Map St Joseph Cistercians

Top Panel

በመጽሐፍ ቅዱስ ዙርያ

በእናንተ ስላለው ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።  1ጴጥ. 3:15

በመጽሐፍ ቅዱስ ዙርያ የሚዘወተሩ ጥያቄዎች

ከዚህ በታች በጥያቄና መልስ መልኩ የቀረበው ትምህርት ሆሣዕና በሚገኘው ቅድስት ሥላሴ የሲታውያን ገዳም መነኮሳን የተዘጋጀ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ዙርያ በሚነሡ አንዳንድ ጥያቄዎች ላይ ያተኮረ ነው። አጠር ያለና ብዙ ነጥቦችን የሚዳስስ ቢሆንም እንኳ በምንም መልኩ ግን ሁሉን ያካተተ ነው ለማለት አንችልም። ስለዚህ በዚህ ትምህርት ውስጥ የተነሡም ሆነ ያልተነሡ አንዳንድ ነጥቦችን እንዳስፈላጊነታቸው በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደፊት ሰፋ አድርጎ የማየቱ ሁኔታ ይኖራል ብለን እናስባለን። ያንብቡት…

1-ከአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የጻፈው መጽሐፍ አለን? ሐዋርያትስ እንዲጽፉ አዝዟቸዋልን?

ጌታችን መጽሐፍ አልጻፈምም ሐዋርያትም እንዲጽፉ አላዘዘም። ነገር ግን የእርሱን ትምህርት እንዲያስተምሩና እንዲሰብኩ አዟቸዋል። በሰማይና በምድር ሥልጣን ሁሉ የተሰጠው እሱ (ማቴ.28:18) መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጥ ተስፋ ሰጠ፤ እርሱም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከቤተ ክርስቲያን ጋር እንደሚሆን አረጋግጧል።

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ብቻ ለደኅንነት በቂ ቢሆን ኖሮ ራሱ በቀጥታ በመጻፍም ሆነ ሐዋርያት እንዲጽፉ በማዘዝ መንገድን ባዘጋጀ ነበር። ለቤተ ክርስቲያኑ የሰጠው ትእዛዝ የርሱን ትምህርት እንድታስተምር ነው፤ ጽሑፍ የትምህርት አንዱ ክፍል እንጂ የትምህርት ሁሉ ድምዳሜ አይደለም።

2-ከሐዋርያቶች ውስጥ ስንቶቹ ወይም በአዲስ ኪዳን ከጌታ ዕርገት በኋላ ወዲያው የተነሡ ሰባክያን ሌሎች ጸሐፊዎች ዛሬ አዲስ ኪዳን የምንለውን መጽሐፍት ጻፉ?

ከ12ቱ ሐዋርያት መካከል አዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ መጻሕፍትን የጻፉ የተወሰኑ ናቸው። እነዚህም፦ከሐዋርያት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ይሁዳ፣ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ ሲሆኑ ከጌታ ዕርገት ኋላ ከተንሡ ሰባክያን ደግሞ ጳውሎስ ብቻ ነው አዲስ ኪዳን ውስጥ ጽሑፍ የተዉልን።

እያንዳንዱ እንዳሻው በግል የሚተረጉመው መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛ የእምነት መመሪያ ከሆነ ትምህርታቸውንና መልእክታቸውን አዲስ ኪዳን ውስጥ ሳይጽፉልን በማስተማርና በመስበክ ብቻ ዕድሜያቸው ያለፈ የጥንት ሐዋርያትም ሆኑ ከዚያ በኋላ የተነሡ ሰባክያን ሁሉ ከትክክለኛ መንገድ ወጥተዋል ማለት ነው። <<መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ>> የሚሉ ሰዎች አዎ የሚል መልስ ካልሰጡ ራሳቸውን ይቃወማሉ ማለት ነው።

3. ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት ቤተ ክርስቲያን አስተማሪ ነበረች ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ ቤተ ክርስቲያን?

<<እምነት ከመስማት ነው መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል ነው>> ሮሜ 10:17።

<<ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው፤ እነሆ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ>> ማቴ.2819-20።

<<ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ>> ማር. 16:15።

እነዚህ የጌታችን ትእዛዛትን ካስተዋልን <<መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ>> የሚለው የተወሰኑ ሰዎች  አመለካከት መሠረተ ቢስ መሆኑን ያሳያል። ምክንያቱም አዲስ ኪዳን እንደ መጽሐፍ ከመቀመጡ በፊት አስተማሪ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ነበረች፤ ይህም ማለት አዲስ ኪዳን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሲሆን ትምህርቷ ሁሉ ግን እሱ ውስጥ ይገኛል ማለት አይደለም።

4-ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱ እንዲያስተምሩ ባዘዛቸው ትእዛዝና በአዲስ ኪዳን መካከል መሠረታዊ ልዩነት አለን?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተላለፈውን ትውፊት ሁሉ ሐዋርያት እንዲያስተምሩ፤ ያዘዛቸውንም ሁሉ እንዲያስተላልፉ አዟቸዋል (ማቴ. 28:20)። ቤተ ክርስቲያን ጌታዋ የነገራትን ሁሉ ማስተማር አለባት (ዮሐ.14:26)። ነገር ግን አዲስ ኪዳን ራሱ የኢየሱስን ትምህርት ሁሉ እንዳልያዘ ይመሰክራል፦ <<ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር አለ፤ ሁሉም ቢጻፍ ለተጻፉት መጽሐፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ነበር ይመስለኛል>> ዮሐ.21:25።

በዚህ መሠረት <መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ> የምንል ከሆነ ከአዲስ ኪዳን ውጭ ምንም የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን የማንቀበል መሆናችንን እንመሰክራለን። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ሙሉውን እውነት ሳንይዝ ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት እምነት ተከታዮች ነን ማለት ያዳግታል።

 

5. አዲስ ኪዳን በቀጥታ ያልተጻፉ የክርስቶስ ሥራዎችና ትምህርቶች እንዳሉ ይጠቁማልን?

<<ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀመዛሙርቱ ፊት አደረገ>> ዮሐ.20:25።

እነዚህ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያልተካተቱ የክርስቶስ ብዙ ምልክቶች ሙሉ የሚያደርጋቸው ነገር ያስፈልጋቸዋል። ይህም ሐዋርያት በቃል ያስተላለፉት ትምህርት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተዘግቦ የምናገኘውና በክርስትና ታሪክም <ትውፊት> በመባል የሚታወቀው ነው። ይህ ቃል መሠረቱ የግእዝ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም የተሰጠ፣ የተላለፈ…እንደማለት ነው።

 

6. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያት ያስተማሩት ግን በአዲስ ኪዳን ያልተጻፈው እውነት ምን ሆነ?

ከላይ እንደጠቀስነው ይህን ያልተጻፈውን እውነት ቤተ ክርስቲያን በጥንቃቄ ይዛ እስካሁን ድረስ ትውፊት ተብሎ በሚታወቀው ታሪኳ አቆይታዋለች።

<<እንግዲያውስ ወንድሞች ሆይ! ጸንታችሁ ቁሙ። በቃላችንም ቢሆን በመልእክታችን የተማራችሁትን ትውፊት ያዙ>> 1ተሰ.2:15

<<ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን፤ ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ>> 2ጢሞ.2:2

ስለዚህ ሙሉ የክርስቶስን ትምህርት ለማግኘት አዲስ ኪዳን ብቻ አይበቃም። በአዲስ ኪዳን ብቻ የተመሠረተ እምነት ማደግና መገንባት ካለበት ትውፊት ያስፈልገዋል።

 

7. አዲስ ኪዳን እንደ አንድ መጽሐፍ መቼና የት ተዘጋጀ?

በ397 ዓ.ም. አካባቢ በሰሜን አፍሪካ በካርተጅ ጉባኤ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተዘጋጀ። ካቶሊክ ያልሆኑት ሁሉ አዲስ ኪዳንን ያገኙት ከዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ክርስቲያኖች መልክ  ያልያዙ ጽሑፎች ብቻ ነው የነበራቸው።

መጽሐፍ ቅዱስን ከዚች ቤተ ክርስቲያን የተቀበሉ ሁሉ ሌላውን ትምህርቷን ያለመቀበላቸው ሁኔታ ሊስማማ አይችልም።

 

8. አዲስ ኪዳን በመጽሐፍ መልክ ሳይዘጋጅ የቆየባቸው ብዙ ዓመታት ወቅት የአዲስ ኪዳን ጽሑፋት ሁኔታ እንዴት ነበር?

ከላይ ከተጠቀሰው ዓመት በፊት ብትን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በተለያዩ ካቶሊክ ምእመናን እጅ ይገኙ ነበር። በቤተ ክርስቲያን ላይ የነበረው ስደት የመጽሐፍቱን ትክክለኛነት መርምሮ በአንድ ላይ ለመጠረዝ አልፈቀደም ነበር። በ397 ዓ.ም. ይህ ሥራ ሊሠራ የተቻለው ንጉሠ ነገሥት ቁስጥንጢኖስ ክርስትና በግዛቱ በነጻነት እንዲዘወተር በ313 ዓ.ም. ፈቅዶ ሰላም በመስፈኑ ነበር።

ይህ ሁኔታ እንደገና የሚያሳየው ቢያንስ እስከ 400 ዓ.ም. ድረስ <መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ> የሚል እምነት መሠረት የሌለው መሆኑን ነው።

9. ቤተ ክርስቲያን ጥንት አዲስ ኪዳን መጽሐፍት እነዚህ ናቸው ብላ ስትወስን ያጋጠማት ሌላ ችግር ምንድን ነበር?

በወቅቱ ሌሎችም የተጻፉ ብዙ መጽሐፍት ስለነበሩ ዋነኛው ችግር የነበረው የትኛው መጽሐፍ እውነተኛ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የያዘ መሆኑን መለየት ነበር። ሆኖም ጥንቃቄ የተሞላው ጥናት በማድረግና ራሷ በሆነው ጌታ በመመራት ውሳኔ ላይ ደረሰች። በዚያን ጊዜም ቢሆን ብዙ ካቶሊካውያን ምሁራን የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋንና ታሪክን በማጥናት በቅድስት ምድር(እስራኤል) ጊዜያቸውን ያሳለፉ ነበሩ፤ መጽሐፍትን በመለየቱ ሂደት የነዚህ ምሁራን ሚናም ትልቅ ነበር።

በአሁኑ ጊዜ እንዳለው አመለካከት ቢሆን በዚያን ጊዜ የነበረች ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እነዚያን መጽሐፍት እያንዳንዱ ሰው በግሉ አንብቦ እንዲወስን መተው ነበረባት ማለት ነው። እንደዚያ ቢደረግ ኖሮ ዛሬ አዲስ ኪዳን የሚባል መጽሐፍ ባልኖረንም ነበር። የዚህም መዘዝ አንዲት በሁሉም ቦታ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን እንዳትኖር ያደርጋት ነበር።

 

10. የስህተት ትምህርት ከያዙት መጻሕፍት መካከል ሐቀኛና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉትን መለየት የማን ሥልጣን ነበር?

አስቀድመን እንደጠቀስነው በ397 ዓ.ም. በካርተጅ ባደረገችው ጉባኤ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በተሰጣት ያለመሳሳት ስጦታ በመጠቀም በመንፈስ ቅዱስ አነሣሽነት መጻፋቸውን ወሰነች። ቤተ ክርስቲያን ይህን ስታደርግ ያልተሳሳተች ከሆነ ዛሬም ቢሆን እምነትንና ሞራላዊ ሕይወትን በሚመለከት ስትወስን አትሳሳትም ማለት ነው። ይህ ስጦታ ባይኖራት ኖሮ አዲስ ኪዳን ባልኖረንም ነበር። ባለመሳሳቷም ምክንያት ዛሬ ተንሥቶ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ይህ ክፍል ትክክል አይደለም አስተካክላለሁ ለማለት የሚደፍር የለም። ስለዚህ ዛሬ በብዙ ስም ተለያይተው ለሚገኙ ካቶሊካውያን ያልሆኑ ወገኖች በሙሉ አዲስ ኪዳንን አዘጋጅታ ያቀረበች እርስዋ ናት።

11. እስከ 400 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ አዲስ ኪዳንን በግል እንደፈለጉ መተርጎም ይቻል ነበርን? የኅትመት መኪና እስከተገኘበት ጊዜስ የመጽሐፍ ቅዱስ ሂደት ምን ይመስል ነበር፤ ማንስ አስተላለፈው?

እስከ 400 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ አዲስ ኪዳንን በግል እንደፈለጉ መተርጎም አይቻልም ነበር፤ ምክንያቱም አዲስ ኪዳን የሚባል መጽሐፍ ራሱ እስከዚያ ዘመን ድረስ ስላልነበረ ማለት ነው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የኅትመት መኪና(ማተሚያ) እስከተጀመረበት 1440 ዓ.ም. ድረስ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንና ኋላም የተለዩ ኦርቶዶክስ መነኮሳን መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ በብራና ላይ እየገለበጡ አድካሚ በሆነ ሥራ ሕይወታቸውን እያሳለፉ ከዘመን ወደ ዘመን ይተላለፍ ነበር። በዚህ ሁኔታ የሚባዛው መጽሐፍ ቅዱስ በብዛት ሊሰራጭና ሰው እጅም ሊገባ ስላልቻለ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል በስዕል፣ በድራማና መሰል መንገዶች ታስተላልፍ ነበር። እንደፈለጉ የመተርጎሙም ዕድል ጠባብ ነበር። የኅትመት መኪና ከተገኘ በኋላ ግን ይህ ሁኔታ ተለወጠ። የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርጭት ጨመረ በዚሁ መጠንም በፈለጉት አቅጣጫ የመተርጎም ስህተት እየተስፋፋ መጣ። ቤተ ክርስቲያን ለመጽሐፍ ቅዱስ ቦታ የማትሰጥ ሆኖ ሲንገር መስማቱ በጣም ያሳዝናል፤ ምክንያቱም እሷ የመጽሐፍ ቅዱስን ዋጋ ስለምታውቅና ስለምታከብር ነው ለ1500 ዓመታት በአድካሚ ሁኔታም ቢሆን ጠብቃ ያቆየችው።

12. <<አንድ እምነት አንድ መንጋ አንድ እረኛ>> የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት <<መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ>> በሚል አባባል የተኩ ሰዎች ይህን ለማድረግ ማን ሥልጣን ሰጣቸው?

መልሱን በሐዋርያው ጳውሎስ አፍ እግዚአብሔር ይናገራል፦

<<ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፤ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።>> ገላ.1:8

 

13. በታሪክ በሰፋ ሁኔታ <<መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ>> የሚለውን አመለካከትና በየግሉ የመተርጎም ልማድ ያስፋፋው ሉተር መሆኑ ይታወቃል፤ ታዲይ ይህን መሰል አካሄድ ምን ውጤት አስከተለ?

አሁንም መልሱን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት።

<<ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሱበት ዘመን ይመጥልና፤ ነገር ግን ጆሯቸውን የሚያሳክክ ስለሆነ እንደገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።>> 2ጢሞ.4:3

በዚህ ምክንያት የአንዱ ትምህርት ለሌላ ስለማይጥመው አዳዲስ ቡድኖች እንደ አሸን ይፈላሉ። ሉተራውያን ራሳቸው በ20 ቡድኖች ይከፈላሉ። መኖናይት በ17፣ ፕረስቢተራን በ10፣ ባፕቲስቶች በ23፣ ሜተዲስቶች በ20፣ ወንድማማቾች የሚባሉ በ8፣ የመጨረሻ ቀን ቅዱሳን በ7፣ አድቬንቲስቶች በ5፣…ወዘተ የተከፋፈሉ ናቸው። በዚህ ሁኔታ ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚለው መመሪያ ወደ መለኮትዊ እውነት ከማድረስ ይልቅ የራስን ፍላጎት ለማርካት ምቹ መሆኑን መረዳት ይቻላል።

14. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ቦታ የቱ ጋር ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የመለኮታዊ እውነት ምንጭ ነው። ነገር ግን ብቸኛ ምንጭ አይደለም፤ ሌሎች ሁለት ምንጮችም ትውፊትና በቤተ ክርስቲያን እስከ ዘመን ፍጻሜ ድረስ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ በርስዋ ዘወትር የሚያስተምረን ትምህርቶች ናቸው። ከነዚህ አንዱ ከጎደለ በስህተት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ መግባት ይከተላል።

 

15. በጊዜያችን መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ነው፤ ሁሉም ሊያገኘውም ይችላል። ታዲያ አሁን ያለው ችግር ምንድነው?

ችግሩ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን በራሱ መግለጽ ያለመቻሉ ነው። ይህን ሳይረዱ ሰዎች  መጽሐፍ ቅዱስን በየግላቸው በመተርጎማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያዩ ቡድኖች እየተከፋፈሉና እየተበታተኑ ይሄዳሉ (በዓመት በትንሹ 100 የፕሮቴስታንት ቡድኖች ይፈጠራሉ)። ይህም የሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ሥልጣን ያለው አካል ማስፈለጉን ነው። በግል መተርጎም እንደማንችልና ሥልጣንም እንደሚያስፈልግ አስረጅ ጥቅሶችን እንይ፦

<<በመጀመሪያ ይህን እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ለተረጉም አልተፈቀደም>> 2ጴጥ.1:20

<<የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፤ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፤ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።>> 2ጴጥ.3:16

<<እኔም እልሃለሁ አንተ ጴጥሮስ ነህ በዚች ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ። የገሀነም ደጆችም አይችሏትም>> ማቴ.16:18

<<ካህኑ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና ከንፈሮቹ እውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባል። ሰዎችም ከአፉ ሕግን ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል>> ሚል.2:7

<<ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ (ኢትዮጵያዊው አዛዥና ጃንደረባ)  ሰማና በእውኑ የምታነበውን ታስተውላለህን? አለው። እርሱም የሚመራኝ ሳይኖር እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው።>> የሐዋ. ሥራ 8:30-31

16. የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና አስተማሪ ማነው?

ብቸኛ አስተማሪው መንፈስ ቅዱስ ነው። እሱም የሚያስተምረውና የሚያስረዳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በመሠረታት ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ነው። የእግዚአብሔር ሕግና ቃል ማብራርያ በማን አማካይነት እንደሚመጣ ክርስቶስ እንዲህ ይላል፦

<<የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፤ እናንተን የጣለ እኔን ይጥላል። እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል።>> ሉቃ.10:16/ሚል.2:7

 

17. የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም ውጤት ምንድነው?

ብዙዎች አሉታዊ አመለካከት ቢኖራቸውም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርስቶስ ከመሠረታት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ አንድ መመሪያ አንድ እምነትና አንድ መሪ እንዲኖራት ለመሥራቿም መንፈስ ታማኝ ሆና እንድትኖር አድርጓታል (ዮሐ.17:20-23)።

በግላቸው መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡና የሚተረጉሙ ግለሰቦች መንፈስ ቅዱስ ወደ እውነት እንደሚመራቸው ይናገራሉ። እውነቱ ይህ ከሆነ በዓመት ቢያንስ ቢያንስ መቶ ቡድኖች ይፈጠራሉ? መንፈስ ቅዱስ ሰዎችን ወደ ተለያየ እምነት ይመራቸውልን? መንፈስ ቅዱስ መለያየትን ያመጣልን? ብለን መጠየቅም አለብን።

 

18. ካቶሊክ ያልሆኑ ቤተ ክርስቲያናትና ማኅበራት ለምን ተባዝቶ ይገኛሉ?

መልሱ በግላቸው መጽሐፍ ቅዱስን በተልያየ መንገድ ስለሚተረጉሙ ነው። በዚህም ምክንያት ብዙ ስሕትቶች ይፈጠራሉ፤ ምክንያቱም የመተርጎሙ ዘዴው ራሱ ስህተት ስለሆነ ነው። በዚህ ሁኔታ አንድ መንጋ አንድ እረኛ አንድ እምነትና አንድ ጥማቀት ሊኖር አይችልም (ኤፌ.4:5)።

19. ያለ መለኮታዊ መሪነት ካቶሊካዊት ቤት ክርስቲያን አንድነቷን ጠብቃ እስካሁን መኖር ትችል ነበር?

በመንፈስ ቅዱስ ባትመራ ኖሮ ካቶሊክ ያልሆኑት እንደሆኑ ሁሉ እርስዋም ትበታተን ነበር።

ካቶሊኮች መጽሐፍ ቅዱስን ያፈቅራሉ ያከብራሉ ይገለገሉበታልም። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻውን ክርስቶስ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን ሙሉ ማንነት አያመለክትም። መጽሐፍ ቅዱስ ክቡር መዝገብ ነው። ቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋን ለመፈጸም የምትገለገልበት መሣሪያ ነው፤ ማለትም ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ለመስበክ ከምትገለገልባቸው ከዋና ዋና መሣሪያዎቿ አንዱ ነው። ስለዚህ ከሁሉም ምንጮች በምታገኘው መለኮታዊ መሪነት ብቻ ነው አንድነቷን ጠብቃ የምትጓዘው።

 

20. ከሉተር በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ታትሞ ነበርን?

በ1440 ዓ.ም. የኅትመት መኪና ግኝት ወቅት በራሱ በዮሐንስ ጊተንበርግ መጀመሪያ ከታተሙት መጻሕፍት አንዱ የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ሉተር በ1534 ዓ.ም. ካሳተመው መጽሐፍ ቅዱስ በፊት 626 የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱሶች ታትመው ወጥተው ነበር። እነዚህም በልዩ ልዩ የአውሮጳ ቋንቋዎች የታተሙ ነበሩ።

በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በየቀኑ ይነበባል። በቤተ ክርስቲያን መንፈስ ሆኖ እያንዳንዱ ሰውም እንዲያነበው ቤተ ክርስቲያን ታደፋፍራለች። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱሶች በየዓመቱ ይሸጣሉ።

የአብያተ ክርስቲያናት የዘመናት ጉዞን በአጭር አገላለጽ ይመልከቱ (ጽሑፉን ይጫኑት)። 

ይትባረክ እግዚአብሔር!

የቅድስት ሥላሴ ገዳመ ሲታውያን መንኮሳን- ሆሣዕና።

 

 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት