እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘክረምት 2ኛ - ጴጥሮስ ወጳውሎስ

ጴጥሮስ ወጳውሎሰ ዘክረምት2ኛ - ዘርዕ-ደመና- ጴጥሮስ ወጳውሎስ

{ምስባክ}አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ፤ ውስተ ኩሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ፤ ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ።-ንግግር ወይም ቃል የላቸውም፤ ድምፃቸውም አይሰማም፤ ነገር ግን መልእክታቸው ወደ ዓለም ሁሉ ይሰራጫል። መዝ. 18:3-4

2ጢሞ.4:1-22 2ጴጥ.1:12-18 ሐዋ. ሥራ 23:10-35 ሉቃስ 6:1-19

በዛሬው ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኃይልና ፈቃድ ምሶሶ የሆኗትን ታላላቅ ሐዋርያት ቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስ ታከብራለች። እንደ ወትሮው ለሁሉም ቅዱሳን እንደሚሆነው ሁሉ ማክበሩ ለነርሱ ክብር ለመጨመር ሳይሆን እያንዳንዳችን በክርስቶስ ፊት ያለንን ክብር የምናጤንበትን ሁኔታ ለማመቻቸትና በነርሱ ምሳሌና አማላጅነት ሕይወታችንን መምራት እንጀምር ዘንድ ነው። ቀላል ጥያቄ በመጠየቅ እንጀምር፦ ቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስ ለምንድነው ከተራ ሰውነት፣ ከከሃዲነትና ካሳዳጅነት ወደ ኃያል የክርስቶስ ተከታይነት የተለወጡት? አንድ ጥያቄን ቀላል የሚያሰኘው ያው ቀላል መልስ ስላለው ነው። ስለዚህም ቀላል መልሱ የነርሱ የለውጥ ምክንያትም ለእግዚአብሔር ጸጋ የመለሱት ክርስቶስን የማፍቀር ውሳኔ ነው።

 ጴጥሮስ ክርስቶስን ስለማፍቀሩ ክርስቶስ "የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! እነዚህ ከሚወድዱኝ ይበልጥ ትወድደኛለህን" ብሎ ደጋግሞ ሲጠይቀው መልሱ አዎን፣ አዎን፣ አዎን ነበር (ዮሐ.21:15-19)። እንዲሁም ሐዋርያቱም እንደሌሎቹ ትተውት ይሄዱ እንደሆን ክርስቶስ ሲጠይቃቸው "ጌታ ሆይ! ካንተ ወደ ማን እንሄዳለን" በማለትም የመለሰው ጴጥሮስ ነበር (ዮሐ.6:68)። እነዚህ የጴጥሮስ ምላሾች የሚያሳዩን እውነት ቢያንስ ጴጥሮስ በልቡ ክርስቶስን ለማፍቀርና ለመከተል መወሰኑን ነው። ሆኖም ሕይወት በወሰንነው ነገር ብቻ አትመራምና በሌላ አጋጣሚ ጴጥሮስ ክርስቶስን ሲክደው እናገኛለን: ክርስቶስ ሊሰቀል ወታደሮቹ ከያዙት በኋላ የርሱ የሆኑትም ላይ ጠላትነት ተጀምሮ ስለነበር ጴጥሮስም እንደ ክርስቶስ ተከታይነቱ ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርህ ተብሎ በባለሥልጣን ያይደል በማንም ሰው ሲጠየቅ "እኔ ይህን ሰው አላውቀውም" በማለት መለሰ። ፍቅር ቀላል ውሳኔ ብቻ አይደለም፤ መስዋዕትነትና በሌላ አቅጣጫ የምንሳሳለትን፣ የምናስቀድመውን ነገር እንክድ ዘንድ ተግባራዊ ነገር ይጠይቃል። ይህ ነበር የጴጥሮስ ፈተና፦ የፍቅር ውሳኔውን በተግባር የመግለጽ ቆራጥነት ማጣት!

ለኛም ይህ እውነት መልእክት ይኖረዋል፤ ክርስቶስን ትጠላዋለህ/ትጠይዋለሽ ወይ ብንባል መልሳችን በፍጹም ምን አደረገንና ነው የምንጠላው...ወዘተ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን እንደ ጴጥሮስ የምንወደውን ሌላ ነገር ወይም ክርስቶስን፣ ትምህርቱን... መምረጥ ግድ ሲሆንብን "ይህን ሰው አላውቀውም" የሚል የአንደበት ባይሆንም የተግባር ምላሽ መስጠቱ ይቀለን ይሆናል። ይህ ተከሰተ ወይም ሆነ ማለት ግን ሁሌ እንደዚህ መቀጠል አለብን ማለት አይደለም። ጴጥሮስ ወደ ክርስቶስ መመለሱንም ያስተምረናል። ከክህደቱ በኋላ ወዲያው ክርስቶስ የተናገረው ትዝ ሲለው "ወደ ውጪም ወጣና ምርር ብሎ" አለቀሰ ይላል ማቴ.26:75። እኛም ይህን እናደርግ ዘንድ ዘወትር የእግዚአብሔር ቃል ይጋብዘናል። በዚህ ሁኔታ ለክርስቶስ ያለን ፍቅር ከታደሰ ለርሱ መኖር እንጀምራለን።

 

ሐዋርያው ጳውሎስም ይህን መሰል ታሪክ ነው ያለው። ራሱ ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ያለውን ታሪኩን ሲናገር ክርስቲያኖችን "እስከ ሞት የማሳድድ ሰው ነበርሁ፤ ወንዶችንና ሴቶችን እያሰርሁ ወደ ወህኒ ቤት እንዲገቡ የማደርግ ነበርሁ..." ይላል (ሐ.ሥ. 22:4)። ክርስቶስ በደማስቆ መንገድ "ሳውል! ሳውል! ለምን ታሳድደኛለህ? " የሚል ድምጽ ሲሰማ "ጌታ ሆይ! አንተ ማን ነህ?" ሲል ድምጹም "እኔ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ" አለው ፤ በዚህም ጊዜ ጳውሎስ "ጌታ ሆይ! ምን ላድርግ? " ብሎ ጠየቀ። ክርስቶስም ጳውሎስ ማድረግ ያለበትን እንደሚንግረው ቃል ገባለት (ሐ.ሥ.91-19)። ከዚችም ቅጽበት ጀምሮ ሳውል ማንነቱ ተቀየረ ጳውሎስም ተባለና ክርስቶስ የሚነግረውን በመስማት በታዝዥነትና በፍቅር ኖሮ ለክርስቶስ በመመስከሩ በሰይፍ ለመሞት በቃ።

እንደ ጴጥሮስ ሁሉ ለጳውሎስም ለክርስቶስ ያለው ፍቅር ለዚህ መሥዋዕትነት መሠረት ነበር። አሳዳጅና ገዳይ መሆኑ ቀርቶ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ተሰዳጅና ተገዳይ ሆነ። ሮሜ 8:35-39 ላይ " ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን የሚችል ማንም የለም፤ ችግር ወይም መከራ፣ ስደት ወይም ራብ፣ ራቁትነት ወይም አድጋ፣ ወይም ሰይፍ ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን አይችልም። ስለ አንተ ፍቅር በየቀኑ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎችም ተቆጠርን..." ይላል። ይህ ሥር የሰደደ ፍቅሩን ይኖረው ነበር። ምናልባት ራሳችንን እንድናይ የሚያግዘን አንዱ ነጥብ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለዩንን ነገሮች ማስተዋል መቻል እንዳለብን ነው። ለጳውሎስ ስደት፣ መከራ፣ ሰይፍ፣ ሞት...ከፍቅሩ ጋር አይወዳደርም ነበር።

እኛም በሕይወታችን የክርስቶስን ፍቅር የሚሰርቁብን፣ ከርሱ የሚለዩን ነገሮች ምናልባት መከራ፣ ስቃይ ላይሆን ይችላል። ማግኘት፣ ስኬት፣ ምቾትም ከእምነት ሕይወት የመለየት ኃይላቸው ቀላል አይደለምና የራሳችንን ምክንያቶች እንመርምር። ጴጥሮስም ሆነ ጳውሎስ የሆኑትን የሆኑት ልዩ ችሎታ ስለ ነበራቸው አይደልም፤ ይልቁስ ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር የሁሉ ነገር አንደኛ ስላደረጉት ነው። ያፈቀረ ሰውኮ ላፈቀረው የማይሆነው ነገር የለም። ሰው ሰውን አፍቅሮ ብዙ ነገር የሚሆን ከሆነ፤ ክርስቶስን ያፈቀሩ ጴጥሮስና ጳውሎስ እንዴት የበለጠ ነገር አያደርጉ!

አፍቅሪያለሁ ስለምንለው ነገር ምን ያህል መሥዋዕትነትን እንደምንከፍል ወይም እንደከፈልን እናስብ። በተመሳሳይ መልኩ ለክርስቶስ ያለንን ፍቅርና የምንከፍለውን መሥዋዕትነት እንመርምር። በዚህም ሁኔታ ስንዘጋጅ ነው እንደ ጴጥሮስ "ጌታ ሆይ! ካንተ ወደ ማን እንሄዳለን" እንዲሁም እንደ ጳውሎስ በዕለታዊ ሕይወታችን "ጌታ ሆይ! ምን ላድርግ? " በማለት የክርስቶስን ምሪት እንፈልጋለን። በዚህ በመጨረሻው የጳውሎስ ቃል አስተንትኗችንን እንዝጋው "ጌታ ሆይ! ምን ላድርግ? " (ሐ.ሥ.22:10)።

 

 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት