እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ካህን የመለኮታዊ ምህረት አገልጋይ ነው

ካህን የመለኮታዊ ምህረት አገልጋይ ነው

የዕርቅ ምሥጢር የአዳኙ የኢየሱሰስ ክርስቶስ ተልዕኮ ነው፡፡ በዚህ ምሥጢር አማካኝት ክርስቶስ የምሕረት ሥጦታውን መስጠቱን ይቀጥላል፡፡ በምሥጢረ ኑዛዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በካህኑ ቃል እና ተግባር ውስጥ ሕያው ሆኖ ምሕረቱን ፈልጋ ወደ መንበረ ኑዛዜ ከመጣችው ነፍስ ጋር ይተዋወቃል፡፡

በዚህ ዓይነት የምሥጢረ ንስሐ አገልግሎት የዕርቅ በዓል ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እና በካህኑ በእንተ-ክርስቶሳዊ ተግባር ሰው ከአምላኩ ጋር ታርቆ በመልካሙ እረኛ ጥበቃ ሥር ይሰማራል፡፡ ይህ የመመለስ እና የመለወጥ ጉዞ የደስታ በዓል መሆኑን ኢየሱስ ያስተምራል (ሉቃ 15፡5-7፤ 9-10፤22-32)፡፡ በመሆኑም ዘላቂ የሆነ የዕርቅ አገልግሎ ሱታፌ የሚበረታታ እና አስፈላጊ ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ምሥጢረ ንስሐን የምታዝዝ እና የምትሰconfessionጥ ብቻ ሳይሆን በምሥጢረ ንስሐ ውስጥ የምትሳተፍም ነች፡፡ የዕርቅ ሱታፌ በመቀበል ራሷን ዕለት በዕለት በምሥጢረ ኑዛዜ ጸጋ የምታድስ ነች፡፡ ቤተክርስቲያን ሰው እና እግዚአብሔር በዕርቅ ምሥጢር እንዲገናኙ ድልድይ ከመሆን ባሻገር እርሷም በዚህ ምሥጢር የእግዚአብሔርን ምሕረት ሳታቋርጥ በመለመን ጉዞዋን የምሕረት ጉዞ አድርጋ ትቀጥላለች፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ኃጢአትን ይቅር እንዲሉ ሥልጣኑን በሰጣቸው ጊዜ የዚህ ምሥጢር አገልጋይ ብቻ ሳይሆኑ የዚህ ምሥጢር ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ካህናት ከምሥጢረ ንስሐ ጸጋ መራቅ አይገባቸውም፤ ይልቁንም ከእግዚአብሔር ጋር የታረቁ አስታራቂዎች መሆን ይገባቸዋል፡፡ ር.ሊ.ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “እረኞችን እሰጣችኋለሁ” በተሰኘው ድህረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ መልእክታቸው ካህናት የምሥጢረ ንስሐ አገልጋዮች ብቻ ሳይሆኑ ተጠቃሚዎችም እንዲሆኑ ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ፡፡

“ካህናት የምሥጢረ ንስሐ አገልጋዮች ሆነው መንፈሳዊ ኃላፊነታቸውን ሲፈጽሙ የምሥጢረ ንስሐ ጸጋ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ እግዚአብሔር ለኃጢአተኞች ያለውን ትልቅ ምሕረት በሕይወታቸው በመለማመድ የመለኮታዊ ምሕረት ምሥክሮች መሆን አለባቸው፡፡ የካህናት ሕይወት መንፈሳዊነት የበለጠ እየበለጸገ እና ሥር እየሰደደ የሚሔደው በምሥጢረ ንስሐ በሕይወታቸው የእግዚአብሔርን ጸጋ በተለማመዱ መጠን ነው፡፡ ካህን በምሥጢረ ንስሐ ካልታደሰ ውሎ አድሮ ፍሬ እንደማታፈራዋ የበለስ ዛፍ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ ካህን በተወሰነ ጊዜ በታላቅ እምነት እና ፍቅር ላይ የተመሠረተ ዘላቂ የንስሐ ሱታፌ ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ራሱን ለእግዚአብሔር ምሕረት አሳልፎ የሰጠ ካህን ሕይወት የሚያገለግለውን መንጋ ወደ እግዚአብሔር ምሕረት ይመራል” (John Paul II PDV 15:AA S 84 (1922),680)

የካህን ሕይወት በምሥጢረ ንስሐ ሲታደስ ሐዋርያዊ ፍሬው ይበዛል፡፡ ምሥጢረ ንስሐ የሌለበት ሕይወት ዘላቂ ሐዋርያዊ ፍሬ ሊኖረው አይችልም፡፡ የሐዋርያዊ ፍሬ ምንጩ የእግዚብሔር መለኮታዊ ምሕረት ነው፡፡ ስለዚህ ካህናት ይህንን ምሥጢር ለመካፈል እና ምሥጢሩን ለማክበር ከፍተኛ ሐዋርያዊ ዝግጅት ማድረት አለባቸው፡፡ ይህ የሰላም፣ የዕርቅ፣ የመመለስ እና የመደሰት ምሥጢር በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ተገቢውን ሥፍራ ይዞ መገኘት አለበት፡፡ ካህናት ሕዝቡን ለምሥጢረ ንስሐ በማዘጋጀት፣ መልካም ኑዛዜ እንዲያደርጉ ለመርዳት እና የእግዚአብሔርን ምሕረት በሕዝቡ መካከል ሕያው አድርገው ለመጠበቅ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ 

በመንበረ ኑዛዜ የሚገኝ ካህን እረኛ፣ አባት፣ መካሪ፣ መምህር፣ መንፈሳዊ ዳኛ እና የነፍሳትን ቁስል የሚያክም የነፍስ ሐኪም ነው፡፡ ንስሐ በሚፈጸምበት ጊዜ ካህን መንፈሳዊ ዳኛ እና የነፍሳት ሐኪም መሆኑን በማስታወስ የነፍሳትን ቁስል መፈወስ እና ወደ እግዚአብሔር መንገድ መመለስ ይገባዋል፡፡ ካህን የመለኮታዊ ምሕረት አገልጋይ ነው፡፡ በመሆኑም የእግዚብሔርን መለኮታዊ ምሕረት በሕዝቡ መካከል ለመመስከር ዘወትር ዝግጁ መሆን አለበት፡፡

ካህን አገልግሎቱን የሚፈጽመው በክርስቶስ ሥም እንደመሆኑ መጠን ልክ እንደ መልካሙ እረኛ የመንጋውን ሕመም በማድመጥ እና ቁስሉን በትኩረት በመመልከት አስፈላጊውን መንፈሳዊ መድኅን ሊሰጠው ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ አገልግሎቱ ራሱን በጸሎት በማዘጋጀት፣ ተናዛዡን በጥሞና በማድመጥ፣ ጥያቄ በመጠየቅ እና በመርዳት ዕለት በዕለት ራሱን ማሳደግ አለበት፡፡

ከዚህ ባሻገር ካህን ምሥጢረ ንስሐ ፈልገው ለሚመጡት ሁሉ ዘወትር ዝግጁ ሆኖ መቆየት አለበት፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወደ መንበረ ኑዛዜ የሚመራትን ነፍስ ካህኑ ለመቀበል ቦታው ላይ መገኘት አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ካህን የምሥጢረ ኑዛዜን ምሥጢራዊነት ማክበር እና መጠበቅ አለበት፡፡ ንስሐ በኢየሱስ ልብ ውስጥ የሚቀር በመሆኑ ካህን ይህንን ምሥጢር በልቡ መያዝ እና በታማኘነት መጠበቅ አለበት፡፡ በዚህ ዓይነት የንስሐን ምሥጢራዊነት እየጠበቀ ለነፍሳት በጸሎቱ ይታገላል፡፡

የሰው ልጅ በተፈጥሮው ወደ እግዚአብሔር የመመልከት ዝንባሌ አለው፡፡ ከእያንዳንዱ ሰው ኃጢአት እና የኑሮ ዘይቤ በስተጀርባ በሰው ልጆች ዘንድ ጥልቅ የሆነ ውስጣዊ ፍላጎት አለ፡፡ በማኅበረሰባችን መካከል ለምንም ነገር ግድ የሌላቸው የሚመስሉን ሰዎች ሳይቀሩ እግዚአብሔርን በብርቱ ይፈልጉታል፡፡ ይህ እግዚአብሔርን የመፈለግ ጥማት የሰው ልጅ ከአዳም ኃጢአት አስቀድሞ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው አንድነት እና ፍቅር ፍሬ ነው፡፡ ቅዱስ አውጉስጢኖስ ይህንን የፍቅር መፈላለግ በተመለከተ “ለአንተ ተፈጥረናልና አንተን ካላገኘ ልባችን እረፍት የለውም” ይላል፡፡ የሰው ልጅ ልብ ዘወትር በመንፈሱ ወደ እግዚአብሔር ይቃትታል፡፡ ነገር ግን ወደ ሥፍራው ደርሶ ከፈጣሪው ጋር በሙላት አንድ ይሆን ዘንድ ብርቱ ፈተና አለበት፡፡ ይህም የአዳም ኃጢአት ወይም የሰው ልጅ ወደ ኃጢአት ቀንበር ለመግባት ያለው ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ ነው፡፡ ይህ በአዳም ኃጢአት ምክኒያት በሰው እና በፈጣሪው መካከለው የመጣው መለያየት ውስጣዊና ምሥጢራዊ በሆነ መልኩ የመፈላለግ ገጽታም አለው ሰው እግዚአብሔርን እንደሚፈልግ ሁሉ እግዚአብሔርም የሰው ልጆችን ይፈልጋል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ እና የቤተክርስቲያን አስተምሕሮ እንደሚያረጋግጡልን እግዚአብሔር በራሱ አርአያ እና አምሳል ወንድ እና ሴት አድጎ የሰው ልጆችን ፈጥሯል (ዘፍ 1፡27)፡፡ የመጀመርያው ሰው አዳም ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም የሆነ አንድነት ነበረው፡፡ በጸጋ ውስጥ ይመላለስ የነበረው አዳም ፈቃዱ እና ነፃነቱ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም የተስማማ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ከእግዚአብሔር መለኮታዊ ፈቃድ ጋር ተስማምቶ የሚኖረው አዳም ሥጋው በነፍሱ ቁጥጥር ሥር ነበር፤ ሥጋው የነፍሱ ፈቃድ ተገዢ እና አገልጋይ ነበር፡፡ ከሰው እና ከተፈጥሮ ጋር የነበረው ግንኙነት በሰላም እና በፍቅር የተሞላ ስለነበር ፍጥረት በሙሉ ይገዛለት ነበር፡፡ ይህ መለኮታዊ የሕይወት ግብረገብ ፈቃዱን እና ፍላጎቱን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር በማስረከብ በጸጋ ውስጥ እንዲመላለስ የሚያስችል መለኮታዊ የቅድስት ሥላሴ ሕይወት ሱታፌ ፍሬ ነው፡፡ ነገር ግን በኃጢአት ምክኒያት ጸጋ ከእርሱ ዘንድ ሲጎድል እነዚህ ሁሉ መለኮታዊ ሥጦታዎች ከአዳም ሕይወት ውስጥ አልነበሩም፤ አዳም ሁሉን ነገር እንዳጣ ሲያመለክት “ራቁቴን መሆኔን አወቅሁ” (ዘፍ 3፡10) ይላል፡፡ ሥጋው እና ነፍሱን፣ ፈቃዱ እና ፍላጎቱ ሁሉ በአንድነት ሊሰማሙ አልቻሉም፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ ጎድሏልና ሥጋው በነፍሱ ላይ ጠላት ሆነ፡፡ አንዱ ለሌላው መገዛት ስለማይችል የሰብዓዊ ማንነቱ ኃይሎች ሁሉ በየራሳቸው መንገድ ለፍላጎቱ እርካታ ለማግኘት ሽኩቻ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይህ የተዛባ ዝንባሌ የኃጢአት ፍሬ በመሆኑ ዘሩ በአዳም ብቻ ሳያበቃ በእርሱ ዘሮች ሁሉ ዘንደ ደረሰ፡፡ ይህንን እውነታ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በራሱ የሕይወት ምሥክርነት ሲያረጋግጥ “እንዲህ ከሆነ ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፤ በእኔ የሚያድር ኃጢአት ነው እንጂ” (ሮም 7፡17)፡፡

የዚህ ፍለጋ ምንጭ በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የመፈጠራችን መለኮታዊ ሥጦታ ነው፡፡ እግዚብሔር ፍጥረትን ሁሉ የሚያፈቅር አምላክ በመሆኑ (መዝ 136፡ 4-6) ምሕረቱን ለሚፈልጉ ሁሉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ እርሱ በሰው ልጆች “እሺ” ላይ ተመርኩዞ ወደ እያንዳንዱ ሰው ውስጣዊ ሕይወት በመግባት የነፍስን ስቃዮች ሁሉ እየፈወሰ እና ኃጢአትን ይቅር እያለ ቀስ በቀስ ወደራሱ ይስበናል፡፡ እግዚአብሔር ስለ ምሕረቱ ለሙሴ ሲናገር “እግዚአብሔር መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽ፣ ባለብዙ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ምሕረትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል” (ዘፍ 34፡5-6) መሆኑን ይገልጣል፡፡ 

ስለዚህም እርሱ “ዓለምን እንዲሁ ወድዷልና በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይኖረው ዘንድ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል” (ዮሐ 3፡16)፡፡ ይህ እግዚአብሔር ወደር የሌለው ምሕረቱን የገለጠበት ሥጦታ ነው፡፡ ይህንን በማመላከት ቅዱስ ቬንሰንት ፓሎቲ “ወደር የሌለው ፍቅር፣ የማያልቅ ምሕረት የሆንክ አምላክ ሆይ በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የተገኘው የማያልቅ ጸጋ፣ ያልተገባሁ የነበርኩትን እኔን ከኃጢአቴ ሁሉ አነፃኝ፣ የሕይወቴ ደካማ ጎኖች ተለወጡ፤ እኔም የመለኮታዊ ምሕረትህን ፍቅር እና ጥልቀት ለዘላለሙ በደስታ እዘምራለሁ” ይላል፡፡

ፍጹም አምላክ እና ፍጹም ሰው የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ እና የእርቅ ድልድይ ለመሆን ያልተገባውን የሞት ፍርድ በመቀበል “ስለመተላለፋችን ቆሰለ፣ ስለበደላችንም ደቀቀ፣ የደህንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን” (ኢሳ 53፡5)፡፡ ስለዚህ በአንዱ በአዳም ምክኒያት ከእግዚአብሔር ጋር እንደተለያየን በአንዱ በክርስቶስ ምክኒያት ከእግዚአብሔር ጋር ታረቅን፡፡ የኢየሱስ የማዳን ሥራ የእግዚአብሔር የምሕረት ሥጦታ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር በልጁ መሥዋዕት ገልጧልና ሁሉም ሰው ከማያልቀው ከእግዚአብሔር ምሕረት እንዲሳተፍ ተጠርቷል፡፡

ሰው ይህንን ጥሪ ተቀብሎ ፍሬ ለማፍራት እምነት ያስፈልገዋል፡፡ እምነት ለእግዚአብሔር ሥራ ራስን ክፍት አድርጎ መቀበል፣ በማዳን ኃይሉ መታመን እና ራስን ለእርሱ አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ እምነት የእግዚአብሔር ነጻ ሥጦታ በመሆኑ በጸሎት ይህንን ሥጦታ ዕለት በዕለት ማሳደግ ይገባናል፡፡ በዚህ እምነት ወደ እግዚብሔር ምሕረት መቅረብ እና እግዚአብሔርን ወደ ሕይወታችን መጋበዝ ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ ያለን ፍላጎት የመጀመርያው ተግባራዊ እርከን ነው፡፡ እዚህ ላይ ለመለወጥ እና እግዚብሔርን ለማግኘት ቁርጥ ፈቃድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጽኑ ክርስቲያናዊ ውሳኔ በማድረግ በጸጋ ሕይወት ለማደግ በየዕለቱ ተጋድሎ ማድረግ የግድ ነው፡፡

 

ሴሞ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት