ጥሪ
- Category: ቅዱሳን
- Published: Saturday, 23 May 2009 21:55
- Written by Super User
- Hits: 5300
- 23 May
ጥሪ ማለት የተወሰኑ ሰዎችን ከተለመደው አናኗር ልዩ ዓይነት የሕይወት ምርጫን እንዲከተሉ የሚያደርግ የእግዚአብሔር ፈቃድን መከተል ማለት ነው። ጥሪ የተለየ ተልእኮ ወራሽ ያደረገንን ሰማያዊው አብን የማፍቀራችን መገለጫ ምልክት ነው...።
ጄምስ አልበሪዮን (አባ)
የተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ማስታወቂያዎችን አስተውሉ፤ ወጣቶች ውስጣቸውን እንዳያዳምጡ በማድረግ ቁሳዊና ጊዜያዊ የሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጓቸዋል። የነገሮችንም ትርጉም ያዘበራርቃሉ፤ ስለዚህም 'በሕይወት ውስጥ የእኔ ሚና ምንድነው?' የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ለመመለስ ለወጣቶች አዳጋች ጊዜ ሆኗል።
አንዲት ካናዳዊት ምእመን
ጥሪ ማለት በርግጥ አጭር ገለጻ ሰጥተን ማለፍ የምንችለው ጉዳይ አይደለም። በተለያየ መልኩ ቃሉን ማስገባት ስለለመድን በድፍኑም ቀላል ሃሳብ ያለው ነገር አድርገን መደምደም የለብንም። የስልክ ጥሪ፣ የሠርግ ጥሪ፣ የምርቃት ጥሪ፣ አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪ፣ ሙያዊ ጥሪ፣ የምንኩስና ጥሪ፣ የክህነት ጥሪ፣ የተክሊል ጥሪ፣...የሞት ጥሪ። እነዚህና ሌሎችም መሰል አጠቃቀማችን ውስጥ በጣም የትርጉም ልዩነት ቢኖርም ጥሪ የሚለው ሃሳብ ግን ሁሌ አንድ የጋራ መልእክት አለው:- ከ...ወደ፣ ጠሪና ተጠሪን፣ ጥያቄና ምላሽን...ያመለክታል።
በዚህ ገጽ እኛ ልናነሣ የምንፈልገው ጥሪ ጊዜያዊ የሆኑ ጥሪዎችና በሞት ጥሪ ድምዳሜ የሚያገኙትን የጥሪ ዓይነቶች ሳይሆን በዚህች ምድር የሚጀመርና ሞት መሻገሪያው በመሆን ከጠሪው እግዚአብሔር ጋር የሚያስተሳስሩን ዓይነት የጸጋ ጥሪዎችን ነው። የሰው ልጅ በሙሉ ዐቢይ ጥሪ የቅድስና ጥሪ ነው። ይህም ሰው ጎደሎ ማንነቱን ከእግዚአብሔር ፍጽምና የሚሞላበት፣ ክርስቲያናዊ ሕይወቱን በእርሱ ፈቃድ መምራት ማለት ነው።
በቤተ ክርስቲያናችን ብሎም በአዲስ ኪዳን የምናገኛቸው ጥሪዎች አንድም በትዳሩ ዓለም በእግዚአብሔር እንደተሳሰሩ በመገንዘብ የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያኑ ግንኙነት ምልክት በመሆን የፍቅር፣ የትእግስትና የመቻቻል አብነት ሆኖ መኖር (ኤፌ. 5:22-ፍጻሜው) አሊያም ጌታ ራሱ ይህ ለሁሉም አልተሰጠም (ማቴ.19:12፤29 )ያለውን የድንግልና ሕይወት በመምረጥ በንጽሕና መኖር (ምንኩስና) ነው።
ሰው ሕይወቱን የጥሩ ነገሮች ሁሉ ጥሩ፣ የውብ ነገሮች ሁሉ ውብና የመጨረሻ እውነት ብሎ ላመነበት ነገር መስጠት ሲችልና የዚህም አጋዥና ፈጻሚ እግዚአብሔር መሆኑን ሲያውቅ ያ የጥሪ ሕይወት ነው። ትልቅ ነገርን ዓላማው አድርጓልና በእንደዚህ ዓይነት ሕይወቶች ውስጥ የሚነሡት ፈተናዎችም በተፈጥሯቸው ቀላል ሊሆኑ አይችሉም። ነገር ግን አሻግሮ የሚያየው ነገር ስላለ በጉዞ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ማዶ በሚያየው ጠሪው ኃይል ይሻገራል። ይህ እውነት የሚያስገነዝበንም ሌላ ቁምነገር ቢኖር ጥሪ አንድ ጊዜ ተጠርቻለሁ አከተመ የሚባልለት ነገር ያለመሆኑን ነው። ጠሪያችን ጋር ደርሰን ፊት ለፊት ማየት እስክንችል ድረስ ድንግዝግዝ ነው፤ ድንግዝግዝ ደግሞ በየጊዜው ማስተዋልና የተጠራንበትን አቅጣጫ ለመጠብቅ ዘወትር ዝግጁ ካልሆንን የጠሪያችንን መንገድ ሊያስተን ይችላል።