Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. የታላቋ ብሪታንያ ሐዋርያዊ ጉብኝት በሰላም ተፈጸመ

 

goodbye_from_pope_frontራድዮ ቫቲካን - ቅዱስነታቸው በታላቋ ብሪታንያ ያደረጉትን የ4 ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ትላንትና ወደ ቫቲካን ተመልሰዋል።
ሓዋርያዊ ጉብኝቱ እጅግ ማራኪና ስኬታማ እንደነበረና ሂደቱንም በሙሉ በአካል በብዙ ሺ የሚቆጠር ሕዝብ  እንደተከታተለው፤ እንዲሁም በቴሌቪዥን በኢንተርኔትና በሬድዮም በቀጥታ በብዙ ሚልዮን የሚቈጠር ሕዝብ እንደተከታተለው ብዙ የብዙኃን መገናኛ ገልጠዋል።
ቅዱስነታቸው  ቅዳሜ ዕለት በሃይድ ፓርክ ለንደን ከተማ ውስጥ ከ200 ሺ በላይ በሚሆኑ ምእመናን ታጅበው የካርዲናል ኒውማን የብጽዕና ሥርዓት የዋዜማ ጸሎትን ጥልቅ በሆነ መንፈስ ኣሳርገዋል።
በማግስቱ ጠዋትም ወደ ዊምብልዶን ፓርክ ከተጓዙ በኋላ
ወደ በርሚንግሃም በማቅናት የካርዲናል ሄንሪ ጆን ኒውማንን ሥርዓተ ብጽዕና ፈጽመዋል።
ይህንን ሥርዓት የፈጸሙበትን መሥዋዕተ ቅዳሴ ያሳረጉበት ቦታ ረንዳል በሚባለው የበርሚንግሃም ቀበሌ የሚገኝ ኮፍቶን ፓርክ ሲሆን  ይህ ሕዝባዊ መናፈሻ የኣትክልት ሥፍራ እስከ ሰባ ሺ ሰው የመያዝ አቅም ያለው ነው።
በዚሁ ሥርዓት ላይ ከ60 ሺ በላይ ምእመናን የተግገኙ ሲሆን ሥርዓቱ ከመጀመሩ በፊት የበርኒንግሃም ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ኣቡነ ቤርናርድ ሎንግሊ የእንኳን ደህና መጡ ሰላምታን አቅርበዋል።
ቅዱስነታቸው የካርዲናል ኒውማን ብጽዕናን ባወጁበት ጊዜ ከታላቋ ብሪታንያና ከአየርላንድ ለተሰበሰቡ 60 ሺ ምእመናን “የክቡር የእግዚአብሔር ኣገልጋይ ጆን ሄንሪ ካርዲናል ኒውማን ብጽዕናን እናውጃለን” በማለት የሚከተለውን የብጽዕና ኣውጅ ኣንብበዋል።
“የበርሚንግሃም ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ኣቡነ ቤርናርድ፤ ሌሎች በጵጵስና ውንድሞቻችን የሆኑ ጳጳሳት እና የብዙ ምእመናን ልመና በመቀበል እንዲሁም የቅዱሳንን ጉዳይ ከሚከታተል ማኅበር ጋር በመወያየት በሓዋርያዊ ሥልጣናችን ክቡር የእግዚአብሔር አገልጋይ የሰባክያን ማኅበር ካህን ጆን ሄንሪ ካርዲናል ኒውማንን ብጽዕና እናውጃለን። ከአሁን ወዲህ እንደ ብጹዕ ለአማላጅነት ይቀርባሉ፣ ዝክረ በዓሉም በየዓመቱ ጥቅምት 19 ቀን በቤተ ክርስትያን ሕግ መሠረት በተቋቋሙ ቦታዎች ይከበራል።” ብለዋል። ሕዝቡም ይህን እወጃ በመከተል በሆሆታና ብጭብጨባ ደስታውን ገልጧል።
ቅዱስነታቸው በቅዳሴ ወቅት ባሰሙት ስብከት ‘በብጹዕ ኒውማን ሕይወት ሕያው ምስክር የሆነ የአበ ነፍስ ቅድስናን እናገኛለን፤ በስብከተ ወንጌል ግብረ ተልእኳቸው በትምህርታቸው እና በደረሷቸው ጽሑፎች ይህንን ኣጉልተው ኣሳይተዋል፡ በኚህ አዲስ ብጹዕ የቅድስና ምንጭ የሆነውን የታላቋን ብሪታንያ የማስተማርና የጥልቅ ሰብኣዊ ጥበብ ባህል እንዲሁም ለጌታ ያላቸውን የጋለ ፍቅር ማግኘት እንደሚቻል ገልጠዋል።
የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መሪ ቃል ያደረጉትን ‘ልብ ለልብ ይናገራል’ የሚለው የካርዲናል ኒውማን መፈክር ምን እንደሚያስተምረን ሲገልጡ፤ ይህ መሪ ቃል የክርስትና ሕይወት የቅድስና ጥሪ መሆኑን ለመረዳት ያስችለናል እንዲሁም የሰው ልጅ ልብ ምንኛ ያህል ከእግዚአብሔር ልብ ጋር ሊገኛኝ እንደሚፈልግ ያብራራልናል፤ ብጹዕ ኒውማን ለጸሎት ታማኝ መሆን ቀስ በቀስ ወደ መለኮታዊ ሕይወት እንደሚያሻግረን ያስተምራል፤ ስለዚህ የኒውማን ትምህርት ክርስትያን ምእመን ለእያንዳንዳችን የሚሆን ዕቅድ ለሰጠን ጌታ እንዴት በውሳኔና በቊርጠኝነ ማገልግል እንድምንችል ያስተምራል”ብለዋል።
የኒውማን ትምህርት በመልእልተ ባህርያዊ ነገሮች ብቻ ሳይወሰን፤ አእምሮና እምነትም እንደሚገናኙና እንድሚረዳዱ ያብራራል፤ ቅዱስነታቸው ይህንን ሲገልጡ ‘ኒውማን መልእልተ ባህርያዊ ግልጸት (መለኮታዊ) በሰለጠነው ኅብረተሰብ ስላለው የእምነትና የአእምሮ ግኑኝነት ያስተማረው በጊዜው ለነበረችው ታላቅ ብሪታንያ ብቻ ሳይሆን ገና ዛሬም በመላው ዓለም ላሉ ሰዎች እያተማረና እየተብራራ ነው፤’ በማለት ከገለጡ በኋላ ስለትምህርትም ቢሆን የኒውማን ሥነ ሓሳብ ለካቶሊካውያን ትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚሆን መሠረታዊ የአእምሮ ግንባታ እንዳቋቋሙ ገልጠዋል።
በመጨረሻም ስለ ክህነታዊ ኣገልግሎት በተለይም ትናንትና ተዘክሮ በዋለው 70ኛ የእንግሊዝ ጦርነት ብጹዕ ኒውማን ያበረከቱትን በማስታወስ እሳቸውም የውግያውን ጊዜ እንደሚዘክሩት ከጠቀሱ በኋላ ለሕመምተኞች፣ ለድሆች እንዲሆም ለእስረኞች ያበረከትት ኣገልግሎት የማይረሳ መሆኑን ገልጠዋል።
የሥርዓተ ብጽዕና ቅዳሴ ከተፈጸመ በኋላ የመልአከ እግዚአብሔር ትምህርት ሲያቀርቡም ይህንን ከ70 ዓመታት በፊት በናዚ ጀርመንና በታላቋ ብሪታንያ መካከል የተደረገውን አሰቃቂና አሳፋሪ ጦርነት በማስታወስ ሁላችን ለሰላም መሥራት እንዳለብን አደራ በማለት ሁሉንም ፈጽመዋል።
የሥርዓተ ብጽዕና ቅዳሴ ከተፈጸመ በኋላ ቅዱስነታቸው የቅዱስ ፊሊፖ ኔሪ የግብረ ሠናይ ማእከልን ጐበኝተዋል። ይህ ማእከል ከላይ እንደተጠቀሰው በብጹዕ ኒውማን የተመሠረት ሆኖ ብዙ የእርዳታ ሥራ ያበረከቱበት ቦታ ነው፤ ብጹዕ ኒውማን ከአንግሊካን ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት ከተመለሱ በኋላ እስከ ዕለተሞታቸውም የተቀመጡት በዚህ ቦታ ነበር፤ ቅዱስነታቸው ወደ ማእከሉ በደረሱበት ወቅት የማእከሉ ኃላፊ ተቀብለዋቸውል፤ በቤተ ጸሎትም የግል ጸሎት ካሳረጉ በኋላ የብጹዕ ኒውማን መኖርያ ቤት የነበረውና አሁን ግን ቤተ መዘከር የሆነውን ክፍል ጎብኝተዋል።
ቅዱስነታቸው እንደገና ጉዞኣቸውን በመቀጠል ወደ ቅድስት ማርያም ኮሌጅ ኦስኮት በመሄድ 50 ከሚሆኑ የኢንግላንድ የዌልስና የእስኮትላንድ ጳጳሳት ጋር በመሆን ተመግበዋል፤ ከምግብ በኋላ ከጳጳሳቱ ጋር በመገናኘት ስለ ልዩ ልዩ የግብረ ተልእኮ ጉዳዮች ተናግረዋል።
በዚያኑ ምሽት በበርሚንግሃም ዓለም አቀፍ የአየር ማረፍያ የታላቋ ብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስተር ር. ሊ. ጳጳሳትን ስለጉብኝታቸው አመስግነው ቅድስናቸውም በበኩላቸው ስለተደረገላቸው አቀባበል በማመስገን ተለያይተዋል፤ በሮም ሰዓት ኣቆጣጠር ከምሽቱ 10.30 ቻምፒኖ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ በሰላም ገብተዋል።

 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።