ብሂላታተ ሊቃውንት ወቅዱሳን
- Category: ብሂላታተ ሊቃውንት ወቅዱሳን
- Published: Tuesday, 26 May 2009 17:46
- Written by Super User
- Hits: 16473
- 26 May
ነኝ ግን...
"ካቶሊክ ነኝ ግን..." የሚል ሰው በርግጥ ካቶሊክ አይደለም።
ሊ.ጳ. ፉልተን ሺን
ከፍ እንበል
የምንሆነው የምንወደውን ነገር ነው፤ ተራ ነገር ካፈቀርን ተራ እንሆናለን፤ ከፍ ያለ ነገር ካፈቀርን ግን ከፍ እንላለን።
ሊ.ጳ. ፉልተን ሺን
ሸክም ላለመሆን
ሰው ሌላን ሰው ማገልገል ባቆመበት ሰዓት የሌላው ሸክም መሆን ይጀምራል።
ሊ.ጳ. ፉልተን ሺን
ትሑትና ራስህን ሁን!
ትሑት ሁን ነገር ግን ፈሪ አትሁን፤ ገር ሁን ሆኖም ሞኛ ሞኝ አትሁን፤ የአእምሮ ብቃት ይኑርህ ቢሆንም ሌሎች እስከማይገባቸው አይሁን፤ ከሌሎች ጋር ተወያይ ነገር ግን ራስህን ሁን!
ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው
ክርስቶስ ተነስቷልና ተነሥ! - አትርመጥመጥ!
እኔ ግን በፈቃዴ ዙሪያ ከሚሾሩት ከሰውነት ደስታዎች ሁሉ በፊት የተገባ የሆነውን ትቼ ርካሹን የዚህን ዓለም ደስታ ለመካድ እየተጎተትኩ እርመጠመጣለሁ... ለአንተም አልኩ 'ንጽሕናን፣ ራስንም መግዛት ስጠኝ፤ ግን አሁን አይደለም'። ምክንያቱም ልመናዬን ሰምተህ ወዲያው እንዳታደርገውና ከማስወገድ ይልቅ ላረካው የምፈልገውን የፍትወት በሽታዬን በአጭሩ በመፈወስ እንዳታስቆመው ከመፍራት የተነሣ ነበር...
ቅ. አውግስጢኖስ - "ኑዛዜ" - ገጽ 112
ያለፍቅር እምነት የለም!
ፍቅር ያለውን ነገር ሁሉ ያካፍላል፤ በፍቅር የማይገለጽ እምነት እምነት አይደለም።
ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ
የምንሻገርበትን ድልድይ አንስበር!
የሌሎችን በደል ይቅር የማይል ሰው ራሱ የሚሻገርበትን ድልድይ ሰባሪ ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም ሰው ይቅርታ ያስፈልገዋልና።.
ፉልተን ሺን - ሊቀ ጳጳሳት
ቤኔዲክቶስ 16ኛው - ር.ሊ.ጳ.
ጭብጤን መክፈት አስተምረኝ!
ጁሊያን ግሪን - ካቶሊክ ደራሲ
ሄንሪ ኖዌን (አባ)
መንፈስ ቅዱስ ሆይ ና! ከሰማያት ጮራህን ላክልን፤
ስጦታዎችን አዳይ የድኾች አባት፣ የልቦች ብርሃን ሆይ ና!
ትክክለኛ አጽናኝ፣ የነፍስ ተስማሚ እንግዳ፣ አስደሳች እፎይታ ሆይ ና!
በድካም እረፍት፣ በኀዘን ጽናት የሆንህ አስደሳች ብርሃን ሆይ! የአማኞችህን ልብ ውረር!
ያለ አንተ ኃይል ለክፋት ብቻ እንጂ ለተቀረውስ ሰው ከንቱ ነው፤
ያደፈውን አንጻ፣ የደረቀውን አረስርስ፣ ድውዩን ፈውስ።
ደንዳናውን አለስልስ፣ ቀዝቃዛውን አሙቅ፣ ጠማማውን አቅና፤
የሚያምኑብህ ባንተ ብቻ ይማጠኑ ዘንድ የተቀደሱ ስጦታዎችህን አድላቸው።
በጥሩ ምግባር መኖርን፣ የተቀደሰ ሞትንና ዘላለማዊ ደስታን ስጠን።
ከላቲን ሥርዓተ ሊጡርጊያ ቅዳሴ የተወሰደ
ቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው
በአንተ ሰላም ተቃጠልኩ!
እጅግ ጥንታዊ፤ እጅግ አዲስ ውበት ሆይ! የማታ ማታ አፈቀርኩህ። አንተ በውስጤ ነበርህ እኔ ግን በውጪ ነበርሁ፤ የፈለግሁህም በዚያ ነበር። በእኔ አስቀያሚነት አንተ ከእኔ ጋር ነበርህ እኔ ግን ከአንተ ጋር አልነበርኩም፡፡ ፍጥረት ካንተ አራቀኝ ዳሩ ግን ፍጥረት ባንተ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር ሕልውና የለውም፡፡ ተጣራህ፣ ጮህክ፣ ድንቁርናዬንም ሰብረህ ገባህ፡፡ አንተ ብልጭ አልክልኝ፣ በደንብ አበራህልኝና እውርነቴን ገፈፍክ፡፡ መዓዛህን በእኔ ላይ ተነፈስክ፣ እኔም እየተነፈስኩ ወዳንተ ቀረብሁ አሁን ይበልጡን እጠማለሁ፡፡ ቀመስኩህ አሁንም ይበልጡን አንተን እራባለሁ፣ እጠማለሁም አንተ ዳሰስከኝ እኔም በአንተ ሰላም ተቃጠልኩ...
ቅዱስ አውጎስጢኖስ
የአምላካችን አብሮነት ሕይወት ይሰጠናል
ዋዣቂና ተለዋዋጭ ከሆነው የሕይወታችን ባሕርይ የላቀ አንዳች አዲስ ነገር ተከስቷል። ዘመነ ትንሣኤ የተስፋ ወቅት ነው። ደስተኞች ወይም ያዘኑ፣ ጨለምተኞች ወይም ተስፈኞች፣ የተረጋጉ ወይም ብስጩዎች ብንሆንም ከነዚህ የአእምሯችንና የልቦቻችን ትናንሽ ወጀቦች የበለጠ የአምላካችን ሕያው አብሮነት (መገኘት) ሕይወት ይሰጠናል።
ሄንሪ ኖዌን
ለሕይወት ለውጥ መሥራት
ሕይወት ለዋጭ የሆነው የክርስቶስ ትንሣኤያዊ ድል ተካፋይ የምንሆነው እግዚአብሔር አናኗራችንን ይለውጥ ዘንድ ስንፈቅድለት ማለትም ለሕይወታችን መለወጥ ስንሠራ ብቻ ነው።
ቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው
ዳግም ላግኝህ!
በትንሣኤህ ስትገለጥ አውቅህ ዘንድ ካንተ ጋር ባንተ ውስጥ መሞት ይገባኛል፤ አዎን ጌታ በኔ ውስጥ ካሉ ነገሮች ውስጥ መሞት ያለባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤ የሽንገላ ቅርርብ፣ ስስት፣ ቁጣ፣ ትእግስተ ቢስነት፣ ለኔ ብቻ ባይነት… ጌታ ሆይ! ምን ያህል በጥቂቱ ብቻ ካንተ ጋር እንደሞትኩ፣ በመንገድህ ታማኝ ሆኜ ያለመጓዜም አሁን ይታየኛል። ጌታ ሆይ! ይህን የጾም ወቅት ከሌሎቹ ጊዜያት የተለየ አድግልኝ፤ ዳግም ላግኝህ! አሜን።
ሄንሪ ኖዌን (አባ)
ጸጥታን ማዳመጥ
እያንዳንዷ ክፍት ቦታና ነጻ ሰዓት በሆነ ሥራ ወይም ድምፅ መሞላት እንዳለባት በሚያምን ኅብረተሰብ ውስጥ እየኖርን ነው። ብዙ ጊዜ ለማዳመጥና ለመወያየት የሚሆን ጊዜም የለንም። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም ውጫዊውንና ውሳጣዊውን ጽሞና አንፍራ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን፣ ካጠገባችን ያለውን ሰው (የራሳችንን) እና የሌሎችንም ድምፅ ለማዳመጥ ያስችለናልና።
ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው
ቀጣይ ፈተና
"ፍቅር በቀጣይነት ከእግዚአብሔር ወደኛ የሚላክ ተፈታታኝ ጥያቄ ነው።" - (ከኛ መልስን በመሻት እግዚአብሔር አሁንም አሁንም እወድሃለሁ/እወድሻለሁ ይለናል)
ብፁእ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ
ረዥም ቀጥ ያለ መስመር የብዙ ጥቃቅን እርስ በርሳቸው የተያያዙ ነጥቦች ወጤት ነው። ሕይወትም እንዲሁ የብዙ ሚሊየን ሰከንዶችና ደቂቃዎች ቅጥልጣይ ፍሬ ናት። እያንዳንዷን ነጥብ በትክክል አኑር ረጅሙ መስመር ቀጥ ያለ ይሆናል። እያንዳንዷን ደቂቃ በፍጽምና ኑራት ሕይወትህ ትቀደሳለች።
Cardinal François-Xavier Nguyễn Văn Thuận (ካርዲናል ፍራንቼስኮ ዛቪየር ጙኢን ቫን ቱወን)
እይታን ያለመከተል
የሰው ልጅ ከእውነት ይልቅ እይታን እየተከተለ ነው። እውነተኛ ነጻነትን የምናገኘው ከእውነት ነውና ለታይታ ሲባል ብዙዎች ያሉትን ዝም ብለው የሚቀበሉ ክርስቲያኖች አንሁን።
ቤኔዲክቶስ 16ኛው
እንደ እምነት መኖር
እንደ እምነትህ የማትኖር ከሆነ ቀስ በቀስ አናኗርህን አምነትህ ማድረግ ትጀምራለህ።
ፉልተን ሺን (ሊቀ ጳጳስ)
ነጻነት ዒላማውን ሲስት
ነጻነት ዓላማ ከሌለው፣ በሰው ልጆች ልብ ውስጥ የተቀረጸውን ሕግ ለማወቅም ካልተመኘና የኅሊናንም ድምጽ መስማት ከተሳነው፣ ኅብረተሰብንና የሰው ልጅን ማጥፋት ይጀምራል።
ብጹእ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ
መጀመሪያ ቅድሚያ ለሚገባቸው ነገሮች
ማስቀደም የሚገባንን ነገር ስናስቀድም ተጨማሪ ነገሮች በራሳቸው በቦታቸው ይከተላሉ፤ ተጨማሪ ነገሮችን ስናስቀድም ግን ያለቦታቸው ልናደርጋቸው ሞክረናልና ቅድሚያ የሚገባቸውንም ሆነ ተጨማሪ ነገሮችን እናጣቸዋለን።
C.S. Lewis
"ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል" ማቴ 6፥33
የመደማመጣችን ምክንያት
የሰማያት ፈጣሪ የሆነው ጌታ ለአናጢ (ለቅ.ዮሴፍ) ታዘዘ፤ የዘላለማዊ ክብር አምላክ አንዲት ምስኪን ድንግልን አዳመጣት። ይህን የሚወዳደር ሌላ ነገር መመስከር የሚደፍር ይኖር ይሆን? እንግዲህ ፈላስፋም ቢሆን አንድ ተራ ሠራተኛን ሳይንቅ ያድምጥ፣ ጠቢቡም ሞኙን የተማረውም መሃይሙን፣ የንጉሥ ልጅም ገበሬውን ይስማ።
ቅዱስ አንጦንዮስ ዘፓድዋ
ሰላምን የምትሻ ከሆነ
ሰላምን የምትሻ ከሆነ ሌሎች ሰዎችን ሳይሆን ራስህን ለውጥ፤ እግርህን ከሚጎዱ ነገሮች ለመከላከል ምድርን በሙሉ በቆዳ ከመሸፈን ለራስህ ብቻ ጫማ ማጥለቁ ይቀላል።
አንቶኒ ዴ ሜሎ (አባ)
እርሷ እጅህን ይዛህ መውደቅ አይቻልህም
ወደ ክዋክብት ተመልከትና ማርያምን ጥራ! በአደጋ፣ በችግር ወይም በጥርጣሬ ጊዜ ማርያምን አስብ፡፡ ስምዋን በከናፍርህ አኑረው፡፡ የእርሷ ስም ከልብህ በፍጹም አይውጣ! በእግር ዱካዋ የአንተን እግር አኑር ከቶ አትጠፋም፡፡ ወደርሷ ተማጠን ተስፋ ቁርጠት አይጠናወትህም፡፡ እርሷን አስብ አትሳሳትም፤ እርሷ እጅህን ይዛህ መውደቅ አይቻልህም፣ አትታክትም፣ አትፈራም፣ በጥበቃዋ እየተደሰትክ ወደ ግብህ ትደርሳለህ፡፡
ቅዱስ በርናርዶስ
ክርስቶስን ባልንጀራችሁ አድረጉት!
የዘመኑ ቴክኒካዊና ሳይንሳዊ እውቀት መሠረታዊ የሕይወታችንን ጥያቄዎችና ሥር ሰደድ ሰዋዊ ችግሮቻችንን አይመልሱም፤ ለነዚህ ሁኔታዎች መልስን ለማግኘት በምታደርጉት ጥረት ክርስቶስን ባልንጀራ አድርጉት።
ቤኔዲክቶስ 16ኛው (ር.ሊ.ጳ)
የማሳለፍ ኀላፊነት
የተሰጠን ለሁሉም እናዳርስ ዘንድ ነውና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ካለን ግንኙነት የተሰጠንን የዘላለም ሕይወት ቃል ለራሳችን ብቻ መያዝ አንችልም፤ በእግዚአብሔር ጸጋ ራሳችን የተቀበልነውን ለሌሎች ማሳለፍ ኀላፊነታችን ነው።
ቤኔዲክቶስ 16ኛው (ር.ሊ.ጳ) Verbum Domini, 2010
ፊታችንን ወደ ሰማይ እንመልስ
በልባችን ውስጥ ደስታና ኃዘን አለ፤ እፊታችን ላይ የደስታ ፈገግታና የሥቃይ እንባ አለ፤ በዚህ ዓለም እስካለን ድረስ ሕይወታችን እንዲሁ ነው፤ ሆኖም ግን ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ በመካከላችን ይገኛል፤ ከእኛ ጋር ይራመዳል። ስለዚህ ለተልእኳችን ታማኞች በመሆን ፊታችንን ወደ ሰማይ በማዞር እየዘምርን እንራመድ።
ቤኔዲክቶስ 16ኛው (ር.ሊ.ጳ)
የጥልቁ ቁስላችን ፈውስ!
ሞንሲኞር ግሬኮ - አንኮና
ኢየሱስ ሆይ! እሆን ዘንድ የምትፈልገውን ዓይነት ሰው መሆን እንድችል ሕይወቴን እንዳላወሳስብ እርዳኝ።
ቅድስት ቴሬዛ ዘኢየሱስ ሕጻን
ከ2 ሺህ ዓመታት በላይ የሚጠባበቅህ ወዳጅ!
በመንበረ ታቦት (ቅዱስ ቁርባን) ፊት ስትሆን ኢየሱስ ከ2 ሺህ ዓመታት ጀምሮ የአንተን መምጣት እየተጠባበቀ መሆኑን አስታውስ።
ቅዱስ ሆሴማሪያ ኤስክሪቫ
የፍቅርህ እሳት እንዴት ይሆን?
የፍቅርህ እሳት እንደጭድ እሳት የሚነካውን የማያቃጥልም ሆነ የማያሞቅ ከንቱ የውሸት እሳት አይሁን።
ፍኖት 412
ሁለቱ ገበታዎች
መንፈስ ቅዱስ የመጽሐፍ ቅዱስ ፀሐፊዎችን የእምነት ልብ እንደከፈተ እንዲሁም ትርጉሙን ይረዱ ዘንድ የምዕመናንንም ልብ ይከፍታል፤ ይህም መንፈስ ቅዱስ በምስጢረ ቅዳሴ ካህናት ኅብስቱንና ወይኑን ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም የሚለውጡትን ቃላት ሲናገሩ በዚያ አለ፡፡ ምዕመናንም ሊኖሩና የሕይወታቸውን ጉዞ ሊጓዙ የሚችሉት በቃለ እግዚአብሔርና በክርስቶስ ሥጋና ደም ሲመገቡ ስለሆነ እነዚህ ሁለት ገበታዎች ሊለያዩ አይችሉም፡፡
ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው
ለሰው ልጅ ነፍስ የሚስማማ "የአየር ሁኔታ"
የእግዚአብሔርን በምልአት መገለጽ የማይቀበሉ ሰዎች ርካታ ቢስ ሕይወትን ይገፋሉ። የሰው ልጅ የመፈጠሩ ዓላማ እግዚአብሔርን ለማወቅ፣ ለመውደድና ለማገልገል ነው። እምነትን በማጥፋትም ሆነ በሌላ ምክንያት ይህን ማድረግ ካልቻሉ ከተፈጥሯቸው ሁኔታ የወጣ ሕይወት ውስጥ ይገባሉ፤ ለሰው ልጅ ነፍስ የሚስማማ "የአየር ሁኔታ" እግዚአብሔር ነውና ነፍስ ከእግዚአብሔር ውጪ ልታብብ አይቻላትም
ፉልተን ሺን (ሊቀ ጳጳስ)
የሁለንተናችን አስተዳዳሪን መናፈቅ!
እግዚአብሔር ሁለንተናችንን እንዲያስተዳድር ከመናፈቅና በሁኔታዎች ያልተወሰነ እሺታን ለእርሱ ከመስጠት የላቀ ምንም ነገር የለም፡፡
ዊልፍሪድ ስቲኒሰን (አባ)
እየሰማን የማናስተውለው የእግዚአብሔር ድምጽ!
ጆሮአችን በተለያዩ የድምጽ ሞገድ ጩኸቶች ስለተሞላ የእግዚአብሔርን ድምጽ ማዳመጡ ተስኖናል።
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛው
ልቤ ከእስትንፋሴ በላይ ፍቅርህን ይደጋግመው!!
አምላኬ ሆይ! አፈቅርሃለሁ።
የእኔ ፍላጎት እስከ መጨረሻ የሕይወቴ እስትንፋስ ድረስ እንዳፈቅርህ ነው።
ከመጠን በላይ መፈቀር የሚገባህ አምላክ ሆይ አፈቅርሃለሁ።
ለጥቂት ደቂቃዎች ሳለፈቅርህ በሕይወት ከምኖር፤ አንተን እያፈቀርኹ መሞትን ኣመርጣለሁ።
ጌታዬ ሆይ! አፈቅርሃለሁ።
አንድ እንድትሰጠኝ የምለምንህ ነገር ቢኖር፣ ለዘለዓለም እንዳፈቅርህ የሚያስችለኝን ጸጋ ነው።
አምላኬ ሆይ! ምላሴ በየደቂቃው አፍቅርሃለሁ ማለትን ካልቻለ፤ ልቤ ከእስትንፋሴ በላይ እንዲደጋግመው እፈልጋለሁ።
ስለ እኔ ብለህ የተሰቀልኽ መለኮታዊ መድኅኔ ሆይ! አፈቅርሃለሁ።
እኔን ከመስቀልህ ጋር የምታቆራኘኝ አምላኬ ሆይ! እያፈቀርኩህና እንዳፈቀርኩህ እያወቅኩ እንድሞት የሚያስችለኝን ጸጋ ስጠኝ።
አሜን።
የአርሱ ቅዱስ ዮሐንስ ቪያኔ ጸሎት-(የካህናቶች ባልደረባ)
የማይነጣጠል ክርስቶስ!
በመንበረ ታቦት ላይ በኅብስት አምሳል የሚገለጠውን ክርስቶስን ማመን እስካልቻልን ድረስ በተጎሳቀሉ ነዳያን ራሱን የሚገልጸውን ክርስቶስን ማየት ይሳነናል።
ብፅእት እማሆይ ቴሬዛ
ከዕውቀት መንገድ ይልቅ የቅድስና መንገድ ክፍት ነው፡ ነገር ግን ቅዱስ ከመሆን ይልቅ አዋቂ መሆን ይቀላል። ይህ አነጋገር እውነት ባይመስልም በርግጥ እውነት ነው።
ፍኖት ቁ. 282
ለሰው ይኽን ያህል ታላቅ ክብር ለመስጠት ያነሳሳህ ምን ይሆን?...ወደር የሌለው ፍቅርህ እንደሆነ አይጠረጠርም! በፍቅሩ ተማርከሃል፤ በእውነትም በፍቅር ፈጥረኸዋል፤ በፍቅርም ዘላለማዊ መልካምነትህን የሚያጣጥም ስብእናን ለግሰኸዋል።
ቅድስት ካተሪና ዘሲየና
የማርያም ዘመድ ነህና ደስ ይበልህ!
ሰዎች ከሥነ ጽሑፍ፣ ከፖለቲካ፣ ከጦር ኃይሎች፣ ከቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ሰዎች ጋር ያላቸው ዝምድና ሲነገርላቸው ምንኛ ደስ ይላቸዋል! አንተም ንጽሕት ድንግል ማርያምን አስታውስ። “የእግዚአብሔር አብ ልጅ ማርያም ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ የእግዚአብሔር ልጅ እናት ማርያም ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ የመንፈስ ቅዱስ ሙሽራ ማርያም ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ከእግዚአብሔር በስተቀር ከአንቺ የሚበልጥ ማንም የለም!” በማለትም ዘምርላት።
ፍኖት ቁጥር 496
ላለማድረግ ሰበብ አይጠፋም!
ግዴታህን ላለመፈጸም ሰበብን አትፍጠር፣ ግዴታህን ለመፈጸም ካልፈለግህ ምንጊዜም ቢሆን ሰበብ አይጠፋም። የሆነ ያልሆነውን ሰበብ መፍጠር ከቶ አይበጅም። ስለዚህ ሰበብን ሳታበዛ የሚገባህን ተግባር ፈጽም።
ከፍኖት መጽሐፍ
የእግዚአብሔር መልካምነት
አምላኬ ሆይ! ልክ ሌላ የተፈጠረ ሰው የሌለ እስኪመስል ድረስ እያንዳንዳችንን ትንከባከባለህ፤ እያንዳንዳችንንም እንደምትንከባከበን ሁሉ ደግሞ ሁላችንን ትጠብቃለህ! ያንተ ጥሩነት ሁሉን ቻይ ነው፡፡"
ቅዱስ አውጎስጢኖስ
ለቃላቶቻችን እንጠንቀቅ!
የክርስቶስን ብርሃን የማይሰጡ ቃላት ጨለማን ያስፋፋሉ፡፡
ብፅእት እማሆይ ተሬዛ
በእሳት መልዘብ!
ከእናንተ መካከል አንዱ፣ እሾሆች ካሉበት፣ የመንፈስ ቅዱስን እሳት በእነርሱ ላይ ይጣልባቸው፡፡ ሌላውም ጠንካራና የደነደነ ልብ ካለው፣ ይህንኑ (የመንፈስ ቅዱስን) እሳት በመጠቀም፣ ለስላሳና ልዝብ እንዲሆን ያድርገው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ከእግዚአብሔር ጸጋ ጋር መተባበር!
በሌላ ካልታገዙ በስተቀር ከፍ ብለው መብረር አይችሉምና የሰው ልጆች አንድ ክንፍ ብቻ ያላቸው መላእክት ናቸው የሚባል ነገር አለ። ጌታ ሆይ! ድፍረት አይሁንብኝና ያለኔ መብረር የማትፈልግ መሆንህ እንዲገባኝ ሌላኛውን ክንፍህን ስለምትደብቀው አንዳንዴ አንተንም አንድ ክንፍ ብቻ ያለህ አድርጌ አስባለሁ፡። (የኛ ትንሣኤ የሚቻለው በርሱ ነው፡ ጌታም የርሱ ትንሣኤ በኛ የሕይወት ትንሣኤ እንዲታጀብ ይፈልጋል)
ምንጩ ያልታወቀ
ወሮታ ቢስ እንዳንሆን!
ቅዱስ ፍራንቼስኮስ የክርስቶስን ሕማማት እያስተነተነ ያለቅስ ነበርና ለምንድነው እንዲህ የምታለቅሰው ብለው ሲጠይቁት፦ ክርስቶስ እንዲህ ስለኛ ተሰቃይቶ ሳለ ወሮታ ቢስ የሆኑና እሱን የማያፈቅሩ እንደውም ይህን ሁሉ ስቃዩን እንኳ የማያስቡ ሰዎችን ሳይ ያስለቅሰኛል ብሎ ይመልስ ነበር።
እውነተኛ ነጻነት!
እስቲ ማንም ላይ ምንም ዓይነት ነገር መፍረድ የግዴታ አስፈላጊ ነገር እንዳልሆነ አስብ፤ ሌላው ሰው ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑን ለመወሰን እንደማትመኝ አስብ።...በመጨረሻም <እኔ ማንም ላይ የማልፈርድ ነኝ ማለት ብችል ኖሮ> ብለህ አስብ፤ ይህ ቢሆን እውነተኛ ውስጣዊ ነጻነት ይኖርህ ነበር። እኛ ብዙ ጊዜ <እሱ እንደዚህ እሷ እንደዚያ>...እንላለን፤ ኢየሱስ ግን እኛን የሚለን ልክ ለጴጥሮስ ያለውን ነው፦ <አንተን ምን አገባህ፤ አንተ ተከተለኝ።>"
ሄንሪ ኖዌን
የተስፋችን ምክንያት!
"ኃጢአተኛ መሆናችን እንድናዝን ሲያደርገን፤ ኃጢአተኛ መሆናችንን ማወቅ ደግሞ ተስፋን ይሰጠናል።"
ፉልተን ሺን
የከፋ አረም!
የተዛባ ሚዛን ለአምላክ ፍቅር ብቻ!
የነፍስ ጠላት
ምስጋና ቢስነት ነው፤ ለርሷ ከተገቡ ነገሮች ሁሉ ባዶ ያስቀራታል፦ ጥሩ የመሆን ኃይሏን ይበታትናል፣ ጸጋዎቿን ያጎድላል። እንደ ደረቅና ሙቀታማ ነፋስ ሁሉ የነፍስን የቅድስና ምንጭነቷን፣ የምሕረት ጤዛዋንና የጸጋ ጅረትነቷን ያደርቃል።
ቅዱስ በርናርዶስ
ትሕትና ርግጠኛ የሆነ የብርታት ምልክት ነው።
ቶማስ ሜርተን (አባ)
የክርስቶስ ልደት ለኛ
ገና (ልደተ ክርስቶስ) ማለት በሕይወት ጉዟችን ላይ መቼምና የትም እግዚአብሔር አብሮን የሆነበት ሁኔታ ማለት ነው። አሳፋሪና ጥፋተኛነታችንን የሚያሳብቁብን የሚመስሉን እንዲሁም የማንደሰትባቸው ድርጊቶቻችን እሱ እንዳይነካቸው የምንፈልጋቸው ቦታዎቻችን በመሆን ከክርስቶስ ርቀን ለብቻችን ለመኖር ይታገሉናል፤ ከርሱ ልንደብቃቸውም እንፈልጋለን...ልደተ ክርስቶስ ግን ከርሱ ጋር እንደ አዲስ የምንቀራረብበትና ወዳጆች የምንሆንበት ወቅት ነው።
ሄንሪ ኖዌን (አባ)
ራስን መቅረጽ
በይፋ ከሌሎች ጋር በምንሆንበት ጊዜ ያለው ማንነታችን በግልና በድብቅ በምናደርገው ነገር ይቀረጻል፤...ድብቅ ድርጊታችንን ሌሎች ይወቁት አይወቁት ችግር የለውም፤ በዋነኝነት እኛ ራሳችን የምናደርገውን ስለምናውቅ ስለክፉው ድብቅ ምግባራችን ራሳችንን እንጠላለን። ይህን በመሰለ ውሸት ውስጥ መኖር ስንቀጥልም ልባችን ይደነድናል።...የሰው ልጅና የእምነት ትልቁ ቤተሰብ አባል እንደመሆናችን መጠን ከሰው ሁሉ ጋር ያለን ውስጠ ውስጣዊ ቁርኝት፤ ልክ ደም ውስጥ የተደበቀ አንድ የማይታይ ተውሳክ መላ ሰውነት ላይ ችግር እንደሚፈጥር ሁሉ ግላዊ ወይም ድብቅ የምንላቸው ድብቅ ምግባሮቻችንም በሰው ልጆች ሕይወት ላይም ችግር ይፈጥራሉ።
ሮናልድ ሮልሄይዘር (አባ)
አይቀሬው መለኮታዊ ወረራ!
በሕይወታችን መለኮታዊ ወረራ መቼ እንደሚካሄድ ነፍሳችን ራሷ በርግጠኝነት ማውቅ አትችል ይሆናል። ልክ ሌባ በሌሊት እንደሚገባ ሁሉ እግዚአብሔርም ወደ ነፍሳችን እንዲሁ ይገባል ማለትም ይቻላል። ስለዚህ የመቀበል ወይም ያለመቀብል ምርጫ እንጂ የነፍሳችን ፈጣሪ ባለቤት እሱ ነውና መምጣቱን በፍጹም ልንከለክለው አቅም የለንም። የሌሊቱን ጨለማ ፈቃድ ሳይጠይቅ የጸሐይ ጎሕ እንደሚቀድ ሁሉ፤ መለኮታዊው ሕይወትም የአእምሯችንን ጨለማ ሳያማክር ይወረናል።
ፉልተን ሺን (ሊቀ ጳጳሳት)
የመልካም ተግባሮች ሁሉ መጀመሪያ
ክፉ ድርጊቶቻችንን (ኃጢአቶቻችንን) መናዘዝ መጀመር ማለት ጥሩ ተግባር የማድረግ የመጀመሪያ ሥራችንን ጀመርን ማለት ነው።
ቅዱስ አውጎስጢኖስ
ውስጥህን ስማ!!!
የሕይወት ለውጥ በየት መጓዝ እንዳለብህ መንገድ የሚያሳይህን ውስጣዊ ድምጽ በማመን እንጂ በፍላጎት ብቻ የሚሆን ነገር አይደለም። ይህንን ድምጽ በቀጣይነት በመስማት (በመታዘዝ) ሕይወትህን ወደ አዲስ የነጻነትና የደስታ ሕይወት መለወጥ ትችላለህ።
ሄንሪ ኖዌን (አባ)
ምን እንደምታስብ አስብ
"ሃሳቦችህ ቃላት ይሆናሉና አስቀድመህ ተቆጣጠራቸው፤ ቃላቶችህም ወደ ተግባር ስለሚቀየሩ አስተውላቸው፤ ተግባሮችህም በተራቸው ልማድህ ስለሚሆኑ ጠብቃቸው። ልማዶችህ ደግሞ የአንተ ባሕርይ ስለሚሆኑ ዝም አትበላቸው። በመጨረሻም ባሕርይህ ፍጻሜህን ስለሚወስን ባሕርይህን በሚገባ መርምር።"
ብፅዕት እማሆይ ተሬዛ
ማንነትህ እግዚአብሔርን አይሸፍን!
"የእግዚአብሔርን ሥራዎች የምታወድስ ከሆነ፤ አንተም የእሱ ሥራ ነህና ራስህን ማወድስ አለብህ። በውስጥህ ያለውን እግዚአብሔር በማመስገን ራስህን ታመሰግናለህ በዚህም ትእቢተኛ ከመሆን ትድናለህ። የሆነ ዓይነት ሰው ስለሆንክ ሳይሆን በእግዚአብሔር የተፈጠርክ ስለሆንህ አመስግን፤ ይህን ወይም ያን ማድረግ የምትችል በመሆንህ ሳይሆን በአንተ እሱ ስለሚሠራ አመስግን። "
ቅዱስ አውጎስጢኖስ
ለመምጠቅ መላቀቅ
"ምንም ያህል ጥሩነት ያለው ነገር ቢሆንም እንኳ፤ ነፍሳችን ከተጣበቀችበት ነገር እስካልተላቀቀች ድረስ ከአምላክ ጋር ኅብረት የመፍጠር ነጻነት ላይ አትደርስም። ምክንያቱም የአንዲት ወፍ ማሰሪያ የተገመደ ጠንካራ ገመድ ይሁን ወይም ቀጭን የክር ማሰሪያ፤ ቁም ነገሩ አስሮ መያዙ ስለሆነ እሱ ሳይበጠስ መብረር አትችልም።"
ቅዱስ ዮሐንስ ዘመስቀል
"ከራእይህና ከተስፋህ ጋር እንጂ ከፍርሃቶችህ ጋር አትማከር። ስላልተሳኩልህ ነገሮች አትጨነቅ፤ ይልቁንስ በአንተ ያለውን ያልወጣ እምቅ አቅምህን አስተውል። ገና ልታደርጋቸው በምትችላቸው እንጂ ሞክረህ ባልሆኑልህ ሁኔታዎች ራስህን አትመዝን ።"
ዮሐንስ 23ኛው (ር.ሊ.ጳጳሳት)
ጊዜ ወይስ የፍቅር እጥረት?
ስለ እግዚአብሔር ነገር ለማሰብ (ለማስተንተን) ጊዜ የለኝም ማለት በፍጹም እውነት ሊሆን የማይችል ነገር ነው፤ አንድ ሰው ስለ አምላኩ በትንሹ ማሰብ በጀመረ ቁጥር ለአምላኩ አናሳ ጊዜ ይኖረዋል። ቅድስናችን የሚወሰነው ባለን የጊዜ ብዛት መጠን ሳይሆን ባለን የፍቅር ብዛት ነው።
ፉልተን ሺን (ሊ.ጳጳሳት)
ግድያ በቤታችን!
የግድያ ወንጀልን፣ በጦርነት መገዳደልን፣ በሰዎች መካከል ጥላቻ መንገሡን ስንሰማ አንደነቅ። እናት ልጇን ከገደለች የሌሎቹ መገዳደል ምን ይገርማል!
ብፅዕት እማሆይ ቴሬዛ
50 ጊዜ ሰማዕትነት!
የክርስቶስ ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ መሆናችንን የሚያሳይ ትልቅ ውሳኔ ፍጹም ላያጋጥመን ይችላል፤ ነገር ግን በየቀኑ 50 ጊዜ የክርስቶስ ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ መሆናችንን የሚያሳዩ ትናንሽ ውሳኔዎች ይጋፈጡናል!
ዴቪድ ሂዩዝ
ክርስቶስን መሳም!!!
ክርስቶስን በምድር በአካል ያዩት ምን ያህል ደስተኞች ናቸው ትሉ ይሆናል፤ ነገር ግን እስቲ ወደ መንበረ ታቦት ማዕድ ኑ! በወንጌል ሌሎች እንዳደረጉት ሁሉ እናንተም በዚያ እሱን ታዩታላችሁ፣ ትነኩታላችሁ፣ ስማችሁም በእንባ ታርሱታላችሁ። እንደ ቅድስት ማርያምም በውስጣችሁ ትሸከሙታላችሁ!
ቅ. ዮሐንስ አፈወርቅ
እጅህ፣ እግርህ...አካልህ የማነው?
ክርስቶስ አሁን የሰውነት አካል የለውም! በኔ አማካኝነት ይጸልያል፣ በኔ አካል ይሠራል፣ በዓይኖቼ ይመለከታል፣ በአንደበቴ ይናገራል፣ በእጆቼ ያደርጋል፣ በእግሮቼ ይራመዳል፣ በልቤም ያፈቅራል!
ቅድስት ቴሬዛ ዘአቪላ
ትልቁ ፍቅር እንዳያመልጠን! እጅህ/ሽ፣ እግርህ/ሽ...አካልህ የማነው!
በሕይወታችን ከሚይዙን ፍቅሮች ሁሉ የላቀ ፍቅር የሚይዘን ከእግዚአብሔር ጋር ስንፋቀር ነው። ወደር የለሽ ፍለጋም እሱን ለማግኘት የምናደርገው አሰሳ ነው፤ እንዲሁም ትልቁ ስኬታችን ሊሆን የሚችለውም እሱን ማግኘት ስንችል ብቻ ነው!"
ቅዱስ አውጎስጢኖስ
ሰማይ ምድር፤ ምድርም ሰማይ ስትሆን!
በቅዱስ ቁርባን ሰማይ ወደ ምድር ይወርዳል፤ የመጪው ጊዜ እግዚአብሔር የአሁን አምላክ ይሆናል። ጊዜ በዘላለማዊ መለኮታዊነት ይሰወራል።
ር.ሊ.ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛው
ጥሩ እምቢተኝነት!
ለጸሎት ጊዜ ይኖርህ ዘንድ አንዳንድ ነገሮችን እምቢ ማለት መቻል አለብህ።።
ፒተር ክረፍትማደግ ይችላል
ለወሳኝነት ወሳኝ መሆን!
ከባድ ቁርጥ ፈቃድ (ውሳኔ) የሚያደርግ ሰው እንኳ ብዙ ጊዜ ጎደሎ ሆኖ ከተገኘ ጥቂት ቁርጥ ፈቃድ ብቻ የሚያደርግ ወይም ምንም ውሳኔ የማያደርግ ሰው በመንፈሳዊ ሕይወት እንዴት ማደግ ይችላል?
ክርስቶስን መምሰል 1:19 ቁ.6
ራስን በመስጠት ራስን ማግኘት
ፍቅር በስተመጨረሻ ራስን በማግኘት የሚደመደም ሁለትዮሻዊ ራስን የመስጠት ሂደት ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን እናገኛለን እሱም እኛን ያገኘናል።
ፉልተን ሺን ሊ.ጳ.
የክርስቶስ ምክር
በሰዎች ዘንድ የከበሩና ቁም ነገር ያላቸው የሚመስሉትን ትተህ፤ በሰዎች ዘንድ የተናቀችውን ሰማያዊ ጠበብ እንድትገዛ መክሬህ ነበር።
ክርስቶስን መምሰል 3:32 ቁ.10
የልብህ በር እጀታ በራስህ እጅ!
"ለክርስቶስ የልብህን በር በደንብ አድርገህ ክፈትለት። አትፍራ!!!!"
ዮሓንስ ጳውሎስ 2ኛ
ክርስቶስን አትፍራ!
"ክርስቶስ ሁሉን ይሰጣል እንጂ ምንም ነገር አይወስድም።"
ር.ሊጳ. ቤኔዲክት 16ኛ
ጊዜ ማነው/ምንድነው?
"ጊዜ አንተ ነህ። አንተ ጥሩ ከሆንክ ጊዜም ጥሩ ነው፤ አንተ መጥፎ ከሆንክ ጊዜም መጥፎ ነው"
ወልደ ሕይወት
ፍቅርበተግባር
"ብዙ ሰዎች ስለ ፍቅርና ስለ የእግዚአብሔር ፍቅር ብዙ ይናገራሉ። እነሱ ግን የሚይፈቅሩትአንዳችምነገር የለም። ፍቅር በተግባር መገለጥ አለበት።"
ማዘር ተሬዛ
ሰማይን መንካት!
"ምንም እንኳ እግራችን ምድር ላይ ቢሆንም አፈጣጠራችን ሰማይንም እንነካ ዘንድ ነው።"
ሄንሪ ኖዌን (አባ)
ኳ..ኳ..ኳ..!!
"ደጃፏ ላይ ቆሞ እግዚአብሔር የማያንኳኳባት አንዲት ነፍስ እንኳ የለችም። ኳኳታው በፍርሃት፣ በተስፋ ቁርጠት፣ በጭንቀት፣ በባዶነት፣ የማያስደስተን በሚመስሉ ነገሮች ሁሉ ሊመሰል ይችላል፤ ግን ፀሐይ ሁሌ እንደምትፈነጥቅ ሁሉ እሱም በነፍሳችን ውስጥ ያለማቋረጥ ያበራል።"
ፉልተን ሺን(ሊ.ጳጳሳት)
ማንን ነው የምናምነው?
"ከወንጌል ውስጥ ደስ የሚልህን ብቻ መርጠህ የምታምንና የማይመችህን ደግሞ የማትቀበል ከሆነ ወንጌልን ሳይሆን ራስህን ነው የምታምነው ማለት ነው።"
ቅዱስ አውጎስጢኖስ
በሰላም ማሸነፍ
በብዙ ሺህ ተኩላዎች የተከበብን በጎች ብንሆንም እረኛችን ኢየሱስ ያድነናል፤ ነገር ግን እኛ ራሳችን ተኩላ ከሆንን የሚደርስልን የለም።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
“መበቀል የእግዚአብሔር ፋንታ ነው፤ ክፉውን በመልካም አሸንፉ እንጂ በክፉ አትሸነፍ”ሮሜ 12
የሚያስደስተን ምንድነው?
እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! የአንተን ጣፋጭነት የቀመሰ ሰው መልካም ያልሆነ ነገር ሊያስደስተው አይችልም።
ክርስቶስን መምሰል 3ኛ መጽ. ምዕ.34
ራሱን የማይፈልግ ሰው ካልሆነ በስተቀር እግዚአብሔርን የማይፈልግ ሰው የለም
ሰው ራሱ ያለብትን ሁኔታ በእውነት ፈልጎ ባገኘ ጊዜ እግዚአብሔር እንደሚያስፈልገው ይረዳል፤ ለእንደዚያች ዓይነት ነፍስ ደግሞ እግዚአብሔር ይበልጥ ራሱን ይገልጣል።
ፉልተን ሺን(ሊ.ጳጳሳት)
በማጨቅ መጨነቅ!
ባዶ መሆናችንን አንወደውም፤ ስለዚህም በነገሮች ራሳችንን እናጭቃለን ቀጥሎም እንጨነቃለን።
ሄንሪ ኖዌን (አባ)
የማፍቀር ጊዜን ያለማባከን
ሰዎች ላይ የምትፈርድ ከሆነ እነሱን ለማፍቀር ገና ጊዜ የለህም ማለት ነው።
ብፅዕት እማሆይ ተሬዛ
ባዶ ድኻ፤ ሙሉ ሀብታም የለም!
አንድ ሰው የመጨረሻ ድኻ ቢሆንም እንኳ ለሌላ ሊሰጥ የሚችለው ነገር አለው፤ እንዲሁም ሌላውም በጣም የተትረፈረፈው ሀብታም ቢሆንም ከሌላ ሰው መቀበል የሚያስፈልገው ነገር አለ።
ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ
ዕድፈተ ነፍስ
ፈቃደኛ ካልሆንን በስተቀር የማናችንም ነፍስ ዕድፋም ሆና አትቀርም።...እግዚአብሔር ሲፈጥረን የኛን ፈቃድ አልፈለገም፤ እኛን ለማዳን ግን ፈቃዳችንን ይፈልጋል።
ቅዱስ አውጎስጢኖስ
አብሮን የሚሰቃይ ወዳጅ - ክርስቶስ
እምነት በስቃይ ውስጥ አብሮን የሚራመድ ወዳጅን እንጂ ከስቃይ መወጣጫ መሰላልን ሊሰጠን ቃል አይገባልንም።
ሮን ሮልሄዠር (አባ)
<<ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።>> ዮሐ.15:15
እውነተኛው ነጻነት
ራስን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር መስጠት የእውነተኛው ነጻነት ጎዳና ነው።
ቤኔዲክቶስ 16ኛው
ይመለከተኝ ይሆን!
ከሕይወት ልምዴ አኳያ እንዲህ ማለት እችላለሁ፦ ስለ መጪው ሕይወቱ ይበልጥ የሚጨነቅና የሚረበሽ ሰው በዚች ሕይወቱ ምን ማድረግ (ምን መሆን) እንደሚገባው የማያውቅ ሰው ነው።
አንቶኒ ዴ ሜሎ (አባ)
<<በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን።>>ሮሜ 14:8
ሞት - ሁለተኛ ዙር ሕይወት!
በሞታችን ጊዜ ከዚች ዓለም ጋር ያለን ግንኙነት አከተመ ማለት አይደለም፤ ይልቁንም የመጀመሪያው ግንኙነታችን ተፈጸመ ማለት ነው።
ካርል ራህነር (ኢየሱሳዊ ካህንና ከ20ኛው ክ.ዘ. የነገረ መለኮት ሊቆች አንዱ)
<<የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን።>>(1ቆሮ.15:49)
ደስ የሚል ትሉኛላችሁ ግን አትወዱኝም
ጀርመን ውስጥ በሚገኝ አንድጥንታዊካቴድራል ውስጥ ብዙክፍለ ዘመናት ያስቆጠረ ጽሑፍ ይገኛል፤ እንዲህ ይነበባል፦
ክርስቶስም እንዲህ ሲል ተናገረ፦
መምህር ትሉኛላችሁ ነገር ግን የምላቸሁን አታደርጉም
ብርሃን ትሉኛላችሁ ግን አታዩኝም
መንገድ ትሉኛላችሁ ግን አትመላለሱብኝም
ሕይወት ትሉኛላችሁ ግን አትመኙኝም
ሊቅ ትሉኛላችሁ ግን አትከተሉኝም
ደስ የሚል ትሉኛላችሁ ግን አትወዱኝም
ሀብታም ትሉኛላችሁ ግን ምንም አትጠይቁኝም
ዘላለማዊ ትሉኛላችሁ ግን አትፈልጉኝም
ቸር ትሉኛላቸሁ ግን አታምኑኝም
ጌታ ትሉኛላችሁ ግን አታገለግሉኝም
ኃያል ትሉኛላችሁ ግን አታከብሩኝም
በትክክል የሚፈርድ ትሉኛላቸሁ ግን አትፈሩኝም
ስለዚህ ብፈርድባችሁ በኔ ማሳበብ አትችሉም።
በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።>>ማቴ.7:21
<<ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ! ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፤ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።>>ማቴ.23:37-38
የኃይል ምንጭ
የማለዳ ቡናዬን ስጠጣና ዳዊቴን ስደግም ብርታቴ ሁሉ ይመለስልኛል።
(ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም...ማቴ.4:4)
ክርስቶስ ወንድማችን፤ ማርያም እናታችን...
አንድ ሰው ንጽሕት ማርያም እናቴ ናት ማለት የማይችል ከሆነ ክርስቶስ ወንድሜ ነው ማለትን አይችልም።
ቅዱስ ማክሲሚሊያን ኮልቤ
(ኢየሱስም እናቱንና ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን፦ አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት። ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን፦ እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት። ዮሐ.19:26-27)
ጠላትን መውደድ
መጽሐፍ ቅዱስ ጎረቤታችንን እንድንወድ ይነግረናል፤ እንዲሁም ደግሞ ጠላቶቻችንን እንድንወድ ያዘናል። ምናልባት ብዙ ጊዜ ሁለቱም አንድ ስለሆኑ ይሆናል።
ጄ.ኬ.ቼስተርቶን
ደጅ ጥናት
እውነት ዘወትር በደጅ ሆና የነፍሳችንን በር ታንኳኳለች፤ ደጅ ትጠናናለች።
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኒሳ
(እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።) ራእይ 3:16
ቅድስና
አብዛኛውን ጊዜ ክርስቲያኖች (ወንድሞችና እህቶች) እርስ በርሳቸው የልባቸውን ምስጢር ስለማይከፋፈሉ በቤተክርቲያን ውስጥ ቅድስና በመጥፋት ላይ ነው።
ካርዲናል ኒውማን
መልካም ነገርን አሁን ማድረግ
እኔ ካላደረግኩት ማን ያደርገዋል፤ አሁን ካልሆነ መቼ አደርገዋለሁ፤ ለራሴ ብቻስ ካደርግኩት ምን ይፈይዳል?
ረቢ ሂለል 110 ዓ.ዓ.-10 ዓ.ም.
ፈሪሃ እግዚአብሔር
ከፍቅር የተነሣ እግዚአብሔርን መፍራት አለብን እንጂ እሱን ከመፍራት የተነሣ ማፍቀር የለብንም።
ዣን ፒየር ካሙስ
ሥጋን ከመግደል አልፈው ነፍስን መግደል የማይችሉትን ሰዎች አትፍሩ...ማቴ. 10:28
በ16ኛው ክ.ዘ. የነበረው የእንግሊዙ ንጉሥ ሄንሪ 8ኛው የሮማው ር.ሊ.ጳጳሳት ከተክሊሉ እንዲፈቱት ቢጠይቃቸው እንደማይችሉ ባሳወቁት ጊዜ ንጉሡ የእንግሊዝ ቤተክርስቲያን(አንግሊካን) ራሷን የቻለች እንድትሆን ወሰነ። በዚህም ምክንያት በዚያን ወቅት ካቶሊክ የነበሩ ሁለት ካህናትን ያስጠራቸውና <<ካቶሊክነታችሁን ትታችሁ የአንግሊካን ቤ/ያንን ካልተቀበላችሁ ቴምስ ወንዝ ውስጥ እወረውራችኋለሁ>> ሲላቸው እነሱም <<እምነታችንን አንክድም፤ ብትፈልግ ግደለንና ወርውረን፤ በውሃ ይሁን በየብስ ግድ የለም፤ የሚገደን መንግሥተ ሰማይ መድረሳችን ብቻ ነው>> ብለው መለሱለት።
ሰው ምን ያህል ንብረት ሲኖረው ይሆን በቃኝ የሚለው ?
በአንድ ወቅት አንድ ከቤቱ አጠገብ ሰፊ ትርፍ ቦታ ያለው ሰው <<ሁሉ ያለውና ምንም የማያስፈልገው ሀብታም ካለ በፍጥነት ጎራ ይበል፤ ይህን ቦታ እሰጠዋለሁ>> የሚል ማስታወቂያ ጎላ አድርጎ በመጻፍ ለጠፈ። አንድ በጣም ሃብታም የሆነ ገበሬ በዚያ ሲያልፍ ጽሑፉን አየና ፈረሱን ቆም አድርጎ <<ይህ ጎረቤቴ እንዲህ ካሰበማ ያው በጣም ሃብታምና ሁሉ የተረፈኝ መሆኔን ሁሉ ያውቃል ስለዚህ መስፈርቱን ስለማሟላ፤ ለሌላ ጊዜ ሳልሰጥ ልንገርውና ልውሰድ>> በማለት ወስኖ ለባለማስታወቂያው ይነግረዋል። ባለማስታወቂያውም <<ሁሉ አለህ ወይ? ምንም የሚያስፈልግህ ነገር የለምን?>> በማለት ሃብታሙን ገበሬ ሲጠይቀው <<አዎን ይህንማ ሁሉም ያውቃል>> በማለት ይመልሳል። ባለማስታወቂያውም በመገረም <<ወንድሜ! ሁሉ ካለህ ታዲያ አሁን ምን እየፈለግክ ነው?>> አለው....።
የዓለም ዘግናኙ እስር ቤት - የራስ ልብ
ከእስር ቤቶች ሁሉ ዘግናኙ እስር ቤት በተዘጋ ልብ ውስጥ መኖር ነው።
ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ
ምክንያት የለሽ ምክንያት
እግዚአብሔርን ለመውደድ ሁለት ምክንያቶች አሉን፤ አንደኛ እሱን ማፍቀር ምክንያት የሚያስፈልገው ነገር ያለመሆኑ ሲሆን ሁለተኛም እሱን ማፍቀሩ ለኛ የበለጠ ነገር ስለሆነ ነው።
ቅ. በርናርዶስ ዘክሌርቮ
በያለንበት ቦታ ፍቅር የመሆን ጥሪ
የእኔ ጥሪ እናቴ በሆነችው ቤተክርስቲያን ውስጥ ፍቅር መሆን ነው...
ቅድስት ተሬዛ ዘሕፃን ኢየሱስ
መስቀል የሕይወት ምርኩዛችን
ረጅም ጉዞ የሚሄድ ሰው በትር እንደሚመረኮዝ ሁሉ ክርስቲያንም በሕይወት ጉዞው የክርስቶስን መስቀል መመርኮዝ አለበት።
ቅ. እንጦንዮስ ዘፓድዋ
የደጋግና የጥሩ ሰዎች ስቃይ ጥልቅ ትርጉም
አንድ ደቀመዝሙር መምህሩን <<መምህር በዚች ምድር ደጋግና ጥሩ ሰዎች ከክፉና ጨካኝ ሰዎች በላይ ለምን ይሰቃያሉ>> በማለት ጠየቃቸው፤ መምህሩም ሲመልሱለት <<ልጄ ሆይ ስማ እስቲ፤ አንድ ገበሬ ሁለት በሬዎች ነበሩት፤ አንዱ በሬ ወፈር ያለና ጠንካራ ሲሆን ሌላኛው ግን ኮስማናና ደካማ ነገር ነበር። ገበሬው ቀንበር መጥመድ ፈልገ፤ ታዲያ የትኛው በሬ ላይ ቀንበሩን የሚጭን የሚስልሃል>>አሉት። <<እሱማ ጠንካራው ላይ ነው>> ሲል በርግጠኝነት መለሰላቸው። በዚህ ጊዜ መምህሩ ቀበል አድርገው <<ስሙ ይመስገንና መሐሪ አምላካችንም እንዲሁ ነው የሚያደርገው፤ ዓለም ወደ ፊት ይራመድ ዘንድ ቅንበሩን በደጋግና በጥሩ ስዎች ጫንቃ ላይ ይጭናል>> በማለት ደመደሙ።
የትንሣኤ ሕዝብ!
ራሳችሁን ለተስፋ ቁርጠት አሳልፋችሁ አትስጡ! እኛ የትንሣኤ ሕዝብ ነን፤ ዝማሬያችንም ሃሌሉያ ነው!
ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ
ከፍቅር የሚበልጥ ሕግ የለም
ፍቅር ከሁሉም ሕጎች በላይ ነው፤ ስለዚህም ሁሉም ሕጎችወደ ፍቅር መምራት አለባቸው።
ቅዱስ ቪንቸንሶስ ዴ ፖል
ሕይወትን ለእግዚአብሔር ያለመሰሰት መስጠት
አንድ ሺህ ሕይወት ቢኖረኝም እንኳ ሁሉን ለእግዚአብሔር እሰዋለሁ፤ ሞትን በመፍራት እምነቴን አልክድም። አቋሜ ይኸው ነውና ከፈለጋችሁ ልትገድሉኝ ትችላላችሁ፤ ለእግዚ አብሔር መሞት ፈቃዴ ነው...
ቅዱስ ላውረንስ ሩይዝ ፊሊፒናዊ ሚሽነሪ ናጋሳኪ ጃፓን ውስጥ በሰማዕትነት ከመገደሉ በፊት የተናገረው። - 1929 ዓ.ም.
አጓጉልነት-ከንቱ
ግማሽ ቅዱስ መሆን አትችልም። ሙሉ ቅዱስ ነህ ወይም ደግሞ ከናካቴው አይደለህም።
ቅድስት ተሬዛ ዘሕፃን ኢየሱስ
ታዲያ እኔ ማነኝ
በጣም መሸሽ የምትፈልገውም ሆነ በጣም ለመቅረብ የምትናፍቀው ነገር ራስህን ነው።
አንቶኒ ዴ ሜሎ (አባ)
ክርስቶስ ሰበበ ቢስ አድርጎናል
ክርስቶስ በመንበረ ታቦት የሚገኘው ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ ቢሆን ኖሮ ንስሐን የሚፈልግ ሰው ሊያጣው የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር በቻለ ነበር፤ ነገር ግን አንድ ኃጢአተኛ ንስሐን ፈልጎ ለቅጽበት ታህል እንኳ ጌታን ማግኘት አልቻልኩም ከሚል፤ ክርስቶስ ራሱበቅዱስ ቁርባን መንበረ ታቦት ላይ ኃጢአተኛን ዘወትር በተስፋ መጠባበቅን መረጠ። እሱ ስለሚያፈቅረን በኛ ተስፋ አይቆርጥም፤ ስለዚህም በትዕግሥት ይጠብቀናል።
ቅዱስ ጴጥሮስ ጁሊያን ኤይማርድ
ክርስቶስ ሁለነገራችን!
ክርስቶስ ለኛ ሁሉ ነገር ነው። ከታመምህ ፈዋሽ ሐኪም፣ ከተጠማህ ምንጭ፣ ከደከምክ ኃይል፣ ሞትን ከፈራህ ሕይወት፣ ከተራብህም ምግብ ነው።
ቅ. አምብሮስዮስ
ማፍቀርን ከክርስቶስ መኮረጅ
·ትልልቅ ነገሮችን ማድረግ አንችልም፤የምንችለው ነገር ቢኖር ትናንሽ ነገሮችን በታላቅ ፍቅር ማድረግ ብቻነው።
·የተሰቀለውን ክርስቶስ ስንመለከት ምን ያህል እንደተፈቀርን ይገባናል፤ ቅዱስ ቁርባንን ስንመለከት ደግሞ አሁንም የፍቅሩን ቀጣይነት እንረዳለን።
ብፅዕት እማሆይ ተሬዛ
ትኩረት ለያንዳንዷ ቅጽበት
በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የምታልፍ እያንዳንዷ ቅጽበትና እያንዳዷ ክስተት በነፍሱ ውስጥ የሆነ ነገር ተክላ ታልፋለች።
ቶማስ ሜርተን
የጥላቻ መንሥኤ
ማንም ሰው መጀመሪያ ራሱን ካልጠላ በስተቀር እግዚአብሔርን መጥላት አይችልም።
ፉልተን ሺን (ጳጳስ)
ራስን መጠየቅ
በዘመናችን ብዙ ሰዎች ለኑሮ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች አሏቸው፤ ለኑሯቸው ግን ትርጉም የላቸውም (ምን እንደሚፈልጉ ያውቃሉ፤ ምን እንደሚያስፈልጋቸው ግን አያውቁም)
ቪክተር ፍራንክል
የተግባር ጉልበት
ወንጌልን ዘወትር ስበኩ፤ አንዳንዴም አስፈላጊ ከሆነ መናገርን ጨምሩበት።
ቅ. ፍራንቸስኮስ ዘአሲዚ
ታላቅ ፍቅር
የኛ ትልቁ ደስታ ሊሆን የሚችለው፤ በእኛ መስዋዕትነት መክፈል ሌሎቹ የተሻለ ነገር ማግኘት መቻላቸውን ስናውቅ ነው።
ፉልተን ሺን (ጳጳስ)
ነጻነት ኀላፊነት ነው
·በኃይልና ዓመፅ ለአንድ ኅብረተሰብ ፍትሕን ማምጣት አይቻልም፤ ዓመፅ ራሱ አመጣለሁ የሚለውን ፍትሕ ያጠፋዋል።
·ነጻነት ማለት የፈለግነውን ማድረግ የመቻል መብት ማለት ሳይሆን፤ ማድረግ የሚገባንን ማድረግ የመቻል መብት ነው።
·እውነተኛ ቅድስና ማለት ከዓለም መሸሽ ማለት አይደልም፤ ነገር ግን ወንጌልን በየአንዳንዷ የዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታና በኅብረተሰብ ውስጥ ለመተግበር የምናደርገው ጥረት ነው።
ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ
አሁን ማድረግ መጀመር
ወደፊት የተሻለና የተለወጠ መሆን ይችላል፤ ይህ እንዲሆን ግን ዛሬን መለወጥና የተሻለ ማድረግ አለብን።
ፒተር ማውረን
ለራስ ብቻ መኖር ኑሮ አይደለም
ጨው ለራሱ አይኖርም፤ ለራሱም ጨው መሆን አይችልም። በተመሳሳይ ሁኔታም ክርስቲያኖች ለዓለም(ለሌሎች) እንጂ ለራሳቸው አይኖሩም።
ቴሬንስ ፕሬንደርጋስት (ጳጳስ)
የመጣላት ችሎታቸውን ያላዳበሩ ሁለት አባቶች
በአንድ ላይ በሰላም የሚኖሩ ሁለት መነኮሳን አባቶች በአንድ ወቅት ሲጨዋወቱ አንደኛው ለሌላኛው መጣላትየሚባለው ነገርን እንደረሱ ሲነግሯቸው ሌላኛውም እኔም በፍፁም ረስቻለሁ ይሏቸዋል፤ እናም እስቲ እንደሌሎቹ እንሞክር ይባባሉና: በሉ እንዲህ እናድርግ ይህን ጡብ በመካከላችን እናስቀምጠውና እኔ ይህ የኔ ነው አይንኩ ስልዎት እርስዎ ደግሞ አይ የኔ ነው ብለው ውሰዱ ከዚያ መጣላት እንጀምራለን ማለት ነው ተባባሉና ተስማሙ።
ስለዚህም ጡቡን በመካከላቸው አስቀመጡና በተባባሉት መሠረት አንደኛው የኔ ነው እንዳይነኩ አሏቸው፤ ሌላኛውም አይ የኔ ነው ሲሉ የመጀመሪያው መነኩሴ በሉ የርስዎስ ከሆነ ጥሩ ይውሰዱት አሉና ሰጧቸው...በዚህ ሁኔታ የመጣላት ስንፍናቸውን አሳዩ።