እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፳፫ - የነቢያት መጻሕፍት ጥናት (ትንቢተ ኤርሚያስ-ክፍል ፩)

ክፍል ሦስት - ትምህርት ሃያ ሦስት

የነቢያት መጽሐፍት ጥናት - ትንቢተ ኤርምያስ - ክፍል ፩

Ermias· ኤርምያስ ማን ነው? ከየትኛው የይሁዳ ክፍል የተገኘ ነቢይ ነው? ቤተሰባዊ ሕይወቱስ ምን ይመስላል?

ኤርምያስ የሚለው የግሪክ ስም የተተረጐመው "የርሜያሁ" ከሚለው ከዕብራይስጥ ስም ነው፡፡ "የርሜያሁ" የሚለው "የርሜ" እና "ያሁ" የሚሉት የሁለት ቃላት ጥምረት ሲሆን "የርሜ" ከፍ ከፍ ማድረግን ሲያመለክት "ያሁ" ደግሞ "ጃቬ" ከሚለው የእግዚአብሔር መጠሪያ ስም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የስሙ ትርጓሜ አስቸጋሪ ቢሆንም ብዙዎች እንደሚተነትኑት የእግዚአብሔር መጠርያ ስም ከሆነው "ጃቬ" ጋር ተያያዥነትና ተቀራራቢነት ስላለው "እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ያደርጋል" በሚል ይተረጐማል። {jathumbnail off}

ኤርምያስ የካህኑ የሕልቅያስ ልጅ ሲሆን አገሩም ከኢየሩሳሌም ወጣ ብሎ የሚገኝ ልዩ ስሙ ዐናቶት በመባል የሚጠራ መንደር እንደሆነ ተጠቅሷል(ኤር 1፡1)። ነቢዩ ኤርምያስ የኖረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በሰባተኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻና በስድስተኛው ምዕተ ዓመት መጀመርያ አካባቢ ላይ ነው። በእርግጥ በ621 ዓ.ዓ ንጉሥ ኢዮስያስ ጥልቅ በሆነ የተሃድሶ መንፈስ በመነሣሣት አረማዊ አምልኮን በማስወገድና እውነተኛ የሆነውን አምልኮተ እግዚአብሔር እንዲስፋፋ ማድረጉን ይታወቃል፡፡ ይህ ኢዮስያስ ያደረገውን ሃይማኖታዊ ለውጥ ወይም ተሃድሶ ነቢዩ ኤርምያስ እጅግ በጣም ደግፎት እንደነበር ከቅዱሳት መጻሕፍት እንረዳለን(2 ነገ 23፡1-25)፡፡ በተጨማሪም ኤርምያስ በ626 ዓ.ዓ አካባቢ ንጉሥ ኢዮስያስ በይሁዳ በነገሠ በአሥራ ሦስተኛው ዓመት ለነቢይነት እንደተጠራና ከተጠራም ከ40 ዓመታት በኋላ የኢየሩሳሌምን መማረክ እንዳየ ከመጽሐፉ እንረዳለን(ኤር 1፡1-10)፡፡

ኤርምያስ ከእግዚአብሔር በታዘዘው መሠረት ለሕዝቡ ምልክት እንዲሆን ሚስት እንዳያገባ፣ ወደ ግብዣም ሆነ ወደ ልቅሶ እንዳይሄድ ተከለከለ(ኤር 16)፡፡ ኤርምያስ ሕዝቡንና ኢየሩሳሌምን እጅግ በጣም ይወድ የነበረ ነቢይ ቢሆንም ከእግዚአብሔር በተገለጠለት የትንቢት ቃል መሠረት ሕዝቡን በባቢሎናውያን መማረካቸውና ወደ ስደት መሄዳቸው እንደማይቀር ነገራቸው፡፡ ከዚህም በላይ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ስጡ፤ ተገዙም፤ ምርኮኞችም እስከ 70 ዓመት ድረስ ወደ አገራቸው አይመለሱም ብሎ ከእግዚአብሔር የተገለጠለትን የትንቢት ቃል ተናግሯል(ኤር 25፡8-11፤ ኤር 27)፡፡

· በነቢዩ ኤርምያስ ስም የሚጠራ ትንቢተ ኤርምያስ የተባለ መጽሐፍ እንዳለ ይታወቃል፤ የዚህ መጽሐፍ ይዘትና ጥንቅር ምን ይመስላል?

ትንቢተ ኤርምያስ በስፋቱና ባካተታቸው ብዙ የትንቢት ቃላት እንዲሁም በትምህርቱ ጥልቀት ምክንያት ከነቢዩ ኢሳይያስ ቀጥሎ የሚጠቀስ ታላቁ ነቢይ ነው፡፡

ትንቢተ ኤርምያስ በራሱ በነቢዩ ኤርምያስ መጻፉ ግንዛቤ የሚሰጡ ማስረጃዎች ቢኖሩም መጽሐፉ ሙሉ በሙሉ በራሱ በኤርምያስ የተጻፈ ስለመሆኑ ግን አጠራጣሪ ሆኖ ኖሯል፡፡ በእርግጥ የመጽሐፉ ይዘት የመረመሩ ሊቃውንት ነቢዩ ኤርምያስ የመጽሐፉ ሙሉ ጸሐፊ መሆኑን ይጠራጠራሉ፡፡ መጽሐፉ በምናይበት ጊዜ ግን ብዙ ዐይነት የአጻጻፍ ስልቶች የተከተለና ወጥነት የሌለው ሆኖ እናገኘዋን፡፡ አጻጻፉም ውስጥ ንግግሮች፣ ያለፉትን ነገሮች አስታዋሽ የሆኑ ታሪካዊ ይዘት ያላቸው ትረካዎች(ኤር 36-37)፣ ራእዮች(ኤር 1፡11-19)፣ ውይይቶች(ኤር 5፡1-8፤12፡1-6)፣ ቤተ መቅደስ ውስጥ የተደረጉ ስብከቶች ወይም ንግግሮች(ኤር 7፡1-15፤ 26፡1-14)፣ ትእዛዞች(ኤር 16፡1-13)፣ ሙሾዎች(7፡29)፣ የንስሓ ጥሪዎች(ኤር 4፡1-4)፣ ትምህርቶች(ኤር 7፡1-15) ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም የነቢዩ የግል ብሶቶች(ኤር 11፡18-23)፣ በሚታዩና መልእክት አስተላላፊ በሆኑ ምልክቶች የተደገፉ የነቢዩ የግል የሕይወት ታሪኮች(ኤር 18-19) የመሳሰሉትንና ሌሎችም እናገኛለን፡፡ ስለዚህ መጽሐፉ እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ በትክክልና ግልጽ በሆነ ሁኔታ እንዲህ የተከፈለ ነው ማለት ቢያዳግትም የአጻጻፉ ዘይቤው ዘርፈ ሰፊነትና ቅደም ተከተል ባለው መልኩ አለመጠናቀሩ ሲታይ ከአንድ ሰውና በአንድ ወቅት ብቻ የተጻፈ ነው ብሎ ለመደምደም ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ምንአልባትም ነቢዩ ኤርምያስን እንደ ጸሐፊ ሆኖ ሲያገለግለው የነበረው ባሩክ በዚህ ሂደት ተሳታፊነቱ እጅግ በጣም የሰፋ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ትንቢተ ኤርምያስ ከሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት ጋር ብዙ ተወራራሽ የሆኑ ሀሳቦች ሲኖሩት ከኦሪት ዘዳግም ጋር ደግሞ አንዳንድ ሀሳቦች ይጋራል፡፡ ነገር ግን የሁለተኛው መጽሐፈ ነገሥትና ኦሪት ዘዳግም የጻፉት ከትንቢተ ኤርምያስ ይውሰዱ ወይም የትንቢተ ኤርምያስ ጸሐፊ የሌሎቹን ሥራ ካመሳከረ በኋላ ትንቢተ ኤርምያስን ይጻፍ በትክክል ለማወቅ የሚረዱ መረጃዎች እንደሌሉ ሊቃውንት ይስማማሉ፡፡ በአጠቃላይ ትንቢተ ኤርምያስ የአጻጻፍ ስልቱ አንድ ወጥ ባይሆንም መጽሐፉ ውስጥ ያሉ ነገሮች የማይጋጩ ወይም እርስ በርሳቸው የማይቃረኑ ከመሆናቸውም በላይ መጽሐፉ ጥልቅ የሆኑ ምስጢሮች የያዘና የአንድን ነቢይ ማንነትና የአገልግሎት ተግባሩን እስከነ መከራውና ሥቃዩ ጋር ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

· ኤርምያስ ገና ከሕፃንነቱ ለነቢይነት እንደተጠራ ይታወቃል፤ እንዲያውም ገና በእናቱ ማሕፀን ውስጥ እያለ እግዚአብሔር ለነቢይነት አጨው፡፡ ኤርምያስ እንዴት ነው ይህንን ትልቅ የአገልግሎት ጥሪ የተቀበለው?

እግዚአብሔር ኤርምያስን ለአገልግሎት ሲጠራው ገና ድሮ በእናቱ ማሕፀን ከመፀነሱ በፊት እንደተመረጠና ከመወለዱም በፊት ለይቶት ለሕዝቦች ሁሉ ነቢይ አድርጎ እንደሾመው ይነግረዋል፡፡ ኤርምያስ ይህንን ጥሪ ሲሰማ እሱ የነበረበት ሕዝብ አኗኗር ሁኔታ ያውቅ ስለነበር የሚጠብቀው ተልእኮ እጅግ በጣም ብዙና ከባድ መሆኑን በመረዳት "ገና ልጅ ስለሆንሁ የመናገር ችሎታ የለኝም" በማለት የጥሪውን ምላሽ ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር ግን ገና ልጅ ነኝ አትበል፤ ምክንያቱም የምትሄደው እኔ ወደ ምልክህ ሕዝብ ነው፤ የምትናገረውም እኔ የማዝዝህን ቃል ሁሉ ነው፤ እኔም ከአንተ ጋር ሆኜ ስለምታደግህ እነርሱን ከቶ አትፍራቸው በማለት ሙሴን እንዳበረታታው ኤርምያስንም ጥሪውን ተቀብሎ ወደ አገልግሎት ጐዳና እንዲሰለፍ ደግሞ ያበረታታዋል፡፡

ነቢይ የእግዚአብሔር ተናጋሪ አፍ ወይም "የእግዚአብሔር መናገሪያ አፍ" እንደሆነ አስቀድሞ ተጠቅሷል፤ ይህ አፍ የሚያስተላልፈው ቃል የተቀደሰ፣ ሕዝብን የሚያንጽና ወደ ቅድስና የሚመራ ቃል ነው፡፡ ስለዚህ ነቢያቶች ሲጠሩ ይህንን የተቀደሰውን ቃል ለመናገር ወይንም ይህንን ተልእኮ ለመወጣት ብቁ አይደለሁም በማለት ትህትና የተሞላበት ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ጥሪውን ላለመቀበል ሙሉ ነጻነትና መብት ቢኖራቸውም የእግዚአብሔር የጥሪ ግብዣ ግን በመቋቋም በእንቢታቸው አይጸኑም፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ መበረታታትና ምልክት ማግኘት ግን ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም ነው ኤርምያስ እግዚአብሔር እጁን ዘርግቶ ከንፈሮቼን ዳሰሰ፤ እነሆ የምትናገረውን ቃል ሰጥቼሃለሁ፤ እነሆ መንቀልና ማፍረስ፣ ማጥፋትና መገለባበጥ፣ ማነጽና መትከል እንድትችል በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ሥልጣን ሰጥቼሃለሁ በማለት እግዚአብሔር እንዳነጻውና ቃሉንም እንዳስታጠቀው የሚናገረው(ኤር 1፡9-10)፡፡

ኤርምያስ የነቢይነት ጥሪውን ተቀብሎ ነቢይ ተብሎ ለመጠራት ብቻ ሳይሆን አስቸጋሪ የሆነውን የነቢይነት ተግባሩን ለመወጣትና ወደ ፊት ለመጓዝ ምንም አላመነታም፡፡ ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን መንቀልና ማፍረስ፣ ማጥፋትና መገለባበጥ፣ ማነጽና መትከል እንዲችል በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ሥልጣን ተሰጥቶታል(ኤር 1፡10)፡፡ ይህ ሲባል የነበረውን ሊያጠፋ ወይንም በመንግሥታት ላይ የተቃውሞና የጥላቻ መንፈስ ከወዲሁ በማሳደር ወደ ተግባሩ ሊገባ ሳይሆን ቀድሞ የነበረውንና ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ የሆኑትን ነገሮችን እንዲያስተካክልና እንዲያቀና ኃላፊነት እንዳለበት ለመግለጽ ነው፡፡

በሌላ መልኩ የኤርምያስ ጥሪ አንደሌሎቹ ነቢያቶች እስራኤላውያንን ወይም አይሁዳውያንን ብቻ ለመስበክ ወይም ለማስተማር ሳይሆን የእግዚአብሔር መልእክት ቃል ለአረማውያንም ጭምር ለማዳረስ ነው። በዚህም መሠረት የነቢይነት አገልግሎቱ በአንድ ሕዝብ ወይም አገር ብቻ ሳይወሰንና ድንበር ሳይገድበው የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት ነቢይነቱን በብዙ ቦታዎች አስተምሮበታል፡፡ እሱ ከሰበካቸው ሕዝቦች መካከል እንደ ምሳሌነት ለመጥቀስ ያህል ሞአብ(48)፣ አሞን(49፡1-6)፣ ኤዶም(49፡7-22)፣ ደማስቆ(49፡23)፣ ግብጽ(46)፣ ፍልስጤም(47)፣ ከዳርና ሀዞር(49፡28-33)፣ ኤላም(49፡34) እና ባቢሎን(50-51) ይገኙበታል፡፡

· ነቢዩ ኤርምያስ እግዚአብሔር መመለክ የሚገባው አምላክ መሆኑንና ከእርሱ ሌላ ጣዓታትን ማምለክ ኃጢአት መሆኑን በረደጋጋሚ አስተምሮአል፡፡ ይህ ትምህርት በምን ዓይነት መልኩ ነው ነቢዩ ኤርምያስ ለሕዝቡ ያብራራውና ያስተማረው?

ነቢዩ ኤርምያስ በነበረበት ወቅት እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ማምለክ፣ ማገልገልና መታዘዝ በመተው እንደ በዓል ያሉ ጣዖታትን ማምለክ ጀምረው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን ገና ጥንት በሙሴ አማካይነት እኔ እግዚአብሔር አምላክህ እጅግ ቀናተኛ ስለሆንሁ ተቀርጾ የተሠራውን ማንኛውንም ጣዖት አታምልክ፤ አትስገድለትም ብሎ ነበር(ዘጸ 20፡4-6)፡፡ ነገር ግን እስራኤላውያን በተለያዩ ጊዜያት ይህንን ትእዛዝ በመተላለፍ ፈተና ውስጥ ሲገቡና ጣዖታትን በማምለክ እግዚአብሔርን ሲያሳዝኑ እንደኖሩ ከቅዱስ ቃሉ እንረዳለን፡፡

ሕዝቡ በሕይወታቸው ጉዞ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተደረገላቸውን በጎ ውለታ ሁሉ ዘንግተው ምንም ማድረግ ወደ ማይችሉት አማልክቶች ዘንድ መሄዳቸውንና ከንቱ ልፋታቸውን ያሳዘነው እግዚአብሔር በነቢዩ አማካኝነት ደጋግሞ ይናገራል፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር እኔን አምላካቸውን ምንም ሊያደርጉላቸው በማይችሉ ከንቱ አማልክት ለውጠውኛል፡፡ የሕይወት ውሃ ምንጭ የሆንሁትን እኔን ትተውኛል፤ ምንም ውሃ መያዝ የማይችሉ ቀዳዳ ጉድጓዶችንም ለራሳቸው ቈፍረዋል በማለት የሕዝቡን ጣዖት አምላኪነት ደግሞ ደጋግሞ ይገልጻል(ኤር 2፡11-13)፡፡ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆኑ ነቢያቶችም በበዓል ስም ትንቢት ተናገሩ፤ ከንቱ የሆኑ ጣዖታትንም አመለኩ፤ የሕዝብ ገዢዎችም በእግዚአብሔር ላይ አመፁ(ኤር­­ 2፡8)፡፡

ይህንን ዓይነት ጣዖት አምላኪነት በተንሰራፋበት ማኅበረሰብ ውስጥ ነው ነቢዩ ኤርምያስ አገልግሎቱ የጀምረውና "እምነታችን እውነተኛው አምላክ በሆነው በአንዱ እግዚአብሔር ብቻ" መሆን አለበት በማለት ያስተማረው፡፡ እምነታቸው በአንዱ እግዚአብሔር ብቻ እንዲያደርጉ ነቢዩ የተለያዩ ዘዴዎች በመጠቀም ለማስረዳት ሞክሯል፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ጣዖቶችን በማምለክና ለባዕዳን አማልክቶች በመስገድ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ማሳዘንና ማስቆጣቱን በመተው ወደ እውነተኛው አምላክ መመለስ ምንም ዓይነት አማራጭ የሌለውና ትክክለኛ የሆነ መፍትሔ ከመሆኑም በላይ ሕዝቡን ከሚመጣውም ጥፋት ሊያድናቸው እንደሚችል የነቢይነት ጥሪውን ደጋግሞ ያሰማቸዋል(ኤር 3፡14-18)፡፡

በሌላ መልኩ ይህ እውነተኛ አምላክ ታጋሽ፣ ርኁሩኅ፣ መሐሪ፣ ቸርና ሰዎችን አፍቃሪ እንደሆነ ነቢዩ በተለያየ መልኩ ይገልጻል፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ከብዙ የትዕግስት ጥበቃ በኋላ ቁጣውን ይነዳል፤ ነገር ግን ለተጸጸቱት ምሕረቱን በድጋሚ ያወርዳል፡፡

· እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን ቻይ፣ ሁሉን አድራጊ አምላክ መሆኑን ነቢዩ ኤርምያስ በተደጋጋሚ በተለያየ መልኩ ገልጾአል፤ ይህንን አሳብ በምን ዓይነት መልኩ ነው ሕዝቡን ማስረዳት የመረጠው?

ነቢዩ ኤርምያስ በሸክላ ሠሪው ቤት ሆኖ የሸክላ ሠሪውንና የሚሠራውን ዕቃ ምሳሌ በመጠቀም የሁሉ ነገር (የሁሉ ሥራ) ባለቤት እግዚአብሔር መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ሸክላ ሠሪው ጭቃውን ለውሶ በሚፈልገው ዓይነት እንደሚሠራውና ጭቃውንም በሸክላ ሠሪው እጅ እንደሚገኝ ሁሉ ሕዝቡም በእግዚአብሔር እጅ ወይም በሥልጣኑ ሥር እንደሆነና በሕዝቡ ላይ ሁሉንም ነገር የማድረግ ኃይል እንዳለው ያስረዳል(ኤር 18፡6)፡፡

በሌላ መልኩ ነቢዩ ኤርምያስ ከእግዚአብሔር በታዘዘው መሠረት ከሸክላ የተሠራ ገንቦ በመውሰድ ከሕዝቡና ከካህናቶች መካከል በተመረጡት ሰዎች ፊት ሰባበረው፡፡ ይህ የተሰበረው የሸክላ ገንቦ ተመልሶ ሊጠገን እንደማይችል ሁሉ በአመፃቸውና በእምቢተኛነታቸው የሚጸኑት እልኸኞች ሕዝቦችና የሚኖሩበት ከተማ በዚሁ ዓይነት መሰባበር እንደሚችልና መቅሠፍትም እንደሚያዘንምባቸው ይናገራል(ኤር 18፡12፤ 19፡1-13)፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር የሰውን አእምሮና የሰውን ልብ እንደሚመረምር፣ እያንዳንዱም ሰው በአካሄዱና በሥራው መጠን እንደሚቀጣው ያስረዳል(ኤር 17፡10)፡፡ ለዚህም ነው ነቢዩ ሁሉን ቻይ የሆንህ አምላክ ሆይ! አንተ ግን ሁሉን ነገር በትክክል ትመረምራለህ፤ በልባቸውና በአእምሮአቸው የተሰወረውንም ነገር በትክክል ታውቃለህ በማለት የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት፣ ሁሉ አዋቂነትና ሁሉ አድራጊነት የሚያረጋግጠው(ኤር 20፡12)፡፡

· ዕለተ ሰንበት የማክበርን አስፈላጊነት በተለያዩ ነቢያት በተለያየ ጊዜ ትምህርት ሲሰጥበት ነበር፤ ነቢዩ ኤርምያስ ዕለተ ሰንበት ማክበርን በተመለከተ የነበረው አመለካከት ምን ይመስላል?

ገና ጥንት በሙሴ የነቢይነት አገልግሎት ጊዜ እግዚአብሔር ትእዛዛትን ሲሰጥ የሰንበትን ቀን አክብር፤ ቀድሰውም፤ ሥራህን ሁሉ የምታከናውንባቸው ስድስት ቀኖች አሉልህ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእኔ የተቀደሰ የዕረፍት ቀን ነው፤ በዚያን ቀን ማንም ሰው ሥራ አይሥራ፤ አንተም ሆንህ ልጆችህ፣ አገልጋዮችህም ሆኑ እንስሳትህ፣ በአገርህ ውስጥ የሚኖሩ መጻተኞችም ቢሆኑ ምንም ሥራ አትሥሩበት ብሎ ነበር(ዘጸ 20፡8-10)፡፡ ሆኖም ግን ይህንን ትእዛዝ በተለያዩ ጊዜያት በሕዝቡ ሲጣስና ሕዝቡ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሳይሆን ራሱ የፈቀደውን ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡

ነቢዩ ኤርምያስ በነበረበት ጊዜ የነበረው ሕዝብም ይህንን ትእዛዝ ባለማክበሩ ምክንያት ነቢዩ ዳግመኛ የእግዚአብሔር ትእዛዝ እያስታወሰ ያስጠነቅቃቸዋል፡፡ ነቢዩ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ለሕዝቡ ሲያስተላልፍ የቀድሞ አባቶቻችሁ ቃሌን አላዳመጡም፤ ትእዛዜንም አልፈጸሙም፤ ይልቁንም እልኸኞች በመሆን ለእኔ መታዘዝንና ከእኔ መማርን እምቢ አሉ በማለት ሕዝቡ የቀድሞ አባቶቻቸው የሠሩትን እነርሱም እንዳይደግሙት ያስጠነቅቃቸዋል(ኤር 17፡23)፡፡ በዚህም መሠረት እግዚአብሔር ሰንበትን እንዲያከብሩ ዳግመኛ ሲያዛቸው እንግዲህ የሚያዳምጡኝ ከሆኑ እነዚህ ሕዝብ ትእዛዜን እንዲጠብቁ ንገራቸው፤ በሰንበት ቀን ምንም ዓይነት ሸክም ይዘው በከተማዪቱ በሮች አይግቡ፤ ሰንበትን የተቀደሰ ቀን አድርገው ያክብሩ እንጂ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አይሥሩ ይላቸዋል(ኤር 17፡24)፡፡

የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በልቦናቸው አድሮ ሰንበትን የሚያከብሩት ብዙ በረከትን ከማግኘታቸውም አልፎ ነገሥታቶቻቸውና መሳፍንቶቻቸው ሥልጣናቸው እንደ ዳዊት የተጠናከረ፣ በሕዝቡና በአገሪቱ ተቀባይነታቸው እጅግ በጣም የተወደደ እንደሚሆን ያስረዳቸዋል(ኤር 17፡25-26)፡፡ ይህን ሳያደርጉ ቀርተው እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው በእልከኝነታቸው የሚጸኑ ከሆነ ግን የእግዚአብሔር ቁጣ እንደ እሳት ይፈጃቸዋል፤ የከተማቸው የቅጽር በሮችና ቤተ መንግሥቶቻቸውም በእሳት ይነዳሉ(ኤር 17፡27)፡፡

ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ክፍል ፪ ማጠቃለያ ላይ ይቀርባሉ

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ፤  መሪ ካህን፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ ፦ የትምህርቱ አስተባባሪ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

 

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት