እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ት/ርት ፲፮ - የጥበብ መጻሕፍት ጥናት ክ.2 (መጽሐፈ ምሳሌ)

የጥበብ መጽሐፍት ጥናት - ክፍል ሁለት - ትምህርት ፲፯

መጽሐፈ ምሳሌ

Sapienza2 መጽሐፈ ምሳሌ በማንና መቼ ተጻፈ?  የሚያስተላልፈው መልእክትስ ስለምንድን ነው?

          መጽሐፈ ምሳሌ በፈሊጣዊና በምሳሌያዊ አነጋገር የተዘጋጀ የሥነ ምግባርና የሃይማኖት ትምህርት ነው፡፡ አብዛኛው የሚያወሳው በዕለታዊ ኑሮ ስለሚያጋጥሙ ነገሮች ነው፤ “እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው” የሚለውን መመሪያ በማስገንዘብ ይጀምራል፤ የሚያስተምረውም ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባርን ብቻ ሳይሆን ሰው በዕለታዊ ኑሮው ሊፈጽማቸው የሚገባውን መልካም ጠባይና በጎ ሥራ ጭምር ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ትሕትና ፣ ስለ ትዕግሥት ፣ ስለ ሰብአዊ ርኅራኄና ስለ ታማኝነት ብዙ ትምህርት በምሳሌ ተሰጥቷል፡፡ {jathumbnail off}

          መጽሐፉ የተጻፈበት ጊዜ በግልጽ አይታወቅም፡፡ ምናልባት ሰሎሞን በዘመነ መንግሥቱ ማለትም በ950 ዓ.ዓ ጀምሮት ይሆናል፤ የንጉሥ ሕዝቅያስ ሰዎች በ700 ዓ.ዓ የተወሰነውን ክፍል ጽፈውት እንደሆነ ይታመናል፤ በመጨረሻም አይሁዳውያን ከምርኮ ሲመለሱ ማለትም በ538 ዓ.ዓ በኋላ መጽሐፉን አጠናቀው ሳይጽፉት እንዳልቀረ ይታመናል፡፡ ስለዚህ ምሳሌዎቹ ሁሉ የንጉሥ ሰሎሞን ብቻ አይደሉም፡፡ ከምዕራፍ 1-9 ባለው ክፍል ምክር ሰጪዋ ራስዋ ጥበብ ናት፡፡ በጐዳና ትጮኻለች፤ በከተማዪቱ ከፍተኛ ስፍራ ላይ ትጠራለች(ምሳ 1፡ 20 ፤ 8፡ 1-3 ፤ 9፡ 1-3) ፡፡ ቀጥሎ ከምዕራፍ 10-22 እና ከምዕራፍ 25-29 ራሱ ሰሎሞን የፈጠራቸው ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን ከእግዚአብሔር ዘንድ ልዩ ጥበብን እንደ ተቀበለና ሦስት ሺህ ምሳሌዎች እንደ ተናገረ ታውቋል(1 ነገ 3፡ 10-12 ፤ 4፡ 29-34)፡፡

መጽሐፉ የተጻፈው በግጥም መልክ ነው፤ ምክንያቱም በግጥም የተሰጠ ትምህርት በልብ ስለሚያዝ ነው፡፡ ምሳሌዎቹ ራሳቸውን የቻሉ ናቸውና እያንዳንዱ እየተነበበ ለብቻው ይታሰብበታል እንጂ የተያያዘ ታሪክ እንደሚነበብ ዓይነት ምሳሌዎች አይነበቡም፡፡ ይሁን እንጂ በዓይነት በዓይነቱ በአንድ ክፍል ውስጥ ተጠቅልሏልና እያንዳንዱ ምሳሌ ከተመሳሳዩ ክፍል ጋር ማንበብ ይገባል፡፡ ጌ.ኢ.ክ፣ ጴጥሮስና ጳውሎስም መጽሐፈ ምሳሌን ጠቅሰውታል(ሉቃ 14፡ 8-10 ምሳ 25፡ 6-7 ፤ 1 ጴጥ 4፡ 18 ምሳ 11፡ 31 ፤ 2 ጴጥ 2፡ 22 ምሳ 26፡ 11 ፤ ሮሜ 12፡ 20 ምሳ 25፡ 21-22 ፤ ያዕ 4፡ 6 ምሳ 3፡ 34)፡፡

መጽሐፈ ምሳሌ ገና ከጅምሩ “እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ሞኞች ግን ጥበብና ሥነ ሥርዓት የሚማሩበትን ምክር ይንቃሉ” ይላል(ምሳ 1፡ 7፤ ምሳ 9፡ 10)፡፡ እግዚአብሔር መፍራት ምን ማለት ነው?

እግዚአብሔር አስፈሪ ፣ አሸባሪ ፣ አስደንጋጭ ፣ ቶሎ በመቆጣት የሚቀጣ ፣ ለማጥፋትና በሰዎች ላይ በበቀል መንፈስ ተነሳሥቶ ችግር ለመፍጠር የሚጣደፍ አባት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የሰዎችን ነፃነት በመንፈግ በኃይልና በቁጣ ወይም በአምባገነንነት የሚገዛ አባት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ከሁሉም በፊት አፍቃሪ አባት ነው(1 ዮሐ 4፡ 7-12)፡፡ ይህ አፍቃሪ አባት መሐሪ ፣ ቸር ፣ ለልጆቹ መልካም አሳቢና በጎ አድራጊ ነው፡፡ ይህ አባት ዘወትር ለልጆቹ የሚያስብ ፣ በቀና ጐዳና የሚመራቸው ፣ በችግር ውስጥ ቢገቡ ቶሎ የሚደርስላቸው አባት ነው፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት ማለት እግዚአብሔር አፍቃሪና ሁሉ አድራጊ አባት መሆኑን ተረድቶ ከእርሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መፍጠር ማለት ነው፡፡ የጠበቀ ወዳጅነት ስንፈጥር እርሱን እናደምጠዋለን፤ ሁል ጊዜ በልቦናችን ውስጥ ቦታ እንሰጠዋለን፤ በዕቅዳችን ውስጥ እርሱን እናስቀድማለን፤ የሚያከናውንልን ነገር ሁሉ ተረድተን እናመሰግነዋለን፡፡

          እግዚአብሔር አፍቃሪና ደግ አባት ስለሆነ እኛ በበጎ ጎዳና እንመላለስ ዘንድ ፣ ሕይወታችን ደስታ የተሞላ ይሆን ዘንድ እንዲሁም በመጥፎ ሕይወት ወድቀን እንዳናዝን የሚጠብቁን ትእዛዛት ይሰጠናል(ዘጸ 20፤ ዘዳ 5)፡፡ እነዚህ ትእዛዛት ሁሌም በልባችን ውስጥ ተጽፈው እንዲኖሩ ይፈልጋል፡፡ ሁሌም እነዚህ ትእዛዛት እንድናከብርና እንድንፈጽማቸው ይፈልጋል፤ በእርግጥ እነዚህ ትእዛዛት ራሳችን ከመጥፎ ሕይወት እንድንጠብቅ ይረዱናል እንጂ ነፃነታችን አይገድቡም፡፡ ስለዚህ ጥበበኛ ሰው ከእንቅልፉ ሲነቃ ጀምሮ እስከሚተኛበት ጊዜ ድረስ የእግዚአብሔርን የፍቅር ሕግ እያሰበ ይኖራል፤ ለዚህም ነው “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔር መፍራት ነው” የሚለው፡፡ እግዚአብሔር የሚያከብር ሰውም ሆነ ሕዝብ ይባረካል፤ እግዚአብሔርን እያደመጠና ትእዛዛቱን እየጠበቀ የሚኖር ሰው በሕይወቱ ሙሉ ደስተኛ ሆኖ ይኖራል፤ በመከራና በሥቃይ ቢያልፍም እንኳ ተስፋ ሳይቆርጥ ወደፊት ይጓዛል እንጂ አይደናገጥም፡፡ ስለዚህ ጥበበኛ የሆነ ሁሉ በጥበቡና በችሎታው ሳይሆን በእግዚአብሔር መመካት አለበት፡፡ እግዚአብሔር መፍራት ዕድሜን ያረዝማል፤ ክፉዎች ግን ያለ ዕድሜያቸው በሞት ይቀጫሉ(ምሳ 10፡ 27)፡፡ 

የመጽሐፈ ምሳሌ ጸሐፊ እንዲህ ይላል፤ “ብር ወይም የተሰወረ ሀብት ለማግኘት ጥረት የምታደርገውን ያህል ተግተህ ጥበብን ፈልጋት፡፡ ይህን ሁሉ ብታደርግ እግዚአብሔርን መፍራት ምን እንደሆነ ማስተዋል ትችላለህ፤ የእግዚአብሔርንም ነገር ጠንቅቀህ ለመማር ትበቃለህ፡፡ ጥበብን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፤ ዕውቀትና ማስተዋልን የሚገኙት ከእርሱ ዘንድ ነው፡፡ እርሱ ልበ ቅኖችንና ታማኞችን በጥበቡ ይረዳቸዋል፤ እንደ ጋሻም ሆኖ ይጠብቃቸዋል፡፡ ለተበደሉ ሰዎች በትክክል የሚፈርዱትን ይንከባከባል፤ በታማኝነት የሚያገለግሉትንም ይጠብቃል”(ምሳ 2፡ 4-8)፡፡

በአጠቃላይ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ለራሱና ለቤተሰቡ ጽኑ መታመኛና ዋስትና አለው(ምሳ14፡ 26)፤ እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ስለዚህ ከሞት ወጥመድ ለማምለጥ ከፈለግህ እግዚአብሔርን ፍራ(ምሳ 14፡ 27)፡፡ እግዚአብሔርን ብትፈራ ረዥም ዕድሜ ይኖርሃል፤ ጉዳት ሳይደርስብህ በደስታና በሰላም ትኖራለህ(ምሳ 19፡ 23)፡፡

በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ ስለ ጥበብ ውዳሴ በተለያየ መልኩ ቀርቦአል፡፡ ጸሐፊው ጥበብን ያወድሳታል፤ እንዲያውም እራስዋ አፍ አውጥታ እንደምትናገር ይገልጻታል፡፡ ለመሆኑ በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ ጥበብ በምን ዓይነት መልኩ ተገልጾ እናገኘዋለን?

          ጥበብ ስለራስዋ ስትናገር እንዲህ ትላለች፤ “እግዚአብሔር ከሁሉ ነገር በፊት ፈጠረኝ፤ ከጥንት ጀምሮ የሥራው ተቀዳሚ አደረገኝ፡፡ በጥንት ዘመን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በመጀመሪያ ተሾምሁ” በማለት ገና ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እንደተፈጠረች ትናገራለች(ምሳ 8፡ 22-23)፡፡ በተጨማሪም ከጥንት ጀምሮ ከሁሉ ነገር በፊት ስለመኖርዋ ስትናገር እንዲህ ትላለች፤ “የውሃ ምንጮች ከመፍለቃቸው ፣ ውቅያኖሶችም ከመገኘታቸው በፊት ተወለድሁ፡፡ ተራራዎችና ኮረብታዎች ከመመሥረታቸው በፊት ተወለድሁ፡፡ እግዚአብሔር ምድርንና ሁለንተናዋን ከመፍጠሩ በፊት ፣ ወይም ጥርኝ ዐፈር እንኳ ከመሠራቱ በፊት ተወለድሁ፡፡ እግዚአብሔር ሰማይን በዘረጋ ጊዜ ጠፈርንም ከውቅያኖሶች በላይ ባዘጋጀ ጊዜ እኔ እዚያ አብሬው ነበርሁ” ትላለች(ምሳ 8፡ 24-27)፡፡

          ጥበብ በእግዚአብሔር ከተፈጠረች በኋላ ሰዎችን ወደራስዋ ትጠራለች፤ ጥበበኛ ሆነው እንዲኖሩም ትመክራቸዋለች፡፡ የጥበብ ጥሪ በየከተማውና በየመንደሩ ያስተጋባል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ መጥቀሱ ስለ ጥበብ ጥሪ የበለጠ እንድንረዳ ያግዘናል፡፡ ጸሐፊው እንዲህ ይላል፤ “ጥበብ ቤትዋን ሠራች፤ ሰባት ምሰሶዎችንም ለቤትዋ አቆመች፡፡ ላዘጋጀችውም ግብዣ ፍሪዳ ዐረደች፤ የጣፈጠ የወይን ጠጅም ጠመቀች፤ ገበታም ዘርግታ ማእድ ሠራች፡፡ ገረዶችዋም በከተማው ከፍተኛ ቦታ ላይ ቆመው “ዕውቀት የጐደላችሁ ሰዎች ሁሉ ወደዚህ ኑ !” እያሉ እንዲጣሩ አደረገች፤ ሞኙንም ሰው እንዲህ ትለዋለች ፣ “ና ያዘጋጀሁትን ምግብ ብላ ! የጠመቅሁትንም የወይን ጠጅ ጠጣ ! ዕውቀት ከጐደላቸው ሰዎች ተለይተህ በሕይወት ኑር፤ በማስተዋልም መንገድ ወደፊት ተራመድ” እያለች ትጣራለች(ምሳ 9፡ 1-6)፡፡ 

መጽሐፈ ምሳሌ ለጥበብ ልዩ ትኩረት ይሰጣል፤ ሰዎች ዘወትር ጥበብን እንዲፈልጎ ይቀሰቅሳል፤ ይመክራል፡፡ ለመሆኑ እንደ መጽሐፈ ምሳሌ አገላለጽ ከጥበብ የሚገኘው ጥቅም ምንድን ነው?

ጸሐፊው መጽሐፉ ውስጥ በተለያየ ቦታ ስለ ጥበብ ጠቀሜታ ደጋግሞ ይናገራል፡፡ ጥበብ ከሁሉ ነገር በፊት ያስቀድማል፤ ሰዎች ቀንና ሌሊት ጥበብን እንዲፈልጉ ይመክራል፡፡ እንዲያውም “ሁሉ ነገር በፊት ጥበብን ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው፤ ስለዚህ ሌላ ነገር ለማግኘት ከምትጣጣር ይልቅ ማስተዋልን ለማግኘት ትጋ” ይላል(ምሳ 4፡ 7)፡፡ የጥበብ ጠቀሜታ ብሎ ከዘረዘራቸው ውስጥ ጥቂቶቹ እንደሚከተለው ይጠቀሳሉ፡፡

-       ጥበብን አትተዋት፤ እርስዋም ትጠብቅሃለች፤ ውደዳት፤ እርስዋም ከአደጋ ሁሉ ትከላከልልሃለች (ምሳ 4፡ 6)፡፡

-       ጥበብን ውደዳት፤ እርስዋም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፤ አጥብቀህም ብትይዛት ክብርን ትሰጥሃለች፡፡ የሞገስን አክሊል ታቀዳጅሃለች፤ የተዋበውንም ዘውድ ትሰጥሃለች (ምሳ 4፡ 8-9)፡፡

-       ጥበብ ለሚያስተውለው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል፤ ለመላው ሰውነትም ጤንነትን ይሰጣል (ምሳ 4፡ 22)፡፡

-       ጥበበኛ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሰነፍ ልጅ ግን ለእናቱ ሐዘንን ያተርፋል (ምሳ 10፡ 1)፡፡

-       ጥበበኞች ሰዎች መልካም ምክርን ይቀበላሉ፤ ባለማስተዋል የሚለፈልፉ ሰዎች ግን ወደ ጥፋት ያመራሉ (ምሳ 10፡ 8)፡፡

-        ጥበብን የሚያገኝ ሕይወትን ያገኛል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ደስ ይለዋል፤ ጥበብን ያጣ ራሱን ይጐዳል፤ ጥበብን የሚጠላም ሞትን ይወዳል (ምሳ 8፡ 35)፡፡

-       የጠቢባን ትምህርት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ሕይወትህ በአደጋ ላይ ቢወድቅ እንኳ እንድታመልጥ ይረዳሃል (ምሳ 13፡ 14)፡፡

-       ከጠቢባን ጋር ብትወዳጅ ጠቢብ ትሆናለህ፤ ማስተዋል ከጎደላቸው ሰዎች ጋር ጓደኛ ብትሆን ግን ትጠፋለህ (ምሳ 13፡ 20)፡፡   

መጽሐፈ ምሳሌ ለወጣቶች ሰፋ ያለ ለሕይወት መመሪያ የሚሆን ምክር ይለግሳል፡፡ ከምክሮቹ ውስጥ ጸሐፊው ልዩ ትኩረት የሰጠው ለየትኛው ነው?

ጸሐፊው ወጣቶችን ሲመክር “ልጄ ሆይ ! የማስተምርህን አትርሳ” በማለት ይጀምራል(ምሳ 3፡ 1)፡፡ ከሁሉም በማስቀደም ግን “የጥበብን ቃል አድምጥ፤ በጥንቃቄም አስተውለው” በማለት ለጥበብ ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም “ጥበብ ከውድ ዕንቁ ትበልጣለች፤ አንተ ለማግኘት ከምትመኛቸው ነገሮች ሁሉ ከጥበብ ጋር የሚወዳደር እንድ እንኳ የለም፡፡ ጥበብ ረዥም ዕድሜ ትሰጥሃለች፤ ሀብትንና ክብርንም ትጨምርልሃለች፡፡ ሕይወትህም በደስታና በሰላም የተሞላ እንዲሆን ታደርጋለች፡፡ ጥበብን የሚያገኙ ሰዎች ደስ ይበላቸው፤ ምክንያቱም ጥበብ እውነተኛ ሕይወትን ትሰጣቸዋለች” ይላል(ምሳ 3፡ 15-18)፡፡ በመቀጠልም የተለያዩ ምክሮች ለወጣቶች ይሰጣል፡፡ ከእነዚህም ምክሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

-       ታማኝነትንና እውነተኛነትን አትተው፤ እንደ አንገት ሐብል ተጠንቅቀህ ያዛቸው፤ በልብህም ጻፋቸው፡፡ ይህን ብታደርግ እግዚአብሔርንም ሆነ ሰውን ደስ ታሰኛለህ (ምሳ 3፡ 3)፡፡

-       በሙሉ ልብህ በእግዚአብሔር ታመን እንጂ በራስህ ዕውቀት አትደገፍ (ምሳ 3፡ 5)፡፡

-       በምታደርገው ሁሉ እግዚአብሔርን አስቀድም፤ እርሱም በትክክለኛው መንገድ ይመራሃል (ምሳ 3፡ 6)፡፡

-       “ያለ እኔ ዐዋቂ የለም” በማለት ራስህን በከንቱ አታታልል፤ ይልቅስ ለእግዚአብሔር ታዘዝ፤ ስሕተትንም ከማድረግ ተቈጠብ፡፡ ይህን ብታደርግ እንደተፈተነ መድኃኒት ሰውነትህን በጤንነት ይጠብቃል፤ አጥንትህንም ያጠነክርልሃል (ምሳ 3፡ 7)፡፡

-       ከሀብትህና ምድርህ ከሚያፈራው መልካም ነገር ሁሉ የመጀመሪያውን መባ አድርገህ በመስጠት እግዚአብሔርን አክብር፡፡ ይህን ብታደርግ ጎተራዎችህ በእህል የተሞሉ ይሆናሉ (ምሳ 3፡ 9)፡፡

-       ዕርዳታ እንድታደርግለት ለሚገባው ሰው ዐቅምህ በሚፈቅድልህ መጠን በጎ ነገር ከማድረግ አትቈጠብ፡፡ የተቸገረ ጐረቤትህን ዛሬውኑ መርዳት ሲቻልህ “እሺ ነገ” እያልክ አታመላልሰው (ምሳ 3፡ 28)፡፡

-       አንተን ተማምኖ በአጠገብህ በሚኖረው ጐረቤትህ ላይ በተንኰል ክፉ ነገር ለማድረግ አታስብ (ምሳ 3፡ 29)፡፡

-       ምንም በደል ያላደረሰብህን ሰው ያለ ምክንያት አትክሰሰው (ምሳ 3፡ 30)፡፡

-       በግፈኞች ሰዎች አትቅና፤ ክፉ ሥራቸውንም አትከተል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ክፉ አድራጊዎችን ይጠላል፤ ልበ ቅኖችን ግን አጥብቆ ይወዳቸዋል (ምሳ 3፡ 31-33)፡፡

-       እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይንቃል፤ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል፡፡ ጠቢባን መልካም ዝናን ያተርፋሉ፤ ሞኞች ግን ውርደትን በውርደት ላይ ይጨምራሉ (ምሳ 3፡ 34)፡፡

  መጽሐፈ ምሳሌ ስለ ሥራ ክቡርነትና ሰው ለኑሮው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ለማግኘት መሥራት እንዳለበት በተደጋጋሚ ይመክራል፡፡ ለዚህም ሰነፍ ሰው ከጎበዝ ሰው ጋር በማወዳደር ስለ ሥራ ክቡርነትና አስፈላጊነት ይናገራል፡፡ ጸሐፊው ስለ ሥራ አስፈላጊነት በምሳሌ ከተናገራቸው ውስጥ የተወሰኑትን ማየቱ አስፈላጊ ነው፡፡

-       ሰነፍ ከሆንክ የምትመኘውን ማግኘት አትችልም፤ በትጋት ከሠራህ ግን ትበለጽጋለህ(ምሳ 12፡ 27)፤

-       ሰነፍ አንድ ነገር ለማግኘት አጥብቆ ይመኛል፤ ይሁን እንጂ አያገኝም፤ ትጉህ ሠራተኛ ግን የሚፈልገውን ሁሉ ያገኛል(ምሳ 13፡ 4)፤

-       ተግተህ ብትሠራ መተዳደሪያህ ታገኛለህ፤ ሥራ ፈትና ወረኛ ብትሆን ግን ትደኸያለህ፡፡

-       መሥራት የማይፈልግ ሰነፍ ሰው ራሱን የገደለ ያህል ይቈጠራል(ምሳ 21፡ 25)፡፡

-       ሰነፍ ሰው ከአጥፊ ሰው ተለይቶ አይታይም(ምሳ 18፡ 9)፡፡

-       ያለ ሥራ መቀመጥ እንቅልፍን ያስከትላል፤ ስለዚህ ሰነፍ ሰው ረሀብተኛ ይሆናል(ምሳ 19፡ 15)፡፡

-       አንዳንድ ሰዎች በጣም ሰነፎች ናቸው፤ ሌላው ቀርቶ በወጥ ያጠቀሱትን እንጀራ መጉረስ ይታክታቸዋል(ምሳ 19፡ 24)፡፡

-       መሬቱን በወቅቱ የማያርስ ሰነፍ ገበሬ በመከር ጊዜ የሚሰበስበው ምርት አይኖረውም(ምሳ 20፡ 4)፡፡

-       በሰነፍና ማስተዋል በጐደለው ሰው እርሻ ውስጥ በወይኑም አትክልት ቦታ ሄድሁኝ፤ በአረምና በቁጥቋጦ ተሞልቶ ነበር፤ በዙሪያውም ያለ የግንብ አጥር ፈርሶአል(ምሳ 24፡ 30-31)፡፡   

-       በጎችህንና ከብቶችህን በተቻለ መጠን በጥንቃቄ ጠብቅ(ምሳ 27፡ 23)፡፡

-       ሰነፍነ ሰው መልእክተኛ ማድረግ የገዛ እግርን እንደመቁረጥና መከራን እንደመጋበዝ ይቈጠራል(ምሳ 26፡ 6)፡፡

-       በመንገድ የሚተላለፉትን ሰነፎች ወይም ሰካራሞች የሚቀጥር አሠሪ ያገኘውን ሰው ሁሉ እንደሚያቈስል ቀስተኛ ነው(ምሳ 26፡ 10)፡፡

-       ሰነፍ መቶ ጊዜ ተገርፎ ከሚማረው ይልቅ አስተዋይ ሰው ከአንድ ጊዜ በማይበልጥ ተግሣጽ የሚማረው ይበልጣል(ምሳ 17፡ 10)፡፡

-       ሥራውን በጥንቃቄ የሚሠራ ሰው ከብዙ ሰዎች በመሻል የነገሥታት ባለሟል መሆን ይችላል(ምሳ 22፡ 29)፡፡

-       ታታሪ ገበሬ በቂ ምግብ ይኖረዋል፤ ጥቅም በሌለው ሥራ ላይ ጊዜን ማባከን ግን ሞኝነት ነው(ምሳ 12፡ 11)፡፡

-       ሰነፍ ሰው ሀብት ማግኘት አይችልም፤ ታታሪ ሰው ግን ሀብታም ይሆናል(ምሳ 11፡ 16)፡፡

በአጠቃላይ ጸሐፊው ሥራ ክብር እንደሆነና ኃላፊነቱን በሚገባ የሚወጣ ሠራተኛ ብልኅ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ሰነፍ ሰው ወይም ስንፍናን ግን አጥብቆ ይጠላል፡፡ ሁሉም ሰው በዕለታዊ ሕይወቱ ለሥራ ዋጋ በመስጠት ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ ጸሐፊው ሲናገር “ያለ ድካም በቀላሉ የተገኘ ሀብት መዲያው ይጠፋል፤ ተግቶ በመሥራት የተገኘ ሀብት ግን እየበዛ ይሄዳል” በማለት ስለ ሥራ ክቡርነት ይናገራል፡፡ በተጨማሪም “አስተዋይ ሰዎች ለሚሠሩት ሥራ አስቀድመው ዕቅድ ያወጣሉ፤ ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች ግን አላዋቂነታቸው ይገልጣሉ” በማለት በሥራ ሂደት ውስጥ የዕቅድ አስፈላጊነት ይናገራል(ምሳ 13፡ 16)፡፡ በተጨማሪም “ሰው ዕቅድ ያወጣል፤ ነገር ግን ዕቅዱ በሥራ ላይ የሚውለው እግዚአብሔር “ይሁን” ብሎ ሲፈቅድ ብቻ ነው” ይላል(ምሳ 16፡ 1)፡፡    

መጽሐፈ ምሳሌ ትኩረት ከሚሰጣቸው ነገሮች ውስጥ “ስለ ሰዎች ኃጢአትና ስለ እግዚአብሔር ምሕረት” አንዱ ነው፡፡ ለመሆኑ ጸሐፊው በዚህ ዙሪያ ምን ይላል፤ ምንስ ይመክራል?

-       ከሁሉም በፊት ጸሐፊው ስለ ኃጢአተኛ ሰው እንዲህ ይላል፤ “ኃጢአትህ ለመደበቅ ብትሞክር በኑሮህ ሁሉ ነገር አይቃናልህም፤ ኃጢአትህን ተናዝዘህ ዳግመኛ ኃጢአት ከመሥራት ብትቈጠብ ግን የእግዚአብሔር ምሕረት ታገኛለህ” በማለት ሰው ኃጢአቱን መደበቅ እንደሌለበት ይናገራል(ምሳ 28፡ 13)፡፡

-       የዐመፀኞች መታወቂያ ምልክት ትዕቢታቸውና ትምክሕታቸው ነው፤ ይህም ኃጢአት ነው(ምሳ 21፡ 4)፡፡

-       ዐመፀኞች መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ ስለማይወዱ በግፍ ሥራቸው ይጠፋሉ፡፡ ኃጢአተኞች በጠማማ መንገድ መሄድ ይወዳሉ፤ ልበ ንጹሖች ግን መልካም የሆነውን ነገር ያደርጋሉ(ምሳ 21፡ 8)፡፡

-       በኃጢአተኞች አትቅና፤ እግዚአብሔርን መፍራት የዘወትር አሳብህ ይሁን፤ ይህን ብታደርግ የወደፊት ኑሮህ የተቃና ይሆናል፤ ተስፋህም አያቋርጥም(ምሳ 23፡ 14)፡፡

-       የሰው ኅሊና የእግዚአብሔር መብራት ስለሆነ ውስጣዊ ሰውነታችንን ሁሉ ይመረምራል(ምሳ 20፡ 27)፡፡

-       እውነተኛ የሆነ አምላክ በዐመፀኞች ቤት የሚደረገውን ሁሉ ያያል፤ ዐመፀኞችንም አሽቀንጥሮ በመጣል ያጠፋቸዋል(ምሳ 21፡ 12)፡፡

-       እግዚአብሔር ትምክሕተኞች ሁሉ ይጸየፋል፤ ከቅጣት እንዲያመልጡም አያደርጋቸውም(ምሳ 16፡ 5)፡፡ ታማኝና እውነተኛ ሁን፤ እግዚአብሔር ኃጢአትህን ይቅር ይልልሃል፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ምንም ዓይነት ክፉ ነገር አያገኝህም(ምሳ 16፡ 6)፡፡

-       ሰነፎች ኃጢአት ሲሠሩ በመጸጸት ፈንታ ያፌዛሉ፤ ደጋግ ሰዎች ግን ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸው ይፈልጋሉ(ምሳ 14፡ 9)፡፡

-       ኃጢአተኞች በሄዱበት ስፍራ ሁሉ መከራ ይከተላቸዋል፤ ደጋግ ሰዎች ግን የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ(ምሳ 13፡ 21)፡፡

በአጠቃላይ ኃጢአቱን ተረድቶ ለእግዚአብሔር የሚናዘዝና ዳግመኛ ላለመውደቅ የሚጥር ሰው በእግዚአብሔር ይባረካል፡፡ ለዚህም ነው ጸሐፊው “ደጋግ ሰዎች በምድር ላይ ሳሉ የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ፤ ክፉዎችና ኃጢአተኞች ግን እጅግ የበረታ ቅጣትን ይቀበላሉ” በማለት የሚናገረው(ምሳ 11፡ 31)፡፡ በተጨማሪም ከእግዚአብሔር ሊሰወር የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ሲገልጽ “እግዚአብሔር በየቦታው የሚደረገውን ነገር ሁሉ ያያል፤ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር ብናደርግ ይመለከተናል” ይላል(ምሳ 15፡ 3)፡፡ 

የመጽሐፈ ምሳሌ ጸሐፊ ስለ በጎ ሥራ ወይም አንድ ሰው በሕይወቱ በጎ ሥራ ማከናወን እንዳለበት ይመክራል፤ የሚሠራው በጎ ሥራ ለወዳጅ ብቻ ሳይሆን ለጠላትም ጭምር መሆን እንዳለበት ይመክራል፡፡ ይህ ከሆነ ሰው በሕይወቱ ብዙ በረከት ያገኛል፡፡ ጸሐፊው ከጠቀሳቸው ምክር አዘል ትምህርቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኝበታል፡፡

-       ጠላትህ ቢርበው አብላው፤ ቢጠማውም አጠጣው፤ ይህን ብትፈጽም በሐፍረት እሳት እንዲቃጠል ታደርገዋለህ፤ ለአንተ ግን እግዚአብሔር የመልካም ሥራህን ዋጋ ይከፍልሃል(ምሳ 25፡ 21)፡፡

-       በጠላትህ ላይ መከራ ሲደርስበት ደስ አይበልህ፤ በሚወድቅበትም ጊዜ ሐሤት አታድርግ፤ በዚህ ነገር ደስ ቢልህ ግን እግዚአብሔርን ታሳዝናለህ፤ እግዚአብሔርም በጠላትህ ላይ ቁጣውን ከማሳየት ይቈጠባል(ምሳ 24፡ 28)፡፡

-       መሥዋዕት ከማቅረብ ይልቅ ትክክልና ቅን የሆነውን ነገር ማድረግ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል(ምሳ 21፡ 3)፡፡

-       ለድኾች ብትሰጥ ለእግዚአብሔር እንዳበደርክ ይቈጠራል፤ እግዚአብሔርም የመልካም ሥራህን ዋጋ ይከፍልሃል(ምሳ 19፡ 17)፡፡

-       የደግ ሰው ቤት በብዙ ሀብት የተሞላ ነው፤ የክፉ ሰው ግቢ ግን ችግርን ያስከትልበታል(ምሳ 15፡ 6)፡፡

-       ለጋሥ ሁን፤ ትበለጽጋለህ፤ ሌሎችን እርዳ፤ አንተም ዕርዳታ ታገኛለህ(ምሳ 11፡ 25)፡፡

-       ርኁሩኅ ብትሆን ራስህን ትጠቅማለህ፤ ጨካኝ ብትሆን ግን ራስህን ትጐዳህ፡፡ ክፉ ሰዎች የሚያገኙት ጥቅም አይኖርም፤ ትክክል የሆነውን ብታደርግ የመልካም ሥራህን ዋጋ ታገኛለህ(ምሳ 11፡ 18)፡፡

በአጠቃላይ መልካም መሥራትና ደግነትን ተላብሶ መኖርን በዕለታዊ ሕይወት ውስጥ መንፈሳዊ እርካታ እንደሚሰጥ ጸሐፊው በተደጋጋሚ በተለያየ መልኩ ያስገነዝባል፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ

መሪ ካህን ፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ

የትምህርቱ አስተባባሪ ፦ ተስፋዬ ባዴዢ

 ለጥናቱ የሚያግዙ ጥያቄዎች

1.      ጽሐፈ ምሳሌን በተመለከተ ትክክል ያልሆነውን የትኛውን ነው?

ሀ) መጽሐፈ ምሳሌ በፈሊጣዊና በምሳሌያዊ አነጋገር የተዘጋጀ የሥነ ምግባርና የሃይማኖት ትምህርት ነው፡፡ ለ)ንጉሥ ሰሎሞን ከእግዚአብሔር ዘንድ ልዩ ጥበብን እንደ ተቀበለና ሦስት ሺህ ምሳሌዎች እንደ ተናገረ ታውቋል(1 ነገ 3፡ 10-12 ፤ 4፡ 29-34)፡፡ ስለዚህ ምሳሌዎቹ ሁሉ የንጉሥ ሰሎሞን ናቸው፡፡ ሐ) ጥበብ ገና ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እንደተፈጠረች ትናገራለች፡፡ መ)ጥበብ በእግዚአብሔር ከተፈጠረች በኋላ ሰዎችን ወደራስዋ ትጠራለች፤ ጥበበኛ ሆነው እንዲኖሩም ትመክራቸዋለች፡፡ ሠ) እንደ መጽሐፈ ምሳሌ ጸሐፊ  አንድ ሰው ብር ወይም የተሰወረ ሀብት ለማግኘት ጥረት የሚያደርገውን ያህል ተግቶ ጥበብን መፈለግ አለበት፡፡

2.     መጽሐፈ ምሳሌ ስለ ሥራ ክቡርነትና ሰው ለኑሮው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ለማግኘት መሥራት እንዳለበት በተደጋጋሚ ይመክራል፡፡ በተጨማሪም ለወጣቶች ሰፋ ያለ ለሕይወት መመሪያ የሚሆን ምክር ይሰጣል፡፡ ጸሐፊው ስለ ሥራ ክቡርነትና ጥበብ ለወጣቶች ስለሚሰጠው የሕይወት መመሪያ ከተናገራቸው ውስጥ ትክክል ያልሆነውን ምረጥ፡፡

ሀ)መሥራት የማይፈልግ ሰነፍ ሰው ራሱን የገደለ ያህል ይቈጠራል፡፡ ለ) ሥራውን በጥንቃቄ የሚሠራ ሰው ከብዙ ሰዎች በመሻል የነገሥታት ባለሟል መሆን ይችላል፡፡ ሐ)የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፡፡ መ)ጥበብን የሚያገኙ ሰዎች ደስ ይበላቸው፤ ምክንያቱም ጥበብ እውነተኛ ሕይወትን ትሰጣቸዋለች፡፡ ሠ) በምታደርገው ሁሉ ጥበብን አስቀድም፤ እርሱም በትክክለኛው መንገድ ይመራሃል፡፡

3.     ከጥበብ ስለሚገኘው በረከት ትክክል ያልሆነውን የትኛው ነው?(ይህንን ለመመለስ ከምዕራፍ 1 እስከ 4 ያለውን በአስተውሎት ማንበብ ያስፈልጋል)፡፡

ሀ)ጥበብና ምክር ለሚያስተውለው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል፤ ከመላው ሰውነት ጤንነት ግን የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም፡፡ ለ)ጥበብን ጥራት ማስተዋልን ወደ አንተ አቅርባት፡፡ ሐ)በጥበብ ብትራመድ በመንገድህ ላይ ዕንቅፋት አያጋጥምህም፤ ብትሮጥም አትሰናከልም፡፡ መ) ጥበብ ከውድ እንቁ ትበልጣለች፤ አንተን ለማግኘት ከምትመኛቸው ነገሮች ሁሉ ከጥበብ ጋር የሚወዳደር የለም፡፡ ሠ)ዕውቀት የጐደላቸው ሰዎች ከጥበብ በመራቃቸው ምክንያት ይሞታሉ፤ ሞኞችም ከቸልተኛነታቸው የተነሣ ይጠፋሉ፡፡ ጥበብን የሚሰማ ግን ለሕይወቱ ዋስትና ይኖረዋል፡፡

4.     ስለ ባለሙያ ሚስት ከተነገረው ውስጥ የተሳሳተውን ምረጥ⁄ምረጭ፡፡(ምሳሌ 31 ማንበብ ያስፈልጋል)፡፡

) ባለሙያ ሚስት ብርቱና የተከበረች ናት፡፡ ለ) ቁንጅና መልካም ነው፤ ውበትም ጥሩ ነው፤ እግዚአብሔር የምትፈራ ሴት ግን ውብ ባትሆንም እንኳ ወንዶች ሊያገቡአት መጣደፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ሐ) ባልዋ ይተማመንባታል፤ ድኽነትም ከቶ አይደርስባትም፡፡ መ) እርስዋ ብርቱና የተከበረች ናት፤ በመጪው ጊዜ ሁሉ ደስ ብሎአት ትኖራለች፡፡ ሠ) ሁሉም ትክክል ናቸው፡፡

5.     የመጽሐፈ ምሳሌ ጸሐፊ ከገለጻቸው ነገሮች ውስጥ ትክክል ያልሆነውን ምረጥ፡፡ (እነዚህ ነገሮች የሚገኙት ከምዕራፍ 28 እስከ 30 ባለው ክፍል ውስጥ ነው)፡፡

ሀ)ሀብታም ሆኖ አታላይ ከመሆን ይልቅ ድኻ ሆኖ ታማኝ መሆን ይሻላል፡፡ ለ) ከአባቱና ከእናቱ ሰርቆ “ኃጢአት አላደርኩም” የሚል ሰው ከማንኛውም አጥፊ ሰው የተሻለ አይደለም፡፡ ሐ) ልጅህን ብትቀጣ ዕረፍትና ሰላም አጥተህ የበለጠ ትበሳጫለህ፡፡ መ) በአባቱ የሚያፌዝና እናቱ በምታረጅበት ጊዜ የሚንቃት ሰው የሸለቆ ቁራዎች ዐይኖቹን ጐጥጉጠው ያወጡታል፤ ጆፌ አሞራዎችም ይበሉታል፡፡ ሠ) ጸሐፊው ሊያስተውላቸው ከማይችላቸው እጅግ ምስጢር ከሆኑ ነገሮች ውስጥ አንዱ “ከሴት ጋር ፍቅር የያዘው ወንድ ነው”፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት - ብሉይና አዲስ ኪዳናት 

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት