እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፳፬ - የነቢያት መጻሕፍት ጥናት (ትንቢተ ሕዝቅኤል)

ክፍል ሦስት - ትምህርት ሃያ አራት

የነቢያት መጽሐፍት ጥናት - ትንቢተ ሕዝቅኤል

Hizkiel· ሕዝቅኤል ማለት ምን ማለት ነው ? ነቢዩ ሕዝቅኤል ለነቢይነት የተጠራውና ያገለገለው በየትኛው ወቅት ነው?

ሕዝቅኤል የሚለው ስም "ሔዜክ" እና "ኤል" የሚሉት የሁለት የተለያዩ ቃላት ጥምረት ሲሆን ትርጓሜውም "እግዚአብሔር ያበረታል"፤ "እግዚአብሔር ብርታትን ይሰጣል"፤ "እግዚአብሔር ያጠነክራል" ማለት ነው፡፡ በተቀራራቢነት ደግሞ "እግዚአብሔር ያጽናናል" የሚለውም ትርጓሜ ይሰጣል። ሕዝቅኤል ከአራቱ ታላላቅ ነቢያቶች በሦስተኛነት የሚገኝ ታላቅ ነቢይ ነው፡፡ ካህን የነበረው ነቢዩ ሕዝቅኤል በአምስት መቶ ዘጠና ሰባት ዓ.ዓ (597) በምርኮ ወደ ባቢሎን ተወሰደ፡፡ ኢየሩሳሌም ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስት መቶ ሰማንያ ስድስት ዓመተ ዓለም ከመፍረስዋ በፊት ሕዝቅኤል ያወቃትና የኖረባት ሲሆን ከፈረሰችም በኋላ በስደት ባቢሎን ውስጥ ከወገኖቹ አይሁዳውያን ጋር ይኖር ነበር(ሕዝ 1፡1-3)፡፡ ለተማረኩት ወገኖቹ ቃሉን ያሰማ ዘንድ እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው(ሕዝ 2፡1-4)፡፡ {jathumbnail off}

ሕዝቅኤል የእግዚአብሔር የትንቢት ቃል ለሰዎች በደንብ ለማሰማት በማለት ለረጅም ጊዜ በጐኑ በመተኛት፣ የሚያረክሰውን በመብላት፣ ጠጉሩን ቈርጦ በመበተን፣ ዲዳ በመሆን፣ ሚስቱ ስትሞት ባለማልቀስና ሌሎች የተለያዩ ዘዴዎች በመጠቀም ያስተምር ነበር፡፡ የእርሱ የትንቢት ቃል የተላለፈው ባቢሎን ውስጥ በስደት ለሚገኙትና ኢየሩሳሌም ለሚኖሩት ሕዝብ ነበር። ወደ ባቢሎን ተማርኮ የተወሰደው ወጣት እያለ እንደነበር ከሚሰጣቸው መረጃዎች እንረዳለን። ሕዝቅኤል ባቢሎን ውስጥ ለ27 ዓመታት ያህል በስደት እንደቆየ ይናገራል (ሕዝ 29፡17)። ሕዝቅኤል ባለ ትዳር ነበር፤ ነገር ግን ባለ ቤቱ በስደት እያሉ ባቢሎን ውስጥ በሞት ተለይታዋለች (ሕዝ 24፡15-27)።

· በነቢይነት የአገልግሎት ዘመኑ ነብዩ ሕዝቅኤል የነበረው ባሕርይና የአገልግሎት ሕይወቱ ምን ይመስል ነበር?

በነቢይነት የአገልግሎት ሕይወቱ ውስጥ ነቢዩ ሕዝቅኤል የተለየ ባሕርይ እንደነበረውና የሚናገረውም የትንቢት ቃል ለመረዳት በሚከብዱ በራእይ የተሞላ ስለሆነ ከሌሎች ነቢያት ለየት ያደርገዋል፡፡

የሚተርካቸው ራእዮች ጥልቀትና በራእዮች ውስጥ የሚዘረዝራቸው ረቂቅ ፍጡራን የትንቢት ቃሉ ለየት ያደርገዋል፡፡ አንድ ሰው ያየውን ምሥጢራዊ ራእይ በቃላት ለመዘርዘርና መለኮታዊ ፍጥረት የሆኑትን ነገሮች ሰብአዊ ቋንቋንና በዓለም ውስጥ ያሉትን የሚታዩ ቁስ አካላዊ የሆኑ ነገሮች በመጠቀም መግለጹ እጅግ አዳጋች ቢሆንም ሕዝቅኤል ግን ይህንን በተረጋጋ መንፈስና ጥበብ በተሞላበት መልኩ ይገልጸዋል፡፡ ሌላው ከነቢዩ ሕዝቅኤል መጽሐፍ ከመጀመሪያ ዕይታ ወይንም ንባቡን ብቻ ቃል በቃል በመውሰድ ለመረዳት የሚያስቸግሩ፤ ነገር ግን ከበስተጀርባቸው ተጨማሪ የሆነ ሌላ ምሥጢራዊ መልእክት የሚያስተላልፉ ነገሮችን ይገልጻል፡፡ ለምሳሌ እንደ እሳት ነበልባል የሚያበራ የሰው አምሳያ ነቢዩ ሕዝቅኤልን በራስ ጠጉሩ ይዞ ከምድር ወደ ሰማይ አነሣውና ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳደረሰው ይናገራል(ሕዝ 8)፡፡ በሰብአዊ ዕይታ ሰው በራስ ጠጉሩ ተይዞ ወይም ተንጠልጥሎ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ሊወሰድ ይችላል ተብሎ ማመኑን የሚከብድ ቢሆንም ሕዝቅኤል ግን ይህን በራሱ ሕይወት እንደተከናወነ ይገልጻል፡፡

ሰው በተፈጥሮ ባሕሪው ብዙውን ጊዜ የሚወደውን ሰው በሞት ሲለየው ምንም እንኳ ቀድሞት ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚሄድ ቢሆንም ያን ሰው በአካል በመለየቱ ምክንያት ያዝናል፤ እንባውን ያወርዳል፡፡ ምንም እንኳ ሕይወቱን ለአገልግሎት የሰጠና በመንፈሳዊ ሕይወቱም የበረታ ቢሆንም ሰብአዊነቱ ሊጠፋ የማይችል ተፈጥሮአዊ ባሕርይ ነውና በተወሰነ መልኩ እንደ ሰው ማዘኑ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት በእስራኤላውያን ባሕል ውስጥ የተለመደ ባህላዊ ድርጊት ነበር፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤል ግን የሚወዳትን ሚስቱ ተቀሥፋ በሞት ስትለየው እንዳያለቅስና እንዳያዝን ስለተነገረው አለማልቀሱን ተገልጿል(ሕዝ 24)፡፡ ሕዝቅኤል የእግዚአብሔር የትንቢት ቃል ለሰዎች በደንብ ለማሰማት በማለት ለረጅም ጊዜ በጐኑ በመተኛት፣ የሚያረክሰውን በመብላት፣ ጠጉሩን ቈርጦ በመበተን፣ ዲዳ በመሆን፣ ሚስቱ ስትሞት ባለማልቀስና ሌሎች የተለያዩ ዘዴዎች በመጠቀም ያስተምር ነበር፡፡ ሕዝቅኤል ለ390 ቀናት በግራ ለ40 ቀናት ደግሞ በቀኛ ጐኑ በጡብ ላይ ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ተኝቶ አሳለፈ(ሕዝ 4፡ 4)፡፡

በአጠቃላይ ትንቢተ ሕዝቅኤል የበለጠ ለመረዳትና የነቢዩንም ማንነት በደንብ ለማወቅ መልእክቱን ቃል በቃል ሳይሆን በመልእክቱ ዙርያ ያሉት ነገሮችና እንዲሁም ከመልእክቱ በስተጀርባ ሊኖሩ ስለሚችሉ ምሥጢራዊ የሆኑ ተጨማሪ ትምህርቶች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ማጥናቱ አስፈላጊ ነው፡፡

· የትንቢተ ሕዝቅኤል መጽሐፍ የተዋቀረው እንዴት ነው? ወይም ጥንቅሩ ምን ይመስላል?

መጽሐፉ የሚጀምረው በእርግጥ በራእይ የተገለጸው የሕዝቅኤል የነቢይነት ጥሪን በመግለጽ ነው(ሕዝ 1-3)፡፡ ከነቢይነት ጥሪው በኋላ የሚገኘው ትልቁ ክፍል አራት የተለያዩ ክፍሎች ሲኖሩት ትኩረቶቹም በአራት የተለያዩ ነገሮች ዙርያ ላይ ያደረገ ነው፡፡ እነዚህም በይሁዳ ላይ ስለሚመጣው ቅጣት፣ ስለ ኢየሩሳሌም መውደቅና የቤተ መቅደስዋም መፈራረስ(ሕዝ 4፡24)፣ አጐራባች በሆኑ የጐረቤት ባዕዳንና ኀያላን አገራት ላይ ስለሚመጣው ቅጣትና(ሕዝ 25-32)፣ ስለ ወደፊቱ ተስፋ የተመለከቱ ናቸው(ሕዝ 33-48)፡፡

መጽሐፉ ውስጥ የመጀመርያውና ጎልቶ የሚታየው ወይም ነቢዩ ብዙ ጊዜ የነቢይነት መልእክቱን ለማስተላለፍ የተጠቀመበት መንገድ ራእይ ነው። ይህም "እግዚአብሔር በራእይ አየሁት" እያለ አራት ጊዜ ያያቸው የተለያዩ ራእዮች ይተርካል፡፡ እነዚህም ከጥሪው ጋር በተያያዘ መልኩ ያየው አራት ሕያዋን እንስሳት(ሕዝ 1)፣ የኢየሩሳሌምን ውድቀትና መቀጣት በማረጋገጥ ረገድ ያየው እንደ እሳት ነበልባል የሚያበራ የሰው አምሳያ(8-11)፣ አይሁዳውያን ወደ ከነዓን ምድር በድጋሚ ሊመለሱ መሆኑን ለመግለጽ ያየው የደረቁ አጥንቶች የተከማቹበት ሸለቆ ራእይና(37) ወደ ፊት ስለሚሠራው ቤተ መቅደስ የተገለጠ ራእይ ናቸው(40-48)።

ሌላው በተጨማሪ ማስተዋል ያለብን ነገር መጽሐፉ ውስጥ ነቢዩ ስለሚጠቀመው ለየት ያለ የአነጋገር ዘይቤ ነው፡፡ ይህም እንደ ሰምና ወርቅ ከበስተጀርባቸው ሌላ መልእክት የሚሰጡ ምሳሌያዊ ንግግሮችን መጠቀሙ ነው። ለምሳሌ፦ የወይን ተክል እንዴት ከዛፍ ጋር ሊነጻጻር ይችላል?(ሕዝ 15)፤ ኢየሩሳሌም ሆይ የተወለድሽው በከነዓን ምድር ነበር፤ አባትሽ አሞራዊ ሲሆን እናትሽም ሒታዊ ነበረች(ሕዝ 16፡1-63)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የንስርና የወይን ተክል ምሳሌ(17፡1-21)፣ በዝሙት ኃጢአት ስለተባበሩት እኀትማማቾች(23፡1-21)፣ ዝገት ስለ በላው የብረት ድስት(24፡1-14)፣ ስለ ዝግባ ዛፍ(ሕዝ 31)፣ ስለ እስራኤል እረኞችና(34፡1-10) ሌሎችም የተለያዩ ነገሮች በመጠቀም የነቢይነት መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

· ነቢዩ ሕዝቅኤል በነበረበት ዘመን ውስጥ ጣዖት አምልኮ የተስፋፋበት ጊዜ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህንን የሕዝቡ ጣዖት አምላኪነት ሕይወት ለመለወጥ ነቢዩ እንዴትና በምን ዓይነት መልኩ አስተማረ ? እንዴት ሊቀርፈው ቻለ?

ነቢዩ ሕዝቅኤል በአገልግሎት ጅማሬው ጣዖት አምልኮን እጅግ በጣም በመቃወም ሕዝቡን ወደ ንስሓ ይጠራል፡፡ በእርግጥ ሕዝቦች ከእግዚአብሔር በመራቅና ትእዛዛቱንም በመጣስ በተራራዎች፣ በኮረብታዎችና፣ በገደላማ ሸለቆዎች ሁሉና በትልልቅ ዋርካ ዛፎች ሥር ጣዖትን ያመልኩ ነበር(ሕዝ 6፡ 3)፡፡ በዚህም ምክንያት መሠዊያዎቻቸውና ጣዖቶቻቸው ተሰባብረው እንደሚደቁ፣ የዕጣን ማቅረቢያዎቻቸውም እንደሚንከታከቱ፣ የሠሩትንም ነገር ሁሉ እንዳልነበረ እንደሚሆን ይናገራል፡፡ ከዚህም በላይ ከተሞቻቸውም ሁሉ እንደሚደመሰሱ፣ ከሞት ተርፈው በሕይወት የሚኖሩት ግን የእግዚአብሔርን ማንነት አውቀው እንደሚረዱ ነቢዩ ለሕዝቡ ይናገራል(ሕዝ 6፡5-7)፡፡ በተጨማሪም ሕዝቡና መሪዎቻቸው ቤተ መቅደስ ውስጥ እንኳ ሳይቀር ጣዖታት ማምለክና ለማይታወቁ ምስሎች መስገዳቸውን በመቀጠል እግዚአብሔርን አሳዝነዋል፡፡

ሕዝቡ ቤተ መቅደስ ቅጽር ግቢ ውስጥ ያመልኳቸው ከነበሩት ነገሮች ውስጥ እባቦች፣ ንጹሕ ያልሆኑ እንስሳትና የሌሎችም ነገሮች ሥዕል የተሳለበት የነበረ ነገር ይገኙበታል(ሕዝ 8፡10)፡፡ ሰባ የእስራኤላውያን መሪዎች እያንዳንዱ የዕጣን ማጠንት ይዞ ምስል በተሞላበት ክፍል እየገቡ ይሰግዳሉ፤ ሌሎች ጀርባቸውን ወደ ቤተ መቅደስ አድርገው የምትወጣዋን ፀሐይ በማምለክ ወደ ምሥራቅ ተንበርክከው ይሰግዳሉ፤ ከዚህም አልፎ እግዚአብሔር አገሪቱንም ጨርሶ ትቶአታል በማለት ራሳቸውን ያታልላሉ(ሕዝ 8፡9-16)፡፡ በተጨማሪም ከብርና ከወርቅ እንዲሁም ከዕንቁ ጣዖታትን በመሥራት ያመልካሉ(ሕዝ 7፡19-20)፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ማስቈጣታቸውን ቀጠሉ፡፡

ስለዚህ ነቢዩ ሕዝቅኤል ሕዝቡ ንስሓ የማይገቡ ከሆነ ቅጣት እንደሚመጣባቸው ይናገራቸዋል፡፡ ቅጣቶቹም መቅሠፍት በመቅሠፍት ላይ ይወርዳል፤ ጦርነት በየቦታው ይደረጋል፤ በየቤቱም በሽታና ረሀብ ይከሰታል፤ ከሀብታቸውም ሆነ ከውበታቸው ወይም ከክብራቸው የሚቀርላቸው አንድ ነገር እንኳ አይኖርም፤ ካህናት ሕዝቡን የሚያስተምሩት ነገር፣ ሽማግሌዎችም ለሕዝቡ የሚሰጡት ምክር አይኖራቸውም፤ ንጉሡም ያለቅሳል፤ መስፍኑም ተስፋ ይቈርጣል፤ ሕዝቡም ከፍርሃት የተነሣ ይርበደበዳል (ሕዝ 7፡1-27)፡፡ በአጠቃላይ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ስለሆነ ሕዝቡ በጣዖት አምልኮ ምክንያት ከእርሱ ሲርቁ ስሕተታቸውን ተረድተው በንስሓ እንዲመለሱ ከስሕተታቸው የሚማሩበት ቅጣት እንዳዘጋጀላቸው ነቢዩ ይገልጻል፡፡

· ነቢዩ ሕዝቅኤል ከተናገራቸው የትንቢት ቃል ውስጥ ስለ ኢየሩሳሌም መቀጣትና ወደፊት ስለሚጠብቃት ሕይወት በስፋት የሚያትተው ክፍል ይገኝበታል፡፡ ለመሆኑ ኢየሩሳሌም ለምን እንድትቀጣ ተፈረደባት?

እንደሚታወቀው ኢየሩሳሌም ለአይሁዳውያን በሃይማኖታዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ወሳኝ የሆነች ከተማ ነች፡፡ ለእነርሱ ይህች ከተማ ማጣት ማለት የታቦቱ ማደሪያ የሆነውን ቤተ መቅደሳቸውና የንጉሣቸው መቀመጫ የሆነውን ቤተ መንግሥት ማጣት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ውርደት ነው፡፡

አይሁዳውያን ጣዖታት በማምለካቸው፣ ትእዛዛትን በመተላለፋቸውና ብዙ አጸያፊ ነገሮች ፈጽመው እግዚአብሔር በማሳዘናቸው ምክንያት መቅሥፍቶች እንደሚመጣባቸው ቢነግራቸውም ወዲያውኑ አልተቀጡም፡፡ እግዚአብሔር በነቢዩ ሕዝቅኤል አማካይነት ስሕተታቸውን የሚረዱበት መንገዶች በማመቻቸት እንዲጸጸቱና ከተሳሳተው አካሄዳቸው እንዲመለሱ ደጋግሞ ጥሪ ሲያደርግላቸው ቈይቷል፡፡ ለምሳሌ በጠላት መከበቧን ለሕዝቡ በምሳሌ ሲያስረዳ ጡብ ወሰደ፤ በላዩም ላይ የኢየሩሳሌም ከተማ የሚያመለክት ካርታ ነደፈበት፤ የከተማዪቱን መከበብ እንዲያመለክት በዙሪያው ጉድጓድ ማሰ፤ ዐፈር ቈለለ፤ ጦር ሰፈርና የምሽግ ማፍረሻ ሠራ፤ የብረት ምጣድም ወስዶ በእሱና በከተማዪቱ መካከል እንደ ቅጽር አቆመው፤ ፊቱን ወደ ከተማዪቱ አቀና፤ ለእስራኤል ሕዝብ ምልክት ትሆን ዘንድ የተከበበችም ሆነች፤ ከዚያም ስለ እስራኤል ኃጢአት በግራ ጐኑ ለ390 ቀኖች ስለ ይሁዳ ኃጢአት በቀኝ ጐኑ ለ40 ቀናት በመተኛት እየተሰቃየ አሳለፈ፡፡

በተያያዘ መልኩ ወደ ከተማዪቱ ክንዱን በመነቅነቅ የከተማዪቱን መከበብና የሚመጣባትን በመግለጥ ትንቢት ተናገረ(ሕዝ 4፡1-8)፡፡ በሌላም መልኩ ሕዝቅኤል ጠጉሩንና ጢሙን በመላጨትና ሦስት ቦታ በመክፈል አንዱን እጅ በከተማው ውስጥ አቃጠለው፤ ሁለተኛውን እጅ በከተማዪቱ ውስጥ እየተዘዋወረ በሰይፍ በመተፍተፍ ቈራረጠው፤ ሦስተኛው እጅ ደግሞ ለነፋስ በተነው፡፡ የዚህ ድርጊት ምልክትነቱ ከሕዝቡ ውስጥ አንድ ሦስተኛው እጅ በረሃብና በበሽታ እንደሚያልቅ፣ አንድ ሦስተኛው ከከተማው ውጪ በሰይፍ እንደሚገደልና ሌላው አንድ ሦስተኛው እጅ በአራቱ ማእዘን በነፋስ ተበትኖ በአሳዳጆች እንደሚገደል ይናገራል(ሕዝ 5፡1-12)፡፡

ይህንን ሁሉ ማስጠንቀቂያዎች በምልክት፣ በምሳሌዎችና ግልጽ በሆነ ቋንቋ ነቢዩ ደግሞ ደጋግሞ የኢየሩሳሌም በጠላት የመከበብዋንና ሕዝቡ በችግር የመውደቁና የፍጻሜው ጊዜ መድረሱን ቢናገርም ሕዝቡ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት በአመፃቸው ቀጠሉበት(ሕዝ 7)፡፡ ቀጥሎም ነቢዩ የኢየሩሳሌም በጠላት የመከበብዋ ምክንያት ሊሆኑ የቻሉትን ነገሮች በድጋሚ አበክሮ ያስረዳል(8-11)። ከእነዚህም ውስጥ በተደጋጋሚና በትኩረት የተገለጸው የእስራኤላውያንን ማመጽ፣ ባዕዳን አማልክት ማምለክ፣ እጅግ የከፋ ኃጢአት በመሥራት መበደላቸው ይጠቀሳሉ፡፡ በተጨማሪም በምድሪቱ ላይ ግድያ መፈጸማቸው፣ ኢየሩሳሌምን በግፍ ሥራ የተሞላች በማድረጋቸውና ባደረጉት ክፋት ከመጸጸት ይልቅ እግዚአብሔር አያየንም በማለት ራሳቸውን ማታለላቸው ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው(ሕዝ 9፡9-11፤ ሕዝ 20፡33-38)።

ሕዝቡ በጦርነት፣ በረሃብ፣ በበሽታና በሚገድሉ አደገኛ አራዊቶች አማካኝነት ይቀጣሉ(ሕዝ 14፡21)፡፡ እግዚአብሔር ይህንን ለማድረግ መወሰኑንና ውሳኔውን የማይቀየርና የማይሻር መሆኑን ሲገልጽ ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ እንኳ በዚያ ቢኖሩ በደግነታቸው የራሳቸውን ሕይወት ብቻ ያድናሉ እንጂ የገዛ ልጆቻቸው እንኳ ማዳን አይችሉም በማለት ደጋግሞ ውሳኔውን ያስገነዝባል(ሕዝ 14፡12-22)፡፡ በሕዝቡ አመፀኛነት ምክንያት ይህን ሁሉ ቢደርስም ከሕዝቡ መካከል ተጸጽተውና የእግዚአብሔር ትእዛዝ ፈጽመው የኖሩትን ግን በግንባራቸው ላይ ልዩ ምልክት ስለተደረገባቸው ልዩ ጥበቃ እንደተደረገላቸውና ከእነዚህ ጥፋቶችም ሆነ መቅሠፍቶች እንደዳኑ ነቢዩ ያስረዳል(ሕዝ 9፡4)፡፡

· ነቢዩ ሕዝቅኤል በኖረበት ዘመን ሐሰተኞች ነቢያት እንደነበሩ ይታወቃል፤ ሕዝቅኤል ስለ ሐሰተኛ ነቢያት ማንነትና ሥራቸው እንዴት አድርጎ ገለጸው ? እንደ ነቢዩ አገላለጽ ሐሰተኛ ነቢያት እንዴት ሊታወቁ ይችላል?

ነቢይ ከእግዚአብሔር የተነገረውን መልእክት የተለያዩ መንገዶች በመጠቀም፣ በምንም ዐይነት ጥቅማ ጥቅም ሳይታለልና ማንንም ሳይፈራ፣ ነቀፋም ሆነ ተቃውሞ ቢደርስበትም ለምንም ለማንም ሳይበገር ለሕዝብ የሚያስተላልፍ መልእክተኛ ነው፡፡ ነቢይ ሁሌም በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሆነውን ነገር ለሕዝብ ይገልጻል፤ ሕዝቡን ያሳውቃል፡፡

በአንጻሩ ሐሰተኞች ነቢያቶች ከራሳቸው እየፈጠሩ፣ ራእይ ሳያዩ አይተናል እያሉ፣ ሳይላኩ በእግዚአብሔር ተመርጠናል ብለው እየተመኩ የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም ትንቢት ይናገራሉ(ሕዝ 13፡3)፡፡ ከዚህም በላይ ሰላም ሳይኖር ሁሉም ነገር ሰላም ነው እያሉ ሕዝቡን ያስታሉ(ሕዝ 13፡10)፡፡ እንደነዚህ ያሉት ነቢያቶች ትንቢታቸው ከንቱና ግራ የሚያጋባ፣ ራእያቸው ሐሰት፣ ቃላቸውም ተፈጻሚነት የማያገኝ መሆኑን እግዚአብሔር ይናገራል(ሕዝ 13፡6-7)፡፡ እግዚአብሔርም ለሐሰተኞች ነቢያት ሲናገር ትንቢታችሁ ከንቱ፣ ራእያችሁም ሐሰት ስለሆነ በእናንተ ላይ በቁጣ እነሣለሁ ይላል(ሕዝ 13፡8)፡፡

ከእንግዲህ ወዲህ እነዚህ ሐሰተኞች ነቢያቶች ከቅጣት አያመልጡም፤ ስማቸውም ከእስራኤል ዜጋዎች ጋር አይቈጠርም፤ ከነበሩበት የስደት ሕይወት ወደ አገራቸውም አይመለሱም በማለት ነቢዩ ሕዝቅኤል ያረጋግጣል(ሕዝ 13፡9)፡፡ እነዚህ ሐሰተኞች ነቢያት ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶችም ጭምር እንዳሉ ይናገራል፡፡ በእርግጥ ሐሰተኞች ሴቶች ነቢያቶች ትንቢት መናገር ብቻ ሳይሆን በክንድ ላይ የሚደረግ አስማት ይሰፋሉ፤ በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ ኃይል እንዲኖራቸው ለማድረግ አስበው ረዣዥም የራስ መጠምጠሚያ ያበጃሉ፤ ሞት የማይገባቸውን ይገድላሉ፤ እፍኝ ገብስ ወይም ቁራሽ እንጀራ ለማግኘት ብለው አሳፋሪ ነገር በማድረግ እግዚአብሔርን ያዋርዳሉ(ሕዝ 13፡17-19)፡፡ ከእንግዲህ ግን አሳሳች ትንቢታቸውና የውሸት ራእያቸው እንዳበቃና እግዚአብሔርም ሕዝቡን ከእነርሱ ኃይል እንደሚታደግ ያረጋግጣል(ሕዝ 13፡23)፡፡

· ነቢዩ ሕዝቅኤል ከተናገራቸው የትንቢት ቃል ውስጥ ስለ ሕዝብ እረኝነት የሚገልጸው ይገኝበታል፤ ለመሆኑ እረኛ ማለት ምን ማለት ነው ? በነቢዩ ሕዝቅኤል ጊዜ የነበሩት የሕዝብ እረኞች ተግባር ምን ይመስል ነበር?

እረኛ ወይም የእረኝነት ተግባር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ሕዝብን ከማገልገል ኃላፊነት አኳያ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ በተለምዶ እረኛ በጎችና ፍየሎችን ከብቶችንም ጭምር የሚያሰማራ(መዝ 23፡2)፣ የጠፋውን የሚፈልግ(ሉቃ 15፡3-7)፣ እንዲሁም ከአደገኛ የዱር እንስሳት መንጋውን የሚጠብቅ ነው(1 ሳሙ 17፡34-35)፡፡ እረኛ በጎቹን በስማቸው እንደሚያውቃቸውና እንደሚከተሉትም እንዲሁም ስለ መንጋው ሕይወቱን እንኳ ሳይቀር አሳልፎ እንደሚሰጥ እንረዳለን (ዮሐ 10፡1-15)፡፡ ስለዚህ በአብዛኛው ቦታ የእረኝነት ተግባር ከትልቅ የአገልግሎት ኀላፊነት ጋር በተያያዘ መልኩ እንደተገለጸ እንረዳለን፡፡ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በተገቢው መልኩ የማይጠብቁ ባለሥልጣኖች ከባድ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ነቢዩ ኤርምያስ ያስገነዝበናል(ኤር 23፡1-4፤ ኤር 25፡32-38)፡፡ ከሁሉም በላይ ሕዝቡን በተገቢው መልኩ ቀንና ሌሊት ሳይሰለች የሚጠብቀው እውነተኛው እረኛ እግዚአብሔር ነው(መዝ 23፡1፤ ሕዝ 34፡11-31)፡፡ በአዲስ ኪዳን ደግሞ ይህንን ሕይወቱን እንኳ ሳይሰስት ስለ በጎቹ አሳልፎ በመስጠት የእረኝነት ተግባሩን የተወጣው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው(ዮሐ 10)፡፡

ሕዝቅኤል እንደ ሕዝብ እረኛ ሆነው የተመረጡት የእስራኤል መሪዎች ላይ ትንቢት የመናገር ኃላፊነት እንዳለበት ተነግሮታል(ሕዝ 34፡1)፡፡ የእስራኤል እረኞች በጎቻቸው በማሠማራት በሚገባ አልጠበቁም፤ ለደከሙት ክብካቤ አላደረጉም፤ የታመሙትን አላዳኑም፤ የተሰበሩትን አልጠገኑም፤ የባዘኑትን አልመለሱም፤ የጠፉትን አልፈለጉም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ በግፍና በጭካኔ ገዟቸው(ሕዝ 34፡4)፡፡ በጎቹም እረኛ ስለሌላቸው ተበታተኑ፤ በከፍተኛ ኮረብታዎችና ተራራዎች ተንከራተቱ፤ በምድርም ገጽ ተበተኑ፤ የሚጠብቃቸውና ፈልጎ የሚያገኛቸውም አልተገኝም፤ የምድር አራዊትም ቦጫጭቀው በሉአቸው(ሕዝ 34፡5-6)፡፡ በአጠቃላይ እረኞቹ በጎቹን ሳይሆን ራሳቸውን ብቻ የሚንከባከቡና የሚጠብቁ ሆነዋል(ሕዝ 34፡8)፡፡ እረኛ ካለመኖሩ የተነሣ በጎቹ በአራዊቶች ተሰደዱ፤ ተበታተኑ፤ እረኞች የተባሉትም በጎቹን ፈልገው ለማግኘት አልተሰማሩም፤ በራሳቸው ጥቅም ብቻ ተጠመዱ(ሕዝ 34፡7)፡፡

ይህንን የተመለከተው እግዚአብሔር ራሱ በጎቹን እንደሚፈልግና በጥንቃቄ እንደሚጠብቃቸው፣ ከተበተኑበትም እንደሚሰበስባቸው፣ ወደ እስራኤል ተራራዎችና ምንጮች ሁሉ እንደሚመራቸው፣ በእስራኤል ለምለም የሆኑ የመሠማሪያ መስኮች በሚገኙባቸው ተራራዎችና ሸለቆዎች ሁሉ አሠማርቶ ያለ ስጋት እንዲመገቡ እንደሚያደርጋቸው ያረጋግጥላቸዋል(ሕዝ 34፡13-15)፡፡ እግዚአብሔር በቅንነት የሚፈርድ እረኛ ስለሆነ መልካሙን ከመጥፎ ይለያል፤ የተጨቈኑትን ነፃ ያወጣል፤ አደገኛ የሆኑት አራዊት ከምድር ያስወግዳል፤ የተሰበሩትን ይጠግናል፤ የታመሙትን ይፈውሳል፤ በዚህ ዓይነት ሁኔታ በጎቹን ይታደጋል(ሕዝ 34፡16-18)፡፡

· በትንቢተ ሕዝቅኤል ውስጥ ሰፊ ቦታ ይዘው ከሚገኙት የትንቢት ቃል ውስጥ "ስለ ሕዝቡ የወደፊት ተስፋ" የሚናገረው ክፍል ይገኛል፡፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሰጠው የወደፊቱ የተስፋ ሕይወት በምን ዓይነት መልኩ ተገልጾአል?

በትንቢተ ሕዝቅኤል ውስጥ የተስፋ ሕይወት በተለያየ መልኩ ተገልጾ ይገኛል፡፡ እስራኤላውያን ባቢሎን ውስጥ በስደት በመንከራተት ላይ እንደነበሩ፣ ነቢዩ ሕዝቅኤልም በዚሁ ሕዝብ መካከል እንደኖረና የነቢይነት ተግባሩን እንደተወጣ ይታወቃል፡፡ ይህ በመከራና በሥቃይ ውስጥ የነበረው ሕዝብ እግዚአብሔር እርግፍ አድርጎ እንደማይተወውና ወደፊት ኑሮውን የተሻለ እንደሚሆን በተስፋ ይጠብቅ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም የሕዝቡን መጸጸትና ወደ ንስሓ መመለስ አይቶ ለሕዝቡ የተለያዩ ተስፋዎች በተለያየ መልኩ ሲገልጽና ሕዝቡን በማጽናናት ሲያበረታታ ይታያል፡፡ እነዚህም የወደፊቱ የተስፋ ሕይወት መገለጫዎች እንደሚከተለው ተጠቅሰዋል፡፡

- በደረቅ አጥንቶች የተመሰሉትና ተስፋ በመቁረጥ ላይ የነበሩት እስራኤላውያን ሕይወት ዘርተው ዳግመኛ ወደ አገራቸው ተመልሰው አዲስ ሕይወት መኖር ይጀምራሉ(ሕዝ 37፡1-14)፡፡

- የሕዝባቸውም ቁጥር እጅግ የበዛ ይሆናል፤ ቤተ መቅደሳቸውም ለዘላለም ጸንቶ በሚኖርበት ሁኔታ ዳግመኛ ይታነጻል፤ እነሱርም ለእግዚአብሔር የተመረጠ ቅዱስ ሕዝብ ሆነው ይኖራሉ(ሕዝ 37፡15-28)፡፡

- ይሁዳና እስራኤል አንድ መንግሥት ይሆናሉ፤ ሁሉንም በአንድነት የሚያስተዳድር አንድ ንጉሥ ይኖራቸዋል፤ ዳግመኛም ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፤ መንግሥታቸውንም በሁለት አይከፈልም(ሕዝ 37፡22)፡፡

- እግዚአብሔር እራሱ መልካም እረኛ ይሆንላቸዋል፤ ከዳዊት ዘር የሆነ መልካም እረኛ ያስነሣላቸዋል(ሕዝ 34)፡፡

- በቀድሞ ጊዜ እስራኤልና ይሁዳ በጎረቤቶቻቸው ተወረው፣ ንብረታቸው ተዘርፈው፣ ቤተ መቅደሳቸው ረክሶ፣ እነርሱም ተዋርደው ለመሰደድ ይገደዱ ነበር፡፡ ከአሁን በኋላ ግን በጦርነት ኃያል ነው የተባለው በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ እንኳ እስከነ ሠራዊቱ ይሸነፋል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በሰላም ይኖራሉ(ሕዝ 38)፡፡

- እስራኤላውያን ለመንጎቻቸው፣ ለእርሻቸውና ለራሳቸው ውሃ በቀላሉ አያገኙም ነበር፡፡ የድርቅ አደጋ በተደጋጋሚ ይገጥማቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሰውና እንስሳ እንዲሁም ሰብሎቻቸው ይጐሰቋቈሉ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ውሃ ብዙ ጊዜ የግጭት ምክንያት ሆኖ እስራኤልና አጐራባች አገሮች ወደ ጦርነት ሁሉ ይገቡ ነበር፡፡ ወደፊት ግን የውሃ ችግራቸው ይቀረፋል፤ ከቤተ መቅደስ ሥር እንኳ ሳይቀር ውሃ ይፈልቃል፡፡ የሙት ባሕር ወይም ጨው ባሕር በመባል የሚታወቀው እንኳ ታድሶ ጥሩ ውሃ ይሆናል። ልዩ ልዩ ፍጥረታት በውስጡ መኖር ይጀምራሉ( ሕዝ 47፡1-12)፡፡

- ኢየሩሳሌም በድጋሚ ታንሰራራለች፤ ያማረ ቤተ መቅደስም በውስጥዋ ይታነጻል፤ የእግዚአብሔር ክብር ወደ ቤተ መቅደስ በድጋሚ ይመለሳል፤ በተጨማሪም ኢየሩሳሌም የዓለም ሁሉ መናገሻ ወይም ማዕከል ከመሆንዋም በላይ የእግዚአብሔር በረከት ምንጭ ትሆናለች፡፡

ምድሪቱን በድጋሚ በነገዶቻቸው ቁጥር ይከፋፈልዋታል፤ ዘላቂ ርስትም ትሆንላቸዋለች፡፡ ልጆች ወልደው በእስራኤላውያን መካከል የሚኖሩትም የውጭ አገር ተወላጆች አብረው ከሚኖሩት ከእስራኤል ሕዝብ ነገድ ጋር የራሱ ድርሻ ይኖረዋል(ሕዝ 47፡21-23)፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

1. ነቢዩ ሕዝቅኤል ስላገለገለበት ወቅት፣ ስለ ነቢይነት የአገልግሎት ሕይወቱና ስለነበረው የግል ባሕርይ በተመለከተ ትክክል ያልሆነው የትኛውን ነው?

ሀ) ሕዝቅኤል ለ390 ቀናት በቀኝ ለ40 ቀናት ደግሞ በግራ ጐኑ በጡብ ላይ ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ተኝቶ ያሳለፈ ነቢይ ነው፡፡ ለ) ሕዝቅኤል በስደት ላይ ሆኖ ከወገኖቹ ጋር ባቢሎን ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ ሐ)ነቢዩ ሕዝቅኤል የሚወዳትን ሚስቱ ተቀሥፋ በሞት ስትለየው እንዳያለቅስና እንዳያዝን በተነገረው መሠረት አላለቀሰም፡፡ መ) እንደ እሳት ነበልባል የሚያበራ የሰው አምሳያ ነቢዩ ሕዝቅኤልን በራስ ጠጉሩ ይዞ ከምድር ወደ ሰማይ አነሣውና ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳደረሰው፡፡ ሠ) ሕዝቅኤል ነቢይ ብቻ ሳይሆን ካህንም ጭምር ነበር፡፡

2. ስለ ጣዖት አምልኮና በጣዖት አምልኮ ምክንያት ወደፊት ይመጣል ተብሎ በነቢዩ ሕዝቅኤል ስለተነገረው ቅጣት ትክክል ያልሆነው የትኛውን ነው?

ሀ) ሕዝቡና መሪዎቻቸው ቤተ መቅደስ ውስጥ እንኳ ሳይቀር ጣዖታት አመለኩ፤ ለማይታወቁ ምስሎችም ሰገዱ፡፡ ለ)የሕዝብ መሪዎች ኢየሩሳሌምን በግፍ ሥራ የተሞላች አደረግዋት፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ያየናል በማለት ይፈሩ ነበር፡፡ ሐ)የእግዚአብሔር ትእዛዝ ፈጽመው የኖሩት በግንባራቸው ላይ ልዩ ምልክት ስለተደረገባቸው ልዩ ጥበቃ ተደረገላቸው፡፡ መ)ኢየሩሳሌም ለአይሁዳውያን ለሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ወሳኝ የሆነች ከተማ ነች፡፡ ሠ)የእስራኤላውያን መሪዎች ጀርባቸውን ወደ ቤተ መቅደስ አድርገው የምትወጣዋን ፀሐይ በማምለክ ወደ ምሥራቅ ተንበርክከው ይሰግዱ ነበር፡፡

3. ነቢዩ ሕዝቅኤል በስፋት ከተናገራቸው የትንቢት ቃል ውስጥ ስለ ወደፊቱ የተስፋ ሕይወት በዋናነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ተስፋ ከተገለጸባቸው መንገዶች ውስጥ ትክክል ያልሆነው የትኛውን?(ሕዝ ከምዕራፍ 34 እስከ 38 መነበብ አለበት)፡፡

ሀ) እግዚአብሔር አደገኞች አራዊት ከምድር ያስወግዳል፤ በጎቹም በሰላም ተሠማርተው ይኖራሉ፡፡ ለ) በበጎች የተመሰሉትና እግዚአብሔር የሚመግባቸው መንጋ የእስራኤል ሕዝቦች ናቸው፡፡ ሐ) አዲስ ልብና አዲስ አእምሮ ይሰጣቸዋል፤ የድንጋይ ልብ አውጥቶ የሚታዘዝ ልብ ይሰጣቸዋል፡፡ መ) እግዚአብሔር መቃብራቸው ከፍቶ ያወጣቸዋል፤ ወደ እስራኤል ምድርም ይመልሳቸዋል፡፡ ሠ)የቱባል ሕዝቦች ገዥ የሆነው ጎግ ኃያል ይሆናል፤ በመጨረሻም በእግዚአብሔር ይሸለማል፡፡

4. ነቢዩ ሕዝቅኤል በዝሙት ኃጢአት ስለተባበሩት እኅትማማቾች ይናገራል፡፡ እነዚህ እኅትማማች የተባሉት እነማን ናቸው? (በመጀመሪያ ስለ እነዚህ አመንዝራ እኅትማማቾች የሚናገረውን ምዕራፍ ፈልጎ ማግኘት ያስፈልጋል)

ሀ) ሰማርያና ግብጽ ለ)እስራኤልና ሰማርያ ሐ) ሰማርያና ኢየሩሳሌም መ) ይሁዳና ባቢሎን ሠ) ባቢሎንና ግብጽ ናቸው፡፡

5. ነቢዩ ሕዝቅኤል የደረቁ አጥንቶች ስለተከማቹበት ሸለቆ ይናገራል(ሕዝ 37)፡፡ እነዚህ የደረቁ አጥንቶች ዳግመኛ ሕይወት እንደሚያገኙ ትንቢት ይናገራል፡፡ ለመሆኑ እነዚህ "የደረቁ አጥንቶች" የተባሉት እነማን ናቸው?

ሀ) በስደት ላይ ባቢሎን ውስጥ በጉስቁልና የሚገኙ እስራኤላውያን ናቸው፡፡ ለ) መከራና ችግር የደረሰባቸው ነቢያት ናቸው፡፡ ሐ) በአገልግሎት ሕይወት የደከሙና የተሰላቹ ካህናቶች ናቸው፡፡ መ) ጣዖት ሲያመለኩ የነበሩት የሕዝብ መሪዎች ናቸው፡፡ ሠ) በጦርነት ምክንያት የሞቱ ሕዝቦች ናቸው፡፡

6. "የሰው ልጅ ሆይ ይህ የብራና ጥቅል ብላ፤ ወደ እስራኤል ሕዝብ ሄደህ ተናገር አለኝ" ይላል ነቢዩ ሕዝቅኤል፡፡ ቀጥሎም "እኔም የብራናው ጥቅል በበላሁት ጊዜ ጣፋጭነቱ እንደ ማር ሆነልኝ" ይላል(ሕዝ 3)፡፡ ለመሆኑ ይህ የብራና ጥቅል የተባለው ምንድን ነው?

ጣፋጭነቱ እንደማር ነው የተባለበት ምክንያት ምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት