ማርያምን ተመልከት፣ ጥራትም፣ አትጠፋምና!
- Category: እመቤታችን ማርያም
- Published: Friday, 21 August 2015 02:45
- Written by Super User
- Hits: 7333
- 21 Aug
ማርያምን ተመልከት፣ ጥራትም፣ አትጠፋምና!
ጌታችን በቅዱስ መስቀሉ ላይ ሳለ ለሰው ልጆች በሙሉ ሊሰጥ ያለውን ልዩ ስጦታ በሐዋርያው ዮሐንስ በኩል አደረገው፤ እናም «ይህችውልህ እናትህ አለ፣ ለእርሷም እነሆ ልጅሽ» በማለት በእመቤታችንና በተከታዮቹ መካከል ያለውን የልጅና የእናትነት ትስስር በጉልህ አሳየ። በዮሐ. 19፡26-27 ላይ እንደምናነበው ቅ. ዮሐንስም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ ቤቱ ወሰዳት። ከዚያን ሰዓት ጀምሮ እስከ እድሜያችን ብዙ ቅዱሳን አባቶችና እናቶች የዮሐንስ ወንጌላዊውን አደራ ተረክበው፣ የክርስቶስ በመሆናቸው እናቱንም እናታቸው በማድረግ በሕይወታቸው የእርሷን አብነትና አማላጅነት እንደ ትልቅ ትሩፋት ኖረው አልፈዋል። እመቤታችንም እናት የመሆን አደራዋን ልጅ ለሆኑላትና ለቀረቧት ከልጇ ጋር እያጣመረች ታቅፋቸዋለች። ከነዚህ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች አንዱና «የእመቤታችን ዘማሪ» በመባል የሚታወቀው የ12ኛው ክ.ዘ. ቅ. በርናርዶስ ዘክለርቮ (ሲታዊ) ይጠቀሳል (ክብረ በዓሉ ነሐሴ 14 ነው)። በልዩ የአጻጻፍና አገላለጽ ዘዬው ስለእመቤታችን ማርያም ልዩ መንፈሳዊ ሥልጣንና ርኅራኄ በመደነቅ ልጇንና ጌታዋን በታማኝነትና በፍቅር ባሳደጉ፣ በያዙ እጆቿ መያዝን እንመርጥ ዘንድና እርሷ እናታችን ክርስቶስንም ወንድማችን ይሆኑ ዘንድ እንዲህ አለ፡-
- ማርያም ማለት የባሕር ኮከብ ማለት ነው። እንግዲህ አንተ በዚህ ዓለም ውስጥ በደረቅ መሬት ላይ ሳይሆን በማዕበልና በአውሎ ነፋስ መካከል የምትሄድ ሰው ሆይ! በማዕበሉ እንዳትሰምጥና በአውሎ ነፋስ እንዳትወሰድ ከፈለግህ ዓይንህን ከዚህች ኮከብ ብርሃን አታርቅ።
- የፈተና ማዕበል ከተነሣብህ፣ የጭንቀት ዓለት ካጋጠመህ ወደዚህች ኮከብ ተመልከት፣ ማርያምን ጥራት።
- የትዕቢት፣ የቅናትና የክብር ፍላጎት አውሎ ነፋስ ካናወጠህ ይህችን ኮከብ ተመልከት፣ ማርያምን ለምናት።
- ቁጣ፣ ንፍገትና የሥጋ ፍትወት ነፍስህን ከረበሻት ማርያምን ተመልከት።
- በኃጢአትህ ብዛትና በኅሊናህ መቆሸሽ ምክንያት በእግዚአብሔር ፍርድ ቀን ደንግጠህ በኀዘንና በተስፋ መቁረጥ መስጠም ከጀመርህ ማርያምን አስብ፣ አስታውሳትም።
- በአደጋና በችግርህ ጊዜ፣ በጥርጣሬህም ጊዜ ማርያምን አስባት፣ ማርያምን ጥራት።
- እርስዋ ከአፍህ አትለይ፣ ከልብህም አትራቅ።
- የጸሎትዋን እርዳታ እንድታገኝ የሕይወት አርአያዋን ተከተል።
- እርስዋን ከተከተልህ መንገዱ አይጠፋህም፤ ከለመንሃትም ተስፋ አትቆርጥም። እርስዋን ካሰብህ አትሳሳትም፣ እርስዋ ከያዘችህ አትወድቅም።
- እርስዋን ከተጠጋህ አትፈራም፣ እርስዋ ከመራችህ አትደክምም። እርስዋ ወደ ልጅዋ /ወደ መንግሥተ ሰማያት/ ታደርስሃለች።