እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

  የጌታ ፈተናዎች በምድረ-በዳ

  የጌታ ፈተናዎች በምድረ-በዳ

R-1የማቴዎስ ወንጌል የጌታን ጾም በሚመለከት ከተቀሩት ወንጌሎች በተሻለ ዘርዘር ያለ መረጃ ያቀርብልናል፤ በዚህ መሰረት ማቴዎስ በወንጌሉ “አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ፤ ፈታኙም ወደ እርሱ ቀረበ...” (ማቴ 4፡3) እያለ ጌታ ከጾመ በኋላ በፈታኙ ፊት እንደቆመ እና ፈታኙም ጌታን ሦስት መሰረታዊ ጥያቄዎች እንደጠየቀው ይናገራል። የመጀመርያው ጥያቄ የኢየሱስን ነባራዊ ሁኔታ የሚመለከት መሠረታዊ ጥያቄ ነበር። ሰይጣን ወደ ኢየሱስ ፊት ቀርቦ ጥያቄውን ለማቅረብ የሞከረው ኢየሱስ “በተራበበት” ቅጽበት ነበር። ይህ ጊዜ ለሰይጣን የተወደደ ጊዜ ነው፤ የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት ወይም ደግሞ ለሰብዓዊ ፍላጎቶቹ ምላሽ ለመስጠት በሚፈልግባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ሰይጣን እነዚህን ገጠመኞች ለራሱ መልካም አጋጣሚ ይጠቀምባቸዋል። ለዚህም ነው ርዕሠ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ ክርስትያኖችን “በመጠን ኑሩ፣ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ በዙርያችሁ ያደባል” (1ኛ ጴጥ 5፡8) እያለ በንቃት እንድንመላለስ ይመክራል።

ጾም ይህንን የዲያብሎስን ሽንገላ መቋቋም የምንችልበት ኃይል ነው። በጾም ውስጥ የመንፈስ ነጻነት፣ የነፍስ የመለየት፣ የመወሰን እና ለጌታ የመለየት ዐቅም እጅጉን ያድጋል። በዚህም ነፍስ የጌታን ድምጽ የምትሰማበት እና ከእርሱም ጋር በጥልቀት የምትገናኝበትን ነጻነት ትጎናጸፋለች። ነፍስ በዚህ ነጻነት ስትመላለስ የፈታኙን ጥያቄ ከቀረበበት ነባራዊ ዐውድ እና አሁናዊ የሕይወት ሁኔታ ባሻገር ጥያቄውን ከዘላለም ሕይወት ጥሪዋ አንጻር እንድትመለከተው ዕድል ታገኛለች። ነፍስ ነገሮችን ከአሁናዊ ሁኔታዋ ባሻገር መመልከት እና መተርጎም እንድትችል ራዕይ ያስፈልጋታል፤ ጾም ራዕይ ይሰጣል! በመሆኑም ነፍስ ከጊዜአዊ ሁኔታዎቿ ባሻገር ወደ ዘላለማዊ ክብሯ እንድትመለከት፣ ከእሾህ አክሊሏ ባሻገር “እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ” (ራዕ 3፡11) ያለውን ጌታ ተስፋ የምታደርግበት እምነት ትጎናጸፋለች።

ሰይጣን ለጌታ ያቀረበለትን ጥያቄዎች ዘለቅ ብለን ስንመለከት የጥያቄውን ብዥታ ማስተዋል እንችላለን። ይህ ጥያቄ ተራ ጥያቄ አይደለም፤ ይልቁንም ጥያቄውን ከተጠየቀበት ዐውድ አንጻር ለመመለስ የሚሞክር ሰው ሁሉ የሚሰናከልበት ወጥመድ ያለበት ጥያቄ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን የምታረጋግጠው በምሥጢረ ጥምቀት በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከቤተ ክርስትያን ማኅጸን በተወለድክበት እምነት እንጂ “ድንጋይን ዳቦ” በማድረግ ችሎታህ አይደለም። ሰይጣን ማንነትህን እንድትጠራጠር፣ የሆንከውን እንዳልሆንክ፣ ያልሆንከውን ደግሞ እንደሆንክ አድርጎ በማቅረብ ወጥመዱን ይዘረጋል፤ ስለዚህም በጌታ ፊት ቀርቦ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ” እያለ ጥያቄውን ያቀርብለታል። ይህ የሰይጣን ጥያቄ በመሰረቱ አዲስ ጥያቄ አይደለም፤ ነገር ግን ሰይጣን በዔደን ገነት ለአዳም እና ለሄዋን ያቀረበው ጥያቄ ነው “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዟልን?” (ዘፍ 3፡1) ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሕግ፣ የእግዚአብሔርን ቃል እና የእግዚአብሔርን ድምጽ እንድንጠራጠር ግማሽ እውነት፣ ግማሽ ብርኀን፣ ግማሽ ተስፋ ይዞ ወደ እያንዳንዳችን ይመጣል። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በሚገጥሙን ፈተናዎች እና መሰናክሎች መካከል ይህንን የሰይጣንን ጥያቄ አቀራረብ ቆም ብለን ማስተዋል ከቻልን ብዙ ነገር እናተርፋለን።

አንተ በእውነት “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል” (ማቴ 4፡3) ይህ ጥያቄ የሞኝ ጥያቄ አይደለም፤ ይልቁንም በውስጡ የሰው ልጅን ፍጥረታዊ ማንነት አደጋ ውስጥ የሚጥል፤ በክፉ ጥበብ የተለሰነ ከውጪ ለዐይን ሲታይ ችግር ያለው የማይመስል ነገር ግን ወደ ውስጡ ሲገባ ዐይን የሚያሳውር ጨለማ ያለበት ስፍራ ነው። ሰይጣን ይህንን ጥያቄ የሚያቀርበው ጌታ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጾሞ ፍጹም በተራበበት ወቅት ነው፤ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን ቁምነገር የሰይጣን ጥያቄ ድንጋይን ዳቦ የማድረግ ተራ የተዓምራት ጥያቄ ሳይሆን፤ ይልቁንም በጌታ ርሃብ ላይ ያነጣጠረ፣ በሥጋዊ መሰረታዊ ፍላጎቶቻችን አንገብጋቢነት ውስጥ የተተከለ ጥያቄ ነወ። እንደ ሰው ባሉን ፍላጎቶች ባሕርያዊ በሆነው ነገር ብቻ አተኩረን መልዕልተ ባሕርያዊ የሆነውን ነገር ለማየት ቀና ማለት በማንችልበት አዘቅት ውስጥ አቀርቅረን እንድንቀር አሁናዊ ሁኔታችንን ሁሉ የሞት እና የሕይወት ጥያቄ አድርጎ የሚያቀርብ ጥያቄ ነው።

ድንጋይን ዳቦ የማድረግ ጥያቄ ከቁሳዊ ይዘቱ ይልቅ መንፈሳዊ ይዘቱ በእጅጉ የሰፋ ነው። በዚህ ጥያቄ ርሃብ የሥጋዊ ፍላጎቶቻችን ሁሉ መሪ ተደርጎ ይጠራል፤ በመሆኑም ሥጋ በራሱ መሠረታዊ ፍላጎቶች ውስጥ አባት እና መጋቢ የሆነ አምላክ ሳያስፈልገው በራሱ ለራሱ አምላክ እንዲሆን የቀረበ ጥያቄ ነው። በዚህም የእግዚአብሔር ልጅነት ጥያቄ የተሸሸገውን ነገር ለመሰወር የገባ እንጂ በመሠረቱ ሰይጣን ያቀረበው ጥያቄ ልክ ለቀደመው አዳም በዔደን ገነት እንዳቀረበለት ጥያቄ አይነት “ለራሴ ራሴ አምላክ ነኝ” የሚያስብል ጥያቄ ነበር። የእግዚአብሔር አምላካዊ አባትነት እና መጋቢነት ሳያስፈልገኝ “የዕለት እንጀራዬን” በገዛ እጄ የማሰናዳት ትንሽ አምላክ የመሆን ጥያቄ ነው፤ ለዚህም ነው ይህንን የመንፈስ አሰራር በተራ ቃላት ማፍረስ የማይሞከረው!። ስለዚህ ጌታ ወደ ብሉይ ኪዳን ተመልሶ የሙሴን ቃላት በመዋስ “ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት እንዳይኖር ያስታውቅህ ዘንድ አስጨነቀህ፥ አስራበህም፥ አንተም ያላወቅኸውን አባቶችህም ያላወቁትን መና አበላህ” (ዘዳ 8፡3) እያለ የሰይጣንን ሐሳብ በእግዚአብሔር ቃል ሲያፈርስ እንመለከተዋለን። ይህ የጌታ ተግባር ለመንፈሳዊ ውጊያ የሚያስፈልገንን ቁምነገር ሁሉ የሚሰጠን ቁም ነገር ነው፤ ጌታ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያስፈልገን እና ቀናችንን የምንገጥምበት ኃይል የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ያስተምረናል።

በእርግጥ የሰው ልጅ በእንጀራ መኖሩ ለባሕርዩ ተገቢና የተስማማ ነገር ነው፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በእንጀራ ብቻ አይኖርም! የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ቃል ተፈጥሯልና የኅልውናው መሠረት ከእግዚአብሔር አፍ የሚወጣው ቃል ነው። ይህ ቃል እግዚአብሔር በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ የሚናገረው አዲስ ትንቢት ሳይሆን እግዚአብሔር አምላክ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሁሉም ነገር ላይ ስለ ሁሉም ነገር የተናገረው ቃል፤ ጊዜው በደረሰ ጊዜ ሥጋ ለብሶ የተገለጠው ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። ስለዚህ ሙሴ በኦሪት ዘዳግም 8፡3 ላይ ውብ በሆነ መልኩ “አንተም ያላወቅኸውን አባቶችህም ያላወቁትን መና አበላህ” እያለ ሲናገር፣ ይህንን የሰውን ልጅ ርሃብ ሁሉ የሚያጠግብ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ እና ደም ያመላክተናል። ዛሬም ለርሃባችን ሁሉ ምግብ የሆነው ቅዱስ ቊርባን በመንበረ ታቦት ላይ አለልን።

የሰይጣን ጥያቄ በእግዚአብሔር አዳኝነት እና ትኩረቱን አድርጎ የተለመደውን ማደናገርያ ያቀርባል፤  “መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር” (ማቴ 4፡6) እያለ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ተጠቅሞ እምነትህ ሁሉ ባዶ እንደሆነ ሊያሳይህ ይሞክራል። ይህ የእግዚአብሔርን አዳኝነትን የሚመለከት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው የተፈጠርንበትን ዓላማ ጭምር የሚያዛባ ጥያቄ ነው። የተፈጠርነው እግዚአብሔርን የምንፈታተን ወይም የተናገረውን ነገር ሁሉ የሚያደርግ መሆን እና አለመሆኑን የምንመረምር መለኮታዊ አጣሪ ኮሚቴ እንድሆን ሳይሆን እንደ ልጅ በአባት ላይ ባለን መተማመን በነጻነት እንድንመላለስ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ጥያቄውን ሲመልስ “ጌታን አምላክህን አትፈታተነው” (ማቴ 4፡7) ተብሎ ተጽፏል እያለ ይመልሳል። በመሆኑም የተፈጠርነው እግዚአብሔርን ለመፈታተን አይደለም፤ እምነታችንም በእግዚአብሔር ላይ እንጂ እግዚአብሔር በሕይወታችን እንዲያደርግልን በምንጠብቀው ነገር ላይ አይደለም። እምነታችን እንደዚህ ቢሆን ኖሮ በእራሳችን እንጂ በእግዚአብሔር ማመን ገና አልጀመርንም ማለት ነው።

ፈታኙ ወደ ጌታ ቀርቦ ለመጨረሻ ጊዜ ያለውን ጥያቄ ያቀርባል፤ “ደግሞ ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ። ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው” (ማቴ 4፡8-9)። በዚህም ጥያቄው እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ሁሉ የሰውን ልጅ መሠረታዊ ፍላጎት እና ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገባውን ነገር ይቀላቅላል። የሰይጣን ትልቁ ስልት በምንፈልገው ነገር እና በሚያስፈልገን ነገር መካከል ግማሽ ብርኀን ያለው ብዥታ መፍጠር ነው።

የሰው ልጅ በኃጢአት በተጎዳ ባሕርይው ክብርን፣ ዝናን እና ባለጠግነትን ይፈልጋልና ሰይጣን ይህንኑ የሰውን ልጅ ፍላጎት ለራሱ ለሰው ልጅ ወጥመድ አድርጎ ያቀርብበታል። ሰይጣን እጅግ በምትፈልገው ነገር እንጂ በትርፍ ነገርህ አይመጣም! ስለዚህ የመጨረሻው ጥያቄ “ስገድልኝ” የሚል ነው! “ስገድልኝ” የሚለው ጥያቄ አምላክህን ምረጥ! ለማን እንደሆንክ ለይ! የሚል ጊዜ የማይሰጥ ጥያቄ ነው። አሁን የመጨረሻው ሰዓት ደርሷል፤ ሰይጣን በግልጽ ከመጨረሻ ፍላጎቶቹ ሁሉ ጋር ተገልጧል። አሁን እነሆ ሞት እና ሕይወት በፊትህ ናቸው፤ አሁን “ማን እንደ እግዚአብሔር” ብለን አሸናፊ የሆነውን ክንዳችንን የምናነሳበት ወይም ደግሞ በምርኮ የምንበዘበዝበትን ወሳኝ ምርጫ የምናደርግበት ጥያቄ ነው። ጌታ ለመጨረሻው ጥያቄ የመጨረሻ መልስ ሲሰጥ እንመለከተዋለን “ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና!” (ማቴ 4፡10)።

መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በኋላ ፈታኝ ጌታን ጥሎት እንደሄደ እና በእግዚአብሔር ቃል ፊት ሰይጣን ሥልጣን እንደሌለው ሲናገር “ያን ጊዜ ዲያቢሎስ ተወው፥ እነሆም፥ መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር” (ማቴ 4፡11) ይለናል። ኢየሱስ ከሰይጣን ጋር በነበረው ንግግር ለሰይጣን ጥያቄዎች የሰጠው ምላሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር ቃል የተወሰደ ነበር። በመሆኑም በዚህ በዐቢይ ጾም ወቅት ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ብሎም ከቅዱስ ቊርባን ጋር ያለንን ግንኙነት እንድንፈትሽ እንጋበዛለን። በእግዚአብሔር ቃል እና በቅዱስ ቊርባን ራሳችንን፣ ቤተሰቦቻችንን፣ ሀገራችንን እና ቤተ ክርስትያናችንን ሁሉ ለእግዚአብሔር መንግሥት ተስፋ መጠበቅ እንችላለን። የተባረከ የዐቢይ ጾም ጉዞ ይሁንልን!

ሴሞ

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት