እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአጭሩ

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአጭሩ

የቤተ ክርስቲያን ታሪክን ለማየት ሲሞከር ዘወትር የመጀመሪያ ጥያቄ ሊሆን የሚችለው ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው መቼ ነው የሚለው ነጥብ ሊሆን ይችላል ነው። ለዚህ ጥያቄ አንድ መልስ መስጠት ቀላል አይሆንም። ምክንያቱም ይህ ነጥብ ራሱ ቤተ ክርስቲያን ምንድናት ወደሚለው ጥያቄ ስለሚያመራን ማለት ነው። ስለዚህ ይህንንና መሰል ጥያቄዎች ውስጥ ጠለቅ ብለን ሳንገባ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ስምና ቃል በዙሪያው በመሰብሰብ ትምህርቱን የሕይወታቸው ተቀዳሚ ፋይዳ ያደረጉ፤ በእርሱም የእግዚአብሔርንና የሰውን ምንነት ይበልጥ የተረዱ፣ በእምነት አንድ በመሆን እርሱን ለመከተል የሚጥሩ ስብስብ ናት በሚል የጋር ግንዛቤ ከተስማማን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚጀምረው ከኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት ታሪክ ጋር ብለን መጀመር እንችላለን።

ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ስም ስናስተውል በቀላሉ የሚያስተላልፍልን ትርጉም የክርስቲያኖች ቤት፣ ኅብረት ሲሆን ይህ ኅብረት ወይም መሰባሰብ ደግሞ በምን ዙሪያ ወይም ዓላማ ነው የሚለውን ሃሳብ ክርስቲያን የሚለው ስያሜ ይመልስልናል። ክርስቲያን የሚለው ቃል ክርስቶስ በአካል ከተገለጠበት ዘመን አንሥቶ በስሙ እየተጠሩ የርሱ ተከታይ መሆናቸውን የሚመሰክሩ ሰዎችን ለማመልከት የሚያገለግል ነው። በዚህም መሠረት የቤ/ያን ታሪክ በቀጥታ ወደ ክርስቶስ ታሪክ ያመራናል። በርግጥ በእግዚአብሔር ቃል ዙሪያ መሰባሰብ በአዲስ ኪዳን የሆነ ነገር ብቻ ሳይሆን በብሉይ ኪዳንም ሕዝበ እስራኤል በእርሱ ቃል የተሰባሰበ ሕዝብ እንደነበር እናነባለን፤ ሆኖም እንደተቀሩት ነገሮች ሁሉ ብሉይ ኪዳን በአዲስ ኪዳን ሊሆን ያለው ነገር ጥላ እንጂ በራሱ ሙሉ አልነበረም። ይህ በእግዚአብሔር ቃል መሰባሰብ ሙሉ እውነታ የሚሆነውና ሕዝበ እስራኤል በቤተ ክርስቲያን የተተካው በክርስቶስ ቃልና በራሱ በክርስቶስ አካል ዙሪያ መሰባሰብ ከተጀመረ ወዲህ ነው።

በታሪክ እይታ ሲታይ ስለ ክርስቶስ ታሪክ ማውራት በጣም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም በርሱ ዘመን የተጻፈ በቂ የጽሑፍ ምንጭ የለንም፤ ክርስቶስ ራሱም የጻፈልን ነገር የለም። በአጭሩ ዘግየት ብለው ከተጻፉት ወንጌሎች ውጭ ስለ ክርስቶስ የተጻፈ ዓለማዊ ታሪክ ምንም የለንም። ወንጌሎች ደግሞ የታሪክ መጽሐፍት አይደሉም፤ ማስተላለፍ ያለሙትም የክርስቶስ ታሪክን ሳይሆን ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የመሆኑን እምነትን ነው። ክርስቶስ ከሞተ 90 ዓመታት ገደማ በኋላ ቢያንስ ክርስቶስ እንደ ነበረ የሚመሰክሩ በጣም ጥቂት አንዳንድ የሮማውያን ዓለማውያን ታሪክ ጸሐፍትን እናገኛለን። ስለዚህም ወንጌልም ሆነ በጠቅላላ አዲስ ኪዳን የሚያስተላልፉት ታሪካዊ እውነት ቢኖራቸውም ሙሉ ታሪክ አልተዘገበባቸውም።

እንደ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤተ ክርስቲያን አንዲት መንፈሳዊት ብቻ የሆነች ማኅበር ሳትሆን ሰብአዊነትና መለኮታዊነት ያላት፤ ክርስቶስ ራሷ ሆኖ የተለያዩ አካላት ያሏትና ሁሉም እርስ በርሳቸው በመዋቅር የተያያዙ አባላትን ያሰባሰበች መሆኗን ታስተምራለች። ይህችን መሰል ቤ/ያን ክርስቶስ ራሱም እንደመሠረታትና በአዲስ ኪዳንም እንደተንጸባረቀች ይታያል። ሐዋርያት እንደ በጳጳሳት ሲወከሉ ከሐዋርያትም ደግሞ ጴጥሮስ የመሪነቱን ስፍራ እንደተሰጠው ክርስቶስ ለጴጥሮስ ቁልፍ በሰጠው ወቅት ተገልጿል(ማቴ.16:16-19)፤ ቁልፍ ደግሞ የኀላፊነትና የመሪነት ምልክት ነው። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ቃል፣ ፈቃድና ተግባር በዘመናት እያስተላለፈች የቆመች የርሱ አካል ናት፤ ስለዚህ ይህ እውነት ራሱ የቤተ ክርስቲያን መሠረት በክርስቶስ እንደሆነና በአዲስ ኪዳንም የአባላትና የአስተዳደር ሁኔታዋ እያደገ መምጣቱን በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል። ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ባህሪይ ብቻ ያላት ብትሆን ኖሮ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ብሎ ማውራቱን ትርጉም የለሽ ነገር ያደርገዋል።

 

የኢየሩሳሌም ጉባኤ

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በታሪክ የምናውቃት ቤተ ክርስቲያን መልክ በዝርዝር ባይሆንም በጅማሬ ሁኔታ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እናገኛታለን። መለኮታዊ ግልጸት የሆነ ነገር ሁሉ በጊዜ ሂደት ይበልጥ ግልጽ ሆኖ እንደሚታይ ሁሉ በጽሑፋቱ የምናገኛት ቤተ ክርስቲያንም በታሪክ ውስጥ መልክ እየያዘች ፍጽምት ወደ ሆነችው ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ትደርሳለች። ይህ እስኪሆን ግን አባላቶቿ ሰዎች ናቸውና ድካምና ብርታት፣ ቅድስናና ውድቀት፣ ብርሃንና ጨለማ…ይፈራረቁባታል። ይህም ተፈጥሮዋ በየጊዜው ራሷን እንድታይና መንገዷን ወደ ጌታዋ ለማቅናት ቆም ብላ እንድትወያይና ራስ የሆነውን ክርስቶስን ለማዳመጥና የርሱን ፈቃድ ለዘመኑ ለማስተላለፍ የተለያዩ መንገዶችን ትጠቀማለች። ከነዚህም መንገዶች አንዱ ጉባኤ መጥራት ሲሆን ይህም ከሐዋርያት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ ቀጥሏል። በግልጽ በብዙ የታሪክ ሰነዶች የምናገኛቸው የቤ/ያን ጉባኤዎች ጥቂቶቹ በኒቅያ 325 ዓ.ም.፣ በኬልቄዶን በ451 ዓ.ም.፣ ላተራል፣ ቶሮንቶ…በቅርብ ክፍለ ዘመናትም የቫቲካን ጉባኤ 1ኛና 2ኛ… ሲሆኑ ባጠቃላይ ሀያ ሁለት ጉባኤያት ናቸው። በሐዋርያት ሥራ ደግሞ የነዚህ ጉባኤዎች ሁሉ ፈር ቀዳጅ የሆነውን በምዕ.15 ላይ እናገኛለን።

ይቀጥላል...

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት