እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘወረደ

ለዘላለማዊነት መገራት

michelangelos-last-judgment-2የዛሬው ወንጌል /ዮሐ. 3፡ 10-24/ መጽሐፍ ቅዱሳችን በሙሉ ሊል የሚፈልገውን እውነት ጭብጥ አድርጎ የያዘ እውነትን ያካፍለናል። ይህን ለመግለጽ ከሚጠቀምባቸውም ወሳኝ ቃላት መካከልም “ዓለም”፣ “ፍርድ”፣ “የእግዚአብሔር ፍቅር” የሚሉት ይገኙበታል። እነዚህ ቃላት ብዙ ጊዜ ግልጽ ሆነው በቀላሉ የማይረዱን ስለሆኑ በዕለታዊ ሕይወታችን ከክንዋኔዎች ጋር አስታርቀን ለመኖሩ ይከብደናል። ስለዚህ በወንጌሉ ይዘት መሠረት መልእክታቸውን ለማየትና ለክርስትናችን ምን ሊፈይዱ እንደሚችሉ እናስተንትን።

ዮሐ.1:10 ላይ “…ዓለምም የተፈጠረው በርሱ ነው፤ ዓለም ግን አላወቀውም” ይላል። ዓለም ሲል የማይያዝ የማይጨበጥ ነገርን ለመጥቀስ ወይም ደግሞ ግኡዝ የሆኑትን ድንጋይና ዛፍ ለማመልከት ሳይሆን በዓለም ኖረን ወደ ደኅንነት እንደርስ ዘንድ የተፈጠርን የሰው ልጆችን ለማለት ነው። ለዘላለማዊነት ያይደል ለጊዜያዊ ነገር የሚሮጥ፣ ራሱን ለተፈጠረበት ዘላላማዊነት የማይስገራ ሁሉ “ዓለም” በሚለው ጠቅላላ መጠሪያ ይካተታል። ክርስቶስን አውቀዋለሁ ወይ ብለን እናስብ። ብዙ ብዙ ነገር እናውቅ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ለማወቅ እናቅድ ይሆናል፤ ሆኖም ግን ክርስቶስን ለማወቅ ውሳኔውም ፍላጎቱም ከሌለን “ዓለም” የተባለው ክፍል መሆናችን ነው።

በእንደዚህ ዓይነት የርሱን አቅጣጫ ባልተከተለ ሕይወት እንኖር ዘንድ እርሱ አይፈልግምና ክርስቶስ ስለ ደቀመዛሙርቱ ሲናገር “እኔ የምጸልየው ለእነርሱ ነው፤…ለዓለም አልጸልይም።” አለ። ለርሱ ያለንን ፍላጎትና ፈቃድ ጭክን አድርገን ከቆለፍን ክርስቶስ ሊሰብረው ስለማይፈልግ አይጸልይልንም። በራሳችን ላይ ከፈረድንኮ እግዚአብሔር አይፈርድብንም፤ ይህ ማለት ግን አይወደንም ማለት አይደለም። ስለሚወደን ፈቃዳችንንና ነጻነታችንን አይጋፋም።

ዮሐንስ በ3:16 ላይ “እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለወደደ አንድ ልጁን ሰጠ፤ ስለዚህ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይኖረዋል እንጂ አይጠፋም። እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም ላይ ለመፍረድ አይደለም።” ይላል። የነፍሳችን ኀላፊነት በእጃችን ነው፤ እሱ እኛ ላይ ካልፈረደ ራሳችን ላይ የምንፈርደው እኛው ነን ማለት ነው። በርግጥ የመጨረሻ እጣ ፈንታችን በርሱ ቢሆንም፤ በየደቂቃዋ፣ በየዕለቷ የምንከተላት ፈቃዳችን ለፍጻሜያችን ወሳኝ ናት።

ይህ የዮሐንስ ወንጌል ምዕ.3:16 መላ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ጠቅልሎ ይዟልና “የመጽሐፍ ቅዱስ እምብርት” ወይም ማዕከላዊ ነጥብ ይባላል። ለምን ካልን ከላይ እንደተመለከትነው በአንድ በኩል እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን እጅግ ፍቅር፤ ከፍቅሩም የተነሣ ልጁን ለኛ መላኩንና ለዚህ የምንሰጠው ምላሽ ውጤትን ማለትም የዘላለም ሕይወትን ውርሻ ስለሚያስረዳ ነው። ይህ እውነት ዕለታዊ ሕይወታችንን ሊመራ ይገባል። በእግዚአብሔር “እጅግ” የተወደድን ነን፤ በሰው መወደድ የመጨረሻ ሙላት በእግዚአብሔር መወደዳችን ነው። የእግዚአብሔር ፍቅር በሰው መወደዳችንን አያጓድልብንም፤ ይልቁንም ሙሉ ያደርግልናል። የእግዚአብሔርን ፍቅር ሳንለማመደውና ሳንመልስ ስለሰው ፍቅር ብናወራ ሁሌም ጎዶሎና ከንቱ ነገር ብቻ መሆኑን ለማወቅ ምናልባት ትንሽ የጊዜ ሂደት ብቻ ነው የሚያስፈልገን። ስለዚህ ነፍሳችን ብሎም መላ ማንነታችንን የሚሞላው ይህ የላቀ የአምላክ ፍቅር ነውና ዛሬ “እጅግ እወድሃለሁ/እወድሻለሁ” ለሚለው ቃሉ መልስ እንስጠው።

የዛሬው ወንጌላችን ቁ.19-21 ላይ “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።” ይላል። ብርሃን-ጨለማ፣ ክፉ-እውነት የሚሉት ሃሳቦችም በትይዩነት ቀርበዋል። ሁለቱ ነገሮች በአንድ ላይ ሊገኙ አይችሉም። ብርሃን ወይም ጨለማ፣ ክፋት ወይም እውነት። 14:6 ላይ ክርስቶስ እኔ እውነት ነኝ ይላልና “እውነት” ለዮሐንስ ራሱ ክርስቶስ ነው። ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ ምክንያቱም ሥራቸው ክፉ ስለሆነ ነው ይላል። እንግዲህ ይህ ምርጫ ነው ወሳኝ ለውጥ የሚያመጣው ወይም ሕይወታችን ላይ እንድንፈርድ የሚያደርገን። ክርስቶስ እኔ ባለሁበት በኩል በብርሃኑና በእውነቱ ወገን ኑ ይለናል። የእግዚአብሔር ቃል እወጃ፣ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ግብ ሁሉ ለዚህ ነውና በምስጢራቱ አንጽቶና መግቦ ከርሱ ጋር እንራመድ ዘንድ ሊያበረታን ወደሚጠብቀን ኢየሱስ እንሂድ።

 

ቅበላ ጾም (ሕንጸታ) - ዘዘወረደ። መዝሙር- ቀነዩ ለእግዚአብሔር

 ዕብ. 13፡ 7-16 || ያዕ. 4፡6-17|| ሐዋ. 25፡13-27

 ምስባክ - ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት (2፡11-12)

 ዮሐ. 3፡ 10-24|| ቅዳሴ እግዚእነ


አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት