ክፍል 7- የአውጎስጢኖስ ጳጳስ መሆን
- Category: የቅዱስ አውጎስጢኖስ የሕይወት ታሪክ
- Published: Saturday, 12 September 2009 10:42
- Written by Super User
- Hits: 3861
- 12 Sep
የአውጎስጢኖስ ጳጳስ መሆን
እ.ኤ.አ. በ391 ዓ.ም. ገደማ አውጎስጢኖስ እየተዘውወረ ሂፖን ሲጎበኝ በሕዝቡ ፍላጎትና በእግዚአብሔር ፈቃድ ጳጳስ እንዲሆን ተመረጠ። እርሱ ግን ከሁሉ ተለይቶ በብሕትውና ኅቡእ ኑሮ መኖር ወስኖ ስለነበር ለዚህ ሢመት ብቁ አይደለሁም ይቅርብኝ፣ እለፉኝ በማለት ለመነ። ቆይቶ ግን የቀረበለት ጥሪ ከእግዚአብሔር መሆኑን በመገንዘቡ በ395 ዓ.ም. ካህን ሆኖ አራት ዓመት ካገለገለ በኋላ በካርታጅ ጳጳስ ፈቃድ የሂፖ ረዳት ጳጳስ ሆነ። ሸምግለው የነበሩትም የሂፖ ጳጳስ በዚያው ዓመት ስላረፉ አውጎስጢኖስ በትረ ጵጵስናን በመያዝ የሂፖ ቤተ ክርስቲያንን መምራት ጀመረ።
አውጎስጢኖስ ስለ ጵጵስናው የነበረውን ስሜት ያስተዳድራቸው ከነበሩ ምእመናን ጋር የተጋራበትን ዝነኛ ንግግሩ ውስጥ የሚከተሉትን ዓረፍተ ነገሮች እናገኛለን፦
“የተሰጠኝ ኃላፊነት ልገልጠው በማልችል መንገድ ዘወትር ያስጨንቀኛል፤ ማለትም ይህ ሥልጣን ለምን ለእኔ እንደተሰጠ ሳስብ እጨነቃለሁ። በውስጡ ለእናንተ ካለው የደኅንነት ጥቅም ይልቅ በእኔ ሥልጣን ውስጥ ባለው አስጊ ነገር የእኔ መማረክ ካልሆነ በጳጳስ ሥልጣን ውስጥ የሚያስፈራ ምንድነው? በአንድ በኩል እኔ በእናንተ ላይ ባለኝ ኃላፊነት ስጨነቅ በሌላ በኩል ደግሞ ከናንተ ጋር በምካፈለው እጽናናለሁ። ለእናንተ አቡን ነኝ፤ ከእናንተ ጋር ክርስቲያን ነኝ።…ሰፊና ጥልቅ በሆነ ባሕር ውስጥ በማዕበል እንደምንገላታ ነን። ነገር ግን በማን ደም እንደምንድን በምናስታውስበት ጊዜ ይህ ሃሳብ በጸጥታ ከባሕሩ ጠረፍ ያደርሰንል። እኔም ተግባራቴን በማከናውንበት ጊዜ በአገልግሎቶቼ ዕረፍትን አገኛለሁ። እኔ በእናንተ ላይ ከመሾሜ ይልቅ ከናንተ ጋር መዳኔ ይበልጥ ካስደሰተኝ የናንተ አገልጋይ ለሆንኩበት ዋጋ ያልተገባሁ እንዳልሆን ጌታ እንደሚያዘው እናንተን የበለጠ ለማገልገል እጥራለሁ።…”
ይህ ንግግሩ በምን ያህል የኃላፊነት ፍርሃትና በእግዚአብሔር ጸጋ የመተማመን መንፈስ በትረ ጵጵስናን እንደ ተቀበለ ያሳየናል። በዚህም ሁኔታ ከእግዚአብሔር የተሰጠው ኃላፊነት መሆኑን በመገንዘብ አውጎስጢኖስ የተሰጠውን አደራ በታላቅ ትጋት ለመወጣት በመጣር አገልግሎቱን በታማኝነት ፈጸመ። የማኅበረ ክርስቲያን መምህር በመሆኑም በቀን ሦስትና አራት ጊዜ ቃለ እግዚአብሔርን ያሰማ ነበር። ከዚህ ሁሉ ኃላፊነት ጋር እንደማንም ክርስቲያን የተቸገሩትን ለመርዳትና ለማጽናናት፣ የተጣሉትን ለማስታረቅ በቂ ጊዜ ነበረው።
በሰሜን አፍሪካ ውስጥ በየጊዜው በተደረጉት የጳጳሳት ሲኖዶሶች በሙሉ ልቡ ለቤተ ክርስቲያን ልዕልና ብርቱ ጥረት አድርጓል። ስለቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና አወሳሰን ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ በዘመናችን ያካተታቸውን መጽሐፎች ይዞ እንዲገኝ ውሳኔ በተላለፈባቸው ጉባኤዎች በብርቱ በመድከም ችሎታውን አበርክቷል። ቤተ ክርስቲያንን ይገጥማት የነበረ ልዩ ልዩ ችግር ስከ አጥንቱ ድረስ ጠልቆ የሚሰማው ሰው ነበር። ለዚሁም መፍትሔ የሚሆነውን ለማግኘት ባለው ችሎታውና ኃይሉ በሚገባ ተጋድሏል። የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማጥቃት የተነሡትን፣ ቅድስናዋንና ንጹሕ ትምህርቷን ሊያራክሱ ይሞክሩ የነበሩ መናፍቃንን ቸል ሳይል እንደ እሳት በሚነድ የእግዚአብሔርና የቤተ ክርስቲያን ፍቅሩ በብርቱ በመቃወም ያሸነፈ፤ በሐስተኞች ሥልጣናት ላይ የእምነት ጦርነትን ተጋፍጦ ድል የተጎናጸፈና በፈታኝና መሥዋዕትነትን በሚጠይቅ ሰዓታት ሁሉ ኃላፊነቱን በሚገባ የተወጣ ጳጳስ ነው።