እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዐቢይ ጾም ከጌታ ጋር በምደረ-በዳ

Jesus and womanዐቢይ ጾም ከጌታ ጋር በምድረ-በዳ

ባለፈው ጽሑፋችን “ዐቢይ ጾም” በሚል ርዕስ ለዐቢይ ጾም መንደርደርያ የሚሆን ንባብ አቅርበንላችሁ እንደነበር የሚታወስ ነው። (ይህንን ጽሑፍ ለማንበብ የሚከተለውን ማስፈንጠርያ በመጫን ማንበብ ይችላሉ ዐቢይ ጾም (ethiocist.org)) በዛሬው ጽሑፋችን ጌታ በመንፈስ ቅዱስ ወደ በረሃ የተወሰደበትን እና ዐርባ ቀን እና ዐርባ ሌሊት የጾመበትን መንፈሳዊ ጉዞ እንዳስሳለን። መልካም ንባብ!

ጌታ ኢየሱስ ዐርባ ቀን እና ዐርባ ሌሊት የጾመበት ግብረገብ እና መንፈሳዊ አቋም ፋይዳ በሰይጣን በተፈተነበት ወቅት በግልጽ ታይቷል። ነገር ግን ጌታ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ በረሃ ከመወሰዱ በፊት በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ የንስሐ ጥምቀት እንዳደረገ ማስታወስ ስለ ጌታ ጾም መሰረታዊ ግንዛቤ ያስጨብጠናል፤  ኢየሱስ ወደ ዮሐንስ የቀረበበት እና ከእርሱም እጅ የንስሐ ጥምቀት የተቀበለበት ትህትና የመንፈሳዊ ህይወት ሁሉ ቁልፍ ነው። ኢየሱስ ኃጥያት የሌለበት ሆኖ ሳለ ለኃጢአተኞች በምትሆን የንስሐ ጥምቀት ለመታጠብ በኃጢአተኞች መካከል ሰልፍ መያዙ በቀራንዮ ከመሰቀሉ አስቀድሞ የእያንዳንዳችንን ኃጢአት ለመሸከም በመካከላችን እንደቆመ መጥምቁ ዮሐንስ ራሱ “እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሟል” (ዮሐ 1፡26) እያለ ይመሰክራል። በዚህ ሰልፍ መካከል ከኃጢአተኞች ጋር መቆሙ፤ ጌታ ለምን እንደመጣ በግልጽ የሚያስረዳ ቁም ነገር ነው። በእግዚአብሔር ፊት ራስን እንደ ተነሳሒ ማቅረብ ራስን በእግዚአብሔር ምህረት ፊት ዝቅ የማድረግ የልጅነት መንፈስ እና ትህትና ነው። ኢየሱስ በዚህ የልጅነት እና የትህትና መንፈስ የንስሐን ሥራ በመፈጸም ከመንፈስ ቅዱስ ለሚመጣው መለኮታዊ ኃይል ራሱን ክፍት እንዳደረገ መመልከት እንችላለን።

የዐቢይ ጾም ዋነኛው ተልዕኮ በንስሐ ትህትና ራስን በእግዚአብሔር ፊት በእውነትና በመንፈስ በማቅረብ ከመንፈስ ቅዱስ በሚመጣው መለኮታዊ ኃይልና ተሐድሶ ለመሞላት ራስን ክፍት ማድረግ ነው። ኢየሱስ በኃጢአተኞች መካከል ሲቆም እና የእነርሱን ሕይወት ሲካፈል ለራሱ የተለየ ህግ አልሠራም፤ ይልቁንም የጽድቅን ነገር ደግሞ መፈጸም ይገባናል (ማቴ 3፡15) በማለት በትህትና በዮሐንስ ሊጠመቅ በሁሉ ፊት ግልጥ ሆኖ በዮርዳኖስ መካከል መቆሙ ዐቢይ ጾም ከራስ ጽድቅ እና ቅድስና ባሻገር በእግዚአብሔር ምህረት ተስፋ በማድረግ ከአብ ልብ ተነስቶ በኢየሱስ መስቀል በኩል ከሚፈሰው መለኮታዊ ምህረት በመንፈስ ቅዱስ እንጠመቅ ዘንድ የምንንበረከክበት የትህትና ዘመን መሆኑን የሚያመላክት የንስሐ ጥሪ ነው።

ይህ የኢየሱስ ትህትና ሰማያትን ከፍቷል፤ በዘላለማዊ አርምሞ ውስጥ የሚኖረውን እግዚአብሔር አብን “የምወደው ልጄ ይህ ነው” (ማቴ 3፡17) እስከሚል ድረስ ለምሥክርነት ጠርቷል፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በእርሱ ላይ እስኪወርድ ደረስ ትህትናው ስቦታል። ራስን በእግዚአብሔር ፊት በእውነተኛ ትህትና ዝቅ ማድረግ አብ የሕይወት ቃል እንዲናገር፣ ወልድ ሥጋ ለብሶ እንዲገለጥ፣ መንፈስ ቅዱስም ከሥጦታዎቹ ሁሉ ጋር እንዲወርድ እና ወደ ተጠራንበት ተልዕኮ እንዲመራን ያደርጋል። ስለዚህ ቅድስት ሥላሴን የምናነጋግርበት ቋንቋ እና ጥበብ፣ ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ መሥዋዕት አድርገን የምናቀርበው መባ ጌታ በዮርዳኖስ ያስተማረን የልብ ትህትና ነው። ዳዊትም በመዝሙሩ “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም” (መዝ 51፡17) እያለ ለዐቢይ ጾም የሚሆን መሪ ቃል ይሰጠናል።

ዐቢይ ጾም እንዲህ ያለውን የአምላክን ትህትና የምናሰላስልበት እና የምንለማመድበት የጸጋ ወቀት ነው። ይህ ትህትና ራስን ለመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ እና ተግባር ክፍት ማድረግ በመሆኑ መንፈስ ቅዱስ የሰውን ልጅ ከባሕርያዊ ማንነቱ ባሻገር ወደ መልዕለተ ባሕርያዊ ተልዕኮው ከፍ ያደርገዋልና የሰው ልጅ በህይወቱ በሚለማመደው የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ አማካኝነት የሚሆኑትን ነገሮች እያስተዋለ “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” (ሉቃ 1፡37) እያለ ይዘምር ዘንድ እነሆ የተቀደሰው የዐቢይ ጾም ጊዜ በደጅ ነው። ዐቢይ ጾም በኢየሱስ ላይ የወረደው ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዳችን ላይ እንዲመጣ እና እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ወዳለው ተልዕኮ እንዲወስደን፤ ለዚሁ ተልዕኮ በመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ሁሉ እንዲያስታጥቀን በጸሎት መብራታችንን አብርተን የምንጠባበቅበት የጸጋ ጊዜ ነው። የዚህ መብራት ዘይት ራስን መግዛት ሲሆን ይህም በጾም፣ በጸሎት እና በምጽዋት በተግባር ተገልጦ ይታያል። ጌታ ከዚህ የጾም ጊዜ በኋላ ለአገልግሎት እንደወጣ እና በአባቱ ላይ ባለው መተማመን ለሞትም እንኳን ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ እንዲሁ ከዐቢይ ጾም ባገኘሁት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ እንደ አዲስ ልጋፈጠው፣ በእግዚአብሔር ስም ልወጣበት እና በኢየሱስ ሥም ሥልጣን የአሸናፊነት ክንዴን ላነሳበት የምፈልገው የሕይወቴ ክፍል የትኛው ነው? ልሻገረው የምፈልገው ገደል፣ በላዩ ላይ የጌታን ስም በትር ላነሳበት የሚያስፈልገኝ ያስጨነቀኝ ቀይ ባሕር የቱ ነው? እነዚህን መሰል ጥያቄዎችን ማንሳትና ሕይወትን በሚገባ ማጤን ለዐቢይ ጾም የተሻለ መንፈሳዊ ዝግጅት እንዲኖረን ያግዛል።

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ አብ ዘወትር ከወልድ ጋር እንደሆነ፣ ወልድም ዘወትር ከአብ ጋር እንደሆነ ይናገራል (ዮሐ 14፡10-12)። ኢየሱስ የሚናገረውን እና የሚያደርገውን ሁሉ ከአባቱ ዘንድ ይቀዳ ነበር። የኢየሱስ የዕለት ተዕለት ህይወት ከአብ ፈቃድ ጋር የተናበበ እና ከአብ ሐሳብ ጋር የተገመደ ነው። ጌታ ወደ በረሃ ሲወርድ ከእርሱ እና ከአባቱ በስተቀር ማንም አልነበረም። እንግዲያውስ ዐቢይ ጾም በኢየሱስ በኩል በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ከአብ ጋር መሆን ነው። ኢየሱስ በጾሙ ውስጥ ራሱን መሉ በሙሉ ለአባቱ ዓላማ ዝግጁ እንደሚያደርገው እንዲሁ ጾም ነፍስን ለእግዚአብሔር ዓላማ ክፍት የሚያደርጋት መንፈሳዊ ኃይል ነው። ስለዚህ ደግሞ እያንዳንዳችን በመንፈስ ቅዱስ መረዳት ከኢየሱስ ጋር በአብ ዘንድ በምንሆንበት በዚህ በዐቢይ ጾም ወቅት ነፍስ በእግዚአብሔር አብ መጋቢነት፣ በእግዚአብሔር ወልድ ጸጋ እና በመንፈስ ቅዱስ ሰላም ስለምትሞላ እኛም ከጌታ ጋር በአንድ ድምጽ “እናንተ የማታውቁት የምበላው ምግብ አለኝ” (ዮሐ 4፡32) ለማለት እንችላለን።

ኢየሱስ ዐርባ ቀን እና ዐርባ ሌሊት በምድረ-በዳ ከአባቱ ጋር በነበረበት ጊዜ ከአባቱ ዘንድ የተማረውን ጥበብ የምናየው በጌተሰማኒ በአትክልቱ ሥፍራ በሞቱ ጽዋ ፊት ቆሞ “በፊቱ ወድቆ ሲጸልይ፤ አባት ሆይ ቢቻልስ ይህቺ ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን” (ዮሐ 17፡) በሚለው ጸሎቱ ለአባቱ ፈቃድ በተገዛበት እምነትና ትህትና ነው። ጌታ ከሞቱ በላይ የአባቱን ፈቃድ መፈጸም ተቀዳሚ ዓላማው እንደሆነ በግልጽ ማየት እንችላለን።ዳዊት በመዝሙሩ “በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህ እና ምርኩዝህ እንርሱ ያጽናኑኛል” (መዝ 23፡4) እያለ የዘመረውን ትንቢት ኢየሱስ በተጨባጭ በሥራ ላይ ሲያውለው እንመለከታለን። ከዚህ መረዳት በመነሳት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን።እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን” (ሮሜ 14፡8) እያለ ያስተምራል። ኢየሱስ እንዳደረገው የእርሱ ደቀ መዛሙርት ተብለን በጥምቀት ከእርሱ ጋር በሕማሙ፣ በሞቱ እና በትንሳኤ የምንካፈል ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ብርኀን ኢየሱስ ባለበት በአብ ዘንድ እኛም እንሆን ዘንድ ዐቢይ ጾም ሥጦታችን ነው። ሕይወታችንን ከአብ ጋር ማስተካከል፣ ከአብ ጋር መጀመር እና ከአብ ጋር መኖር እንማር ዘንድ ኢየሱስ ከእርሱ ጋር ወደ ምድረ-በዳ እንድንወጣ ይጋብዘናል።

 ዐቢይ ጾም ይህንን ሕይወት የምንለማመድበት እና ኢየሱስን እስከምንመስል የምንጋደልበት መንፈሳዊ ውጊያ ነው፤ ውጊያ ከሆነ ደግሞ የጠላት የመጀመርያው ስልት የጦር መሳርያዎችህን ማጣጣል ነው። ስለዚህ ጾም ልማድ ነው፣ ጾም የሚጠቅምህ እጅግም ነው፣ የምግብ ጾም ፋይዳ የለውም፣ ኢየሱስ ሥራህን ሰርቶልሃል ወ.ዘ.ተ የሚሉ ማስተባበያዎችን እንሰማለን። ጠላት መሳርያዎችህን ሁሉ ካጣጣለብህ በኋላ ባዶ እጅህን መሆንህን ሲያውቅ በመሉ ኃይሉ ይመጣብሃል። የዚያን ጊዜ መጽሐፍ እንደሚለው “የሁለተኛው ጥፋት ከመጀመርያው ጥፋት የከፋ ይሆናል” (ማቴ 27፡64)። ስለዚህ በዚህ አይነት ወጥመድ እንዳንያዝ እና ጠላት ባዶ እጃችንን እንዳይማርከን እንዴት መዋጋት እንደምንችል ያስተምረን ዘንድ ከእርሱ ጋር አብረን በበረሃ እንድንሆን ጌታ በዚህ ዐቢይ ጾም ጥሪውን ያቀርባል። ከጌታ ጋር የምንሆንበት ይህ የእርሱን ጥበብ እና ትህትና የምንማርበት የጸጋ ወቅት “በጌታ እና በኃይሉ ችሎት የበረታን ሆነን፣ የዲያብሎስን የሽንገላ ቃላት መቃወም እንችል ዘንድ የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ሁሉ የምንለብስበት” (ኤፌ 6፡11) የመታጠቅ ዘመን ነው።

 ዐቢይ ጾም የምንፈጽመው ሕግ እና ሰው ሠራሽ ሥርዐት ሳይሆን ከኢየሱስ ጋር በመንፈስ ቅዱስ ብርኀን የአብን ፊት የምናሰላስልበት ግብዣ የጽሙና ጥሪ ነው። መምህር ሆይ ወዴት ትኖራለህ? ለሚለው ጥያቄ ጌታ መልስ ሲሰጥ “መጥታችሁ እዩ” (ዮሐ 1፡40) ይላል። እርሱ ባለበት በዚያ እንሆን ዘንድ የኢየሱስ የሁልጊዜ ፍላጎት ነው (ዮሐ 14፡ 1-7) ዐቢይ ጾም ለዚህ ለኢየሱስ ፍላጎት የሚሰጥ ተግባራዊ ምላሽ ነው። ከእርሱ ጋር በአባቱ ዘንድ ለመኖር እና በመንፈስ ቅዱስ ለመዘመር አስቀድመን ከርሱ ጋር ለመኖር የምንችልበትን ጥበብ ዘወትር በአብ ዘንድ ካለው ከልጁ ጋር በምደረ-በዳ መለማመድ እንችል ዘንድ ዐቢይ ጾም እንደ ጸጋ ሥጦታ በደጃችን ነው። በዚህ የጸጋ ወቅት ኢየሱስ ለእያንዳንዳችንን መንፈሳዊ ሕይወታችንን የምንመራበት መሠረታዊ ጥበብ ያስተምረናል፤ ስለዚህ ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥምና ዐቢይ ጾም ለመምህሩ ጠቃሚ፣ አስፈላጊና የእግዚአብሔር ፈቃድ ያለበት ከሆነ ታዲያ ለደቀ መዝሙሩ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ማስተዋል ይገባናል።

ዐቢይ ጾም የተማሪነት፣ በጌታ እግሮች ሥር የመቀመጥ፣ የተሻለውን የምንመርጥበት ዘመን ነው። ጌታ በእነዚህ ዐርባ ቀናት ከጾመ በኋላ ፈታኝ ወደ እርሱ እንደመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ነገር ግን ኢየሱስ ፈታኙን እንዴት አነጋገረው? የፈታኙ ጥያቄ መሰረታዊ ይዘት እና የጥያቄው አቀራረብ የእኛ የዕለት ተዕለት የሕይወት ፈተና አይደለምን? እንግዲህ እነዚህን የፈታኙን ጥያቄዎች እንዴት እንመልስ? ጌታ እነዚህን ጥያቄዎች እንዴት መለሰ? የእርሱ መልስ ለእኛ መንፈሳዊ ህይወት የሚያስተምረን ቁምነገር ምንድነው? እነዚህን እና መሰል ጥያቄዎችን በቀጣዩ ጽሑፋችን የምንመለከት ይሆናል። ይቀጥላል...

ሴሞ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት