እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የሰሙነ ሕማማት ትርጉም

አንድ አፈ ታሪክ ስለ ሁለት ወንድማማቾች ይተርካል። አንደኛው ጥሩ ምግባር የነበረው ሲሆን ሌላኛው ግን ክፋትን ያዘወትር ነበር። አንድ ቀን ክፋትን ያዘወትር የነበረው ወንድም ወደ ቤት በሩጫ መጣ ካባውም በደም ነጠብጣብ ተጨማልቆ ነበር። ቤት እንደገባም እየተረበሸ "አሁን አንድ የዋህ ሰውን ገደልኩ" በማለት ለወንድሙ ነገረው። ባለ መልካም ምግባር ወንድሙም "እንካ፤ አንተ የኔን ነጭ ካባ ልበስ፤ እኔ ደግሞ ያንተን እለብሳለሁ። ከዚያም አንተ ከዚህ አካባቢ ተሰወር" አለው። ወንድሙ እንዳለው አደረገና ገዳዩ ወደ ሌላ ቦታ ሄደ። ወዲያውም ወደዚያ ቤት ወንጀለኛውን ለማሰር የመጡት ሰዎች በደም የተጨማለቀ ካባ የለበሰውን ልጅ ወደ እስር ቤት ወሰዱት፤ ወዲያውም የሞት ፍርድ ተፈረደበት። ልክ ከመሞቱ በፊት ለገዳይ ወንድሙ መልእክት ላከለት፤ እንዲህም አለው "የሰጠሁህን ነጭ ካባ አስታውስ፤ እኔ አንተን ለማዳን ባንተ ምትክ መሞቴንም እንዳትረሳ"።

ባጭሩ ይህ ጌታችን ለኛ ያደረገውን ይነግረናል፦ የኛን የኃጢአት ካባ እሱ ለበሰው።

"በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸክሟል። በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን"....

ማማትና ትንሣኤን በምናከብርበትና የርሱ ስቃይና ትንሣኤ የታሪክ ክፍል ብቻ ሳይሆን የያንዳንዳችን ግላዊ ሕይወት ክፍል እንዲሆን በምንጸልይበትና በምንዘጋጅበት ጊዜ በሥርዓተ አምልኳችንና ባጠቃላይም በአገራችን ክርስቲያናዊ ባህል የምንጠቀምባቸውን የዕለታት አሰያየምና ሥርዓቶች ይበልጥ ለመረዳትና በእውነትም ወቅቱን እንደየስያሜው ውስጣዊ ትርጉም ለመኖር ያግዘን ዘንድ በማሰብ ከhttp://eotc-mkidusan.org ድረገጽ በዲ.ቸሬ አበበ ከተዘጋጀው ጽሑፍ የሚከተለውን በቀጥታ ማካፈሉ ጠቃሚ ይሆናል ብለን ስላሰብን እንደሚከተለው አስቀምጠነዋል በማንበብ እንጠቀምበት:-

ሰሙነ ሕማማት ምንድን ነው?

ሰመነ ስምንት /ሳምንት/ አደረገ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ከዕለተ ሆሣዕና ሰርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ወይም ቀናት የሚያመለክት ነው፡፡ ሐመ ማለት ታመመ ማለት ሲሆን ይህም የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልእት አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡

መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም እግዚአብሔር ይፍታህ አይሉም የሳምንቱ ሥርዓተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመሆኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምጽ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መሆናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡

በሰሙነ ሕማማት የሚገኙ ዕለታትና ስያሜያት

ዕለተ ሰኑይ /ሰኞ/

ይህ ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ /የቤተ መቅደስ መንጻት/ እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ /ማር.11-11፣ ማቴ.21-18-22 ሉቃ.13-6-9/፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ «ወመሰለ ሎሙ ወይቤሎሙ አሐዱ ብእሲ በለሰ ቦቱ ውስተ አጸደ ወይኑ ወየሐውር ይንሣእ ፍሬሃ ወኢይረክብ ...»፤ ይህንም ምሳሌ አለ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም፡፡ በማለት በበለስ ስለተመሰለ የሰው ልጅ ሕይወት በማሰብ እንዲመለስ ንስሐ እንዲገባ በሕይወትም እንዲኖር እግዚአብሔርኢየሱስክርስቶስማሳሰቡን ያጠይቃል፡፡ ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለም በለሷ እንደጠወለገችና እንደተቆረጠች ሁሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቆረጡ እንዲሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባርን ነው፡፡ ሁላችን ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት ወምግባር አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንሆን ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል ልንጠብቅና ልንፈጽም ይገባናል፡፡ በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ዕለተ ሰኑይ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም እንዳይጠወለግ እንዳይደርቅ ወደ እሳትም እንዳይጣል ማድረግ ይገባናል፡፡

ዕለተ ሠሉስ /ማክሰኞ/

ይህ ቀን ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?» የሚል ነበር፡፡ /ማቴ.21-23-27/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ «ወይቤሎሙ ኢየሱስ አማን እብለክሙ ከመ መጸብሓውያን ወዘማውያት ይቀድሙክሙ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር»፤ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው እውነት እላችኋለሁ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል ሲል አስተምሯል፡፡ /ማቴ.21-28/

ዕለተ ረቡዕ

ይህ ዕለት ደግሞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ የምክር ቀን በመባል ይጠራል፡፡

ዕለተ ሐሙስ

ጌታችን ኢየሱስክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም «ወሶበ ኀፀቦሙ እገሪሆሙ ነሥአ አልባሲሁ ወረፈቀ ካዕበ ወይቤሎሙ አእመርክሙኑ ዘገበርኩ ለክሙ ... ወሶበ አነ እንከ ሊቅክሙ ወእግዚእክሙ ኀፀብኩክሙ እገሪክሙ ከማሁኬ አንትሙኒ ይደልወክሙ ትኅፅቡ እግረ ቢጽክሙ፡፡»፤ «እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ እንዲህም አላቸው ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን?... እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል ሲል ተናግሯል፡፡ /ዮሐ.13-12-20/፡፡

ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ በማለት ምሥጢረ ቁርባንን የመሠረተበት ወይም ራሱ ምስጢረ ቁርባንን የጀመረበት ቀን በመሆኑ የምስጢር ቀን ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ለማስቻል ነው፡፡ /ማቴ.26-26-29/፡፡

አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ በእነርሱ ጥበብና ፍላጐት ቀስ ብለው መጥተው የያዙበት ቀን ስለሆነ በዚህ ዕለት በለሆሳስ /ብዙ የድምጽ ጩኸት ሳይሰማ/ የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ስለሆነም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በዚህ የሕጽበት፣ የምስጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሓ ታጥበው ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንኦት ታስተምራለች፡፡

ዕለተ ዐርብ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ «አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» /1ቆሮ.1-18/፡፡ እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ /ማቴ.27-35-75/፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡ እነርሱ ግን እኛስ ምን አግዶን?  አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ፡፡ ተማክረውም የሸክላ ሠሪ መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ፡፡ /ማቴ.27-3-9/

የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት /ቁራኝነት/ ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን ስቅለቱን ሞቱን የሚያስቡበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የሕይወት መቅጫ አርማ ሆኖ ሳለ ለእኛ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት መልካሙ ዓርብ በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡

ቀዳሜ ስዑር

ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈበት ዕለት ነች፡፡ ይህች የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናትእግዚአብሔርን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ ስላረፈበት ሰንበት ዐባይ /ታላቋ ሰንበት/ ትባላለች ታላቋን ሰንበት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዘፍ.1፡3፡፡

ዕለተ ቀዳሚት /ሰንበት ዐባይ/ በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንደ ተደረገባት ሁሉ የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ የሆነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው ቸሩ አምላክ በመቃብር አርፎባታል፡፡ ማቴ.27፡61፡፡

በዚህች ዕለት ጌታችን ኢየሱስክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ «ቀዳሜ ስዑር » ትሰኛለች፡፡ ስዑር ቀዳሜ የተባለችው በዓመት አንድ ቀን ስለ ምትጾም ነው፡፡ ምክንያቱም እናቱ ድንግል ማርያም ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብ ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡

ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን በመጾምና በመጸለይ ዕለቷ እንዳከበሯት የተዋሕዶ ልጆች የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው የሚያከፍሉ /የሚጾሙ/ ለሁለት ቀን እህል ውኃ ሳይቀምሱ ያድራሉ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡

እግዚአብሔር ውጪ ሆነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ዘፍ.9-1-29፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡

«ቄጠማ»፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡

ክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲኦል /የሲኦል ቃጠሎ/ ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳሃን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፡፡አሜን፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት