እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፳ - የጥበብ መጻሕፍት ጥናት (መዝሙረ ዳዊት)

ክፍል ሁለት - ትምህርት ሃያ

የጥበብ መጽሐፍት ጥናት- መዝሙረ ዳዊት

Mezmure Dawit► መዝሙረዳዊትከጥበብመጽሐፍትይመደባልን? ለምን?

በእርግጥ በዝሙረ ዳዊት ከጥበብ መጽሐፍት የመመደቡ ነገር በሁሉም ሊቃውንት ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ እውነታ አይደለም፡፡ ብዙዎች መዝሙረ ዳዊት ለብቻው እንዲጠና ይመክራሉ፡፡ ሌሎች ግን ይዘቱን ከመረመሩ በኋላ መዝሙረ ዳዊት ከጥበብ መጽሐፍት መመደቡ ተገቢ መሆኑን አምነው ጥናታቸው ያካሄዳሉ፡፡ የሚመደብበትም ዋና ምክንያት በውስጡ ያካተተው ሰፋ ያለ ትምህርት ነው፡፡ ይህ ትምህርት ጥበብን ጨምሮ ብዙ የሕይወት ክፍሎችን ይዳስሳል፡፡

►መዝሙረ ዳዊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እና በቤተ ክርስቲያን ልዩ ቦታ ይዞ እንደሚገኝ ይታወቃል፤ መዝሙረ ዳዊት በውስጡ ምን ምን ስላካተተ ወይም ይዘቱ ምን ዐይነት ስለሆነ ነው ትልቅ ቦታ እንዲሰጠው ያደረገው?

መዝሙረ ዳዊት በውስጡ 150 መዝሙርና ጸሎት ፣ ትምህርትና ቅኔ በአንድነት ይገኙበታል(መዝ 15፤ 17፤ 31፤ 56)፡፡ "መዝሙረ ዳዊት" ተብሎ የሚጠራበት ዋናው ምክንያት ቅዱስ ዳዊት የጻፋቸው ፣ የዘመራቸውና በአንድነት ያጠናከራቸው ናቸው ተብሎ በተለምዶ ስለሚታመን ነው፡፡ በእርግጥ ዳዊት ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በገና እየደረደረ ይዘምር ነበር(1 ሳሙ 18፡ 10)፡፡ ነገር ግን መዝሙረ ዳዊት ተብሎ በተሰየመው መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱት መዝሙራት ሁሉ እርሱ የጻፋቸው ወይም የዘመራቸው ወይም የሰበሰባቸው አይደሉም፡፡ {jathumbnail off}

መዝሙረ ዳዊት ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለግል ጸሎት እጅግ የተወደደ መጽሐፍ ነው፡፡ በውስጡ ለየጊዜው ሁሉ ወይም ለተለያየ ወቅት የሚሆን ጸሎት የያዘ ነው፡፡ ይህም ለሐዘንና ለደስታ ፣ ለመልካምም ሆነ ለክፉ ፣ የአንድ ሰው ሁኔታ ማንኛውም ቢሆን የሚያመሰግንበት ወይም የሚተክዝበት ተስማሚ መዝሙር ወይም ጸሎት ይገኛል፡፡ በዚህ መጽሐፍ እየተጠቀመ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር በመንፈስ ሊወያይ ፣ ኅብረት ሊያደርግና ሊያድግ ይችላል(2 ጴጥ 3፡ 18)፡፡ እነዚህ ጸሎቶች ሰብስበው በአምልኮ ሥርዓታቸው ጊዜ ሲጠቀሙባቸው የቈዩት የእስራኤል ሕዝብ ናቸው፤ ኋላም ዘግየት ብሎ በቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸው ውስጥ እንዲጨመሩ ተደርገዋል፡፡ ስለዚህ መዝሙሮቹ በግል ወይም በማኅብረት የሚጸለዩ ናቸው፤ የሚጸለዩትም እግዚአብሔርን ለማመስገን ፣ ጥበቃው ፣ ደኅንነቱና ይቅርታውን ለማግኘትና ለተለያየ ምክንያት ነው፡፡ እስራኤላውያን የአምልኮ ሥርዓታቸው ውስጥ መዝሙረ ዳዊት ይጠቀሙበት ነበር፤ አሁንም ይጠቀሙበታል፡፡ በክርስትና እምነትም ለተለያየ የጸሎት አገልግሎት መዝሙር ዳዊት በግልም ሆነ በጋራ ይጠቀሙበታል፡፡

► በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የተካተቱ 150 መዝሙራት (150 ምዕራፍ) እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በአንዳንድ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእነዚህ መዝሙራት ጥንቅር ቅደም ተከተል የተለያየ ነው፤ ይህ ልዩነት ለምን ሊፈጠር ቻለ?

መዝሙረ ዳዊት 150 መዝሙራት ያቀፈ ሆኖ በ150 ምዕራፍ የተከፋፈለ መጽሐፍ ነው፡፡ የመጀመሪያው የመዝሙር ጥንቅር ያቀፈው "የማሶሬቶች መጽሐፍ" የተባለውና በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈው 150 መዝሙራቱ ምንም ሳይዛባ በቅደም ተከተል አስቀምጦታል፡፡ ሰባ ሊቃናት ወይም ሰባ ሊቃውንት የተባሉት ግን ወደ ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ ሲተረጉሙት የተወሰኑ መዝሙራት ጥንቅር ለውጠዋል፡፡ ይህም በዕብራይስጥ በመዝሙር 9 (ምዕራፍ ዘጠኝ) እና መዝሙር 10 (ምዕራፍ 10) የነበረውን ወደ አንድ መዝሙር በማጠቃለል መዝሙር 9 (ምዕራፍ ዘጠኝ) ብለው ጠሩት፡፡ መዝሙር 114 እና መዝሙር 115 በአንድ በማጣመር መዝሙር 116 ብለው ጠሩት፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በዕብራይስጡ መዝሙር 116 የነበረው ለሁለት በመክፈል መዝሙር 114 እና መዝሙር 115 ብለው ሰየሙት፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በዕብራይስጡ መዝሙር 147 (ምዕራፍ 147) የነበረው መዝሙር 146 እና መዝሙር 147 ብለው ከፈሉት፡፡ ስለዚህ ከግሪኩ ቋንቋ (ከሰባ ሊቃውንት መጽሐፍ) ወደ አማርኛና ግእዝ የተተረጐሙት ላይ ከመዝሙር 8 (ምዕራፍ 8) ጀምሮ ለውጥ ስለሚያስከትል በቅንፍ ውስጥ ( ) ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሆን የምዕራፍ ቀጥር ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ይህም ማለት በዕብራይስጡ መጽሐፍ መዝሙር 10 የሆነውን ከግሪክ በተተረጐመው ላይ ምዕራፍ ዘጠኝ ይሆናል፤ አንባቢን ለመርዳት በቅንፍ ውስጥ ግን ምዕራፍ 10 ይጻፋል፡፡ ይህንን የበለጠ ለመረዳት የሚከተለውን ሰንጠረዥ መመልከቱ ጥሩ ነው፡፡

የመዝሙረ ዳዊት ጥንቅር በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ

የመዝሙረ ዳዊት ጥንቅር በግሪክ (ሰባሊቃውንት) መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ

ከምዕራፍ አንድ (1) እስከ ስምንት (8)

ከምዕራፍ አንድ (1) እስከ ስምንት (8)… ምንም ልዩነት የለም

ምዕራፍ ዘጠኝ (9) እና ምዕራፍ ዐሥር (10)

ምዕራፍ ዘጠኝ (9)

ከምዕራፍ 11-113

ምዕራፍ 10-112…. የምዕራፍ ቅደም ተከተል ለውጥ ተከሰተ

ምዕራፍ 114-115

ምዕራፍ 113

ምዕራፍ 116

ምዕራፍ 114-115

ምዕራፍ 117-146

ምዕራፍ 116-145

ምዕራፍ 147

ምዕራፍ 146-147

148-150

148-150 ምንምልዩነትየለም

በአጠቃላይ የመዝሙራት ቁጥር ጥንቃቄ ይጠይቃል፤ ምክንያቱም በምሥራቅና በምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ልዩነት አለ፡፡ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን 70 ሊቃውንት ሲተረጉሙት በተጠቀሙባቸው ቁጥሮች ሲሠሩ ምዕራባውያን የዕብራይስጥን ይዘዋል፡፡ ስለዚህ ከመዝሙር 9 አንሥቶ እስከ መዝሙር 146 ድረስ ምሥራቃውያን(እንደ ኢትዮጵያዊት ቤተ ክርስቲያን ያሉት) በምዕራባውያን ለምሳሌ በእንግሊዝኛ ቁጥር ላይ 1 መጨመር ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንዲሁም በአማርኛ መጽሐፍ መዝ 22 የሆነው በእንግሊዝኛ መጽሐፍ 23 ይሆናል፤ መዝ 106 የሆነው ደግሞ መዝ 107 ይሆናል፡፡ ይህ መጽሐፍ የዕብራይስጥን ቁጥሮች ይከተላል(በድሮው መጽሐፍ ቅዱስ በቅንፍ ውስጥ ያሉትን ማለት ነው)፡፡ በአሁኑ ጊዜ የምንጠቀምበት ቀለል ባለ አማርኛ ተተረጉሞ የተዘጋጀው ግን የዕብራይስጡ ትርጓሜ የተከተለ ስለሆነ ችግር አይፈጥርም፡፡

►150 መዝሙራት ሁሉ ቅዱስ ዳዊት ጻፋቸውን ወይስ የሌላ ሰውም ተሳትፎ ያለበትና በብዙዎች የተሰበሰቡ ናቸው?

መዝሙራቱ ሁሉ ዳዊት የጻፋቸው አይደሉም፤ ሆኖም በአርእስቱ ላይ የዳዊት ስም ተጠቅሷል፤ በቀሩትም የቆሬ ልጆች ስም ተጠቅሷል(መዝ 42፤ መዝ 44)፤ የአሳፍ ስም ተጠቅሷል(መዝ 50፤ 73)፤ የኤማንና የኤታን የሙሴም ስም ተጠቅሶአል(መዝ 88-89)፡፡ ስለዚህ መዝሙራቱ በብዙዎች የተጻፈና የተሰባሰበ ነው እንጂ በቅዱስ ዳዊት ብቻ የተደረሱ አይደሉም፡፡ ይህም ማለት ይህን መጽሐፍ ያዘጋጁት ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ የተገኙና የተለያዩ ሰዎች ሲሆኑ አንዳንዶቹ ግን በንጉሥ ዳዊት የተጻፉ ናቸው፡፡

መዝሙራቱ ማን እንዳሰባሰባቸው በትክክል ባይታወቅም በ1 ዜና መዋ 16 ላይ ዳዊት በታቦቱ ፊት የሚዘምሩ መዘምራንን እንዳደራጀ ስለተገለጸ እርሱ ሥራውን ጀምሮ ይሆናል፡፡ ከእርሱ በኋላ ግን ሌላ ሰው በነገሩ ተሳትፎአል።

ይህንን የምንረዳው ከመዝሙራቱ ይዘት በመነሣት ነው፡፡ ከመዝሙሮቹ መካከል ከቅዱስ ዳዊት በፊት የነበሩ አሉ፤ በቅዱስ ዳዊት ወቅት የተጻፉና የተዘመሩ አሉ፤ ከቅዱስ ዳዊት በኋላ ብዙ ቆይቶ የተቀናበሩ መዝሙራት አሉ፡፡ የምናውቀውም ከምርኮ ዘመን በኋላ የተዘጋጁት እንደ መዝ 74፤ 96፤ 137፤ የሐጌና የዘካርያስ እንደተባሉትም እንደ 146፤ 147፤ 148 ስለሚገኙ ነው፡፡ መዝሙሮቹ ውስጥ የተለያየ ወቅት ውስጥ የነበረውን የኑሮ ሁኔታ እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ እስራኤላውያን በባቢሎን ስደት በነበሩበት ወቅት ማለትም ከክ.ል.በፊት ከ598 እስከ 537 ዓ.ዓ በነበረው አስቸጋሪ ጊዜ የተዘመሩ አሉ፡፡ ይህም የምንረዳው ዘማሪው እዚህ በስደት ላይ ሳለሁ ልቤ በሐዘን ተሰብሮአል፤ ስለዚህ አሳቤን ወደ እርሱ እመልሳለሁ እያለ የነበረበትን ሁኔታ ስለሚገልጽ ነው(መዝ 42፡ 6)፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር ለዘወትር ይጥለናልን? ከእንግዲህስ ወዲህ ለእኛ ቸርነት አያደርግምን እያለ ስለነበረበት ሁኔታ ይናገራል(መዝ 77፡ 7)፡፡ በዚህ ወቅት እስራኤላውያን በስደት ስለነበሩ ስለ ስደት ኑሮ ይዘምሩ ነበር፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ከስደት ሲመለሱ የነበሩበት ሕይወት የሚያንጸባርቁ መዝሙራትም አሉ፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ ባመጣን ጊዜ ሕልም እንጂ እውነት አልመሰለንም ነበር በማለት ከስደት መመለሳቸውን ይናገራል(መዝ 128፡ 1)፡፡ ስለዚህ መዝሙራቱ ከእስራኤላውያን የወቅቱ ፖለቲካዊ ፣ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ሕይወት በተያያዘ መልኩ የተዘመሩ ስለሆኑ በተለያየ ወቅት በተለያየ ሰው የተጠናቀሩና በኋላ ግን በአንድ ሰው አማካይነት በአንድነት የተሰባሰቡ መዝሙራት ናቸው፡፡

► መዝሙር ዳዊት 150 መዝሙራት ያካተተ ከሆነ እንዴትና በስንት መጻሕፍት ይከፈላል?

መዝሙረ ዳዊት በአምስት መጻሕፍት ተከፍሏል፡፡ እነዚህም መጻሕፍት፦

ከምዕራፍ 1-41፤ ከምዕራፍ 42-72፤ ከምዕራፍ 73-89፤ ከምዕራፍ 90-106፤ ከምዕራፍ 107-150 ናቸው ፡፡ የአንዱ መጽሐፍ ፍጻሜ የሚታወቀው "ከዘላለም እስከ ዘለዓለም እግዚአብሔር ይባረክ፡፡ አሜን አሜን ይሁን ይሁን" የሚሉ ቃላት ስለተጻፉበት ነው፡፡

►የመዝሙራት ዓይነቶች እንዴት መለየት እንችላለን? መዝሙራት በምን ዓይነት ሁኔታ ይከፈላሉ? አመዳደባቸውስ እንዴት ነው?

የመዝሙራት ዓይነቶች መለየት አስቸጋሪ ቢሆንም ቀጥሎ የተጻፈው ሰንጠረዥ ሊመራን ይችላል፡፡

የምስጋና መዝሙሮች ፦

ሀ) የእግዚአብሔርን ስም የሚያመስግኑ(መዝ 8፤ 20፤30፤34፤65፤68፤75፤76፤83፤87፤88፤91፤95፤107፤136)፡፡

ለ) ከመከራ ማዳኑን የሚያወድሱ (መዝ 18፤30፤34፤65፤75፤115፤116፤118፤138)፡፡

እነዚህ መዝሙሮች ዋና ትኩረታቸው እግዚአብሔርን ማመስገንና ማወደስ ነው፡፡ የሚያመሰግኑትም እግዚአብሔር ለፍጥረት ሁሉ ስላደረገውና እያደረገው ስላለው ድንቅ ሥራ ነው፡፡

ኃጢአተኛ በኃጢአቱ የሚያዝንበት(መዝ 6፤ 32፤38፤51፤102፤130፤143)፡፡

የዚህኛው ክፍል ዋና ትኩረት የኃጢአተኛ ሰው መጸጸትና ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበው ልመና ነው፡፡ ኃጢአተኛው እግዚአብሔርን እንዳሳዘነ አምኖ በመገንዘብ ስሕተቱን ይቀበላል፤ ያዝናል፤ ይጸጸታል፤ ወደ እግዚአብሔር እየጸለየ ምሕረት ይለምናል፡፡

በመከራ ያለ ሰው የሚጸልይበት (የሚጽናናበት)(መዝ 3፤5፤7፤17፤20፤30፤31፤54፤59፤142)፡፡

በመከራ ውስጥ ያለ ሰው ስለደረሰበት መከራ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻል፤ ይመጸናል፤ መከራውን ለእግዚአብሔር ይናገራል፤ መከራ እንዲደርስበት ያደረጉት ሰዎችን ይራገማል፤ በመከራ ውስጥ እያለ እግዚአብሔር ለምን ዝም እንዳለው ይጠይቃል፤ ከመከራው እንዲያወጣውም ይማጸናል፡፡

ዘማሪው እግዚአብሔርን ፣ ሕጉንና ቤቱን የሚናፍቅበት(መዝ 16፤ 17፤ 19፤ 40፤ 42፤ 45፤ 63፤ 73፤ 84፤ 119፤ 122፤ 128፤ 132)፡፡

እነዚህ መዝሙሮች የሚያተኩሩት በእግዚአብሔር ሕግ ፣ በቤተ መቅደስና በኢየሩሳሌም ከተማ ዙሪያ ላይ ነው፡፡ ቤተ መቅደስ እንደ የእግዚአብሔር ማደሪያ ቦታ የተጠቀሰበትም አለ፡፡ ስለዚህ ዘማሪው ወደ እግዚአብሔር ቤት ለመሄድ እንደሚናፍቅና እንደሚደሰት ይናገራል፡፡ ዘማሪው እግዚአብሔርን ለማየት እንደሚናፍቅ በተለያየ መልኩ ይገልጻል፤ ለምሳሌ ዋለያ የምንጭ ውሃ ለማግኘት እንደሚናፍቅ እኔም አንተን ለማየት እናፍቃለሁ ይላል(መዝ 42፡ 1)፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር ሆይ ! አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ለማግኘት በብርቱ እናፍቃለሁ፤ ሁለንተናዬ አንተን ይመኛል፤ ውሃ በማጣት ደርቆ እንደተሰነጣጠቀ መሬት ነፍሴ አንተን ተጠማች ይላል(መዝ 63፡ 1)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የእግዚአብሔር ሕግ እንደ ብርሃን ሆኖ ሰዎች የሚመራ ስለሆነ መከበር እንዳለበትና የሚያከብሩትም በረከት እንደሚቀዳጁ የሚናገር ክፍል ነው፡፡ ለምሳሌ መዝሙር 128 ላይ እግዚአብሔር የሚያከብሩና ትእዛዛቱን በመጠበቅ የሚኖሩ ደስ ይበላቸው እያለ ይዘምራል(መዝ 128፡ 1)፡፡ በተጨማሪም ቃልህ እንደ መብራት ይመራኛል፤ ለመንገዴም ብርሃን ነው እያለ የእግዚአብሔር ሕግ ወደ እውነተኛው መንገድ እንደሚመራ ይናገራል(መዝ 119፡ 105)፡፡

ስለ መሲሕ የሚናገሩ(መዝ 2፤ 8፤ 16፤ 22፤ 40፤ 45፤ 69፤ 72፤ 110)፡፡

ይህ የሚያተኩረው እግዚአብሔር ስለሚልከው መሢሕና ስለዘሚያደርግለት ጥበቃና እንክብካቤ ላይ የሚናገር ነው፡፡ ይህ መሢሕ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ(መዝ 2፡ 7) ፣ በቀኙ እንደሚያስቀምጠውና(መዝ 110፡ 1) እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን እንደሆነ ይናገራል(መዝ 110፡ 4)፡፡

ለትምህርት የሚሆኑ (መዝ 37፤ 49፤ 50፤ 52-55፤ 60፤ 74፤ 78፤ 89፤ 104፤ 119፤ 127)፡፡

እነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ብዙ ምክር አዘል አባባሎችና ትምህርቶች ተካተዋል፤ እነዚህም አባባሎችና ምክሮች መጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ ከተገለጹት ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው፡፡ የሰዎች ትዕግሥት ፣ ታማኝነት ፣ ትሕትና ፣ በጎ ተግባራትና የመሳሰሉት ባሕርያት ወይም ክንውኖች ለሰው ልጅ መንፈሳዊ እርካታ እንደሚያሰጡና ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋ እንደሚያቀደጁ ይናገራል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ክፉ ማድረግና የእግዚአብሔር ትእዛዝ መዘንጋት ወደ ጥፋት እንደሚመራና ከእግዚአብሔርም ጋር እንደሚያቈራርጥና መጨረሻውም እንደ በረሓ አበባ በፍጥነት መርገፍ እንደሆነ ያስተምራል(መዝ 37፡ 20)፡፡

ካህናት የቤተ መቅደስን ደረጃዎች ሲወጡ የሚዘምሩአቸው የመዐረግ መዝሙሮች (መዝ 120-134)፡፡

እነዚህ መዝሙሮች በተለያየ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ የእነዚህ መዝሙሮች አብዛኛው ትኩረት የእግዚአብሔር ጠባቂነት ለማግኘት ቢሆንም ሌሎች አሳቦችም በመዝሙሮች ውስጥ በጸሎትና በልመና መልክ ተካተዋል፡፡

ሃሌሉያ ብለው የሚጀምሩት የሃሌል መዝሙሮች (የስብሐት መዝሙሮች) (መዝ 111-113፤ 146፤ 148-150)፡፡

እነዚህ መዝሙሮች ከሌላው ክፍል የሚለዩበት ዋናው ምክንያት ገና ከመዝሙሩ ጅማሬ እግዚአብሔርን ያመስግናል፡፡ መዝሙሮቹ ሲጀምሩ "እግዚአብሔር ይመስገን" ወይም "እግዚአብሔርን አመስግኑት" በማለት ይጀምራሉ፡፡ ስለዚህ መዝሙሮቹ የምስጋና መዝሙሮች ተብለው ይታወቃሉ፡፡

► መዝሙራት በሙሉ ጠቃሚነታቸው የታወቀ ቢሆንም ብዙ ጊዜ የሚዘወተሩና በስፋት የሚዘመሩ የትኞቹ ናቸው?

መዝሙራት በሙሉ በተለያየ መልኩ ተከፋፍለው ለግልና ለማኅበር የጸሎት አገልግሎት ይውላሉ፤ ሁሉም መንፈሳዊ ጠቀሜታቸው ብዙ ነው፤ ቢሆን እንኳ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እጅግ የታወቁት የእረኝነት መዝሙር (መዝ 23) ፣ የይቅርታ መዝሙር (መዝ 32) ፣ የንስሐ እና የረዳትነቱ (መዝ 51) ፣ የኑዛዜ (መዝ 91) ፣ የጠባቂነቱ (መዝ 103) ፣ የምስጋና (መዝ 104) ፣ የፍጥረት (መዝ 119) ፣ የሕግ (መዝ 121) ፣ የመንገደኛ (መዝ 139) እና ስለ ድንቅ ዕውቀቱ (መዝ 139) የሚናገሩት ናቸው፡፡

►በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ዘማሪው ጠላቶቹን ሲረግምና እግዚአብሔር እንዲበቀልለት ሲማጸን ይታይል፤ ይህ የጠላትነት እንዲሁም የብቀላ መንፈስና ምኞት እንዴት ሊገለጽ ይችላል?

በእርግጥ በጥቂት መዝሙሮች ላይ ጸሐፊው ጠላቶቹን ሲረግምና በቀል ሲመኝባቸው ይገኛል(መዝ 35፤ 59፤ 69፤ 109)፡፡ በእርግጥ በወቅቱ የእስራኤል ሕዝብ ጠላቶች የነበሩት እንደ የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደሆኑ ይታሰብ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የማያመልኩ አሕዛብ በእስራኤል ሕዝብ ላይ በጦርነት ወይም በተለያየ ምክንያት ችግር ሲፈጥሩ ዘማሪው እነዚህ ችግር ፈጣሪዎችን ይረግማል፤ እግዚአብሔር እንዲያጠፋቸውም ይመኛል፡፡ ለምሳሌ በመዝሙር 79 ላይ አምላክ ሆይ ! አረማውያን ምድርህን ወረሩ፤ ቤተ መቅደስህን አረከሱ፤ ኢየሩሳሌምን አፈራረሱአት፡፡ የሕዝብህንና የአገልጋዮችን ሬሳ ለሰማይ አሞራዎችና ለዱር አራዊት ምግብ አድርገው ሰጡ እያለ ማንነታቸውና የፈጸሙት የጭካኔ ተግባር ይገልጻል(79፡ 1)፡፡ ስለዚህ በመዝሙር 83 ላይ ዘማሪው እንዲህ ይላል፦ አምላክ ሆይ ! እባክህ ዝም አትበል፤ አትዘግይ፤ ቸልም አትበል፡፡ እነሆ ጠላቶችህ ዐምፀዋል፤ የሚጠሉህ ሁሉ ሸፍተዋል፡፡ በሕዝብህ ላይ በስውር ያደባሉ፤ አንተ በምትወዳቸው ላይ ያሤራሉ እያለ እግዚአብሔር አንድ ነገር እንዲያደርግ ይማጸነዋል(83፡ 1-4)፡፡ ቀጥሎም ስለነዚህ ሰዎች ሲናገር የእግዚአብሔርን ርስት የራሳችን እናደርጋለን ብለው ነበር ይላል(83፡ 12)፡፡ ለዘማሪው እነዚህ ሰዎች የሕዝብ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርም ጠላቶች ናቸው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲበቀላቸው ይማጸነዋል፤ እንደ ትቢያ በትናቸው እያለም እግዚአብሔር በፍጥነት እርምጃ እንዲወስድባቸው ይማጸነዋል(መዝ 83፡ 13)፡፡

በአጠቃላይ መዝሙራቱ በወቅቱ የነበረው የሕዝቡ ደስታ ፣ ኃዘን ፣ መከራ ፣ ስደት ፣ ጦርነት ፣ ሃይማኖት ባህልና የአምልኮ ሥርዓት መሠረት አድርጎ የተጻፉ ስለሆነ ዛሬ እነዚህ መዝሙራት ስናነብ በደንብ ላንረዳው እንችላለን፤ እንዲያውም ግራ ልንጋባና ልንገረምም እንችል ይሆናል፡፡ ስለዚህ የመዝሙራቱ መልእክት በደንብ ለመረዳት መዝሙራቱ በተጻፉበት ወቅት የነበረው የሕዝቡ አኗኗር ግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡

►መዝሙረ ዳዊት በጸሎትም ሆነ በንባብ መልክ በቅዳሴ ጸሎት ውስጥ ይካተታልን? ከተካተተ በምን መልኩ እንደሆነ ቢገለጽ፡፡

መዝሙረ ዳዊት በቅዳሴ ጸሎት ውስጥ ይካተታል፡፡ በላቲን የሊጡርጊያ ሥርዓት በቅዳሴ ላይ ከሚነበቡት ንባባት መካከል አንዱ መዝሙረ ዳዊት ነው፡፡ በቅዳሴ ሰዓት በንባብ ወይም በመዝሙር መልክ ይቀርባል፡፡ ስለዚህ በላቲን ሊጡርጊያ የቅዳሴ ሥርዓት ውስጥ መዝሙረ ዳዊት ሁሌ ይነበባል፤ ይጸለያል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በግእዝ የቅዳሴ ሥርዓት ወስጥም መዝሙረ ዳዊት በተለያየ መልኩ ተካትቶ ይገኛል፡፡ ካህኑ ቅዳሴ ለመጀመር መንበረ ታቦት ላይ በሚዘጋጅበት ጊዜ በቅዳሴው መጀመሪያ ሃሌሉያ "እኔ በቸርነትህ ብዛት ወዳንተ ቤት እገባለሁ" በማለት የሚጸልየው ጸሎት ከመዝሙረ ዳዊት የተወሰደ ነው፡፡ ሌላው በቅዳሴ ጊዜ ሁል ቀን ወንጌል ከመነበቡ በፊት ዲያቆን የሚጸልየው ጸሎት አለ፤ ይህም ጸሎት ምስባክ በሚል መጠርያ ስም ይታወቃል፡፡ ይህ የዕለቱ ምስባክ የሚወሰደው ከመዝሙረ ዳዊት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ በተራ ቀናት ማለትም በዓላት በሌሉበት ቀን የሚባለው ምስባክ፦ ጌታ ሆይ ጸሎቴን ስማ፤ ጩኸቴም ወዳንተ ይድረስ፤ በመከራዬ ቀን ፊትህን ከእኔ ወዲያ አትመልስብኝ የሚለው ሲሆን የተወሰደውም ከመዝሙር 101፡ 1-2 ላይ ነው፡፡

ዕለቱ የማርያም ቀን ከሆነ ወይም በእመቤታችን የተሠየመ ቀን ከሆነ ፦ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋለች፤ ልጄ ሆይ ስሚ፤ እይ፤ ጆሮሽንም ዘንበል አድርጊ የሚለው ሲሆን የተወሰደውም ከመዝሙር 44፡ 9-10 ላይ ነው፡፡ ወይም የልደታ ማርያም ዕለት ከሆነም፦ መሠረቶችዋ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው፤ ከያዕቆብ ድንኳኖች ሁሉ ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል የሚለው ይሆናል(መዝ 86፡ 1-2)፡፡ የክርስቶስ ልደት ከሆነ፦ የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ፤ ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል(መዝ 71፡ 10-11)፡፡ የጥምቀት በዓል፦ ጌታ ሆይ ውኃዎች አዩህ፤ ውሃዎች አይተውህ ፈሩ፤ ጥልቀቶች ተናወጡ፤ ውኃዎቹ ጮሁ(መዝ 76፡ 16)፡፡ ለትንሣኤ(ፋሲካ) በዓል፦ እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤ የወይን ስካር እንደተወው ሰው፤ ጠላቶቹን በስተኋላቸው መታቸው(መዝ 77፡ 25-26)፡፡ የጻድቃን ማሰቢያ ዕለት ከሆነ፦ ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፤ እንደ ሊባስ ዝግባም ያድጋል፤ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋልና(መዝ 91፡ 12-13)፡፡ የመላእክት ዕለት ከሆነ፦ በመላእክት ፊት እዘምራለሁ፤ ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለ ምሕረትህና ስለ እውነትህ ስምህን አመሰግናለሁ የሚሉት እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ(መዝ 137፡ 1-2)፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን ፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

የትምህርቱ አስተባባሪ ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

 ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

1- ኃጢአተኛ በኃጢአቱ የሚያዝንበትና የሚጸጸትበት መዝሙሮች ከላይ በዝርዝር ቀርበዋል፤ ከእነዚህ መካከል በመዝሙር 32፤38 እና 51(ምዕራፍ 32፤ 38፤ 51 ማለት ነው) መሠረት ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው? ሀ) ኃጢአታቸው ይቅር የተባለላቸውና በደላቸውም ያልተቈጠረባቸው ሰዎች ደስ ሊላቸው ይገባል፡፡ ለ) ዘማሪው በደሉ እንደ ጐርፍ ውሃ እንዳጥለቀለቀውና እንደ ከባድ ሸክም እንደተጫነው ይናገራል፡፡ ሐ) ዘማሪው ኃጢአተኛ ሆኖ መወለዱንና ከተፀነሰበትም ጊዜ ጀምሮ ኃጢአተኛ መሆኑን ይቀበላል፤ ይገልጻል፡፡ መ) እግዚአብሔር ለኃጢአት ሥርየት የሚሆን የሚቃጠል መሥዋዕት ከሰዎች ይፈልጋል፡፡ ሠ) ዘማሪው ኃጢአቱ ሳይናዘዝ ቀኑን ሙሉ በማልቀሱ ምክንያት ሰውነቱ ደከመ፡፡

2 - ከጠቅላላው መዝሙር ውስጥ ዘማሪው እግዚአብሔርን ፣ ሕጉንና ቤቱን የሚናፍቅበት ሁኔታ የሚገልጸውን ሰፋ ያለ ቦታ ይዞ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ መዝሙሮች መካከል ዘማሪው ስለ እግዚአብሔር ሕግ በስፋት የሚናገርበት መዝሙር 119 እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመዝሙር 119 መሠረት ከሚከተሉት ውስጥ ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው? ሀ) የእግዚአብሔር ሕግ የሚወዱ ፍጹም የሆነ ሰላም አላቸው፤ ከቶ ምንም ነገር ሊያሰናክላቸው አይችልም፡፡ ለ) ዘማሪው እግዚአብሔርን የበለጠ ማመስገን እንዲችል ዕድሜውን እንዲያረዝምለት ይማጸናል፡፡ ሐ) ዘማሪው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ አብልጦ ይወዳል፡፡ መ) ዘማሪው የእግዚአብሔር ሕግ ዘወትር ስለሚያሰላስል ከአስተማሪዎቹ ሁሉ የበለጠ ማስተዋል አለው፡፡ ሠ) ስለ አውነተኛ ፍርዱ እግዚአብሔርን በቀን ሰባ ጊዜ እንደሚያመሰግነው ቃል ይገባል፡፡

3 - ዕርዳታ ለማግኘት ከቀረቡት ጸሎቶች ውስጥ አንዱ መዝሙር 69 ላይ የሚገኘው ነው፡፡ በዚህ መሠረት ትክክል ያልሆነው የትኛውን ነው? ሀ) ዘማሪው ያለ ምክንያት የሚጠሉት ሰዎች ከራሱ ጠጉር በላይ የበዙ ናቸው፡፡ ለ) ሰውነቱ በጾም ሲያዋርድና የሐዘን ልብስ ሲለብስ ሰዎች ያከብሩታል፡፡ ሐ) ዘማሪው በሥቃይና በተስፋ መቁረጥ ላይ ይገኛል፡፡ መ) ከእንስሳት መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔር በመዝሙር መመስገን ያስደስተዋል፡፡ ሠ) ዘማሪው በጠማው ጊዜ ጠላቶቹ በውሃ ፈንታ ሆምጣጤ ሰጡት፡፡

4 - ከሚከተሉት ውስጥ ትክክል ያልሆነው የትኛውን ነው? (ይህንን ለመመለስ መዝሙር ከምዕራፍ 1 እስከ ምዕራፍ 10 ያለውን ማንበብ ያስፈልጋል)፡፡ ሀ) በክፉ ሰዎች ምክር የማይሄድ፣ በኃጢአተኞች መንገድ የማይቆም ፣ በፌዘኞች ወንበር የማይቀመጥ የተባረከ ነው፡፡ ለ) እግዚአብሔር ታማኞች የሆኑ ሰዎችን ለራሱ ይመርጣል፡፡ ሐ) ኃጢአተኛ ስለ እግዚአብሔር ግድ የለውም፤ በትዕቢቱም እግዚአብሔር የለም ብሎ ያስባል፡፡ መ) እግዚአብሔር ሰውን ከመላእክት ምንም ሳያሳንሰው የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫነለት፡፡ ሠ) እግዚአብሔር ለራሱ ጡት በሚጠቡ ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀ፡፡

5 - መዝሙረ ዳዊት በአምስት የተለያዩ ክፍሎች እንደሚመደብ ይታወቃል፡፡ መዝሙሩ በአምስት ለመከፈሉ እንደ መለያ ምልክት ሆኖ የሚያስገነዝበን ቃል ወይም ጽሑፍ በየመጽሐፉ ፍጻሜ ይገኛል፡፡ ይህ ገላጭ ምልክት ወይም ጽሑፍ ምንድን ነው?(ምን የሚል ነው?) በያንዳንዱ ክፍል መጨረሻ ላይ የሚገኝበት ምዕራፍና ቁጥር ጥቀስ?

6 - መዝሙረ ዳዊት በመባል የሚታወቁ አንድ መቶ ኃምሳ(150) መዝሙራት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ መዝሙራት ውስጥ ለአንተ⁄ለአንቺ ልብህን⁄ልብሽን የበለጠ የሚነካው (በሚነበብበት ጊዜ ትኩረትህን⁄ትኩረትሽን የሚስበው) የትኛው መዝሙር(ምዕራፍ) ነው? ለምን?

ይህንን የመረጥከው⁄የመረጥሺው መዝሙር ለአንድ ወር ያህል(ቀጣዩ የተልእኮ ትምህርት እስከሚላክ ድረስ) በቀን አንድ ጊዜ እያነበቡ ለመጸለይ ለእግዚአብሔር ቃል መግባት ያስፈልጋል፡፡ ንባቡ ጠዋት ፣ ቀን ወይም ከመኝታ በፊት አልያም በጉዞ ላይ ካልሆነም በእረፍት ጊዜ ሊደረግ ይችላል፡፡ ዋናው ነገር በቀን አንድ ጊዜ የመረጡትን መዝሙር ማንበብና ምሥጢሩን ጥቂት እያስተነተኑ መጸለይ አስፈላጊው ነገር ነው፡፡ በጸሎታችሁ እኛን (የዚህ ትምህርት አዘጋጆችና አስተባባሪዎች) አስቡን፡፡

እግዚአብሔር ጸሎታችንን ይቀበልልን ! አሜን !

አምላኬ ሆይ ልመናዬን ስለምትሰማ ወደ አንተ እጸልያለሁ(መዝ 17፡ 6)፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት