እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘኒቆዲሞስ - ከእኔነት ቅርፊታችን መውጣት

ከእኔነት ቅርፊታችን መውጣት - ዳግም መወለድ - ዘኒቆዲሞስ

ምስባክ ዘደብረ ዘይት፦ ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፤ አመከርከኒ ወኢተረክበ ዓመፃ በላዕሌየ፤ ከመኢይንብብ አፉየ ግብረ ዕጓለ እመሕያው።

ልቤን ፈተንከው በሌሊትም ጎበኘኸኝ፤ ፈተንከኝ ምንም አላገኘህብኝም፤ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው።

መዝ.16:3-4 ንባባት፦- ዮሐ.3:1-11 - ሮሜ.7:1-18 - 1ዮሐ.4:18-21 - ሐዋ.5:34-42

Nicodemusለሕማማት ሳምንት ብሎም ለብርሃነ ትንሣኤው በምንዘገጃጅበት በዚህ የጾም ወቅት ላይ የዛሬው ሰንበት ወንጌል የኒቆዲሞስንና የክርስቶስን ግላዊ ንግግር ያቀርብልናል። ኒቆዲሞስ አንድ ታሪካዊ ሰው መሆኑን ወንጌሉ አስረግጦ ቢነግረንም ግቡ ግን እንደወትሮው በኒቆዲሞስ ቦታ ራሳችንን አስቀምጠን ከኢየሱስ ጋር ግላዊ የነፍሳችንን ጉዳይ እንድንወያይ ለመጋበዝ ነውና ለዚህ ዓላማ የሚያግዙንን አንዳንድ ነጥቦች እንካፈል።

ኒቆዲሞስ በጊዜው በነበሩ የሰው መስፈርቶች በሙሉ "አንቱ" ሊያሰኙት የሚችሉ ነገሮችን ያሟላ ሰው እንደነበረ ወንጌል "ከፈሪሳውያን ወገን የሆነ፣ የአይሁድ አለቃ፣ የእስራኤል መምህር መሆኑን" በማለት ያስረዳናል። በሰው እይታ አዋቂና የተከበረ ሰው እንደነበረ አያጠራጥርም፤ በክርስቶስም ዓይን የተከበረ መሆኑ ቢቀጥልም አዋቂነቱ ግን ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ኢየሱስ "አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ይህን አታውቅምን?" ሲለው ገና ማወቅ የሚገባው ብዙ ነገር እንዳለ ያሳየናል። ለኛ ይህ መነሻ ነጥብ ነው፤ በኢየሱስ ፊት ሁል ጊዜ ነገሮችን ለማወቅና ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለብን።

ማንም ሰው በእግዚአብሔር ቃል ፊት ሁሉን ጠቅልሎ ሊያውቅ አይችልም። ስለ ደኅንነት ቢወራ ገና በየቀኑ ማወቅ የሚገባንና ማድረግ የሚጠበቅብን ነገር አለ፤ ስለ ማፍቀርና ይቅር ማለትም ቢነገር በየቀኑ የሚያጋጥሙንን ሰዎች ገና እንደ አዲስ ለማፍቀርና ይቅር ለማለት በየቀኑ ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን እንጂ ባለፉት ጊዜያት አፍቅሪያለሁ፣ ይቅር ብያለሁ...ብለን የምንደመድመው ጉዳይ አይደለም። በሕይወት እስካለን ድረስ ዘወትር ለበለጠ ነገር መዘጋጀት አለብን። "እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው እንደገና ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም" የሚሉት የክርስቶስ ቃላት የሚያንጸባርቁትም እውነት ክርስትና አንዴና ለሁልጊዜ በአንድ ቀን ተአምራዊ ለውጥ ያከተመለት ሕይወት ሳይሆን ሁሌም ለማያልቀው የእግዚአብሔር ጸጋ ራስን ከፍቶ እንደ ሕጻን መሆንን የሚጠይቅ ጥሪ መሆኑን ነው። ድኛለሁ፣ አውቂያለሁ፣ ዳግም ተወልጃለሁ፣ በቃ... ብለን የቆምን ሰዎች እንዳንሆንና ሁለነገራችን በየቀኑ እያደገ ሲሄድ እምነታችንን በየቀኑ ሳናሳድገውና ሳንኖረው የሆነ ደረጃ ላይ ቆሞ እንዳይሆን ራሳችንን እንመርምር።

ኒቆዲሞስ የክርስቶስ ዳግም ተወለድ የሚለው ትእዛዝ ግራ ቢገባው "እንዴት ሊሆን ይችላል?" ይህ የአንዲት ነፍስ ቀጣይ ንግግር ነው። ነፍስ ስለማንነቷና ምንነቷን ከመጠየቅ መቼም ቢሆን አትቦዝንም። ሁሌም "እንዴት" ትላለች፤ እንዴትና ወዴት መጓዝ እንዳለባት ታስባለች። የሆነ ነገሮችን የምታውቅ ይመስላታል ሆኖም ግን ነገሮችን ጠንቅቃ አውቃ የመጨረስ ብቃት ስለሌላት በእግዚአብሔር ቃል ፊት ሁሌ "ምን፣ እንዴት ማድረግ አለብኝ" ማለቱ የግድ ነው። ምናልባት በሰው ፊት ስንቆምና ስንገኝ የፈለግነውን ስእላችንን ማስተላለፍ እንችል ይሆናል፤ በክርስቶስ ፊት ግን ገና ብዙ ማወቅ የሚገባን ነገር እንዳለ እንገነዘባለን። ለዚህም ነው በርሱ ቃል ፊት መምሰልና ማስመሰላችን ለማንነታችን ቦታቸውን የሚለቁት። በሰዎች ፊት መስለን የምንውለው ነገርና በክርስቶስ ፊት የሆንነው ነገር እንዲመሳሰል በጣርን መጠን ዳግም መወለድን እየተገበርነው እንሄዳለን።

መወለድ ማለት መለየት፣ ከአንድ ዓይነት አናኗር ወደሌላ ዓይነት መምጣት ማለት ነው። ልክ ሕጻን ሲወለድ ሕይወቱ ቢቀጥልም ከነበረበትና ራሱን ያኖርበት ከነበረው ከእናቱ ማሕፀን መውጣት እንዳለበት በእምነትም ማደግ ካለብን በተመሳሳይ መልኩ ከምን መላቀቅ እንዳለብብ ማሰብ አለብን። ካለነርሱ ልንኖር የማንችል የሚመስለንን ነገሮች ለመተው መወሰን አለብን። ሕጻን ሲወለድ የምግብ ማስተላለፊያ የነበረው እትብቱ መቆረጥ የግድ ቢሆንም በሌላ መልኩ መመገቡን ይቀጥላል። እኛም መቆራረጥ ካለብን ሕይወት ክርስቶስ "ተወለድ/ጅ" ሲለን ህልውናችንን የሚፈትን ነገር መስሎን እንዴት ልንልና ልንሸሸው እንችል ይሆናል፤ እውነቱ ግን ያ ካልሆነ ማደግ አንችልም። ዛሬ በሕይወታችን ወደ ክርስቶስ ይበልጥ እናድግ ዘንድ መቆራረጥ ያለብን ነገር ምን ይሆን ብለን እናስተንትን።

ብዙ ጊዜ ራስ ወዳድነታችን ራስን ወደማየት ብቻ ያሳድገንና የእግዚአብሔርን ፈቃድና ሰዎችን ማሰቡ ይከብደናል። ነጋ መሸ "እኔ" ና ለኔ ብቻ በሚል ዓይነት መጓዝን እንመርጥ ይሆናል፤ ይህ ከሆነ ግን በክርስትና ማደጋችን አቁሟል ማለት ነው። ከእኔነት ቅርፊታችን ካልወጣን ከኛ ውጭ የሆነውን መገንዘብ አንችልም፤ ያልተፈልፈለ ማንነት ወይም ያላደገ እምነት ይዘን በሥጋ ወደፊት እንጓዛለን። በዚህ ዓይነት ስብእና የክርስቶስን ሕማማትና ትንሣኤ ማክበሩ ትርጉም አይኖረውምና የዛሬው ወንጌል ከማንነታች ወጥተን ለክርስቶስና ለሌሎች የመኖርን ሕይወት፣ በእምነታችን ከዕለት ዕለት ማደግን እንድንለማመድ ይጋብዘናል። ይህ ካልሆነ ክርስቶስ የከፈለውን ዋጋ ሁሉ እንዳልተከፈለልን እናደርገዋለንና ዳግም መወለድ የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ለእኔ በምን መልኩ ተግባራዊ አድርጌ ለዘንድሮው የክርስቶስ ትንሣኤ ብርሃን ራሴን ላዘጋጅ ብለን በቅዱስ ቃሉና በምስጢራቱ ፊት እናስተንትን።

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት