እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘትንሣኤ

ከዓለም ሁሉ ዘግናኙ እሥር ቤት የተዘጋ ልብ ነው - በትንሣኤ የተደፈነ መቃብር፣ የተዘጋ በር የለም!!! 

fasikaaከዓርብ ስቅለት በኋላ ብዙውን ጊዜ ሀሳባችን ትንሣኤ ማለትም ፋሲካን ማሰብ ሲሆን በሁለቱ መካከል ግን የክርስቶስን ፍቅር የሚገልጽና ለሕይወታችን ትርጉም የሚሰጥ ቀን አለ - ቀዳም ስዑር። በዚህ ቀን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለንና ቤተ ክርስቲያንም እንደምትመሰክርልን ክርስቶስ ከስቅለቱ በኋላ ወደ ሲዖል ማለትም ሞተው ወደ ነበሩት ወረደ። ይህ ዝም ብለን በጸሎተ ሃይማኖት ደግመነው መታለፍ የሌለበትና የብዙ ሃይማኖቶች መጽናኛ ሊሆን የሚገባው መሠረታዊ ሃሳብን የያዘ ነው። ከአዳምና ሔዋን ውድቀት ወዲህ በሙታን ዓለም ተዘግተው የነበሩትን ነፍሳት በርሱ ሞት መፈታታቸውን ለማብሰር ክርስቶስ ወደ ሲዖል ወረደ።

በወንጌሎች ውስጥ የክርስቶስን ሕይወት ስንመለከት እንደ ሰው አባባል ጠያፍ ሊባሉና ለሱ የማይመጥኑ ልንላቸው ቦታዎች ሲገባ ይስተዋላል፤ ሆኖም እሱ በሄደበት ጨለማ ቦታዎች ሁሉ የእግዚአብሔር የሆነውን ብርሃን ያበራል፣ ይፈውሳል፤ በሄደበት ሁሉ ላይ ይሰለጥንበታል። ኃጢአተኞችና የኃጢአተኞች ቦታ ተብሎ እንደ ነውር የሚቆጠሩ ሰዎችና ቦታዎች ጋር ኃጢአትን ሳይሆን ኃጢአተኛውን ፍለጋ ይሄድ ነበር። በነበረው የአስተሳሰብ ግንዛቤም በሽታንና ሞትን በተለየ ሁኔታ መጠየፍ ተቀባይነት የነበረው ወግ ነው፤ ይልቁንም ለመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አይሁዳውያን ሰው የተፈጠረው በሕይወት ሆኖ በእግዜአብሔር እንዲደሰት ነው ብለው ያምኑ ስለነበር የሞት ዓለም ማለት መርገም፣ ገሃነም ማለትም ከእግዚአብሔር ህልውና የራቀና ምንም ተስፋ የሌለበት የስቃይ ዓለም ነበር። ስለዚህም ለእነርሱ ክርስቶስ ወደ ሙታን ወረደ ወይም ሞተ ማለት እግዚአብሔር የሌለበት እዚያ የገሃነም አዘቅት ውስጥ ገባ ማለት ነበር።

ለእኛ ለክርስቲያኖች ክርስቶስ በቀዳም ስዑር ወደ ሞት ወረደ ስንል ከአምላክ ተነጥለው በዚያ የሰቆቃ ዓለም ውስጥ ለነበሩ ነፍሳት ተስፋቸውን እንደመለሰላቸውና ከእግዚአብሔር ጋር በኅብረት እንዲኖሩ ማስቻሉን እናምናለን። ይህም በወንጌላት እንደምናነበው ከትንሣኤው በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በፍርሃትና ተስፋ ቁርጠት በራቸውን ቆልፈው በተሰበሰቡበት ገብቶ ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ ሰላምና ስክነትን እንዳበሰራቸው ሁሉ ወደ ሙታንም ወርዶ ድልንና ነጻነትን አበሰረ። ስለዚህ የቀዳም ስዑር የክርስቶስ ተግባር ራሱ የትንሣኤው ዋነኛና ተቀዳሚ ዓላማ እንጂ አንድ ወደ ሲዖል ወረደ የሚል መስመር በጸሎተ ሃይማኖት ላይ ለመጨመር የታሰብ ድርጊት አይደለም።

ይህን እውነት ለክርስቲያናዊ ሕይወታችን ስንተረጉመው ዛሬም በጣም ይሠራል። ክርስቶስ ዛሬም ሰላምንና ይቅርታን ሊያውጅላቸው የሚሹ የተለያዩ የሲዖል ዓይነቶች በሕይወት አሉ፤ የጭንቀት፣ የተስፋ ቁርጠት፣ የደስታ ቢስነት፣ የረዳት የለሽነት፣ የብስጭት፣ ማለቂያ የሌለው የቂምና የጥላቻ ኑሮ፣ በጥልቁ የቆሰለ ልብ ሸክም፣ ራስን የመጥላትና የማጥፋት እቅድ የሰነቀ ስብእና፣ የሱስ ባርነት...ይህንና መሰል ነገሮችን ስናስብ ለክርስቶስ የተዘጋና ማንም ሊገባበት የማይችል ሕይወትና ልብ የተሸከምን፣ እግዚአብሔርም ላይደርስብን እኛም ላንደርስበት የተማማልን እስከሚመስለን ከእርሱ የራቀ ሕይወት በተዘጋ ልባችን ውስጥ እንኖር ይሆናል።

ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከዓለም ሁሉ ዘግናኙ እሥር ቤት የተዘጋ ልብ ነው ያሉት እውነት በክርስቶስ ብቻ ነው በሩ ሳይከፈት በውስጥ ገብቶ ሰላም ላንተ/ላንቺ የሚል ብስራት ሊሰማ የሚችለው፤ ይህም የትንሣኤው በዓል ትልቅ መልእክት ነው። ይህን ተስፋ አድርጋ ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ፋሲካ ተናዘን መቁረብ እንድንጀምር ታዘናለች፤ ምክንያቱም አንዴ ተዘግቶ እስከ ወዲያኛው ተከርችሞ የሚቀርና ክርስቶስ የማይሰብረው ልብ የለምና ነው። በርግጥ በእንደዚህ ዓይነት አናኗር ውስጥ ራሳችንን ስናገኝ ወደ ሰው ወይም ወደ ነገሮች መፍትሔ ፍለጋ ማሰባችን ግድ ነው ሆኖም ግን የውስጥ ውስጣችን ጋር መድረስ ለሰውና ለነገሮች አይቻላቸውም፤ ክርስቶስ ብቻ በተዘጋውና በተቆለፈው ውስጠኛ ማንነታችን ወይም ግላዊ ሲዖላችን የመግባትና የመታደግ ብቃትም ሆነ ፍላጎት አለው። ይህ የአናኗር ትንሣኤ ሲከናወን ብቻ ነው እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ፋሲካችን ማለትም መሸጋገሪያችን ክርስቶስ ነው ማለት የምንችለው።

መልካም ዘመነ ትንሣኤ!!!

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት