነው።{jathumbnail off}
አልፋና ኦሜጋ
እነዚህ የመጀመርያውና የመጨረሻው የግሪክ ፊደል ናቸው። በዮሐንስ ራዕይ 22፤13 ኢየሱስ ራሱን አልፋና ኦሜጋ የመጀመርያና የመጨረሻ መሆኑን ይናገራል። ክርስቶስ የፍጥረት መጀመርያና መጨረሻ ነው። አልፋና ኦሜጋ ምልክቶች በተለያዩ የቤተክርስቲያን ሊጡርጊያዊ አዝማናት ይጠቀሙባቸዋል።
መስቀል
በጣም የተስፋፋው የክርስቲያን ምልክት መስቀል ነው። መስቀል ክርስቲያን ባለበት ሁሉ ይገኛል። በሮማውያን ጊዜ መስቀል እንደ ውርደትና ስቃይ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ወንጀለኞች በምስቀል ተሰቅለው ይገደሉ ነበር። ለክርስቲያን ግን መስቀል የክርስቶስ ሞት ብቻ ሳይሆን የትንሳኤም ምልክት ሆነ።
ልበ ኢየሱስ
የኢየሱስ ልብ ኢየሱስ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ምልክት ነው። ልብ የፍቅር ምልክት ነው። ልቡ በመስቀል ተወግቶና በእሾኽ ተከቦ ይሳላል። ይህ ደግሞ የኢየሱስን ለሰው ልጅ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያሳያል። እሱ ስለ ሰው ልጅ ሊሰቃይና ሊሞት ተዘጋጅቶ ነበር። ፍቅሩ ደግሞ ዘለዓለማዊ ኢዩ።
አይ ኤች ኤስ እና ሲኤአይ-አርኤችኦው ( IHS & CHI-RHO)
እነዚህ ፊደሎች በቤተክርስቲያን አልባሳት፣ በቤተክርስቲያኖች ውስጥ፣ በተጠረቡ ድንጋዮች ላይና የቤተክርስቲያን ዕቃዎች ላይ ተጽፈው ይገኛሉ።
በግሪክ ቋንቋ ክርስቶስ የሚለው የመጀመርያዎቹ ሁለት ፊደሎች “ኤክስ” ና “ፒ” ናቸው፤ “ፒ”ን መስሎ በላቲን ፊደል የምናየው በግሪክኛ "ሮ" የሚል አደማመጥ ነው ያለው። እነዚህ ሁለቱ የመጀመሪያ ፊደሎች ማለትም “ኤክስ” ና “ፒ” ክርስቶስ በሚለው ምትክ ስም ሆነው ይጻፋሉ። በግሪክ ፊደል “ኤክስ” ከ “ሲ ኤች አይ” ጋር “ፒ” ከ “አር” ጋር እኩል ነው።
ሲ ኤች አይ-አር ኤች ኦው (CHI-RHO) በመባልም ሲታወቅ፣ አንዱ በአንዱ ላይ ተደርቦ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግም ብክብ ከበባል።
ዓሳ
ከጥንታውያን የክርስቲያን ምልክቶች አንዱ ዓሳ ነበር። ይህ ክርስቲያኖች - በተለይ በስደት ጊዜ ማንነታቸውን ለመግለጽ ይጠቀሙበት ነበር። ሮም በሚገኙት ካታኮምብ (ክርስቲያኖች በክርስቶስ በማመናቸው ከስደት ለመሸሽ ይደበቁበት የነበረ ቦታ) ውስጥ ይገኛል።
የመጀመርያዎቹ ፊደሎች የክርስቶስ ስሞች ሲነበቡ በግሪክ ቋንቋ ዓሳ የሚል ትርጉም ይሰጣሉ። በግሪክ ቋንቋ ዓሳ ICHTHUS ማለት ሲሆን፤ የኢየሱስ ስም በግሪክ ቋንቋ Iesous CHristos THeou Uios Soter ነው። ትርጉሙ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚኣብሔር ልጅ - አዳኝ” ማለት ነው።
ክርስቶስ ሐዋርያትን “የሰው አጥማጆች” ሲላቸው። የመጀመርያዎቹ ክርስቲያን አባቶች ታማኝ ዓሳዎች ተብለው ይጠሩ ነበር።
ርግብ
ርግብ የመንፈስ ቅዱስ ምልክት ነው። ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ርግብ ወደርሱ ወረደ። (ማቴዎስ 3፤16 እና ማርቆስ 1፤10)
ርግብ እንደ የሰላም ምልክት የወይራ ቅጠል ይዛ ትሳላለች። የእግዚኣብሔር ጸጋንም ያመለክታል።
የኖኅን ታሪክ እናስታውሳለን። እግዚኣብሔርን ምድርን በጥፋት ውሃ በቀጣ ጊዜ፤ ኖኅ ውሃው ደርቆ እንደሆነ ለማረጋገጥ ርግብን ላከ። ርግብም ስትመለስ ከደብረ ዘይት ተራራ የወይራ ቅጠል ይዛ መጣች። ይህም እግዚኣብሔር ለሕዝቡ ምልክት እንዳደረግ ነው።
ጠቦት (በግ)
ከክርስቲያን ምልክቶች አንዱ ጠቦት ነው። በዮሐንስ ወንጌል 1፤35-36 እና በዮሐንስ ራእይ 5፤4-6 እንዲሁም በቅዳሴ ጊዜ ክርስቶስ በአምሳል በግ ይጠቀሳል። በጉ ነጭ መሆኑ ንጹሕና ሐጢኣት የሌለበት መሆኑን ያመለክታል። በብሉይ ኪዳን በጎች ለመስዋዕትነት ይቀርቡ ነበር። ክርስቶስ የሰው ልጅን ከኃጢያት ለማዳን መስዋዕት ሆኖ ሞተ።
በጉ አንዳንድ ጊዜ ሰንደቅ ዓላማ (ባንዲራ) ይዞ ይሳላል። ይህም ክርስቶስ ሞት አሸንፎ መነሳቱን ያመለክታል። የድል ምልክት ማለት ነው።